EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 14 March 2016

የከተሞች ፈጣን ልማት ለሁለንተናዊ ዕድገት

 ገነት ደረጀ  

ሀገራችን ፈጣን የከተሞች እድገትና መስፋፋት እያስተናገዱ ካሉ የአለም ሀገራት መካካል አንዷ ነች፡፡ የከተሞች መስፋፋትና እድገት ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚያያዝ ሲሆን እንደ ቻይና፣ ብራዚልና አርጀቲና ወዘተ ያሉ አገራት ልምድም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ የከተሞች መስፋፋትና እድገት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ የኢንዳስትሪና አምራች ዘርፎች በቂ የሰው ኃይል እንዲኖራቸው በማድረግ ለኢኮኖሚ እድገት መሳለጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡  

አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ 20 በመቶ የሚሆን ህዝብ በከተማ የሚኖር ሲሆን እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትንቢያ እኤአ እስከ 2040 ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የከተማ ህዝብ በሶስት እጥፍ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ ትላልቅ ከተሞች ደግሞ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የህዝብ ብዛታቸው ከዚህም በላይ እንደሚያድግ መረጃው ይጠቅሳል፡፡ ለአብነትም ሀዋሳ በ6እጥፍ፤ መቀሌ በ5 እጥፍ እንዲሁም አዳማና ባህርዳር ደግሞ በ4 እጥፍ የህዝብ ብዛታቸው እንደሚያድግ ተገምቷል፡፡ የቆዳ ስፋታቸውም በዚሁ መጠን እንደሚያድግ ይገመታል፡፡ በሀገራችን አሁን አሁን አዳዲስ ከተሞች ጭምር እየተመሰረቱ ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን የከተሞች እድገት በጥቅሉ ሲታይ በዓመት 5 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የከተሞች እድገት የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና የእድገት ምልክት ቢሆንም በሌላ መልኩ ከተሞችን በእቅድ መምራት ካልተቻለ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንዲሁም ካባቢያዊ ቀውሶችን ያስከትላል፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግስት አቅምና ምላሽ ከከተሞች እድገትና መስፋፋት ፍጥነት ጋር መራመድ ካልቻለ ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡ በመሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ጫና ከመፍጠሩም በላይ እንደ እኛ ላሉት ታዳጊ ሀገራት ፈተናም ይሆናል፡፡

ከገጠር ወደ ከተማ የስራ አማራጮችን ለማግኘት የሚደረገውን የህዝብ ፍልሰት በገጠር የስራ እድሎችን በበቂ ሁኔታ በማመቻቸት መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ አሊያ ግን ከተሞች የሚመጣውን ሃይል የማስተናገድ አቅም ሳይገነቡ ውስብስብ ችግር ውስጥ መውደቃቸው አይቀሬ ነው፡፡      
ሌላው በከተሞች ከህዝብ ቁጥር መጨመርና መስፋፋት ጋር ተያይዞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ያለው የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ነው፡፡ ይህም ከቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ጋር የሚያያዝ ሲሆን ከግንባታ ተረፈ ምርቶች፤ የምግብ ትራፊ፤ ከሆስፒታሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዙ ሺህ ኪሎግራም ደረቅ ቆሻሻ በቀን ይመነጫል፡፡ እንደ ከተሞችና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር መረጃ ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ በአግባቡ የሚሰበሰበው 43 በመቶ ብቻ መሆኑ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላል፡፡ ቀሪው ቆሻሻ በየመንገድ ዳር፤ በሰዋራና ክፍት ቦታዎች እንዲሁም በየወንዞች ይጣላል፡፡ ከተማውን አቋርጠው ወይም በከተሞቻችን ዳር የሚገኙ ወንዞቻችን የደረቅ ቆሻሻ ብቻ ሳይሆኑ ከፋብሪካ የሚለቀቁ ኬሚካሎች፤ የዝቃጭና ከየመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሽ ቆሻሻ ሰለባ መሆናቸውም ከብክለቱም በላይ የአካባቢና የውሃ ስነ ምህዳርን የሚያቃውስ ነው፡፡ በቆሻሻ አማካይነት የሚፈጠረው የአካባቢ ብክለት ተጽእኖ በግልጽ መታየት ጀምሯል፡፡ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ድምር ውጤት በሚያመጡት የአካባቢ ብክለት እና ከግል ንጽህና ጉድለት የተነሳ ከ10 ህጻናት አራቱ ለጤና መታወክ እንደሚጋለጡ የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ ያሣያል፡፡




የአረንጓዴነት ማነስ ሌላው የከተሞች ፈተና ነው፡፡ አረንጓዴነት ከውበትም በላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ስልትም ጭምር ነው፡፡ በተወሰኑ ከተሞቻችን ለዚህ ተብለው የተከለሉ ቦታዎችና ፓርኮች እንዲሁም የመንገድ አካፋዮች በተወሰነ መልኩ እየለሙ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ከከተማ ከተማ ልዩነት ቢኖርም የመንገድ አካፋዮችም በአግባቡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሲለሙ አይስተዋሉም፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ተደማምረው የከተማውን ኑሮ ውስበስብ በማድረግ  ከተሞች ምቹና ለኑሮ ተስማሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ይህ የሚያመላክተው የከተሞች እድገትና መስፋፋት በተለየ ሁኔታና በትኩረት መመራት እንደሚያስፈልገው ነው፡፡  

በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በከተሞች ሊኖር የሚችለውን ውስብስብ ሁኔታ በመረዳት ለከተሞችም ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፤ እየሰራም ይገኛል፡፡ ከተማቻችን ለኑሮ ምቹ አንዲሆኑና እድገታቸውን ማሰለጥ እንዲቻል ከገጠሩ ልማት ጋር ለማስተሳሰር ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ በቀጣይም አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ከከተማ አመራር ምደባ ጀምሮ በትኩረት  ይሰራል፡፡ ከከተሞች እድገትና መስፋፋት ጋር ተያይዘው ችግሮች እንዳይከሰቱ የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ ሲሆን ሌሎችንም ተጨማሪ አሰራሮችን ለመተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ለአብነትም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ስትራቴጂ፤ የከተሞች ኢንዳስትሪ ልማት ስትራቴጂ፤  የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስትራቴጂ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬ የከተሞች የአረንጓዴነት ልማት ስትራቴጂና የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም የከተሞች መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የማህበራዊ አገልግሎቶችን በከተሞች ለማዳረስ የተደረጉ ጥረቶች የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ያደረጉና ኑሮውን ያቃለሉት ሆነዋል፡፡ በተለይም በትላልቅ ከተሞች በቤቶች፤ መንገድ፤ በመብራት፤ በውሃና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ማስፋፋት ተችሏል፡፡

በከተሞች የሚስተዋሉ የስራ አጥነት ችግርን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማትና በህብረት ስራ ማህበራት በርካታ የከተማ ነዋሪዎችን ከስራ አጥነት በማላቀቅ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ እድል መፍጠር የሚችሉበትን ሃብት እንዲያጠራቅሙ ማድረግ ተችሏል፡፡ በቀጣይም በከተሞች የሚስተዋለውን ድህነት በመቅረፍ ሀገራችን በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለከተሞች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ ከተሞችን ውብ፤ ጽዱና ለኑሮ አመቺ እንዲሆኑ ለማድረግም ግብ ተጥሏል፡፡ በተለይም የገጠር ልማትን ከከተማ ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም የከተማ ግብርናና  በከተሞች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ዛፎች በማልማት በአረንጓዴ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ይሰራል፡፡

በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሌላው ሲሆን በ11 ዋና ዋና ከተሞች ከመጭው በጀት ዓመት ጀምሮ ይተገበራል፡፡ በዚህም 4.7 ሚሊየን የከተማ ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በከተሞቻችን የሚስተዋለውን የቆሻሻ ችግር ለመፍታትም ስንታንዳርድ ተዘጋጅቷል፡፡

በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እቅዶችን እቅዶ በመተግበር ህዝባዊነቱንና ለሀገር እድገት ያለውን ቁርጠኝነት እያስመሰከረ ከህዝቡ ጋር ከአንዱ የድል ጎዳና ወደ ቀጣዩ እያተሸጋገረ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ከተሞቻችንን በማዘመን ውብ፤ ጽዱ፤ ለኑሮ ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደተለመደው ሁሉ ህዝቡ ለስትራቴጅዎቹ መተግበር የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment