EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 28 March 2016

የህዳሴው አብሳሪ-የታሪክ አሻራችን ቋሚ ሃውልት

የማነ ገብረስላሴ
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓም በቤንሻንጉል ክልል የምትገኝ ጉባ የተባለች ስፍራ አንድ ድንቅ ታሪክ ታስተናግድ ዘንድ ታጨች፡፡ እንደ ቀደምት የታሪክ ስፍራዎች  ስሟ በታሪክ መዝገብ እንዲሰፍር፣ እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሃረር፣ ጣና.. ወዘተ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችላት አንድ ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታ በጉያዋ እንዲከናወን በህዳሴው መሃንዲስ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በዚህች ስፍራ ተበሰረ፡፡ ለዘመናት ለሌሎች አገሮች ሲሳይ ለኢትዮጵያውያን ግን ከዘፈንና ከእንጉርጉሮ ያለፈ ጠብ የሚል ጥቅም መስጠት ያልቻለው የአባይ ወንዝ ፊቱን ወደ አገሩ አዙሮየአገራችን ህዳሴ ብስራት እንዲሆን ኢትዮጵያውያንም ከድህነት ማምላጫ መንገዳቸውን ብሩህ የሚያደርግላቸው ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡ በአባይ ወንዝ ላይ የቁጭት እንጉርጉሮ ሲያሰሙ የኖሩት ኢትዮጵያውያንም ይህንን ብስራት ሲሰሙ ደስታቸውን ለመግለጽ ቃላት አጠራቸው፡፡ ስሜታቸውን በጭፈራና በእልልታ ገለጹ፡፡

የአባይ ወንዝ የአገራችንን ውሃና ለም አፈር ጠራርጎ እየወሰደ ለሌሎች ህዝቦች እራትና መብራት ለኢትዮጵያን ደግሞ የኪነ ጥበብ ማድመቂያ ብቻ ሆኖ ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያውያን በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት ከአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የልማት ስራ ማከናወን ሳይችሉ ዘመናት አልፈዋል፡፡ በዚህም ስለ አባይ ሲነሳ በቁጭት የማይንገበገብ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ግን ወቅቱና ሁኔታው ፈቀደና “ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት የልማት ፕሮጀክት መስራት አይችሉም” የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ ሊሰብር የሚችል፣ ታሪክ የሚቀይር ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ፡፡

መንግስት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲያበስር ፕሮጀክቱን ከዳር ለማድረስ ያልተቆጠበ የህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገለጸ፡፡ በፕሮጀከቱ መጀመር ወደር የሌለው የደስታ ማዕበል ውስጥ የነበረው ህዝባችን የመንግስትን ጥሪ ተከትሎ  ለግድቡ ግንባታ መሳካት አስፈላጊውን መስዋዕት እንደሚከፍል አረጋገጠ፡፡ቃሉንም ጠብቆ የማያቋርጥ ድጋፉን በማድረግ ለቃሉ ታማኝነቱን በተግባር አሳየ፡፡   ዝቅተኛ የሆነ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ጭምር ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ በልገሳ መልክ ለመስጠት አላቅማሙም፡፡  

ግድቡ በተጀመረበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጨፍ ለህዳሴ ግድብ የሚሆን ቦንድ ሲገዙ ያገኛኋቸው በግምት ዕድሜያቸው  70 ዓመት የሚገመቱ አዛውንት ያሉኝን ላስታውሳችሁ፡፡ አዛውንቱ የአባይ ወንዝ ያለ ጥቅም መፍሰስ እጅግ የሚቆጫቸው ነገር እንደነበርና አሁን ቁጫታቸውን ቦንድ በመግዛት እንደሚወጡ ገልጸው በእጃቸው የያዙትን በትር ከመሬቱ ላይ እያላተሙ አንገታቸውን ወደ ላይ ሰቅለው “ፈጣሪ የዚህን ግድብ ግንባታ መጨረሻን ሳያሳየኝ እንዳይወስደኝ እጸልያለሁ” አሉ፡፡ በባንኩ ውስጥ ያገኛኋችው አንዲት እናትም የወር ገቢያቸው ከ500 ብር ያልዘለለ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ያ ግን አልገደባቸውም  እኚህን እናት ቦንድ ለመግዛት የቀደማቸው አልነበረም፡፡   “አባይ በአገሩ አረፍ ብሎ ህዝቦቹን ሊጠቅም ጉዞ ሲጀምር ካለን ዝቅተኛ ገቢም ቢሆን አብቃቅተን ከዳር ሳናደርሰው አንተኛም” በማለት ወኔ በተሞላበት ንግግር ግድቡ እውን እስኪሆን ድጋፋቸው እንደማይለይ አጫወቱኝ፡፡ እነዚህን ለአብነት አነሳሁ እንጂ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲበሰር በደስታ ስካር ያልፈነጨ፣ ደስታውን በጭፈራና በእልልታ ያልገለጸ ዜጋ አልነበረም፡፡ ተማሪው፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ ሴቱ፣ ወንድ፣ አባቶችና እናቶች …መላው ህዝብ ከጫፍ ጫፍ በግድቡ ግንባታ መጀመር ደስታውን በተለያዩ መንገዶች በመግለፅ የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን አሳየ፡፡




