EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 28 March 2016

የህዳሴው አብሳሪ-የታሪክ አሻራችን ቋሚ ሃውልት

የማነ ገብረስላሴ
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓም በቤንሻንጉል ክልል የምትገኝ ጉባ የተባለች ስፍራ አንድ ድንቅ ታሪክ ታስተናግድ ዘንድ ታጨች፡፡ እንደ ቀደምት የታሪክ ስፍራዎች  ስሟ በታሪክ መዝገብ እንዲሰፍር፣ እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሃረር፣ ጣና.. ወዘተ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችላት አንድ ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታ በጉያዋ እንዲከናወን በህዳሴው መሃንዲስ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በዚህች ስፍራ ተበሰረ፡፡ ለዘመናት ለሌሎች አገሮች ሲሳይ ለኢትዮጵያውያን ግን ከዘፈንና ከእንጉርጉሮ ያለፈ ጠብ የሚል ጥቅም መስጠት ያልቻለው የአባይ ወንዝ ፊቱን ወደ አገሩ አዙሮየአገራችን ህዳሴ ብስራት እንዲሆን ኢትዮጵያውያንም ከድህነት ማምላጫ መንገዳቸውን ብሩህ የሚያደርግላቸው ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ የቁጭት እንጉርጉሮ ሲያሰሙ የኖሩት ኢትዮጵያውያንም ይህንን ብስራት ሲሰሙ ደስታቸውን ለመግለጽ ቃላት አጠራቸው፡፡ ስሜታቸውን በጭፈራና በእልልታ ገለጹ፡፡

የአባይ ወንዝ የአገራችንን ውሃና ለም አፈር ጠራርጎ እየወሰደ ለሌሎች ህዝቦች እራትና መብራት ለኢትዮጵያን ደግሞ የኪነ ጥበብ ማድመቂያ ብቻ ሆኖ ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያውያን በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ከአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የልማት ስራ ማከናወን ሳይችሉ ዘመናት አልፈዋል፡፡ በዚህም ስለ አባይ ሲነሳ በቁጭት የማይንገበገብ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ግን ወቅቱና ሁኔታው ፈቀደና “ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የልማት ፕሮጀክት መስራት አይችሉም” የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ ሊሰብር የሚችል፣ ታሪክ የሚቀይር ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ፡፡

መንግስት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲያበስር ፕሮጀክቱን ከዳር ለማድረስ ያልተቆጠበ የህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገለጸ፡፡ በፕሮጀከቱ መጀመር ወደር የሌለው የደስታ ማዕበል ውስጥ የነበረው ህዝባችን የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ  ለግድቡ ግንባታ መሳካት አስፈላጊውን መስዋዕት እንደሚከፍል አረጋገጠ፡፡ቃሉንም ጠብቆ የማያቋርጥ ድጋፉን በማድረግ ለቃሉ ታማኝነቱን በተግባር አሳየ፡፡   ዝቅተኛ የሆነ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ጭምር ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ በልገሳ መልክ ለመስጠት አላቅማሙም፡፡  

ግድቡ በተጀመረበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጨፍ ለህዳሴ ግድብ የሚሆን ቦንድ ሲገዙ ያገኛኋቸው በግምት ዕድሜያቸው  70 ዓመት የሚገመቱ አዛውንት ያሉኝን ላስታውሳችሁ፡፡ አዛውንቱ የአባይ ወንዝ ያለ ጥቅም መፍሰስ እጅግ የሚቆጫቸው ነገር እንደነበርና አሁን ቁጫታቸውን ቦንድ በመግዛት እንደሚወጡ ገልጸው በእጃቸው የያዙትን በትር ከመሬቱ ላይ እያላተሙ አንገታቸውን ወደ ላይ ሰቅለው “ፈጣሪ የዚህን ግድብ ግንባታ መጨረሻን ሳያሳየኝ እንዳይወስደኝ እጸልያለሁ” አሉ፡፡ በባንኩ ውስጥ ያገኛኋችው አንዲት እናትም የወር ገቢያቸው ከ500 ብር ያልዘለለ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ያ ግን አልገደባቸውም  እኚህን እናት ቦንድ ለመግዛት የቀደማቸው አልነበረም፡፡   “አባይ በአገሩ አረፍ ብሎ ህዝቦቹን ሊጠቅም ጉዞ ሲጀምር ካለን ዝቅተኛ ገቢም ቢሆን አብቃቅተን ከዳር ሳናደርሰው አንተኛም” በማለት ወኔ በተሞላበት ንግግር ግድቡ እውን እስኪሆን ድጋፋቸው እንደማይለይ አጫወቱኝ፡፡ እነዚህን ለአብነት አነሳሁ እንጂ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲበሰር በደስታ ስካር ያልፈነጨ፣ ደስታውን በጭፈራና በእልልታ ያልገለጸ ዜጋ አልነበረም፡፡ ተማሪው፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ ሴቱ፣ ወንድ፣ አባቶችና እናቶች …መላው ህዝብ ከጫፍ ጫፍ በግድቡ ግንባታ መጀመር ደስታውን በተለያዩ መንገዶች በመግለፅ የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን አሳየ፡፡




6ሺ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኃይል አቅርቦታችንን በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል ማመንጨት ከጀመረች በርካታ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም እስከ አሁን ከተገነቡ በርካታ ፕሮጀክቶች የጊቤ 3ን ሳይጨምር እየመነጨ ያለው  ከ2ሺ300 አልዘለለም፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚመነጨው 6ሺ ሜጋ ዋት መሆኑን ሲታይ ግን እውነትም የአባይ ወንዝ በቅርቡ ለአገሩ ህዝቦችም እራትና መብራት እንደሚሆን ማረጋገጫ ነው፡፡
የግድቡ ግንበታ መጀመር ከኃይል ማመንጨት በሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡  አገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ በቆየው ሰላም እጦት፣ ድህነትና ኃላቀርነት የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወን ተስኗት ቆይቷል፡፡ በተለይም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን መገንባት ካለ ዓለም አቀፍ ዕርዳታና ብድር ውጭ የማይታሰብ ጉዳይ ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግብጽ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎች እንዳትሰራ በተለያዩ መንገዶች ጫና ከመፍጠር ጀምራ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ማድረጓ ደግሞ በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን ተነፍገን ቆይተናል፡፡ እናም በአባይ ወንዝ በራስ አቅም ይህንን በግዙፍነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ግድብ ለመስራት ማቀድ “የአይቻልም” መንፈስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሰበር ከማስቻሉ ባለፈ በራስ መተማመንን ከፍ ያደረገ ፕሮጀክት እንዲሆን አስችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ታሪክ የሚነገርባት አገር ብቻ ሳትሆን አዲስ ታሪክ የሚሰራባት አገር መሆንዋንም ዳግም ያረጋገጠ ብርቅዬ ፕሮጀክት የሆነውም ለዚህ ነው፡፡

በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ለዘመናት ሳይቻል በመቆየቱ በነበረው ቁጭትና አሁን ካለው  ከፍተኛ የልማት ፍላጎት ፕሮጀክቱ መላው ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ በመሆኑ ብሄራዊ መግባባትን በመገንባት ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ  ሆ…ብለው በጋራ ድጋፋቸውን የገለጹለት ብቸኛው የልማት ፕሮጀክትም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ “ይህ ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ነው ያረፈበት ነው”ያለውም ለዚህ ነበር፡፡ በዚህም ፕሮጀክቱ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው የህዝቦች አንድነት ይበልጥ ያጠናከረ  ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ በመሸጥ ገቢ እንድታገኝ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የአከባቢውን አገሮች በኃይል አቅርቦት በማስተሳሰር የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኃይል ማዕከልም ያደርጋታል፡፡

ግድቡ አገራዊ አንድነትን ከማጠናከሩ በተጨማሪ ከወንዙ ተፋሰስ አገሮች ጋር ያለው ግንኙነት በጋራ መጠቃቀምና መተባበር እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በወንዙ ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር ሲታይ ወንዙን በፍትሓዊነት የመጠቀም አስተሳሰብ እያደገ ነው፡፡ በተለይ ሆስኒ ሙባረክ የስልጣን ዘመን በተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የግብጽ ህዝብ የነበረው ፍጹም የተሳሳተ ግንዛቤ አሁንም ቀሪ ስራ የሚጠይቅ ቢሆንም ለውጦች አሉ፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድባችን  ያስገኘው ሌላው ትሩፋት የቁጠባ ባህል ማሳደጉ ነው፡፡ መላው የአገራችን ሀዝቦች ለግድቡ ግንባታ በነጻ ቦንድ በመግዛት ፈቃዳቸው የነበረ ቢሆንም በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ካለው ህዝባዊ ባህሪ በመነሳት ልገሳው ወደ ቁጣባ ቦንድ እንዲቀየር አድርጓል፡፡ ይህም ዜጎች በአንድ በኩል ገንዘባቸውን እየቆጠቡ በሌላ በኩል እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚሳሱለትን ግድብ እየደገፉ ታሪክ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እስከ አሁንም ዜጎቻችን የ12 ቢሊዮን ብር ቦንድ ለመግዛት ቃል የገቡ ሲሆን እስከአሁን 8ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡
ህዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው የህዳሴ ግድብን ለመገንባት በከፍተኛ ወኔ በሚረባረቡበት ወቅት አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተለመደው ከመልካሙ ነገር በተቃራኒ ጎራ ሲሰለፉ ተስተውሏል፡፡ ፕሮጀክቱ መስከረም ወር 2003 ዓም ይፋ በተደረገው አንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተካተተና አስቀድሞ የታቀደ መሆኑን ግልጽ ቢሆንም እነርሱ ግን በግድቡ ዙርያ መተማመን እንዳይኖር በማሰብ ግድቡ በወቅቱ በዓረብ አገራት አጋጥሞ የነበረውን ህዝባዊ ዓመጽ ለመቀለበስ በጥድፊያ የተጀመረ እንደሆነ ለመስበክ ጥረት አድርገዋል፡፡ ህዝቡ ለድጋፉ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማኮላሸትም የተለያዩ ጥረቶችን አደረጉ፡፡ ይሁንና ሰሚ አላገኙም፡፡ ይልቁንስ ምንም ዓይነት ህዝባዊ አጀንዳ እንደሌላቸው ህዝቡ በግልጽ ተገነዘበ፡፡ በዚህም ከህዝቡ ይበልጥ ተነጠሉ፡፡ የጽንፈኛ ኃይሎች ኃይሎች የውሸት ፕሮፖጋንዳ አስመለክቶ ጓድ መለስ በወቅቱ እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹እነዚህ የተለያዩ መፈክሮችና ማደናገርያዎች ተደምረው አንድ መልዕክት ነው የሚያስተላልፉት፣ ይሄ ግድብ እንዳይሰራ ፈንጂ ከማጥመድ ጀምሮ የሃሳብ ፈንጂ እስከማጥመድ ድረስ ባለው ማዕቀፍ ውስጥ በሙሉ አቅማቸው እንደሚረባረቡ ነው የሚያሳየው፣ አሁን እነዚህ ነገሮች ተብራርተው ቢያልቁ በሚቀጥለው ጊዜ ሌላ ማደናገርያ መፈብረካቸው አይቀርም››፡፡ በእርግጥም ጓድ መለስ እንዳለው በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የልማት ስራዎችን ሲከናወን የሚያማቸው እነዚህ ኃይሎች በግድቡ ግንባታ ዙርያ ያልፈበረኩት ውሸት የለም፣ ሰሚ አጡ እንጂ፡፡

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንበታ የአሉባልታ ማዕበል ሳይገድበው ከግማሽ በላይ ተከናውኖ አሁን የግንባታው ሂደት በላቀ ፍጥነት እየተካነወነ ይገኛል፡፡ የህዝቡ ተሳትፎም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአዲስ የለውጥ ማዕበል ገብታ ድንቅ ታሪክ እየሰራች እንደሆነችም አንድ ማሳያ ነው፡፡ 

Sunday, 27 March 2016

ውስብስብና አስቸጋሪ የትግል ፈተና ያልበገረው ረጅሙ የኦህዴድ የድል ጉዞ!!







በገነት ደረጀ
በኢትዮጵያ 1980ዎቹ መጀመሪያ ህዝቡ ከበዝባዡ የፊውዳል ስርዓት ለመላቀቅ ያደረገውን ትግልና ድል ነጥቆ ወደ ስልጣን ለወጣው ደርግ ፈታኝ ዘመን ነበር፡፡ ወቅቱ በደርግና የህዝቡን ነጻነት ለማስመለስ ከሚታገሉ ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በህወሓትና በኢህዴን መሪነት በህዝቡ በተደረገው ትግል አብዛኛው የሰሜኑ ክፍል ከጨቋኙ የደርግ ስርዓት ነጻ ለመውጣት ችሎም ነበር፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ያለው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም ደግሞ ሰፊ በሆነው ኦሮሚያ ውስጥ ሁነኛ አታጋይ ድርጅት ባለመኖሩ የደርግ እድሜ እንዲራዘምና ትግሉ ፈታኝ እንዲሆን አደረገው፡፡

በኦሮሞ ሀዝብ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችም የረባ እንቅስቃሴ ማድረግ ባለመቻላቸው ወደ ክልሉ ዘልቀው እንዲገቡ ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ድጋፍ ቢደረግላቸውም ትግሉን ከዳር ማድረስ ተስኗቸው ነበር፡፡ ለአብነትም ኦነግ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲገባ በህወሓት ድጋፍ ተደርጎለት የነበረ ሲሆን የህወሓት ሰራዊት ቀድሞ ወደነበረበት የትግል ስፍራ ሲመለስ ኦነግ ከደርግ ሸሽቶ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተመለሰ ድርጅት ነበር፡፡ በሌላ ወቅትም በሻዕቢያ ድጋፍ ቢደረግለትም በአሶሳ ከተማና አካባቢው የነበሩ አማራዎችን በሚዘገንን ጭፍጨፋ ካጠፋ በኋላ የደርግን ጥቃት መቋቋም ተስኖት እንደተለመደው ወደ ሱዳን ጠረፍ ለማፈግፈግ የተገደደ ድርጅት ነበር፡፡

ኢትዮጵያን ብሎም የኦሮሞ ህዝብን ከጨቋኙ የደርግ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ከሀገራችን ህዝብ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ክብሩንና ነጻነቱን ለማስመለስ በተናጠል ትግል ሲያደርግ የነበረውን የኦሮሞ ህዝብ በተደራጀ ሁኔታ ትግሉ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነ፡፡ ህዝቡን ወደ ተደራጀ ትግል ማስገባት ብቻ ሳይሆን  በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የሀብት ምንጭ ደርግ እንደይጠቀምና መዋቅሩን መበጣጠስ ለድሉ መፋጠን ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ታመነበት፡፡ በመሆኑም ዴሞክራሲያዊና ጠንካራ የህዝባዊ መሪ ድርጅት አስፈላጊነት በኦሮሚያ አንገብጋቢ ሆነ፡፡

በወቅቱ በኢህዴን ውስጥ ሲታገሉና በትግራይ ነጻ መሬት ላይ የነበሩ፤የኦሮሞ ህዝብ ጭቆናና በደል አንገብግቧቸው ለመታገል የወሰኑ የኦሮሞ ታጋዮች ተሰብስበው የኦሮሞ ህዝብ ትግልን መምራት የሚችል ድርጅት ለመመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለ8 ወራት ዝግጅት አደረጉ፡፡ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ በጠራ መስመር አደራጅቶ ለመምራት ከዚህ ቀደም በህዝቡ ስም ተመስርተው ምንም ውጤት ማምጣት ስላልቻሉ ድርጅቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ሂደትን በጥልቀት በመገምገም ለአዲሱ ድርጅት የትግል ፕሮግራም፤ ስትራቴጂና ስልቶች እንዲሁም መተዳደሪያ ደንብ ታጋዮቹ ቀረጹ፡፡

