EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 27 March 2016

ውስብስብና አስቸጋሪ የትግል ፈተና ያልበገረው ረጅሙ የኦህዴድ የድል ጉዞ!!







በገነት ደረጀ
በኢትዮጵያ 1980ዎቹ መጀመሪያ ህዝቡ ከበዝባዡ የፊውዳል ስርዓት ለመላቀቅ ያደረገውን ትግልና ድል ነጥቆ ወደ ስልጣን ለወጣው ደርግ ፈታኝ ዘመን ነበር፡፡ ወቅቱ በደርግና የህዝቡን ነጻነት ለማስመለስ ከሚታገሉ ድርጅቶች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ በህወሓትና በኢህዴን መሪነት በህዝቡ በተደረገው ትግል አብዛኛው የሰሜኑ ክፍል ከጨቋኙ የደርግ ስርዓት ነጻ ለመውጣት ችሎም ነበር፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ያለው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም ደግሞ ሰፊ በሆነው ኦሮሚያ ውስጥ ሁነኛ አታጋይ ድርጅት ባለመኖሩ የደርግ እድሜ እንዲራዘምና ትግሉ ፈታኝ እንዲሆን አደረገው፡፡

በኦሮሞ ሀዝብ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችም የረባ እንቅስቃሴ ማድረግ ባለመቻላቸው ወደ ክልሉ ዘልቀው እንዲገቡ ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ድጋፍ ቢደረግላቸውም ትግሉን ከዳር ማድረስ ተስኗቸው ነበር፡፡ ለአብነትም ኦነግ ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲገባ በህወሓት ድጋፍ ተደርጎለት የነበረ ሲሆን የህወሓት ሰራዊት ቀድሞ ወደነበረበት የትግል ስፍራ ሲመለስ ኦነግ ከደርግ ሸሽቶ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተመለሰ ድርጅት ነበር፡፡ በሌላ ወቅትም በሻዕቢያ ድጋፍ ቢደረግለትም በአሶሳ ከተማና አካባቢው የነበሩ አማራዎችን በሚዘገንን ጭፍጨፋ ካጠፋ በኋላ የደርግን ጥቃት መቋቋም ተስኖት እንደተለመደው ወደ ሱዳን ጠረፍ ለማፈግፈግ የተገደደ ድርጅት ነበር፡፡

ኢትዮጵያን ብሎም የኦሮሞ ህዝብን ከጨቋኙ የደርግ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ከሀገራችን ህዝብ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ክብሩንና ነጻነቱን ለማስመለስ በተናጠል ትግል ሲያደርግ የነበረውን የኦሮሞ ህዝብ በተደራጀ ሁኔታ ትግሉ ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነ፡፡ ህዝቡን ወደ ተደራጀ ትግል ማስገባት ብቻ ሳይሆን  በኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የሀብት ምንጭ ደርግ እንደይጠቀምና መዋቅሩን መበጣጠስ ለድሉ መፋጠን ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ታመነበት፡፡ በመሆኑም ዴሞክራሲያዊና ጠንካራ የህዝባዊ መሪ ድርጅት አስፈላጊነት በኦሮሚያ አንገብጋቢ ሆነ፡፡

በወቅቱ በኢህዴን ውስጥ ሲታገሉና በትግራይ ነጻ መሬት ላይ የነበሩ፤የኦሮሞ ህዝብ ጭቆናና በደል አንገብግቧቸው ለመታገል የወሰኑ የኦሮሞ ታጋዮች ተሰብስበው የኦሮሞ ህዝብ ትግልን መምራት የሚችል ድርጅት ለመመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለ8 ወራት ዝግጅት አደረጉ፡፡ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ በጠራ መስመር አደራጅቶ ለመምራት ከዚህ ቀደም በህዝቡ ስም ተመስርተው ምንም ውጤት ማምጣት ስላልቻሉ ድርጅቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ሂደትን በጥልቀት በመገምገም ለአዲሱ ድርጅት የትግል ፕሮግራም፤ ስትራቴጂና ስልቶች እንዲሁም መተዳደሪያ ደንብ ታጋዮቹ ቀረጹ፡፡

ለአዲሱ ድርጅት ምስረታ በተደረገው ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ቅድመ ሁኔታ ሀገራችን አስከፊ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና የተንሰራፋባት ሀገር እንደሆነችና ሰፊው የኦሮሞ ህዝብም እንደሌሎቹ ወንድም ህዝቦች በተመሳሳይ ጭቆና የሚሰቃይ ህዝብ እንደሆነ በግልጽ ተቀመጠ፡፡ ይህንን ለማስወገድም ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ሊካሄድ እንደሚገባና የደርግ የአፋና መዋቅሮች ሊፈራርሱ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ እናም የስምንት ወራት የዝግጅት ጊዜን ተከትሎ ከመጋቢት 15-17 ቀን 1982 ዓ.ም መስራች ጉባኤ ተካሄደ፡፡ ለሶስት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ ከተለያዩ አካላትና  አካባቢዎች የመጡትን ጨምሮ 225 መስራቾች በተሳተፉበት ከ26 ዓመታት በፊት መጋቢት 17 ቀን 1982ዓ.ም የኦሮሞን ህዝብ ትግል መርቶ ለድል ለማብቃት የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ድርጅት/ኦህዴድ በይፋ ተመሰረተ፡፡

ኦህዴድ በአባላቱ በእህት ድርጅቶች ውስጥ ሆኖ ሲታገልም ሆነ ራሱን ችሎ ተደራጅቶ እንደ ድርጅት ሲመሰረት ቀደምት የትግል ድርጅቶች ያሳለፏቸውን ችግሮችና እንቅፋቶች ባለመድገምና የተቀሰሙ ልምዶችን በመቀመር ለመንቀሳቀስ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡ በሌላም በኩል ጭቆናውና አፋናው ያንገሸገሸው ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ትክክለኛ መስመር ይዞ በህዝቡ ውስጥ ሆኖ የሚያታግል ድርጅትና አመራር የሚፈለግበት ወቅት መሆኑም ለኦህዴድ ምስረታና መጠናከር አጋጣሚው የተመቻቸ ነበር፡፡ ትግሉን መርቶ ከዳር ለማድረስ የመስራች ታጋዮች ዝግጁነትና ቆራጥነት ሌላው ድርጅቱ ጠንካራ እንዲሆን ያስቻለ ነበር፡፡  

በአጠቃላይ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል በትክክለኛ መስመር በመምራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርና ትግሉን ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግል ጋር በማስተሳሰር አኩሪ ድል መቀዳጀት አስፈላጊ በሆነበት ወቅት የተወለደና ጥንካሬውንና ጽናቱን ገና በጠዋቱ ያስመሰከረ ድርጅት ሆነ፡፡  በወቅቱ የማይነጥፍ የህዝብና የድርጅቶች ድጋፍ የነበረው ድርጅት በመሆኑም በአጭር ጊዜ ወስጥ ተጠናክሮ ብሔራዊና ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የቻለ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በትጥቅ ትግል የድርጅቶች ታሪክ በፍጥነት ማደግና መመንደግ የቻለ ድርጅት ነው ኦህዴድ/ኢህአዴግ፡፡

በኦሮሞ ህዝብ ስም ተመስርተው ረጅም እድሜ ካስቆጠሩና ከጠባብ ድርጅቶች በተለየ አሰላለፍ የህዝቡን ትግል በአብዮታዊ ዴሞክራሲዊ አቅጣጫ ለመምራት ኦህዴድ ተመስርቶ ወዲያው ወደ ትግል ሲገባ በታሪኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምስረታው ቀጥሎ 2ኛውን ስኬታማና ታሪካዊ ክስተት አስመዘገበ፡፡ ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኦሮሚያ በመግባት በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ጋር የትግል ግንኙነት ጀመረ፡፡  ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኦህዴድ ህዝቡን እያደረጀና እያስታጠቀ ከደርግ ጋር መፋለም ጀመረ፡፡

ኦህዴድ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደራጀ ሁኔታ በጦርነት ላይ የተካፈለው ዘመቻ ቴዎድሮስ በመባል የሚታወቀውና ጎጀምና ጎንደርን ነጻ ለማውጣት በኢህአዴግ በታቀደ ዘመቻ ነበር፡፡ ይህ ዘመቻ እነዚህን አካባቢዎች ከደርግ ነጻ ካወጣ ደግሞ ኦህዴድ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ዘልቆ እንዲገባ የሚያስችል ነበር፡፡ በአምስት ሪጅመንቶች አቅሙን ያደራጀው ኦህዴድ ወደ ጎጃም በመሻገር ዘመቻ ቴዎድሮስ ላይ በተሳካ ሁኔታ በመሳተፍ ብዙም ሳይቆይ በምዕራብ በኩል ወደ ክልሉ ለመግባት ቻለ፡፡ ቀጥሎም በቢሊሱማ ወልቂጡማ ዘመቻ ደርግን በመደምሰስ ከወለጋ እስከ አምቦ ያለውን ከደርግ ነጻ ማውጣት የነበረና በስኬት የተጠናቀቀ ዘመቻ በማድረግ ከተመሰረተ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደርግን ለመደምሰስ በተደረገው መራራ ትግል ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ለድል በቅቷል፡፡



የኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚከበረው በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማዕቀፍና ትስስር ውስጥ መብቱ ተከብሮ በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት አብሮ ሲኖር ነው ብሎ አምኖ ትግሉን የጀመረው ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከደርግ መውደቅ በኋላም ለአዲስቷ ኢትዮጵያ መፈጠርና መጠናከር ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ከእህት ድርጅቶች ጋር በመሆን ኦህዴድ/ኢህአዴግ ደማቅ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ በሽግግር መንግስት ምስረታና በአዲስቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ውስጥ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በልማት ዙሪያ ህዝቡን የመራና ውጤት ያስዘገበ ድርጅት ነው -ኦህዴድ/ኢህአዴግ፡፡

ኦህዴድ የፌዴራል ስርዓታችን እንዲጠናከር በሚደረገው የትግል  እንቅስቃሴም ይሁን የኦሮሞ ህዝብን ብሔራዊ መብት የሚያስጠብቁ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን የማቋቋም፤ የመገንባትና የማጠናከር፤ በራሱ ቋንቋ የሚሰራ መንግስታዊ መዋቅር የመግንባት፤ ትምህርት እንዲስፋፋና ህዝቡ በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማርና እንዲተዳደር የማድረግ፤ የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ፤ በተለይም በጭቆናው ምክንያት ተስፋ ቆርጦ የማምረት አቅሙ ተሟጦ የነበረውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር በማነሳሳት በርካታና ድንቅ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ አስከፊ መደባዊና ብሔራዊ ጭቆና ስር ወድቆ የጨለማ ህይወትን ሲገፋ የነበረውን ህዝብ በድል ጎዳና በመምራት ወደ ልማታዊና ሰላማዊ ምዕራፍ በማሻገር ሀገራችን በፈጣንና ተከታታይ የእድገት ጎዳና እንድትራመድ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የበኩሉን ድንቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኦህዴድ/ኢህአዴግ ያሳለፋቸው 26 ዓመታት አልጋ በአልጋ ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታ፤ እራሱን እያረመና ህዝባዊነቱን ይበልጥ እያጠናከረ ክልላዊና ሀገራዊ ተልዕኮውን የተወጣ ድርጅት ነው፡፡

ኦህዴድ ከትጥቅ ትግሉ በኋላ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ስርዓት እንዲገነባ እየተደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ ትግል እየተጫወተ ያለው ሚና እጅግ ገዝፎ የሚታይ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኦህዴድ በዴሞክራሲና በልማት ትግል የሚያደርግበት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰፊና በርካታ ህዝብ የሚገኝበት በመሆኑ ይህንን ሰፊ ግዛት የመምራትና በርካታ ቁጥር ያለውን ህዝብ በዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ስርዓት ግንባታው በአግባቡ አደራጅቶ ተሳታፊ እንዲሆን የሚደረገው ትግል ሰፊና ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል በክልሉ በኦሮሞ ህዝብ ስም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ትግላቸውን ማስቀጠል ሲሳናቸው በተቃራኒው በክልሉ ህዝብ ጉያ ተሸሽገው በህገ ወጥ መንገድ እየተገነባ ያለውን ዴሞክራሲና በኢኮኖሚው የተመዘገቡ የልማት ትሩፋቶችን በሚያጠፋና በሚንድ አፍራሽና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት ላይ በመሰማራት እያደረሱ ያለው ጫና በተለያዩ ወቅቶች ባህሪውን በመቀያየር መቀጠሉ ኦህዴድ በዴሞክራሲውና በልማቱ የሚያደርገውን ትግል ውስብስና አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይሁንና በትግሉ ውስብስብና አስቸጋሪ መሆን መፈተን ቢችልም ያልተበገረውና ከረጅም ጉዞው ያልተገታው ኦህዴድ/ኢህአዴግ አሁንም በድል ታጅቦ መገስገሱን ቀጥሎበታል፡፡

በሀገራችን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት እየተደረገ በሚገኘው ርብርብ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የውስጥ ትግልን በማጠናከር ችግሮችን እየፈታ ድሎቹን እያጠናከረ ይቀጥላል፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት! ድልና ድምቀት ለኦህዴድ/ኢህአዴግ 26ኛ ምስረታ በዓል!        





No comments:

Post a Comment