6ሺ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ይህ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኃይል አቅርቦታችንን በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳሽ ኃይል ማመንጨት ከጀመረች በርካታ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም እስከ አሁን ከተገነቡ በርካታ ፕሮጀክቶች የጊቤ 3ን ሳይጨምር እየመነጨ ያለው  ከ2ሺ300 አልዘለለም፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚመነጨው 6ሺ ሜጋ ዋት መሆኑን ሲታይ ግን እውነትም የአባይ ወንዝ በቅርቡ ለአገሩ ህዝቦችም እራትና መብራት እንደሚሆን ማረጋገጫ ነው፡፡
የግድቡ ግንበታ መጀመር ከኃይል ማመንጨት በሻገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡  አገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ በቆየው ሰላም እጦት፣ ድህነትና ኃላቀርነት የልማት ፕሮጀክቶችን ማከናወን ተስኗት ቆይቷል፡፡ በተለይም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን መገንባት ካለ ዓለም አቀፍ ዕርዳታና ብድር ውጭ የማይታሰብ ጉዳይ ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግብጽ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የልማት ስራዎች እንዳትሰራ በተለያዩ መንገዶች ጫና ከመፍጠር ጀምራ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ ማድረጓ ደግሞ በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን ተነፍገን ቆይተናል፡፡ እናም በአባይ ወንዝ በራስ አቅም ይህንን በግዙፍነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ግድብ ለመስራት ማቀድ “የአይቻልም” መንፈስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሰበር ከማስቻሉ ባለፈ በራስ መተማመንን ከፍ ያደረገ ፕሮጀክት እንዲሆን አስችሏል፡፡ ኢትዮጵያ ታሪክ የሚነገርባት አገር ብቻ ሳትሆን አዲስ ታሪክ የሚሰራባት አገር መሆንዋንም ዳግም ያረጋገጠ ብርቅዬ ፕሮጀክት የሆነውም ለዚህ ነው፡፡

በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ለዘመናት ሳይቻል በመቆየቱ በነበረው ቁጭትና አሁን ካለው  ከፍተኛ የልማት ፍላጎት ፕሮጀክቱ መላው ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ በመሆኑ ብሄራዊ መግባባትን በመገንባት ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ  ሆ…ብለው በጋራ ድጋፋቸውን የገለጹለት ብቸኛው የልማት ፕሮጀክትም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ “ይህ ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ነው ያረፈበት ነው”ያለውም ለዚህ ነበር፡፡ በዚህም ፕሮጀክቱ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው የህዝቦች አንድነት ይበልጥ ያጠናከረ  ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ውጭ በመሸጥ ገቢ እንድታገኝ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የአከባቢውን አገሮች በኃይል አቅርቦት በማስተሳሰር የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን ተመራጭ የኃይል ማዕከልም ያደርጋታል፡፡

