EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday 29 August 2014

የአድዋ ትሩፋት፤ መለስ ዜናዊ

በፈድሉ ጀማል
አድዋ ሲነሳ ሁሌም በኢትዮጵያዊያንና በመላ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አንድ ትልቅና በማንኛውም ሰው አዕምሮ ሊረሳ የማይችል ታሪካዊ ድል መታወሱ የማይቀር ነው፡፡ እነዛ ቀደምት ጀግኖች አባቶቻችን ለውጭ ወራሪ ላለመገዛት አሻፈረኝ በማለት በከፍተኛ መስዋዕትነት የተቀዳጁት ድል፡፡ እነዛ ጀግኖች አባቶች ሀገራችን የባርነት ታሪክ ሊኖራት አይገባም በሚል የከፈሉት ከፍተኛ የቆራጥነት ውሳኔ፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ህዝቦች ጭምር የኩራት ምንጭ የሆነው የጥቁር ህዝቦች የጀግንነት ታሪክ እንዲፃፍ ያስቻለው ትልቅ ድል ሁሌም በመታወስ የሚኖር ይሆናል፤ የአድዋ ድል፡፡
የአድዋ ድል ታሪክ ሁሉም ኢትዮጵያዊን በኩራት የሚናገሩለት ታሪካቸው ነው፡፡ የአድዋ ድል የዛሬው ትውልድ ለቀኝ ገዢዎች ያልተንበረከከች የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን እንዲረከብና ይህንንም የራሱ መገለጫ አድርጎ ለተቀረው አለም በኩራት ማስተዋወቅ እንዲችል ያደረገ፣ ሁሌም በኢትዮጵያዊያን ውስጥ ያሸናፊነትና ይቻላል መንፈስ እንዲኖር ያስቻለ ነው፡፡ ይህ ዘመን ተሻጋሪ የቀደምት አባቶቻችን የአሸናፊነት ታሪክ ሁሌም ከትውልድ ትውልድ ሲታወስ ይኖራል፡፡
መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዳር ዳር ተነስተው ይህን  ታሪካዊ ገድል የፈፀሙት በአድዋ ተራሮች ላይ በመሆኑ በፋሺስቶች ላይ የተቀዳጀንው ድል ሲነሳ አድዋንም አብራ እንድትወሳ አድርጓታል፡፡ አድዋ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ እነዛ ቀደምት አባቶቻችን ከውጭ ወራሪ ጠላት ጋር ባደረጉት ጦርነት ከፍተኛ መስዋዕት የተከፈለበትና የዘመን ተሻጋሪው ድል ብስራት የተገለጠባት ቦታ ነች፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ደግሞ አድዋ ሌላ ታሪካዊ ብስራት ይዛ ብቅ ብላለች፡፡ ለሀገራችን፣ ለአፍሪካና ለአለም ጭቁን ህዝቦች ጠበቃ የሆነውን ታላቁን መሪ መለስ ዜናዊን ያፈራችውም ይችው ያን የቀድሞ አባቶቻችንን ገናና ታሪክ መጠሪያ የተጎናፀፈችው አድዋ ናት፡፡ አድዋ ከእርሷ መንደር ተነስቶ አለም አቀፍ ስብዕና የተላበሰውን መለስ ዜናዊን በማበርከት ታሪካዊነቷን ቀጥላበታለች፡፡

መለስም ከአድዋ ተራሮች ስር ተፈጥሮ ለሀገሩ የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆን አንጋፋ ታሪክ ሰርቶ አልፏል፡፡ መለስ ከአፍላ እድሜው አንስቶ ፈታኝና ውስብስብ ሁኔታዎችን በፅናት ተቋቁሞ በማለፍ የትልቅ ስብዕና ባለቤት በመሆን በአለማችን ተፅዕኖ መፍጠር ከቻሉ ጥቂት ግለሰቦች ጋር መሰለፍ ችሏል፡፡ መለስ በተሰማራባቸው መስኮች ሁሉ በሚያጋጥሙት ፈታኝ ሁኔታዎች ተስፋ ሳይቆርጥ በፅናት ተቋቁሞ ድል ማድረግ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ታላቅ መሪ ነበር፡፡ የእድሜ ሁኔታ፣ ለቦታ አዲስ መሆንና ሌሎች መሰል ሁኔታዎች ሳይበግሩት ያሰቡትን ግብ ማሳካት እንደሚቻል የመለስ የህይወት ተሞክሮ በግልፅ ያሳያል፡፡
ለአብነት የመለስን የትምህርት ህይወት ብናይ ትምህርት በጀመረበት አድዋ ካሉ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት በማምጣት ገና በአፍላ እድሜው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ መማር ችሏል፡፡ ከአድዋ ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወር ሊኖር የሚችለው የአካባቢ መለወጥ፣ ከቤተሰብ መለየት፣ የጓደኛና ሌሎች መሰል ሁኔታዎች መለወጥ በአፍላ እድሜ ለሚገኝ ማንኛውም ሰው ተፅዕኖው ከባድ ቢሆንም መለስ እነዚህ ሳይበግሩት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ግንባር ቀደም ሆኖ በማጠናቀቅ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ችሎ ነበር፡፡
መለስ ለጋ እድሜውና በመከታተል ላይ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ሁኔታ ሳያግደው የትግል ህይወትን ከተቀላቀለ ጊዜ አንስቶ የተሰማራባቸውን የስራ መስኮች ፈጥኖ በመላመድ በድል መወጣቱና ለሚያጋጥሙ ችግሮች በሚያመነጨው የመፍትሄ ሃሳብ የተነሳ በሌሎች የትግል አጋሮቹ ዘንድ መታወቅ በመቻሉ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ለከፍተኛ ኃላፊነት እንዲበቃ አድርጎታል፡፡ በትጥቅ ትግሉ ጊዜም ቁልፍ አመራር በመሆን የትጥቅ ትግሉ ምዕራፍ ግቡን እንዲመታ አድርጓል፡፡
የትጥቅ ትግሉን መጠናቀቅ ተከትሎ በሀገራችን ለዴሞክራሲና ለልማት መሰረት ከተጣለበት የሽግግሩ መንግስት ምስረታ ጀምሮ እስከ እለተ ሞቱ በነበረው ጊዜ እንዲሁ በሳል የአመራር ሚናን በመጫወት ያበረከተው በጎ ተፅዕኖ ከሀገራችን አልፎ አህጉራችንን ጭምር ተጠቃሚ ያደረገ ነበር፡፡ መለስ የተከተለው የአመራር ፍልስፍና ሀገራችንን ከመቀየር አልፎ በመላው አፍሪካ ጭምር ተፅዕኖውን አሳርፏል፡፡ በዚህም በተለያዩ ጊዜያት አፍሪካውያን በአንድ ድምፅ ተስማምተው በአለም አቀፍ መድረኮች ተወካያቸው እንዲሆን መርጠውታል፡፡
መለስ ከራሱ አስበልጦ የወገኑን ጥቅም የሚያስቀድም የትልቅ ስብዕና ባለቤት መሆኑን ገና ባፍላ እድሜው ነበር የጀመረውን የከፍተኛ ትምህርት በማቋረጥ ለብዙሃን መብት መከበር ትግል በመጀመር ያረጋገጠው፡፡ መለስ ከዘመን ዘመን የሚሸጋገሩ ሃሳቦችን የማፍለቅ ልዩ ችሎታውን ተጠቅሞ ባለፈባቸው የታጋይነትና የሀገር መሪነት ደረጃዎች ኃላፊነቱን በመወጣት ለመጪው ትውልድ ጭምር አሻራውን ማሳረፍ የቻለ ታላቅ መሪ ነው፡፡ በዚህም ለሰው ልጆች ለውጥ ሳይታክት በመስራት ታላቅ የተግባር ሰው መሆኑን አስመስክሯል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግም ሊቀመንበር ሆኖ በመራባቸው አመታት የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና የልማት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሰርቷል፡፡
በአጠቃላይ መለስ ሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት እንዲኖራት በመታገል እውን ያደረገ፣ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል ስርዓት የፈጠረ፣ የሴቶች መብት ሲከበር ብቻ ልማት ሊመጣ እንደሚችል እምነት ይዞ የሰራ፣ ወጣቱን ኃይል የልማት መሳሪያ አድርጎ ያሳተፈ ታላቅ የዘመኑ መሪ ነው፡፡ ከአድዋ ምድር ለኢትዮጵያ የተበረከተው ታላቅ ሰው የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን የተገበረ፣ ለህዝብ ጥቅም ሳይታክት ሰርቶ ያለፈ፣ ምርጥ ስትራቴጂስትና የታክቲክ ቀማሪ፣ ትጉህ ተማሪ፣ ቆራጥ ታጋይና በሳል መሪ ነው፡፡
መለስ ሰብአዊ ፍጡር በመሆኑ በሞት ያጣንው ቢሆንም እሱንና የትግል አጋሮቹን ያፈራው ኢሕአዴግ አሁንም በተራማጅ አስተሳሰብ እየተመራ አለም የመሰከረለቻውን ድሎች ማስመዝገቡን ቀጥሏል፡፡ ሕዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገው ፈጣኑ የኢኮኖሚ እድገታችን ባለፉት ሁለት አመታትም እንዲቀጥሉ የመሪነት ሚናውን በአግባቡ ተወጥቷል፡፡ በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ የከፈትነው ትግል ከልማታዊ ፋይዳው ባላነሰ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንም የላቀ ድርሻውን ማበርከቱን ቀጥሏል፡፡ በአገራችን አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት ብቻ ሳይሆን በሙሉ ልባቸው በልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡ ኢሕአዴግ ዛሬም እንደትናንቱ በልማት፤ በሰላምና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ከመላ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ጋር በመሆን ወደፊት መጓዙን ይቀጥላል፡፡ መጪው ጊዜም ከኢሕአዴግ ጋር ብሩህ ነው፡፡

1 comment: