EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 21 March 2016

የኢኮኖሚ ዋልታ…ቡና ቡና






 በገነት ደረጀ
የኢኮኖሚ ዋልታ…ቡና ቡና
የገቢ ምንጫችን...ቡና ቡና
የእድገታችን ገንቢ.. ቡና ቡና
ቡና ነው፤ ቡና ነው…ቡና ቡና
ብዙ ተዘምሮለታል፡፡ በአገርም በውጭም ያለው ቡናችንን ለመጎንጨት የታደለ ፍጠሩ ሁሉ አድናቆትን ችሮታል፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሳ አብሮ የሚነሳ የማንነታችን መገለጫም ጭምር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው ቡናችን፡፡ ኢትዮጵያውያኖች እርስ በእርስና ከአለም ህዝቦች ጋር ከሚጋሩት ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ቡና ነው፡፡ የቡና ስነስርዓት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለየ ስርዓት የሚከናወን ሲሆን ከመጠጥም በላይ ያለው ማህበራዊ ትርጉምና የሚፈጥረው ቤተሰባዊ ትስስር እጅጉን የጎላ ነው፡፡ በሀገራችን በአቦል፤ ቶናና በረካ የሚጠጣው ቡና በተለያዩ አካባቢዎች ለሃይማኖታዊ ክንዋኔም ይውላል፡፡ ቡና ከፍሬው ውጭ በሀረር አካባቢ ገለባው ወይም ቁጢ ይጠጣል፡፡ 

ከኢትዮጵያውያን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ቡና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ10ኛው ክፍለ ዘመን ካሊድ በሚባል የፍየል እረኛ አማካይነት የኢንግሊዘኛ መጠሪያውን ካገኘበት ከፋ እንደተገኘ ይነገራል፡፡ ይህ አረቢካ ኮፊ የተባለውና በአለም ላይ እየተጠጣ ከሚገኘው ውስጥ 70 በመቶ የሚሸፍነው የቡና ዘር ልዩ ጠዓም ያለው ቡና ነው፡፡ በአለም ከፍተኛ ቡና አቅራቢ የሆነችው ብራዚል ሁለት ደርዘን የማይሞሉ የቡና ዓይነት ያሏት ሲሆን በኢትዮጵያ ግን በተለያዩ ቦታዎች የሚበቅሉ ወደ 10ሺህ የሚጠጋ የቡና ዓይነቶች እንደሚገኙ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህም መካከል እስከአሁን ግማሽ ያህሉን ብቻ ማወቅ እንደተቻለ የመስኩ ተማራማሪች ይናገራሉ፡፡ ይርጋጨፌ፤ ሲዳማ፤ ሀረርና ወለጋ የሀገራችን ዋናዋናዎቹ የቡና አምራች አካባቢዎች ናቸው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በቀን 1.2 ቢሊየን በዓመት ደግሞ ግማሽ ትሪሊየን ሲኒ ቡና ይጠጣል፡፡ በአፍሪካ ቡና በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠጣው የቡና መገኛ በሆነችው በሀገራችን ሲሆን ቡና ከድፍድፍ ነዳጅ ቀጥሎ 2ኛው ከፍተኛ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ምርት ነው፡፡ በአለም ላይ በቡና ግብይት በዓመት 90 ቢሊየን ዶላር ይዘዋወራል፤ በ70 ሀገራት ይመረታል፡፡ ብራዚል፤ ቬትናምና ኢንዶንኤዥያ የአለማችን ከፍተኛ ቡና አቅራቢ ሀገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያ በ5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡  

ኢትዮጵያ ለቡና ምርት ተስማሚ የአየር ሁኔታና አመቺ የሆነ 6ሚሊየን ሄክታር መሬት አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ በቡና የተሸፈነው ግማሽ ሚሊየን ሄክታር ወይም 3.68 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከሀገራችን ህዝብ ውስጥ 15 ሚሊየን ህዝብ በመስኩ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡ ሀገራችን ከምታመርተው የቡና መጠን 50 በመቶውን ብቻ ወደ ውጭ የምትልክ ሲሆን የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ ዋነኛ ምርትም ነው፡፡ ጀርመን፤ ጃፓንና ሰዑዲ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ ቀዳሚ ሀገራት ናቸው፡፡ አሜሪካም ቡናችንን በመግዛት ያላት ድርሻ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ የማግኘት አቅም ቢኖራትም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ  በዓመት በመቶ  ሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር  ከቡና ታገኛለች፡፡

የቡና ዋጋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም በተለይም አምራቹ አርሶ አደር የሚያገኘው ጥቅም እምብዛም አይደለም፡፡ ከአምራቹ ይልቅ ቡና ገዝተው እሴት ጨምረው የሚሸጡ ኩባንያዎችና ላኪዎች ከዋጋው  በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በአለም ገበያ የቡና ዋጋ መቀነስ አንዱ ምክንያት ሲሆን የአለም የአየር ንብረት ለውጥም እንደአጠቃላይ ምርቱን የሚፈታተን ችግር ነው፡፡ ሀገራችን ቡና ለማምረት ያላትን ከፍተኛ አቅም አሟጣ አለመጠቀሟ፤ የቴክኖሎጂ እጥረትና ከሚመረተው ቡና ግማሽ ያህሉ በሀገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑ ሀገራችን ከቡና ማግኘት የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጉ ችግሮች ናቸው፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታትና ሀገራችን በመስኩ ያላትን አቅም እንድትጠቀም መንግስት  ለመስኩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የቡና ህብረት ስራ ማህበራት እንዲቋቋሙና አምራቹ አርሶ አደር የመደራደር አቅሙ እንድጎለብት ለማድረግ ውጤታማ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በመስኩ በተመቻቸው የኢንቨስትመንት እድል አቅም ያላቸው ባለሃብቶች ተሰማርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና የባለቤትነት ማረጋገጫ እንዲያገኝና በአለም አቀፍ ደረጃ የንግድ ምልክት እንዲሆን በማድረግ በኩልም ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን ጅምር ውጤቶችም ተመዝገበዋል፡፡ ይህ ረዥም ሂደትና እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማስያዊ ግንኙነቶችን የሚጠይቅ ሲሆን እስከአሁን ባለው ሁኔታም የሲዳሞ፤ የይርጋጨፌና የሀረር ቡና ኢትዮጵያ የባለቤትነት ማረጋገጫና የንግድ ምልክትነት እንድትጎናጽፍ አስችሏታል፡፡

ሌላው አለም ስለኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ቡና በደንብ እንዲገነዘብ ለማድረግ አገራችን 4ኛውን አለም አቀፍ የቡና ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ በማስተናገድ የአለም አቀፍ ማህበረሰብና መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የሚሰብ ተግባር መከወን ችላለች፡፡ ጉባኤውን ከዚህ ቀደም ለንደን፤ ብራዚልና ጓትማላ ያዘጋጁ ሲሆን አገራችን ጉባኤውን ያስተናገደች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገርም ለመሆን በቅታለች፡፡ ኢትዮጵያ ለዚህ ጉባኤ እንድትመረጥ ያደረጋት ዋነኛው ምክንያት ከዚህ ቀደም የተለያዩ አለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ በመቻሏና የቡና መገኛ ሀገር በሆኗም ነው፡፡

በጉባኤውም ስለ ቡናችንና በመስኩ ስላለው የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ለማሳየት ተችሏል፡፡ በጉባኤው ማግስትም ሀገራችን 2ኛ ቡና አቅራቢ ለመሆን ከብራዚል ጋር መስራት ጀምራለች፡፡ ብራዚልም በመስኩ ያላትን ልምድ ለማካፈል ፈቃደኛ ሆናለች፡፡ የብራዚል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ድርድሮችም እየተካሄዱ ነው፡፡
ወደፊትም ኢትዮጵያ ከመስኩ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማስቻል በአለም አቀፍ ደረጃ ቀጣይት ባለው መልኩ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ችሮታን ለኢኮኖሚ እድገትና ለህዝቦቿ ተጠቃሚነት እንዲውል ለማድረግ በተዘረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎቿ በመጠቀም እየተጋች ትገኛለች፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስኬቶች እተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

No comments:

Post a Comment