ለአዲሱ ድርጅት ምስረታ በተደረገው ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ቅድመ ሁኔታ ሀገራችን አስከፊ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና የተንሰራፋባት ሀገር እንደሆነችና ሰፊው የኦሮሞ ህዝብም እንደሌሎቹ ወንድም ህዝቦች በተመሳሳይ ጭቆና የሚሰቃይ ህዝብ እንደሆነ በግልጽ ተቀመጠ፡፡ ይህንን ለማስወገድም ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ሊካሄድ እንደሚገባና የደርግ የአፋና መዋቅሮች ሊፈራርሱ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ እናም የስምንት ወራት የዝግጅት ጊዜን ተከትሎ ከመጋቢት 15-17 ቀን 1982 ዓ.ም መስራች ጉባኤ ተካሄደ፡፡ ለሶስት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ከተለያዩ አካላትና  አካባቢዎች የመጡትን ጨምሮ 225 መስራቾች በተሳተፉበት ከ26 ዓመታት በፊት መጋቢት 17 ቀን 1982ዓ.ም የኦሮሞን ህዝብ ትግል መርቶ ለድል ለማብቃት የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ድርጅት/ኦህዴድ በይፋ ተመሰረተ፡፡

ኦህዴድ በአባላቱ በእህት ድርጅቶች ውስጥ ሆኖ ሲታገልም ሆነ ራሱን ችሎ ተደራጅቶ እንደ ድርጅት ሲመሰረት ቀደምት የትግል ድርጅቶች ያሳለፏቸውን ችግሮችና እንቅፋቶች ባለመድገምና የተቀሰሙ ልምዶችን በመቀመር ለመንቀሳቀስ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡ በሌላም በኩል ጭቆናውና አፋናው ያንገሸገሸው ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ትክክለኛ መስመር ይዞ በህዝቡ ውስጥ ሆኖ የሚያታግል ድርጅትና አመራር የሚፈለግበት ወቅት መሆኑም ለኦህዴድ ምስረታና መጠናከር አጋጣሚው የተመቻቸ ነበር፡፡ ትግሉን መርቶ ከዳር ለማድረስ የመስራች ታጋዮች ዝግጁነትና ቆራጥነት ሌላው ድርጅቱ ጠንካራ እንዲሆን ያስቻለ ነበር፡፡  

በአጠቃላይ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል በትክክለኛ መስመር በመምራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ትግሉን ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግል ጋር በማስተሳሰር አኩሪ ድል መቀዳጀት አስፈላጊ በሆነበት ወቅት የተወለደና ጥንካሬውንና ጽናቱን ገና በጠዋቱ ያስመሰከረ ድርጅት ሆነ፡፡  በወቅቱ የማይነጥፍ የህዝብና የድርጅቶች ድጋፍ የነበረው ድርጅት በመሆኑም በአጭር ጊዜ ወስጥ ተጠናክሮ ብሔራዊና ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የቻለ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በትጥቅ ትግል የድርጅቶች ታሪክ በፍጥነት ማደግና መመንደግ የቻለ ድርጅት ነው ኦህዴድ/ኢህአዴግ፡፡

በኦሮሞ ህዝብ ስም ተመስርተው ረጅም እድሜ ካስቆጠሩና ከጠባብ ድርጅቶች በተለየ አሰላለፍ የህዝቡን ትግል በአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ አቅጣጫ ለመምራት ኦህዴድ ተመስርቶ ወዲያው ወደ ትግል ሲገባ በታሪኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምስረታው ቀጥሎ 2ኛውን ስኬታማና ታሪካዊ ክስተት አስመዘገበ፡፡ ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኦሮሚያ በመግባት በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ጋር የትግል ግንኙነት ጀመረ፡፡  ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኦህዴድ ህዝቡን እያደረጀና እያስታጠቀ ከደርግ ጋር መፋለም ጀመረ፡፡

ኦህዴድ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደራጀ ሁኔታ በጦርነት ላይ የተካፈለው ዘመቻ ቴዎድሮስ በመባል የሚታወቀውና ጎጀምና ጎንደርን ነጻ ለማውጣት በኢህአዴግ በታቀደ ዘመቻ ነበር፡፡ ይህ ዘመቻ እነዚህን አካባቢዎች ከደርግ ነጻ ካወጣ ደግሞ ኦህዴድ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ዘልቆ እንዲገባ የሚያስችል ነበር፡፡ በአምስት ሪጅመንቶች አቅሙን ያደራጀው ኦህዴድ ወደ ጎጃም በመሻገር ዘመቻ ቴዎድሮስ ላይ በተሳካ ሁኔታ በመሳተፍ ብዙም ሳይቆይ በምዕራብ በኩል ወደ ክልሉ ለመግባት ቻለ፡፡ ቀጥሎም በቢሊሱማ ወልቂጡማ ዘመቻ ደርግን በመደምሰስ ከወለጋ እስከ አምቦ ያለውን ከደርግ ነጻ ማውጣት የነበረና በስኬት የተጠናቀቀ ዘመቻ በማድረግ ከተመሰረተ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደርግን ለመደምሰስ በተደረገው መራራ ትግል ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ለድል በቅቷል፡፡



የኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚከበረው በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማዕቀፍና ትስስር ውስጥ መብቱ ተከብሮ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት አብሮ ሲኖር ነው ብሎ አምኖ ትግሉን የጀመረው ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከደርግ መውደቅ በኋላም ለአዲስቷ ኢትዮጵያ መፈጠርና መጠናከር ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ከእህት ድርጅቶች ጋር በመሆን ኦህዴድ/ኢህአዴግ ደማቅ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ በሽግግር መንግስት ምስረታና በአዲስቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በልማት ዙሪያ ህዝቡን የመራና ውጤት ያስዘገበ ድርጅት ነው -ኦህዴድ/ኢህአዴግ፡፡

ኦህዴድ የፌዴራል ስርዓታችን እንዲጠናከር በሚደረገው የትግል  እንቅስቃሴም ይሁን የኦሮሞ ህዝብን ብሔራዊ መብት የሚያስጠብቁ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን የማቋቋም፤ የመገንባትና የማጠናከር፤ በራሱ ቋንቋ የሚሰራ መንግስታዊ መዋቅር የመግንባት፤ ትምህርት እንዲስፋፋና ህዝቡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማርና እንዲተዳደር የማድረግ፤ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ፤ በተለይም በጭቆናው ምክንያት ተስፋ ቆርጦ የማምረት አቅሙ ተሟጦ የነበረውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር በማነሳሳት በርካታና ድንቅ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ አስከፊ መደባዊና ብሔራዊ ጭቆና ስር ወድቆ የጨለማ ህይወትን ሲገፋ የነበረውን ህዝብ በድል ጎዳና በመምራት ወደ ልማታዊና ሰላማዊ ምዕራፍ በማሻገር ሀገራችን በፈጣንና ተከታታይ የእድገት ጎዳና እንድትራመድ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የበኩሉን ድንቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኦህዴድ/ኢህአዴግ ያሳለፋቸው 26 ዓመታት አልጋ በአልጋ ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታ፤ እራሱን እያረመና ህዝባዊነቱን ይበልጥ እያጠናከረ ክልላዊና ሀገራዊ ተልዕኮውን የተወጣ ድርጅት ነው፡፡

ኦህዴድ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ስርዓት እንዲገነባ እየተደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ ትግል እየተጫወተ ያለው ሚና እጅግ ገዝፎ የሚታይ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኦህዴድ በዴሞክራሲና በልማት ትግል የሚያደርግበት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰፊና በርካታ ህዝብ የሚገኝበት በመሆኑ ይህንን ሰፊ ግዛት የመምራትና በርካታ ቁጥር ያለውን ህዝብ በዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ስርዓት ግንባታው በአግባቡ አደራጅቶ ተሳታፊ እንዲሆን የሚደረገው ትግል ሰፊና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ በኦሮሞ ህዝብ ስም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ትግላቸውን ማስቀጠል ሲሳናቸው በተቃራኒው በክልሉ ህዝብ ጉያ ተሸሽገው በህገ ወጥ መንገድ እየተገነባ ያለውን ዴሞክራሲና በኢኮኖሚው የተመዘገቡ የልማት ትሩፋቶችን በሚያጠፋና በሚንድ አፍራሽና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ላይ በመሰማራት እያደረሱ ያለው ጫና በተለያዩ ወቅቶች ባህሪውን በመቀያየር መቀጠሉ ኦህዴድ በዴሞክራሲውና በልማቱ የሚያደርገውን ትግል ውስብስና አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይሁንና በትግሉ ውስብስብና አስቸጋሪ መሆን መፈተን ቢችልም ያልተበገረውና ከረጅም ጉዞው ያልተገታው ኦህዴድ/ኢህአዴግ አሁንም በድል ታጅቦ መገስገሱን ቀጥሎበታል፡፡

በሀገራችን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት እየተደረገ በሚገኘው ርብርብ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የውስጥ ትግልን በማጠናከር ችግሮችን እየፈታ ድሎቹን እያጠናከረ ይቀጥላል፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት! ድልና ድምቀት ለኦህዴድ/ኢህአዴግ 26ኛ ምስረታ በዓል!        





Saturday, 26 March 2016

ዓለምም እንደ ኢትዮጵያ የብዙህነት መናኸሪያ ነች!!


                                                                          ከታጋይ ሓዱሽ ካሡ
እ.አ.አ. ከ1990ዎቹ ጀምሮ ዓለም “አንድ መንደር” ሆናለች የሚል አባባል የሚደመጥባት መሆኑ የተለመደ ሆኗል፡፡ አባባሉ ከግሎባላይዜሽን መከሰት ጀምሮ በአራቱም የዓለም አቅጣጫ ያሉ ህዝቦች ቋንቋ ሆኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ “ዓለም አንድ መንደር” ሆናለች የሚባለው፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስለተሳሰረችና የምትመራው በኢንፎርሜሽንና  በዕውቀት ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም በምዕራቡ የዓለም አቅጣጫ የተከሰተ አንድ ጉዳይ በማይክሮ ሴኮንዶች ውስጥ በምሥራቁ ዓለም እንደ ይሠራጫል፤ በተመሳሳይ በምስራቁ የተሰማ ምዕራቡ ጋር ሲደርስ ፋታ የለውም፡፡

የዓለም የግብይት ሥርዓት የሚከናወነውም በኢንተርኔት ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ውድድር ውስጥ ባለችው ዓለማችን መኖር የሚቻለው ጥራትና መጠን ባለው ምርትና አገልግሎት በማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም በፊት የፈጣን ኢንፎርሜሽንና ዕውቀት ባለቤት መሆን ግዴታ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከዚህ አኳያ “ዓለም አንድ መንደር” ሆናለች የሚለው አባባል የሚያከራክር ሳይሆን ዕውነታውን የሚገልፅ ነው፡፡
በእርግጥ ዓለም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኔትዎርክ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ የተነሳ እንደ ድር የተሳሰረ የምርትና የአገልግሎት ልውውጥ በማድረግ ላይ ነች፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከ7.6 ቢልዮን በላይ ህዝቦች በማህፀንዋ የያዘችው ዓለማችን  “አንድ መንደር” ሆናለች የሚለው መጠሪያ ብቻ ይገልፃታል ወይ?! የሚል ጥያቄ ቢነሳ በምላሹ አይደለም የሚል መከራከሪያ የሚያቀርብ ሰው አይጠፋም፡፡ እንዴትና ለምን ቢባል በቀላሉ ከሃብት ክፍፍል አኳያ እንኳን ብናይ፣ ከዓለማችን ህዝብ አንድ ከመቶ/1%/ የሚሆኑት ብቻ ጥቂት ባለሃብቶች የዓለምን ሃብት ተቆጣጥረው የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩባት ሆናለች፡፡ በአንፃሩ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ/99%/፣ የዓለም ህዝቦች፣ የሚበዙት የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ካገኙ በቀን ሁለት ጊዜ አልያም አንድ ጊዜ ብቻ እህል ውሃ ብለው የሚኖሩባት ነች፡፡ ምድራችን ከቆዳ ቀለም አኳያም ጥቁር፣ የቀይ ዳማ፣ ብጫ፣ ቀይና ነጭ ቀለም ያሉዋቸው ህዝቦች መኖሪያ ነች፡፡

        ዓለማችን ከሃብት ክፍፍል፣ በዓለም ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ልሂቃን ከሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም እና አስተሳሰብ እንዲሁም መንግሥታት ከሚመሩበት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ቅኝትና አተያይ አኳያ አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ከዘር ግንድና ከቋንቋ፣ ሃይማኖትና እምነት ወዘተ አኳያ ሲታይም አንድ ዓይነት/ Identical / ሳይሆን የብዙህነት(Pluralism) መናኸሪያ መሆኗን የዘርፉ ተመራማሪዎች በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፈው ይገልፁታል፡፡ ይኸውም አሁን በዓለማችን በአሃዳዊ ሥርዓት (Unitary system) እንዲሁም በህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት(multinational federalism) የሚመሩ፣ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የዘር ሐረጋቸው 86 ከሚሆኑ የተለያዩ ነገዶች እንደተገኘ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡  በዓለማችን ያሉት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከምልክት ቋንቋ ውጭ መነሻቸው ዘጠኝ/9/ ዋነኛ “የቋንቋ ቤተሰብ” ማለትም  Indo-European, Sino-Tibetan, Niger-Congo, Afro-asiatic, Austronesia, Dravidian, Altaic, Austroasiatic and Tai-kadia languages በመባል ከሚጠሩ የፈለቁ 6,000 የተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚናገሩ የቋንቋ ምሁራን ጥናቶችን አስደግፈው ይገልፃሉ፡፡ በኢትዮጵያ እየተነገሩ ያሉት የሚበዙት ቋንቋዎችም Afro-Asiatic  ከሚባል የቋንቋ ቤተሰብ እንደተገኙ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ዓለማችን ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የሀይማኖትና የእምነት ብዙህነትም ሌላው መገለጫዋ ነው፡፡ ይኸውም እ.አ.አ. 2013 ተዘጋጅቶ በ(Wikipedia, free encyclopedia) የተሰራጨ አንድ ጥናት ከ2.2 ቢልዮን እስከ 6 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉዋቸው 20 ትላልቅ ሃይማኖቶችና እምነቶች እንዳሉ አመልክቷል፡፡ እነዚህም  “Christianity, Islam, none religious/Atheist, Hinduism, Chinese traditional religion (Confucianism, Buddhism & Taoism) Buddhism, Ethnic religions, African traditional religions, Sikhism, Spiritism, Judaism, Baha’i, Jainism, Shinto, Cao Dai, Zoroastrianism, Tenrikyo, Ne0-paganism, Unitarian Universalism, & Rastafarianism” የሚባሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም በዋናነት ክርስትና/ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት/ እስልምና እንዲሁም ዋቄ ፈታን ጨምሮ የተለያየ እምነት የሚከተሉ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመቻቻልና በመከባበር በፍቅር የሚኖሩባት አገር ነች፡፡

ምድራችን ከፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብና ፌዴራሊዝም አወቃቀር አኳያም የተለያየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኃይሎች የምትመራ ነች፡፡ በተለይም እ.አ.አ ከ1980ናዎቹ መጨረሻዎች አካባቢ ጀምሮ በዓለም የአስተሳሰብ የበላይነት ያገኘው የኒዮ-ሊበራሊዝም ዋነኛ አቀንቃኝ የነበሩት የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚ/ር ሚስስ ማርጋሬት ታቸር በአንድ ወቅት “ህብረተሰብ ብሎ ነገር የለም”  “There is no such thing as society” ማለትም የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓቱ በግለሰቦች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህም የኒዮ-ሊበራል አስተሳሰብ አቀንቃኞች የግለሰቦች መብት ከተከበረ የብሄርና ብሄረሰቦች መብትም ይከበራል በሚል እምነት በግለሰብና በቡድን መብቶች መካከል ያለውን መስተጋብር በፍፁም እንደማይቀበል በገሃድ የሚያሳይ ነው፡፡ የኒዮ ሊበራል አተያይ ሁሉም የሰው ልጆች አንድ ናቸው፡፡ በጂኦግራፊ፣ በባህል፣ በቋንቋና በእምነት ቢለያዩም ፍላጐታቸው አንድ ዓይነት ነው የሚል አሃዳዊ ንድፈ ሃሣብ (monist theory)የሚከተል ነው፡፡

በአንፃሩ የተለያዩ ዋልታዎች (multi polar) የሚስተናገድባት ምድራችን፣ በየትኛውም የዓለም አቅጣጫ ያሉ ህዝቦች የሰው ልጆች በመሆናቸው ብቻ የሚጋሩዋቸው የጋራ እሴቶች (Universal values) እንዳሉ አሌ አይባልም፡፡ ሆኖም በተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ስነ-ልቦና፣ የፖለቲካ የአመራር ዘይቤ እንዲሁም፣ ማህበረ-ኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው ህብረ ብሄራዊ ዴዴራሊዝም (multinational federalism) ተከትለው የጋራ መግባባት ፈጥረው በመፈቃቀድና በመቻቻል ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መስርተው፣ ከድህነት የተላቀቀና የበለፀገ ማህበረሰብ መስርተው ሊኖሩ ይችላሉ የሚል በብዙህነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት አደረጃጀት ንድፈ ሃሣብ  (multi cultural theory)  የሚከተል ነው፡፡
በአጭሩ ከላይ የተገለፁ ጉዳዮች የሚያመለክቱት ዓለምም እንደ ኢትዮጵያ የብዙህነት መናኸሪያ መሆኗን ነው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ብዙህነት ላይ የተመሠረተ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓት ለመመሥረት መታተሯ፣ ለምንድነው በአንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን (Political elites’) አተያይ ይህ ሥርዓት በቀጣይ ሃገሪቷን ይበታትናል፣ አንድነትን ያላላል? ህዝቦች ያናቁራል?  ወዘተ የሚባለው?  በመሬት ያለው እውነታስ እንደሚባለው ነው ወይ?  ኢትዮጵያ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም በመከተሏ ተጠቀመች ወይስ ተጐዳች በሚሉት ጉዳዮች አንድ ሁለት ማለቱ አይከፋም፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ አገራችን የሰው ልጆች መገኛና ረዥም ዘመን ታሪክ ያላት አገር ናት፡፡ ይህንን ረዥም ታሪክ በዚህ ፅሑፍ መዳሰስ የሚሞከር አይደለም፡፡ ሆኖም በአጭሩ የአገራችን ታሪክ በርካታ ሺህ ዓመታት ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸው አሻራ ያሳረፉበት የረዥም ታሪክ ሂደት ነወ፡፡ ለዚህም ነው በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ “አባይ ወንዝን አባይ ለማሰኘት ከየአቅጣጫው የሚፈሱ የተለያዩ ወንዞች ተቀላቅለው እንደሚፈጥሩት ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ትንንሽ ጅረቶች እየተቀላቀሉት በትልቁ እንደሚፈስ ወንዝ መታየት ያለበት ነው” በማለት የገለፀው፡፡ የኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ወታደራዊ የፋሽስታዊ ደርግ አገዛዝ እስከወደቀ ድረስ በነበሩት ከሦስት እስከ አራት ሺህ ዓመታት ድረስ ጠቅለል ብሎ ይቀመጥ ቢባል፣ አራት ዓበይት ጉዳዮች የተከሰተበት ሂደት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይኸውም 1ኛ/ ኢትዮጵያ አገራዊ ነፃነታቸውን አስከብረው የኖሩ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር መሆኗ 2ኛ/ ብዙህነት በአግባቡ ማስተናገድ ተስኗት የቆየች የብዙህነት አገር፣ 3ኛ/ ከገናና ሥልጣኔ ወደ አስፈሪ ተመፅዋችነት ለመሸጋገር የተገደደች እንዲሁም  4ኛ/ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለእኩልነታቸው ታግለው የሥልጣን ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡባት እና ከ25 ዓመታት በፊት ከዕንቅልፍ ተነስታ በዕድገት ጐዳና እየገሰገሰች ያለች አገር መሆኗ የሚሉት ሊገለፁ ይችላሉ፡፡   

የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የግልና የቡድን መብቶችን ለዘመናት አፍኖ ለከፉ ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ሞት፣ ስደትና እንግልት የዳረጉዋቸው የመሳፍንትና የአምባገነኑ ወታደራዊ የፋሽስት ደርግ አገዛዝ፣ በኢህአዴግ መሪነት በኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መራራ የህይወትና የንብረት መስዋዕትነት ግብአተ መሬታቸው የተፈፀመበት 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ዋዜማ ላይ ባለንበት በአሁኑ ወቅት ሂደቱን ወደኋላ መለስ ብለን ብንቃኘው፣ በበርካታ ድሎች ታጅበን ማለትም በሁሉም ዘርፍ በተመዘገቡ ድሎች እያንዳንዱ ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ መሆን መቻሉንና መጀመሩን በገሃድ የምናይበት ነው፡፡
ከፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አኳያ ሲታይ አገራችን ረዥም ርቀት ተጉዛለች፡፡ ይኸውም በጠመንጃ አፈሙዝ እና “አንድ ህዝብ” በሚል የአስተዳደር ዘይቤ (Assimilation)፣ ማንነታቸው ተረግጦና ብዙህነታቸው እንዲደፈቅ ተደርጐ ለዘመናት የቆዩ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸው ተከብሮ በእኩልነት፣ በመፈቃቀድና በመከባበር በመኖር ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም እስከ አሁን ባለው ሂደት በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት ዕውቅና ያገኙ ከ75 በላይ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  የራሳቸውን አካባቢ ራሳቸው በራሳቸው በማስተዳደር ላይ ናቸው፡፡ የሃይማኖት፣ የፆታ እኩልነት በተግባር ተረጋግጧል፡፡ ከ80 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች እኩል ዕውቅና አግኝተው የየአካባቢው መስተዳደር የመግባቢያና የሥራ ቋንቋ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ አማርኛም የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው፡፡ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ያላቸው 75 በላይ ፓርቲዎች በሃገሪቱ በሕጋዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ የተለያዩ አመለካከት የሚያንፀባርቁ፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የህትመትና ዘመናዊ/ማህበራዊ ሚዲያ አውታሮችም ተስፋፍተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ማንነትን መሠረት ያደረገ ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት አተያይ መከተሏ፣ በህዝቦች ዘንድ በመተማመን፣ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይበልጥ ስር እየሰደደ እንዲሄድ አድርጐታል፡፡ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው የፌዴራል ሥርዓት በሚበዙት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት እንዳለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት(UNESCO) እንዲህ ብሏል፡፡   "Culture takes diverse forms across time and space. This diversity is embodied in the uniqueness and plurality of the identities of the groups and societies making up humankind. As a source of exchange, innovation and creativity, cultural diversity is as necessary for humankind as biodiversity is for our nature." (UNESCO Paris, 2004)
አዎን!  ህብረ- ብሄራዊነታችን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ዕዳ ሳይሆን ውበታችንና ፀጋችን ነው፡፡ ይህ ለዘመናት የቆየ ብዙህነት ወደ አደባባይ መውጣቱ፣ ባለፉት 25 ዓመታት ማንነት በይፋ ዕውቅና ማግኘቱ ይበልጥ ኢትዮጵያዊነትን አጠናከረ እንጂ፣ አንድም ብሄር ወይም ብሄረሰብ ከኢትዮጵያ ልገንጠል አላለም፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ እዚህ እዛም ግጭቶች መከሰታቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ሆኖም በየወቅቱ የተከሰቱ ችግሮች ህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀሩ የወለዳቸው አይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ በዋነኛነት ችግሮቹ የተፈጠሩት የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካል አ.ኮኖሚ የበላይነት ስለያዘ ነው፡፡ ለዚህ ነበር ታላቁ መሪ ታጋይ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት “የድህነት ዘበኛ የነበረው ደርግ አሁንም አለ” ያለው፡፡ ይህ ማለት የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጪያ የሆኑት ትምክህት፣ ጠባብነት፣ አክራሪነትና አሸባሪነት ተቸንፈው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የበላይነት አግኝቶ፣ በምክንያት የሚደግፍና የሚቃወም አስተሳሰብና እሴት(Rational thinking) እስከሚገነባ ድረስ ነገም ከነገ ወዲያም አልፎ አልፎ ግጭት መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ መንግሥትና የኢትዮጵያ ህዝቦች ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር፣ በተለያዩ ምክንያቶች በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶች ፀረ-ሰላምና ፀረ-ህዝብ ኃይሎች ለአፍራሽ ዓላማቸው መጠቀሚያ እንዳያደርጉዋቸው መመከትና መከላከል ነው፡፡
የህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝም አወቃቀርን የማይደግፉ ኃይሎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተለያዩ የአፍ መፍቻ ቋንቋ መጠቀማቸው፣ ኢትዮጵያን እንደሚበታትናትም ሲሰብኩ ከርመዋል፡፡ሆኖም ኢትዮጵያ የምትከተለው አካሄድ ተገቢነት እንዳለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና የባህል ድርጅት(UNESCO)  እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፡፡
 "Local content is the expression of a community's knowledge and experience, and the process of creating and disseminating provides opportunities to the members of the community to interact and communicate with each other, expressing their own ideas, knowledge and culture in their language." (UNESCO Paris, 2004)