ግድቡ አገራዊ አንድነትን ከማጠናከሩ በተጨማሪ ከወንዙ ተፋሰስ አገሮች ጋር ያለው ግንኙነት በጋራ መጠቃቀምና መተባበር እንዲሆን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በወንዙ ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር ሲታይ ወንዙን በፍትሓዊነት የመጠቀም አስተሳሰብ እያደገ ነው፡፡ በተለይ ሆስኒ ሙባረክ የስልጣን ዘመን በተሳሳተ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ የግብጽ ህዝብ የነበረው ፍጹም የተሳሳተ ግንዛቤ አሁንም ቀሪ ስራ የሚጠይቅ ቢሆንም ለውጦች አሉ፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድባችን  ያስገኘው ሌላው ትሩፋት የቁጠባ ባህል ማሳደጉ ነው፡፡ መላው የአገራችን ሀዝቦች ለግድቡ ግንባታ በነጻ ቦንድ በመግዛት ፈቃዳቸው የነበረ ቢሆንም በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ካለው ህዝባዊ ባህሪ በመነሳት ልገሳው ወደ ቁጣባ ቦንድ እንዲቀየር አድርጓል፡፡ ይህም ዜጎች በአንድ በኩል ገንዘባቸውን እየቆጠቡ በሌላ በኩል እንደ ዓይን ብሌናቸው የሚሳሱለትን ግድብ እየደገፉ ታሪክ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እስከ አሁንም ዜጎቻችን የ12 ቢሊዮን ብር ቦንድ ለመግዛት ቃል የገቡ ሲሆን እስከአሁን 8ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡
ህዝብና መንግስት እጅና ጓንት ሆነው የህዳሴ ግድብን ለመገንባት በከፍተኛ ወኔ በሚረባረቡበት ወቅት አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተለመደው ከመልካሙ ነገር በተቃራኒ ጎራ ሲሰለፉ ተስተውሏል፡፡ ፕሮጀክቱ መስከረም ወር 2003 ዓም ይፋ በተደረገው አንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተካተተና አስቀድሞ የታቀደ መሆኑን ግልጽ ቢሆንም እነርሱ ግን በግድቡ ዙርያ መተማመን እንዳይኖር በማሰብ ግድቡ በወቅቱ በዓረብ አገራት አጋጥሞ የነበረውን ህዝባዊ ዓመጽ ለመቀለበስ በጥድፊያ የተጀመረ እንደሆነ ለመስበክ ጥረት አድርገዋል፡፡ ህዝቡ ለድጋፉ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማኮላሸትም የተለያዩ ጥረቶችን አደረጉ፡፡ ይሁንና ሰሚ አላገኙም፡፡ ይልቁንስ ምንም ዓይነት ህዝባዊ አጀንዳ እንደሌላቸው ህዝቡ በግልጽ ተገነዘበ፡፡ በዚህም ከህዝቡ ይበልጥ ተነጠሉ፡፡ የጽንፈኛ ኃይሎች ኃይሎች የውሸት ፕሮፖጋንዳ አስመለክቶ ጓድ መለስ በወቅቱ እንዲህ ብሎ ነበር ‹‹እነዚህ የተለያዩ መፈክሮችና ማደናገርያዎች ተደምረው አንድ መልዕክት ነው የሚያስተላልፉት፣ ይሄ ግድብ እንዳይሰራ ፈንጂ ከማጥመድ ጀምሮ የሃሳብ ፈንጂ እስከማጥመድ ድረስ ባለው ማዕቀፍ ውስጥ በሙሉ አቅማቸው እንደሚረባረቡ ነው የሚያሳየው፣ አሁን እነዚህ ነገሮች ተብራርተው ቢያልቁ በሚቀጥለው ጊዜ ሌላ ማደናገርያ መፈብረካቸው አይቀርም››፡፡ በእርግጥም ጓድ መለስ እንዳለው በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የልማት ስራዎችን ሲከናወን የሚያማቸው እነዚህ ኃይሎች በግድቡ ግንባታ ዙርያ ያልፈበረኩት ውሸት የለም፣ ሰሚ አጡ እንጂ፡፡

ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንበታ የአሉባልታ ማዕበል ሳይገድበው ከግማሽ በላይ ተከናውኖ አሁን የግንባታው ሂደት በላቀ ፍጥነት እየተካነወነ ይገኛል፡፡ የህዝቡ ተሳትፎም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአዲስ የለውጥ ማዕበል ገብታ ድንቅ ታሪክ እየሰራች እንደሆነችም አንድ ማሳያ ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment