አጠቃላይ
ዳሰሳ
የአፋር
ብሔራዊ ክልል ከትግራይ በሰሜን ምዕራብ፣ ከአማራ በደቡብ ምእራብ እና ከኦሮሚያ በደቡብ በኩል የሚዋሰን ሲሆን ከኤርትራ ጋር በሰሜን
ምስራቅ፣ ከጅቡቲ ደግሞ በምስራቅ በኩል ይዋሰናል። የክልሉ ሕዝብ በ27,000 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፍራ ላይ ይኖራል። በአምስት
የዞንና በ32 የወረዳ አስተዳደሮች የተዋቀረው ክልሉ በምስራቅ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ከሌላው አለም ጋር የሚያገናኝ የተፈጥሮ ድልድይ
ሲሆን የብሔረሰቡ አባላት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በጅቡቲ ሰፍረው ይገኛሉ።
የአፋር
ክልል በ39o34’ እና 42o 28’ ኬክሮስና በ8o 49’ እና
14o 30’ ኬንትሮስ ላይ ይገኛል። የክልሉ መልክአምድራዊ አቀማመጥ በአብዛኛው ረባዳና ዝቅተኛ ነው። ሙሳ አሊ
የተባለው ከፍተኛው ተራራ 2063 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ይሆናል። ዝቅተኛው ደግሞ 115 ሜትር ከባህር ወለል በታች ያለውና
በአለም የመጨረሻው ዝቅተኛው እንደሆነ የሚነገርለት ዳሎል የሚባለው ስፍራ ነው። የክልሉ 35.47 በመቶ የሚሆነው መሬት ከባህር
ወለል በላይ ከ400 ሜትር እስከ ከባህር ወለል በታች 116 ሜትር፣ 51.44 በመቶ ያህሉ ደግሞ ከ400 እስከ 900 ሜትር ከባህር
ወለል በላይ፣ 13 ከመቶ ያህሉ ከ900 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ይገኛል።
በክልሉ
የሚገኘው የአሰል ሃይቅ /ከባህር ወለል በታች 155 ሜትር/ እና ዳሎል /ከባህር ወለል በታች 116 ሜትር/ በዝናብ ሰዓት የሙቀት
መጠናቸው እስከ 25 ዲግሪ ሴሊሼዬስ ስለሚደርስ በአለም የመጨረሻዎቹ ሞቃታማ ስፍራዎች ያስብላቸዋል። እነዚህ ስፍራዎች ከመስከረም
እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ውስጥ እስከ 48 ዲግሪ ሴሊሼዬስ የሚደርስ የሙቀት መጠን አላቸው።
የአፋር
ሕዝብ ከኩሽ ነገዶች አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ500 ዓ.ዓ እስከ 15 ዓ.ም ድረስ ከየመን፣ ከግብጽ፣
ከአክሱም ነገሥታት ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውና በስተሰሜን ከዳህላክ ደሴቶች ጀምሮ በስተደቡብ እስከ ዘይላ ድረስ ባለው አካባቢ
እንደኖሩ ይነገራል።
የአፋር
ስምጥ ሸለቆ የታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካል ሲሆን ይህም የጥንታዊ የሰው ልጅ ቅሪተ አጽምና ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ መሳሪያዎች
የሚገኙበት ስፍራ ነው። እነዚህ ቅሪተ አካል በመገኘታቸው የሰው ልጅ አመጣጥን በሚመለከት ምርምር ለሚያደርጉ አጥኚዎች ክልሉ የወርቅ
ጉድጓድ ያህል ቀልባቸውን ለመሳብ በቅቷል። እስከ ዛሬ የተደረጉ ጥናቶችም አፋር የሰው ልጅ መገኛ እንደሆነች አመላካች ናቸው።
በአፋር
ክልል ከሚገኙት ታሪካዊ ስፍራዎች አንዱ በሆነው በመካከለኛው አዋሽ 6 ሚሊዮን አመት ያስቆጠሩ ቅሪተ አካሎች ተገኝተዋል። ከእነዚህም
መካከል አርዲፒተከስ ከደባ የተባለውና እ.ኤ.አ.በ2001 የተገኘው ቅሪተ አፅም የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። ቀጥሎም አርዲፒተከስ
ረሚደስ ከ1994 - 1995 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የተገኘ ሲሆን ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል። ሦስተኛው አውስትራሎፒተከስ ነመንሲስ
ሲሆን በ2006 ዓ.ም የተገኘ ነው። አውስትራሎፒተከስ ፋሪስስ /ሉሲ/ በ1978 ዓ.ም የተገኘች ስትሆን ለሰው ቅርብ የሆነች ዝርያ
መሆኗን ሳይንቲስቶች ያምናሉ። አውስትራሎፒተከስ በ1999 ዓ.ም ላይ በመካከለኛው አዋሽ የተገኘ ትልቅ አጥቢ እንስሳ ከትልልቅ የማደኛ
ድንጋይ መሳሪያዎቹ ጋር ተገኝቷል። በ2002 ዓ.ም ውስጥም ቡሪ በተባለ ስፍራ ሆሞኢረክተስ የተባለ ዝርያ መገኘቱ ይፋ ሆኗል። በ2003
ዓ.ም ሄርቶ ቡሪ በተባለው ስፍራ ከ160 ሺህ አመታት በፊት የነበረና የተሟላ ቅርጽ ያለው የሆሞሳፒያን ዝርያ ተገኝቷል።
ሃዳር
ተብሎ የሚታወቀው ስፍራ ሉሲና ሌሎች ቅረተ አካሎች የተገኙበት በመሆኑ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት
የአለም ታሪክ ቅርስ አካል ሆኖ ተመዝግቧል። በመሆኑም አካባቢው የኢትዮጵያና የምስራቅ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአፍሪካን
ታሪክ ያኮራ አዲስ የሳይንስ ምርምር እንዲካሄድ በር የከፈተ ለመሆን በቅቷል።
የክልሉ ቁሳዊ
ባህሎችና አሰራራቸው
ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣
የአፋር ሴቶች ከቆዳ፣ ከኡንጋ /ዘምባባ/ የተለያዩ የቤት
ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ይሰራሉ። ኡንጋን የተለያዩ ቀለማት በመንከር ወይም በማቅለም ለስፌት ያዘጋጁታል። መገልገያ ቁሳቁሶቹ
ውብና ሳቢ እንዲሆኑ ኡንጋኑን ከማቅለማቸውም በተጨማሪ በቆዳ ነት /በለስላሳ ቆዳ/ ላይ የተለያዩ መልክ ያላቸው ስንደዶዎችና ዛጎሎችን
በመጠቀም ያስጌጧቸዋል።
ባህላዊ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎቹ ሙዴይና እና መካሮ የተባሉ
መስፊያዎችን ለማያያዥነት ይጠቀማሉ። ሁሉም የስፌት እቃዎች የሚዘጋጁት በእጅ ነው። የአሠራራቸውም ትውፊታዊ እውቀትና ክህሎት ሲወርድ
ሲዋረድ የመጣ ነው። በአሁኑ ጊዜ የክልሉ ሴቶች በማህበር ተደራጅተው ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶቻቸውን ለተለያዩ ከተሞች እያቀረቡ
ይገኛሉ። ዋና ዋና የሚባሉትን ባህላዊና የወግ እቃዎችንም እንደሚከተለው
ለማቅረብ ሞክረናል።
ለምንጣፍና
ለመኝታ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች
ሀ.
ወሉ /wallu/፤
ለመኝታ ወይንም ለምንጣፍ የሚያገልግል ከከብት ቆዳ የሚሰራ፣
ለ.
ሰላት ፊዶ፤
ከኡንጋ ለመስገጃ አገልግሎት የሚሠራ፣
ሐ.
ዲቦራ፤ ከኡንጋ የሚሰራ ለግመል መጫኛ የሚያገልግል በጭነት ወቅት ወገቡን ጭነቱ እንዳይልጠው መከላከያ
መደላድል /ዳውላ/ ነው፣
መ. ፊዲማ፤ ለመሬት ምንጣፍ የሚውል ሲሆን የሚሰራውም ከሰሌን /ኡንጋ/ ነው። ሰሌኑ ቀለም ሳይነከር ወይም ተነክሮ ለምንጣፍ
ውበት ሊሰጥ በሚችል መልኩ የተለያዩ ቅርፆችን በማውጣት ይሰራል።
ፊዲማ (ምንጣፍ)
|
የወተት ዕቃዎች
የብሄረሰቡ አባላት የወተት ማለቢያና መጠጫ እቃዎችን የሚሠሩት
ከእንጨት፣ ከኡንጋና ከቆዳ ሲሆን ውበት እንዲኖራቸው የለፋ ቆዳ /ነት/፣ ቀለም ያልተነከሩ የተለያዩ መልክ ያላቸው ስንደዶዎችንና
ዛጎሎችን ይጠቀማሉ።
ሀ. አይኒ፤ ለከብቶች ማለቢያ የሚጠቀሙበት፣
ለ. አሙር፤ ለግመል ማለቢያ የሚጠቀሙበት፣
ሐ. አራሪ፤ የታለበው የከብቶች ወተት ማጠራቀሚያ ከስፌት የሚሰራ፣
መ. ኮራ፤ ከእንጨት
ተጠርቦ የሚሰራ ሲሆን ይሄም ለወተት መጠራቀሚያነት ያገለግላል፡፡
አራሪ እና ኮራ |
የውሀ ማጠራቀሚያዎች
ሀ.
የውሃ ማቀዝቀዣና መያዣ፤
የውሀ መያዣና ማቀዝቀዣው ከትንሽ ፍየል ግልገል (በከል) ቆዳ ተለፍቶ የተሰራ ነው። ብዙውን
ጊዜ ውሀ ለማቀዝቀዝ ሲገለገሉበት ረጅም መንገድ ሲጓዙ ለውሀ መያዣነትም ይጠቀሙበታል። መንገድ ሲጓዙ በብትራቸው /በዘንጋቸው/ ጫፍ
አንጠልጥለው ነፋስ እያስመቱት ስለሚጓዙና በቤት /አሪ/ አካባቢም ከፍ /ረዘም/ ካለ ቦታ ላይ ስለሚያስቀምጡት ውሀው በፍጥነት ይቀዘቅዛል።
ለ. ሣር /የውሀ መቅጃ/ አፍሌይታ፤
የውሀ መቅጃና መያዣ ሲሆን ከትልቅ የፍየል ቆዳ ይዘጋጃል። ሴቶች ከወንዝ፣ ከኤላ፣ ወ.ዘ.ተ ውሀ የሚቀዱበት ከመሆኑም ባሻገር በአህያ
ወይም በግመል ላይ ሊጫን ይችላል። አፍሌይታ ራቅ ብለው ሲጓዙ
እንደ ኮዳ የሚጠቀሙበት የውሃ መያዣ ሲሆን ከበግና ፍየል ግልገል ቆዳ የተሰራ /ስልቻ/ ነው።
አፍሌይታ |
የስለት እቃዎች
ከብረት የሚሰሩ
የተለያዩ አይነት የስለት እቃዎች ሲኖሩ በተለይም ለብሄረሰቡ እንደ ጦር መሳሪያ፣ ባህላዊ ጌጥና ግመልን እና የቀንድ ከብቶችን ለማረድ
የሚጠቀሙበት ጊሌ /ሰይፍ/ በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ። እነዚህም እንደየአጠቃቀማቸው ይለያያሉ።
ሀ. ላክኦ ጊሌ፤ በመባል የሚታወቀው ከጠንካራ ብረት የተሰራና ቅርጹ ከጉራዴና ከሰይፍ ለየት
ያለ መሀሉ ሰፋ ጎበጥ ብሎ በሁለቱም ጎን ስለት ያለው ጫፉ ሹል ሲሆን እጀታው ከእንጨት የተሰራ ሆኖ የብር ጌጣጌጥ ይለብሳል።
ለ. ታጎሪታ፤ በመባል የሚታወቀው ከጠንካራ ብረት የተሰራና ቅርጹ ከጉራዴና ከሰይፍ ለየት
ያለ መሀሉ ሰፋ ጎበጥ ብሎ በሁለቱም ጎን ስለት ሆኖ ጫፉ ሹል ያለው ሲሆን እጀታው ከእንጨትና ሽቦ የተሰራ ጌጣጌጥ ይለብሳል።
ታጎሪታ
|
ሌሎች የተለያዩ እቃዎችን መያዣዎች /ማስቀመጫዎች/
ሀ. ከትሆ /katho/፤ ከእንጨት የተሠራ ቆፊ
ሲሆን ለወተት መጠጫ፣ ለንፍሮና እንጀራ ወይም ዳቦ ፈርፍሮ ለመብላት ያገለግላል።
ለ. ሲፋላ፤ ከኡንጋ በተለያዩ ዲዛይን የሚሠራ ለግድግዳ ጌጥ፣ ለደረቅ
ምግቦች መያዣና ለክዳን የሚያገለግል ነው።
ሐ. ሚድራ፤ ከኡንጋ የሚሰራ ሲሆን ለእጣንና ለሌሎች ነገሮች መያዣ ያገለግላል።
መ.ገድቦ፤ ለደረቅ ምግቦች መያዣ የሚያገለግል ከኡንጋ የሚሰራ ነው።
መ. ኦካስ፤ ከበግና ፍየል ግልገል ቆዳ የወጣ /ስልቻ/ ሲሆን ለቅቤ ወይንም
ለማር መያዣ ያገለግላል።
ሰ. ኡዊ ሃዳ፤ ለቤት ቁሳቁሶች ማስቀመጫ ወይም ማንጠልጠያ ይጠቅማል።
ረ.ኦሊ፤ ከክብት ቆዳ የተሠራ፣ ለልብስ ወይም ሌሎች እቃዎች መያዣ
/ማስቀመጫ/ ያገለግላል።
ሠ.ጊሪቢ፤
ከቆዳ የተሰራ አቅማዳ /ስልቻ/ ነው።
ሸ. ሰሮ ሀዳ፤
ልብሶችን ለማጠኛ የሚያገለግል ከእንጨት የተሠራ ነው።
ባህላዊ
ዘፈንና ጭፈራ
የአፋር ባህላዊ
አጨዋወት ዘፈንና ጭፈራው አይነቱ የበዛና የሰፋ ቢሆንም በዋነኛነት የሚታወቁት በሰርግ፣ በሃይማኖታዊና ማህበራዊ በአላት እድሜና
ጾታን በመለየት እንዲሁም ሁሉም በጋራ ተሳትፎ የሚያደርጉበት የአጨዋወት ስልቶች ናቸው።
ከዚህ በታች የተጠቀሱት
አበይት የብሄረሰቡ ባህላዊ የዘፈንና የጭፍራ ዓይነቶች በመጠኑም ቢሆን ለማስተዋወቅ እንጂ በእያንዳንዱ ዘርፍ በተለያዩ መጠሪያ የሚጠቀሱ
አያሌ የአጨዋወት ስልቶች መኖራቸውን ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ሀ. ሆራ፤ ይህን የጫወታ አይነት የሚጫወቱ ወንዶች ብዛታቸው ከስድስት ማነስ የለበትም። አጨዋወቱም፡-ተጫዋቹ በመጀመሪያ
በቀኝ እጅ ጊሌ ይይዛል፤ ከዚያ እግር ማንሳት ይጀምራል፤ የሁሉም
እግር እኩል ይነሳል። እግር በጉልበት ላይ በመታጠፍ እስከ መቀመጫ ይነሳል። ጨዋታው ወደ ዘመቻ ሲኬድ፤ በኢድ፣ በሰርግና ወዘተ…
ጊዜ ይከናወናል።
ለ. ሰደአ፤ የሚባለው ደግሞ ሁሉንም ጾታዎች የሚያሳተፍ ቢሆንም ልጃገረዶች ብቻቸውን የሚጨፍሩበት እንዲሁም ለአካለ መጠን
የደረሱና ከዚያም በላይ የሆኑ ግን ከጾታ ተቃራኒያቸው ጋር አብረው መጫወት የሚችሉበት የጨዋታ አይነት ነው።
ሐ. ትርትራ፤ የሚባለው ለዘመቻ ሲሄዱና ድል አድርገው ሲመለሱ የጀግንነት ስሜት የሚገልጹበት
አንደ ፉከራና ቀረርቶ ዓይነት አጨዋወት ሲሆን በአብዛኛው ጎሳዎች በእድሜ በሰል ባሉት ዘንድ ይታወቃል።
መ. ላሌ፤ በመባል የሚታወቀው ጨዋታ በየትኛውም የበዓል ጊዜ የሚዘፈንና በተቀባይና አቀንቃኝ
መካከል እድሜ ሳይለይ ወንዶች ብቻ የሚጨፍሩበት ሲሆን በድምጽ፣ በጭብጨባና በእግር ዝላይ እንቅስቃሴ የሚታጀብ ይሆናል።
ሰ. ኬኬ፤ በመባል የሚታወቀው ጨዋታ በየትኛውም የበዓል ጊዜ የሚዘፈንና በተቀባይና አቀንቃኝ መካከል እድሜ ሳይለይ ወንዶችና
ሴቶች በጋራ የሚጨፍሩበት ሲሆን በድምጽ፣ በጭብጨባና በእግር ዝላይ እንቅስቃሴ የታጀበ የጨዋታ አይነት ነው።
ኬኬ
|
ረ. መላቦ፤ ጨዋታ ወንዶችን አያሳትፍም። አብዛኛውን ጊዜ በሰርግና በኢድ በአል ጊዜያት ሴቶች ብቻቸውን በመሆን ተቀባይና
አቀንቃኝ በሁለት ረድፍ ተሰልፈው ጊሌ /ሰይፍ/ በመያዝ እንደቦታው ስፋትና ጥበት የመዞር እንቅስቃሴ
እያደረጉ የሚጫወቱበት የጨዋታ አይነት ነው።
ዳጉ /የመረጃ ልውውጥ ዘዴ
ዳጉ በአፋር ብሄረሰብ
ውስጥ ህብረተሰቡ መረጃ ለመለዋመጥ የሚጠቀምበት ዘዴ ነው። መረጃ ልውውጡ ከአንዱ ሰው ወደ ሌላኛው ሰው በቃል የሚተላለፍ ነው።
ከአንድ ሰው /ሁለት ወይም በላይ/ በሚገናኙበት ወቅት ስላምታ ከተለዋወጡ በኋላ የመረጃ ልውውጥ ያደርጋሉ። አንደኛው ወገን በመንገድ
ላይ፣ በቤት ውስጥ፣ ወጪ፣ ወዘተ… የተመለከተውንና የሰማውን በሙሉ ይናገራል። አንድ ሣያሰቀር ወይም ውሸት /ሀሰት/ ሣይጨምር ያወራል።
አጭር መረጃ ለመለዋወጥ
ከሆነ ከሰላምታ በኋላ ቆመው ይጫወታሉ፣ ረዥም መረጃ ከሆነ ቂጢጥ ብለው /አረፈ ብለው/ ይጨዋወታሉ። ከቤት ውስጥ ከሆነ ከሰላምታ
በኋላ ይጨዋወታሉ። ምግብ ይቀርባል፣ ከምግብ በኋላ በመቀጠል የዳጉ ልውውጥ ያካሂዳሉ። በዚህ የዳጉ ልውውጥ ሀሰት የሚጨምር ሰው
የለም። የዚህ ምክንቱ አንደኛው ወገን ተሳስቶ ቢናገር ማህበራዊ ክብሩን ስለሚያጣና ሲናገርም ስለሚታወቅበት ነው። በተለይ በዳጉ
ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ዘዴ ውሸት መናገር አጅጉን በጣም የተከለከለ በመሆኑና የሌሎች ሰዎችንም ስም ሊያጎድፍና ጉዳት ሊያስከትል
በመቻሉ ነው።
የመረጃ ልውውጡ በአንድ
ወገን ብቻ ሣይሆን በሁለተኛውም ወገን ነው። በሂደቱ ላይ ግን አንዱ ወገን ተናግሮ ሳይጨርስ አቋርጦ መናገር የተከለከለ ነው። የዳጉ
ስርአት ጥሬ መረጃዎችን ብቻ ማቀበልና መስማት ላይ የተመሠረተ ነው። በዳጉ ስነ ስርአት አንዱ ግለሰብ ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ
ለምን እንደሚንቀሳቀስ ይገልፃል።
ህብረተሠቡ ከግጦሽ መሬት፣
ውሃና ዝናብ ጋር የተያየዘ ኑሮ ስለሚኖር ተንቀሳቃሽ ነው። በሚንቀሳቀስበት ወቅት ትቶት ስለመጣው አካባቢ በጎዞው ወቅት ያጋጠሙትን
ደስታና ችግሮች የሰማውንና ያየውን ስለሚሄድበት አድራሻ ሁኔታ ይገልፃል። ስለ አካባቢው ያለው እወቀት አነስተኛ ከሆነ ከሌላው ወገን
መረጃ ማግኘት ይችላል። መረጃው በቤት ውስጥ ስለሚገኝ እንስሳትም ሆነ ወደ ወጪ ስለተሠማሩ የቤት እንስሳት ሁኔታ ሊሆን ይችላል።
ስለቤተሰብ ጤንነት፣ ስለ ክልሉ ደህንነት፣ ፀጥታ፣ ጦርነት፣ ግጭት፣ ስለ ግለሰቦች ሁኔታም ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የመረጃ
ልውውጡ ሚስጥርን አይጨምርም።
ከመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ
ማናቸውም መረጃዎች በህዝቡ በግለሰብም ደረጃ በዳጉ ከአንዱ ወደ አንዱ ወገን በፍጥነት ይሠራጫሉ። ዳጉ ከህይወታቸው ጋር በጣም የተያያዘ
በመሆኑ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው እውነተኛ መልእክት ይተላለፋል፣ በፍጥነት ይሠራጫል። ስለዚህ ዳጉ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ
ግንኙነቶችን ለማጠናከር ህብረተሠቡ የሚጠቀምበት የመረጃ ልውውጥ ዘዴ ማለት ይቻላል።
የሚከሰቱ ማንኛቸውንም
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በዳጉ ይተላለፋሉ። የተሰፋፋ በሽታዎች፣ ዝረፈያና ስርቆት፣ የልማትና የሰላም ጉዳዮች፣
ከመንግስትና ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያሉ ግንኙነቶች እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ያሉ ችግሮች ሳይቀሩ በዳጉ ሰርአት የመረጃ ልውውጥ
ይደረግባቸዋል። ስለዚህ ዳጉ የመረጃ ልውውጥ ዘዴ ብቻ ሣይሆን የብሄረሰቡ ስላምና መረጋጋት ማስከበሪያ እና የልማታዊ አስተዋፆ ማበርከቻ
ዋነኛ መሳሪያም ነው። በጥቅሉ የህዝብ ግንኙነት የመረጃ ማዕከል ነው ማለት ይቻላል።
የብሄረሰቡ ባህላዊ ጋብቻ
በአፋር
ሁለት ዓይነት የጋብቻ ስርአቶች አሉ። አብሱማና ፋይዲ ይባላሉ።
የአብሱማ
ጋብቻ ስርአት ወንድ ልጅ ከአክስቱ ልጅ /የአባቱን እህት ልጅ/ ጋር በጋብቻ የሚተሣሠርበት ስርዓት ሲሆን ሴቷ ደግሞ የእናቷን ወንድም
ልጅ የምታገባበት ሆኖ ምናልባትም ከወንድምየው ወንድ ልጅ ከእህትየዋ ልጅ ባይገኝ ከእህትየዋ ሴት ልጅ ብትገኝ ከወንድምየዋ ወንድ