አገራችን 25ኛውን ዓመት የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓል የምታከብረው በራሷ የዘመን አቆጣጠር 2017 የምትደርስበትን ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ (Lower middle income) ራዕይ ለማሳካት፣ እና የተያያዘችውን የዕድገት ግስጋሴ ለማስቀጠል ወሳኝ የሆነው የቀጣይ አምስት ዓመታት /ከ2008-2012 ዓ.ም./ 2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ  መተግበር በጀመረችበች በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት በኢህአዴግ እየተመራች፣ የራሷን ውስጣዊ ሁኔታ መሠረት አድርጋ የቀመረችው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ ሊበታትናት አፋፍ ላይ አድርሷት የነበረውን ፋሽስታዊ ወታደራዊ አገዛዝ መገርሰስ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቦችዋን እግር ተወርች አስሮ ተመፅዋች ያደረጋቸውን ድህነትም በመደርመስ ላይ ነች፡፡ ይኸውም በ1988 ዓ.ም. ከድህነት ወለል በታች (Under absolute poverty) ይማቅቅ የነበረው 45.5 ከመቶ ህዝብ፣ በ2007 ዓ.ም.  ወደ 22 ከመቶ ዝቅ እንዲል አድርጋለች፡፡ ይህ በራሱ በጣም ትልቅ ድልና ዕድገት ነው፡፡ የነብስ ወከፍ ገቢም በ2003 ዓ.ም. 396 የአሜሪካ ዶላር የነበረው በ2007 ዓ.ም. 691 የአሜሪካ ዶላር ደርሷል፡፡ በማህበራዊ ዘርፍም ኢትዮጵያ የሚሊኒየም ግቦች ካሳኩ አገሮች አንዷ ሆናለች፡፡ የገቢ ክፍፍሉም “Gini coeffiencient” በሚባለው መለኪያ 0.3 በመሆኑ ፍትሃዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የቱሪስትና የውጭ ኢንቬስተሮች መዳረሻ ሆናለች፡፡ ለአብነት ያህል 1984 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሦስት/3/ የውጭ ባለሃብቶች ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በየዓመቱ በአማካይ በተለያዩ መስኮች የሚሰማሩ ከ500-600 የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገራችን ገብተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ2003 -2007 ዓ.ም. ባለው የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም በየዓመቱ በአማካይ ብር 10 ቢሊዮን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትሜንት(Foreign direct Investment) በመሳብ ወደ ተግባር ማሸጋገር ተችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት ብር 7.48 ቢልዮን ካፒታል ያላቸው 132 ፕሮጀክቶች ወደ ምርትና አገልግሎት ተሸጋግረዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ፈጥረዋል፡፡
ይህ ሁሉ ውጤት በዋነኛነት በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ሃሳብ አፍላቂነትና መሪነት የተቀመረው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች “የጋራ ፕሮጀክት” የሆነው የህዳሴው መስመር ነው፡፡ በአጭሩ የውጤቱ ባለቤቶች የሆኑት የኢፌዴሪ መንግሥት እና የኢትዮጵያ ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ቀንና ሌሊት በመረባረባቸው ድህነት ወገቡ እየተቆረጠ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ እየተጓዘች ነው ያለችው፡፡

ከኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የፈለቀው የህዳሴው መስመር ካስገኛቸው ውጤቶች በዋነኛነት የሚጠቀሰው ህብረ-ብሄራዊ የፌዴራሊዝም ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓታችን የኢትዮጵያ መሠረት መሆኑ፤ በአራቱም አቅጣጫ ያሉት የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ነው፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ ዋነኛ ጠላታቸው የሆነውን ድህነት በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና ገንዘባቸውን አቀናጅተው እንዲፋለሙ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ የነገ ብሩህ ተስፋ በቅርብ ርቀት አሻግሮ እያየ ራሱ ጥሮና ግሮ መለወጥ እንዳለበት በአስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅቶ እያደረገው ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ከ120 ዓመት በፊት አድዋ ላይ የጣልያን ቅኝ ገዢዎችን፣ እንዲሁም ከ75 ዓመታት በፊት ደግሞ የፋሽስት ጣልያን ድል አድርገው ነፃነታቸውን እንዳስከበሩ ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት 25 ዓመታት ካደረጉዋቸው ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ “የይቻላል” መንፈስ ጨብጠው “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን” በራሳቸው ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ ገንብተው፣ ትላንት መርፌ መሥራት አትችሉም የተባሉበት አንገት የሚያስደፋ አስተሳሰብ ሰብረው፣ የሚያስብ ጭንቅላትና የሚሠሩ እጆች ያሉዋቸው መሆናቸው እና ከተመፅዋችነት ወጥተው በራሳቸው ዓቅም የኢኮኖሚ ነፃነታቸውን በማረጋገጥ ላይ መሆናቸው በተጨባጭ ለዓለም ማሕብረሰብ አሳይተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ከተመዘገቡት ድሎችም ከሁሉም የላቀው የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ማስመዝገባቸው ነው ቢባል እውነታውን መግለፅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ 5ኛው ዓመት በዓለም “ታላቁ የህዳሴ ግባችን የማንነታችን አሻራ ያረፈበት የህዳሴአችን ብርሃን ነው” በሚል መሪ ቃል የታላቁ መሪያችን ታጋይ መለስ አደራ ጠብቀው ያጋመሱትን የህዳሴው ግድብ ግንባታ በተባበረ ክንድ ለማጠናቀቅ በተለያየ መልክ በመረባረብ ላይ ናቸው፡፡ ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብዝሃነትን ባከበረና ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን ባጠናከረ አገባብ የምንፈጥራት የበለፀገች ኢትዮጵያ ማሳያ ነው፡፡ በአጭሩ ይህ ዓለምን ያስደመመ በጐ ተግባር ለብዙህነታችን ዕውቅና መስጠታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም መከተላችን ትክክል ብቻ ሳይሆን በተባበረ ክንዳችን ምን ያህል ተአምር መሥራት እንደምንችል በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡

በቀጣዩ ወር የምናከብረው 75ኛው የአልማዝ ኢዮቤልዩ የነፃነት በዓላችንም ድህነትን እየደረመስን የቅድመ አያቶቻችን፣ የአያቶቻችን ታሪክ የምንደግመው ብዝሃነታችን ላይ በገነባነው አንድነታችን ላይ በመሆኑ ድሉ ድርብ ያደርገዋል፡፡
በአጭሩ ዓለምም ኢትዮጵያም የብዝህነት መናኸሪያ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከሁለት ወራት በኋላ በድምቀት የምናከብረው የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ 25ኛው ዓመትም ኢትዮጵያ ብዝህነት ፀጋ መሆኑን በውል ተገንዝባ በየትውልዱ የአንፀባራቂ ድል ሀገር መሆኗን ለዓለም በማሳየት ነው፡፡

Monday, 21 March 2016

የኢኮኖሚ ዋልታ…ቡና ቡና






 በገነት ደረጀ
የኢኮኖሚ ዋልታ…ቡና ቡና
የገቢ ምንጫችን...ቡና ቡና
የእድገታችን ገንቢ.. ቡና ቡና
ቡና ነው፤ ቡና ነው…ቡና ቡና
ብዙ ተዘምሮለታል፡፡ በአገርም በውጭም ያለው ቡናችንን ለመጎንጨት የታደለ ፍጠሩ ሁሉ አድናቆትን ችሮታል፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሳ አብሮ የሚነሳ የማንነታችን መገለጫም ጭምር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው ቡናችን፡፡ ኢትዮጵያውያኖች እርስ በእርስና ከአለም ህዝቦች ጋር ከሚጋሩት ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ቡና ነው፡፡ የቡና ስነስርዓት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለየ ስርዓት የሚከናወን ሲሆን ከመጠጥም በላይ ያለው ማህበራዊ ትርጉምና የሚፈጥረው ቤተሰባዊ ትስስር እጅጉን የጎላ ነው፡፡ በሀገራችን በአቦል፤ ቶናና በረካ የሚጠጣው ቡና በተለያዩ አካባቢዎች ለሃይማኖታዊ ክንዋኔም ይውላል፡፡ ቡና ከፍሬው ውጭ በሀረር አካባቢ ገለባው ወይም ቁጢ ይጠጣል፡፡ 

ከኢትዮጵያውያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ቡና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ10ኛው ክፍለ ዘመን ካሊድ በሚባል የፍየል እረኛ አማካይነት የኢንግሊዘኛ መጠሪያውን ካገኘበት ከፋ እንደተገኘ ይነገራል፡፡ ይህ አረቢካ ኮፊ የተባለውና በአለም ላይ እየተጠጣ ከሚገኘው ውስጥ 70 በመቶ የሚሸፍነው የቡና ዘር ልዩ ጠዓም ያለው ቡና ነው፡፡ በአለም ከፍተኛ ቡና አቅራቢ የሆነችው ብራዚል ሁለት ደርዘን የማይሞሉ የቡና ዓይነት ያሏት ሲሆን በኢትዮጵያ ግን በተለያዩ ቦታዎች የሚበቅሉ ወደ 10ሺህ የሚጠጋ የቡና ዓይነቶች እንደሚገኙ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህም መካከል እስከአሁን ግማሽ ያህሉን ብቻ ማወቅ እንደተቻለ የመስኩ ተማራማሪች ይናገራሉ፡፡ ይርጋጨፌ፤ ሲዳማ፤ ሀረርና ወለጋ የሀገራችን ዋናዋናዎቹ የቡና አምራች አካባቢዎች ናቸው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በቀን 1.2 ቢሊየን በዓመት ደግሞ ግማሽ ትሪሊየን ሲኒ ቡና ይጠጣል፡፡ በአፍሪካ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠጣው የቡና መገኛ በሆነችው በሀገራችን ሲሆን ቡና ከድፍድፍ ነዳጅ ቀጥሎ 2ኛው ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ምርት ነው፡፡ በአለም ላይ በቡና ግብይት በዓመት 90 ቢሊየን ዶላር ይዘዋወራል፤ በ70 ሀገራት ይመረታል፡፡ ብራዚል፤ ቬትናምና ኢንዶንኤዥያ የአለማችን ከፍተኛ ቡና አቅራቢ ሀገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያ በ5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡  

ኢትዮጵያ ለቡና ምርት ተስማሚ የአየር ሁኔታና አመቺ የሆነ 6ሚሊየን ሄክታር መሬት አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ በቡና የተሸፈነው ግማሽ ሚሊየን ሄክታር ወይም 3.68 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከሀገራችን ህዝብ ውስጥ 15 ሚሊየን ህዝብ በመስኩ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ሀገራችን ከምታመርተው የቡና መጠን 50 በመቶውን ብቻ ወደ ውጭ የምትልክ ሲሆን የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ ዋነኛ ምርትም ነው፡፡ ጀርመን፤ ጃፓንና ሰዑዲ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ ቀዳሚ ሀገራት ናቸው፡፡ አሜሪካም ቡናችንን በመግዛት ያላት ድርሻ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ የማግኘት አቅም ቢኖራትም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ  በዓመት በመቶ  ሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር  ከቡና ታገኛለች፡፡

የቡና ዋጋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም በተለይም አምራቹ አርሶ አደር የሚያገኘው ጥቅም እምብዛም አይደለም፡፡ ከአምራቹ ይልቅ ቡና ገዝተው እሴት ጨምረው የሚሸጡ ኩባንያዎችና ላኪዎች ከዋጋው  በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በአለም ገበያ የቡና ዋጋ መቀነስ አንዱ ምክንያት ሲሆን የአለም የአየር ንብረት ለውጥም እንደአጠቃላይ ምርቱን የሚፈታተን ችግር ነው፡፡ ሀገራችን ቡና ለማምረት ያላትን ከፍተኛ አቅም አሟጣ አለመጠቀሟ፤ የቴክኖሎጂ እጥረትና ከሚመረተው ቡና ግማሽ ያህሉ በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑ ሀገራችን ከቡና ማግኘት የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጉ ችግሮች ናቸው፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታትና ሀገራችን በመስኩ ያላትን አቅም እንድትጠቀም መንግስት  ለመስኩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የቡና ህብረት ስራ ማህበራት እንዲቋቋሙና አምራቹ አርሶ አደር የመደራደር አቅሙ እንድጎለብት ለማድረግ ውጤታማ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በመስኩ በተመቻቸው የኢንቨስትመንት እድል አቅም ያላቸው ባለሃብቶች ተሰማርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና የባለቤትነት ማረጋገጫ እንዲያገኝና በአለም አቀፍ ደረጃ የንግድ ምልክት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን ጅምር ውጤቶችም ተመዝገበዋል፡፡ ይህ ረዥም ሂደትና እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማስያዊ ግንኙነቶችን የሚጠይቅ ሲሆን እስከአሁን ባለው ሁኔታም የሲዳሞ፤ የይርጋጨፌና የሀረር ቡና ኢትዮጵያ የባለቤትነት ማረጋገጫና የንግድ ምልክትነት እንድትጎናጽፍ አስችሏታል፡፡

ሌላው አለም ስለኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ቡና በደንብ እንዲገነዘብ ለማድረግ አገራችን 4ኛውን አለም አቀፍ የቡና ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ በማስተናገድ የአለም አቀፍ ማህበረሰብና መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የሚሰብ ተግባር መከወን ችላለች፡፡ ጉባኤውን ከዚህ ቀደም ለንደን፤ ብራዚልና ጓትማላ ያዘጋጁ ሲሆን አገራችን ጉባኤውን ያስተናገደች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገርም ለመሆን በቅታለች፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ጉባኤ እንድትመረጥ ያደረጋት ዋነኛው ምክንያት ከዚህ ቀደም የተለያዩ አለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ በመቻሏና የቡና መገኛ ሀገር በሆኗም ነው፡፡

በጉባኤውም ስለ ቡናችንና በመስኩ ስላለው የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለማሳየት ተችሏል፡፡ በጉባኤው ማግስትም ሀገራችን 2ኛ ቡና አቅራቢ ለመሆን ከብራዚል ጋር መስራት ጀምራለች፡፡ ብራዚልም በመስኩ ያላትን ልምድ ለማካፈል ፈቃደኛ ሆናለች፡፡ የብራዚል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ድርድሮችም እየተካሄዱ ነው፡፡
ወደፊትም ኢትዮጵያ ከመስኩ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል በአለም አቀፍ ደረጃ ቀጣይት ባለው መልኩ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ችሮታን ለኢኮኖሚ እድገትና ለህዝቦቿ ተጠቃሚነት እንዲውል ለማድረግ በተዘረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎቿ በመጠቀም እየተጋች ትገኛለች፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስኬቶች እተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

Monday, 14 March 2016

የከተሞች ፈጣን ልማት ለሁለንተናዊ ዕድገት

 ገነት ደረጀ  

ሀገራችን ፈጣን የከተሞች እድገትና መስፋፋት እያስተናገዱ ካሉ የአለም ሀገራት መካካል አንዷ ነች፡፡ የከተሞች መስፋፋትና እድገት ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚያያዝ ሲሆን እንደ ቻይና፣ ብራዚልና አርጀቲና ወዘተ ያሉ አገራት ልምድም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ የከተሞች መስፋፋትና እድገት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ የኢንዳስትሪና አምራች ዘርፎች በቂ የሰው ኃይል እንዲኖራቸው በማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት መሳለጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡  

አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ 20 በመቶ የሚሆን ህዝብ በከተማ የሚኖር ሲሆን እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትንቢያ እኤአ እስከ 2040 ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የከተማ ህዝብ በሶስት እጥፍ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ ትላልቅ ከተሞች ደግሞ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የህዝብ ብዛታቸው ከዚህም በላይ እንደሚያድግ መረጃው ይጠቅሳል፡፡ ለአብነትም ሀዋሳ በ6እጥፍ፤ መቀሌ በ5 እጥፍ እንዲሁም አዳማና ባህርዳር ደግሞ በ4 እጥፍ የህዝብ ብዛታቸው እንደሚያድግ ተገምቷል፡፡ የቆዳ ስፋታቸውም በዚሁ መጠን እንደሚያድግ ይገመታል፡፡ በሀገራችን አሁን አሁን አዳዲስ ከተሞች ጭምር እየተመሰረቱ ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን የከተሞች እድገት በጥቅሉ ሲታይ በዓመት 5 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የከተሞች እድገት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና የእድገት ምልክት ቢሆንም በሌላ መልኩ ከተሞችን በእቅድ መምራት ካልተቻለ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንዲሁም ካባቢያዊ ቀውሶችን ያስከትላል፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግስት አቅምና ምላሽ ከከተሞች እድገትና መስፋፋት ፍጥነት ጋር መራመድ ካልቻለ ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡ በመሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ጫና ከመፍጠሩም በላይ እንደ እኛ ላሉት ታዳጊ ሀገራት ፈተናም ይሆናል፡፡

ከገጠር ወደ ከተማ የስራ አማራጮችን ለማግኘት የሚደረገውን የህዝብ ፍልሰት በገጠር የስራ እድሎችን በበቂ ሁኔታ በማመቻቸት መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ አሊያ ግን ከተሞች የሚመጣውን ሃይል የማስተናገድ አቅም ሳይገነቡ ውስብስብ ችግር ውስጥ መውደቃቸው አይቀሬ ነው፡፡      
ሌላው በከተሞች ከህዝብ ቁጥር መጨመርና መስፋፋት ጋር ተያይዞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ያለው የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ነው፡፡ ይህም ከቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ጋር የሚያያዝ ሲሆን ከግንባታ ተረፈ ምርቶች፤ የምግብ ትራፊ፤ ከሆስፒታሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዙ ሺህ ኪሎግራም ደረቅ ቆሻሻ በቀን ይመነጫል፡፡ እንደ ከተሞችና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር መረጃ ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ በአግባቡ የሚሰበሰበው 43 በመቶ ብቻ መሆኑ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላል፡፡ ቀሪው ቆሻሻ በየመንገድ ዳር፤ በሰዋራና ክፍት ቦታዎች እንዲሁም በየወንዞች ይጣላል፡፡ ከተማውን አቋርጠው ወይም በከተሞቻችን ዳር የሚገኙ ወንዞቻችን የደረቅ ቆሻሻ ብቻ ሳይሆኑ ከፋብሪካ የሚለቀቁ ኬሚካሎች፤ የዝቃጭና ከየመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻ ሰለባ መሆናቸውም ከብክለቱም በላይ የአካባቢና የውሃ ስነ ምህዳርን የሚያቃውስ ነው፡፡ በቆሻሻ አማካይነት የሚፈጠረው የአካባቢ ብክለት ተጽእኖ በግልጽ መታየት ጀምሯል፡፡ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ድምር ውጤት በሚያመጡት የአካባቢ ብክለት እና ከግል ንጽህና ጉድለት የተነሳ ከ10 ህጻናት አራቱ ለጤና መታወክ እንደሚጋለጡ የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሣያል፡፡




የአረንጓዴነት ማነስ ሌላው የከተሞች ፈተና ነው፡፡ አረንጓዴነት ከውበትም በላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ስልትም ጭምር ነው፡፡ በተወሰኑ ከተሞቻችን ለዚህ ተብለው የተከለሉ ቦታዎችና ፓርኮች እንዲሁም የመንገድ አካፋዮች በተወሰነ መልኩ እየለሙ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ከከተማ ከተማ ልዩነት ቢኖርም የመንገድ አካፋዮችም በአግባቡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሲለሙ አይስተዋሉም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ተደማምረው የከተማውን ኑሮ ውስበስብ በማድረግ  ከተሞች ምቹና ለኑሮ ተስማሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ይህ የሚያመላክተው የከተሞች እድገትና መስፋፋት በተለየ ሁኔታና በትኩረት መመራት እንደሚያስፈልገው ነው፡፡  

በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በከተሞች ሊኖር የሚችለውን ውስብስብ ሁኔታ በመረዳት ለከተሞችም ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፤ እየሰራም ይገኛል፡፡ ከተማቻችን ለኑሮ ምቹ አንዲሆኑና እድገታቸውን ማሰለጥ እንዲቻል ከገጠሩ ልማት ጋር ለማስተሳሰር ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ በቀጣይም አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ከከተማ አመራር ምደባ ጀምሮ በትኩረት  ይሰራል፡፡ ከከተሞች እድገትና መስፋፋት ጋር ተያይዘው ችግሮች እንዳይከሰቱ የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ ሲሆን ሌሎችንም ተጨማሪ አሰራሮችን ለመተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ለአብነትም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ስትራቴጂ፤ የከተሞች ኢንዳስትሪ ልማት ስትራቴጂ፤  የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስትራቴጂ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ የከተሞች የአረንጓዴነት ልማት ስትራቴጂና የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም የከተሞች መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የማህበራዊ አገልግሎቶችን በከተሞች ለማዳረስ የተደረጉ ጥረቶች የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረጉና ኑሮውን ያቃለሉት ሆነዋል፡፡ በተለይም በትላልቅ ከተሞች በቤቶች፤ መንገድ፤ በመብራት፤ በውሃና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ማስፋፋት ተችሏል፡፡

በከተሞች የሚስተዋሉ የስራ አጥነት ችግርን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማትና በህብረት ስራ ማህበራት በርካታ የከተማ ነዋሪዎችን ከስራ አጥነት በማላቀቅ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ እድል መፍጠር የሚችሉበትን ሃብት እንዲያጠራቅሙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በቀጣይም በከተሞች የሚስተዋለውን ድህነት በመቅረፍ ሀገራችን በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለከተሞች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ከተሞችን ውብ፤ ጽዱና ለኑሮ አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግም ግብ ተጥሏል፡፡ በተለይም የገጠር ልማትን ከከተማ ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም የከተማ ግብርናና  በከተሞች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ዛፎች በማልማት በአረንጓዴ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ይሰራል፡፡

በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሌላው ሲሆን በ11 ዋና ዋና ከተሞች ከመጭው በጀት ዓመት ጀምሮ ይተገበራል፡፡ በዚህም 4.7 ሚሊየን የከተማ ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በከተሞቻችን የሚስተዋለውን የቆሻሻ ችግር ለመፍታትም ስንታንዳርድ ተዘጋጅቷል፡፡

በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እቅዶችን እቅዶ በመተግበር ህዝባዊነቱንና ለሀገር እድገት ያለውን ቁርጠኝነት እያስመሰከረ ከህዝቡ ጋር ከአንዱ የድል ጎዳና ወደ ቀጣዩ እያተሸጋገረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከተሞቻችንን በማዘመን ውብ፤ ጽዱ፤ ለኑሮ ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደተለመደው ሁሉ ህዝቡ ለስትራቴጅዎቹ መተግበር የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