ልጅ ቢገኝ ወይም ሌላ አጋጣሚ ቢኖር ከዚህ ከዝምድና ተዋርድ የሚቀርበው ወይም የምትቀርበው የሚጋቡበት የጋብቻ ስርዓት ነው።
አብሡማ
ስያሜውን ያገኘው ከዝምድና ሀረግ መጠሪያ ሲሆን ይህ ማለት ከሌላ ጎሣ የምትገኝ የአጎት ልጅ ለወንድምየው /የወደፊት ለሚሆነው/
አብሱማ ወይም የአጎት ልጅ ነች እንደ ማለት ይሆናል። ልጅቱን የሚያገባው አቡ በመባል ይታወቃል፤ ትርጉሙም አጎት እንደ ማለት ነው።
የአብሱማ
ጋብቻ አንድ አፋር ከሌላ ጎሣ የምትመደብ የአባቱን እህት ልጅ የሚያገባበት ስርዓት በመሆኑ ጎሣዎችን እርስ በርስ በማስተሣሠር አንድነትን
ለመመስረት የሚደረግ የአጎትና የአክስት ልጅ /cross-cousins / የጋብቻ ስርዓት ነው።
በአፋር
ብሄረሰብ ማን ከማን ጋር መጋብት እንዳለበት አስቀድሞ የተመለሰ ስለሆነ ማንን አገባለሁ የሚለው ጥያቄ አሣሣቢ ጉዳይ አይደለም
የአብሱማ
የጋብቻ
ስርዓት መብትና ግዴታዎች
እናት ሃላፊነት ወስዳ የማሣጨትና የመዳር መብት ያላት በመሆኑ ለወንድሟ ልጅ ያለመስጠት መብት አላት። የዝምድና ጋብቻው
ከተጣሰም ለወንድ ቤተሰብ የሞራል ካሣ የመክፈል ግዴታ ይኖራል። ጋብቻው የፈረሠው በወንድ ቤተሰብ ከሆነ የመካስ ግዴታ የለበትም፤
ነገር ግን የዝምድናው ሁኔታ የቀዘቀዘ እንዲሆን ያደርገዋል።
በአብሡማ
ስርዓት ከተጋቢዎቹ መካከል በተፈጥሮ ወይም በሠው ሠራሽ ምክንያቶች የአካል ጉዳት ወይም የጤንነት ችግር ቢኖር አሊያም ድሃ ወይም
በእድሜ ያነሰች ወይም በእድሜ የገፋች ብትሆን እነዚህን ምክንያት አድርጎ ጋብቻውን ማፍረስ አይቻልም።
በአፋር
ማህበረሠብ አንዲት ሴት እድሜዋ ለጋብቻ መድረሷ የሚታወቀው የመሀል አናቷ ላይ ፀጉር እንዳይኖራት በማድረግ ነው።ይህ የፀጉር አሠራርም
በኮዚት ይባላል።
ሌላኛው
የጋብቻ ስርዓት ፋይዲ የሚሉት ሲሆን ይህ ዓይነቱ የአፋር የጋብቻ ሁኔታ ከማንኛውም ጎሣ ወይንም ብሄረሠብ ከዝምድና ውጪ በፍላጎት
ላይ የሚመሰረት የጋብቻ ዓይነት ነው። የማጨቱ ተግባር የሚከናወነው በወንዱ ቤተሠቦች አማካኝነት ይሆናል።
ከላይ
የተጠቀሱት የጋብቻ ዓይነቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ትዳራቸውን ለሚመሠርቱ ተጋቢዎች የሚያገለግሉ ሲሆን አንዲት ሴት የመጀመሪያ ትዳርዋን
አፍርሣ ለሁለተኛ ጊዜ የምትመሠርተው ትዳር ደግሞ ሀቤንቶ በመባል ይታወቃል። ባልዋ የሞተባት ሴት የምትፈጽመው ጋብቻ ደግሞ ጉበና ይባላል።
የአፋር ባህላዊ ሕግ
የአፋር
ክልል አምስት የሚሆኑ ባሃላዊ ህጎች ነበሯቸው። እነዚህም ባሃላዊ ህጎች ቡርኢሊ፣ በዶይታሜላ፣ ዴብኔክ-ዌኢማ፣ አፍኪኤክ-ማአድ እና
ቡዱቶ በዲ ህግ ይባላሉ። እነዚህ አምስት ባህላዊ ህጎች አሁን ወደ አንድ እንዲመጡ ተደርጓል። በአፋር ባህላዊ ሕግ የቅጣት ውሳኔ
የሚወሰነው የተከለከሉ ነገሮችን ፈጽሞ በመገኘት ወይም ፈጽም የተባሉ ነገሮችን ሳይፈጽም በመቅረት ነው። ጥፋት ሲፈጸም እያዩ አለመከልከል
ወይም እያዩ ማለፍ ያስቀጣል። ከዚህ ሌላ በአፋር ባህላዊ ህግ ድርጊቱ ባይፈጸም እንኳ ሊፈጸም ከነበረም ያስቀጣል።
የአፋር
ባህላዊ ህግ የተለያዩ ባህርያት አሉት። እነሱም አጥፊው ወይም ወንጀለኛው ሳይያዝ ወይም ሳይታሰር መቅጣት የሚችል መሆኑ ነው። ሌላው
ደግሞ በዚህ ባህላዊ ሕግ ጥፋተኛው አውቆ /ሆነ ብሎ/ መፈጸሙንና ሳያውቅ መፈጸሙን ለይቶ የሚቀጣ መሆኑ ነው። በዚህ ባህላዊ ህግ
ለተፈጸመ ጥፋት አጥፊው ብቻ ሳይሆን የአጥፊው ጎሳ በሙሉ ተጠያቂ ይሆናል።
በችሎት
ላይ ከሴቶችና ሕጻናት በቀር ማንኛውም ሰው መታደም ወይም ሃሳብ መሥጠት ይችላል። ነገር ግን ተከሳሽና ከሳሽ ወገን አሳማኝ የሆነ
ቅሬታ ያቀረቡበት ሰው ችሎቱን መታደም ቢችልም እንኳን ሃሳብ መስጠት ግን አይችልም። የቀረበው ቅሬታ አሳማኝ ካልሆነ ግን ቅሬታ
አቅራቢው የግለሰቡን ክብር በመንካቱ ይቀጣል። የባህላዊ ህጉ ሌላው ባህሪ ካሳን በእንስሳት የሚከፍል ሲሆን ሕይወት ያለውና ሕይወት
የሌለው ይባላል። ሕይወት የሌለውን በገንዘብ ህይወት ያለው ደግሞ በቁም እንስሳት ይከፈላል።
በአጠቃላይ
አፋሮች ከላይ የጠቀስናቸው እንደ ቁሳዊ ባህሎችና አሰራሮች፣ የመረጃ ልውውጥ ዘዴ፣ ባህላዊ የጋብቻ ስነ ስርዓቶች፣ ባህላዊ ህጎች
እና ያልጠቀስናቸው ሌሎች የራሳቸው የሆኑ ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴቶች ያሏቸው ሲሆን በእለት እለት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ
ጉዳዮቻቸው ይጠቀሙባቸዋል። እነዚህን ባህላዊ ሀብቶች ጠብቆና አጎልብቶ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም
ቢሮ ከአሁን በፊት ሲያከናውናቸው የቆዩ ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው የበለጠ ለመስራት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል እንላለን።
ምንጭ፡ ህብረ ብሄር መፅሄት (2010 ዓ.ም)
Very nice but I want more cultural materials of AFAR
ReplyDelete