EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 24 August 2016

ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንንና እኩልነታችንን የሚገልፅ ዓርማ

(በመሃመድ ሽፋ)
የ1987ቱን ሕገ መንግስት መጽደቅ ተከተሎ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የተቀመጠውን ዓርማ በተመለከተ የተዛቡ አረዳዶችና ብዥታዎች በአንዳንዶች ዘንድ ይስተዋላል። ይህ ለምን ተፈጠረ ከተባለ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ይነሳሉ። በአንድ በኩል ይህ ዓርማ ያዘለው መልዕክት ከሚከተሉት በብሄሮችና ሃይማኖቶች እኩልነት ላይ የማያምን የፖለቲካ አቋም ጋር ስለሚጋጭ የዓርማውን ምንነት ቢያውቁትም ሊቀበሉት የማይፈልጉ ሃይሎች ስላሉ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እነዚህ ሃይሎች የዓርማውን ምንነት አዛብተው በማቅረብ በሌሎች ተቀባይነት እንዳያገኝ የሚያደርጉት የማጥላላት ዘመቻ የራሱን አስተዋፆ አበርክቷል። ስለ ሰንደቅ ዓላማችንና ዓርማዎች ታሪካዊ ዳራ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንም ሌላው ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ባንዲራ መጠቀም የጀመረችበትን ትክክለኛ ጊዜ በተመለከተ የታሪክ ፀሃፊዎች የተለያዩ ሀሳቦችን ያቀርባሉ። በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት (ከ1889) ጀምሮ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ቀለም ያለበት ሰንደቅ ዓላማ ጥቅም ላይ መዋል እንደጀመረ የታሪክ ምንጮች ያስረዳሉ። በየዘመኑ ሶስቱ ቀለማት እንደተጠበቁ ሆነው በባንዲራው ላይ የሚያርፈው ዓርማ ግን የሚለያይበት ሁኔታ አለ።
አፄ ሀይለስላሴ ህዝቡም፣ መሬቱም “የእኔ ነው” ብለው ስለሚያምኑ ሰንደቅ ዓላማውም የእሳቸው እንዲሆን ይመስላል በሚፈልጉት መንገድ አድርገውት ነበር። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማቱ እንዳሉ ሆነው በሰንደቁ ላይ ባለ አምስት ኮኮብ የዳዊት ምልክት (David star) ዓርማ ነበረበት። በሰንደቅ ዓላማው በስተምስራቅ በኩል መስቀል የተሸከመና የኢትዮጵያ ነገሥታት ዘውድን የለበሠ አንበሳ (lion of Judah) ምልክት አለበት። በስተምስራቅ የሆነው ወደ እየሩሳሌም ለማመልከት ነው። መስቀሉ ደግሞ የስልጣን መሠረታቸውን ለመግለፅ ነው።
የጃንሆይ ባንዲራ አላማው የአገርና የህዝብን ታሪክና ባህል ለማንፀባረቅ ሳይሆን የንጉሠ ነገሥቱን ሀያልነትና የበላይነት በመስበክ ተቀባይነት ለማስገኘት የተዘጋጀ እንደነበር የዛሬ ትዝብት ሳይሆን የወቅቱም ተቃውሞ ያንኑ ይመሰክራል። ኢትዮጵያ የበርካታ እምነቶች ባለቤት በመሆኗ ባንዲራው የኢትዮጵያን አንድነት መግለፅ አይደለም ኢትዮጵያን ሊወክል የሚችልበት ትክክለኛ መነሻ የለውም። በ5ቱ አመታት የጣሊያን ወረራ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በጣሊያን ባንዲራ ማለትም በአረንጓዴ፣ ነጭና ቀይ ቀለማት ባንዲራ ተተክቶ ነበር። ከነፃነት መልስ በአፄ ሀይለስላሴ ዘመን የነበረው ሰንደቅ ዓላማ ተመልሶ መጥቷል። አብዮቱ ፈንድቶ ጃንሆይ ከስልጣን እስኪወርዱ ድረስ ይሄው ባንዲራ አገልግሏል።
በመስከረም 1966 የደርግ መንግስት ወደ ስልጣን ሲወጣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ ተደረገ። በአፄው ዘመን ከነበረው ሰንደቅ አላማ ላይ የዘውድ ምልክቱን ከአንበሳው ላይ አንስቶ መስቀሉን በጦር ተክቶት ነበር። ነገር ግን ይህ ባንዲራ ያገለገለው ለአጭር ጊዜ ያክል ማለትም ከመስከረም 1966 እስከ ህዳር 1966 ብቻ ነበር። ከዚያም የአንበሳው ምልክት ተነስቶ የዘውድ አገዛዙን የሚያስታውሱ ምልክቶቸ በሙሉ እንዲጠፉ ተደርጓል። በመሆኑም የደርግ ስርዓት ባንዲራ እንደሆነ የሚታወቀው ከ1967-1983 ድረስ ያለው ሲሆን በሰንደቅ አላማው ላይ የሰፈረው ዓርማ “የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የሚል ጽሁፍ ነበረበት። የኢትዮጵያን ህዝቦች ትግል ሰርቆ በአቋራጭ ቤተ መንግስት የገባው ወታደራዊ አገዛዝ የሶሻሊስት ሥርዓትን የበላይነት ለመስበክ ያስችሉኛል ያላቸውን ምልክቶች ባንዲራ ላይ ሲያኖር ነበር።
ወታደራዊ ስርዓት ውድቆ በምትኩ የህዝቦችን አንድነት የሚያጠነክር ስርዓት ሲፈጠር ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚገለፅ አርማ ለዘመናት ስንጠቀምበት በነበረው አርንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት በያዘው ታሪካዊ ባንዲራ ላይ እንዲያርፍ ተደርጓል። በህገ መንግስታችን አንቀጽ 3 ላይ ሰንደቅ ዓላማውን በተመለከተ ግልፅ ድንጋጌ እንዲሰፍር ለማድረግም ተችሏል። ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የተመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና  ሀይማኖቶች በእኩልነት በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ብሩህ ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል። የዓርማውን ትርጓሜ በተመለከተ በሰንደቅ አላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 የተገለፀው ድንጋጌም ይህንኑ ያመለክታል።
በአዋጁ አንቀፅ 8 መሰረት  ክብ የሆነው ሰማያዊ መደብ ሰላምን የሚያመላክት ነው፡፡ ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እንዲሁም የሃይማኖቶችን እኩልነት የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ በሰንደቁ ላይ የተዋቀረው ኮኮብ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን አንድነት የሚያመላክት ነው፡፡
ቢጫው ጨረር በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት አንድነት ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  የፈነጠቀዉን ብሩህ ተስፋ የሚያመላክት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰንደቅ ዓላማችን የሃገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የእኩልነት መብታቸው ተጠብቆ፣ ወግ፣ ባህልና ሃይማኖታቸው ተከብሮላቸው በፍላጎታቸው በአንድነት የሚኖሩ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ዓርማው ያለፉ ስርዓቶችን የአምባገነናዊነትና የሰማያዊነት ስብከት ከመግታት ባሻገር ባንዲራችን ይበልጥ የጋራችን የሚሆንበትን ሁኔታ ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ባንዲራ የአፍሪካውያን የነፃነት ምልክትና የማነሳሻ አርማ ነው። ከ17 በላይ ሀገራት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት ያበረከተችውን አስተዋፆ ከግምት ውስጥ አስገብተው ሶስቱን ቀለማት ተጠቅመዋል። ብዙ የአፍሪካ ሀገራትና ጥቁር ህዝቦች የኢትዮጵያን ባንዲራ የፓን አፍሪካኒዚም ምልክት አድርገው ይወስዱታል። እንዲህ አይነት የህዝቦች ኩራትና ተምሳሌት የሆነ ባንዲራ ደግሞ እኩልነት አንድነትን የሚያንፀባርቅ እንጂ የሚከፋፉል አይደለም። ሆኖም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራችን የተቀመጠውን አርማ መጠቀም የማይሹ ወገኖች አርማው ኢትዮጵያዊ አንድነት ሳይሆን መከፋፈልን የሚገልፅ ነው የሚል ማደናገሪያ ይነዛሉ። ከላይ እንደጠቀስኩት ግን እውነታው የቱ ነው ብለን ከመረመርን ምላሹ ከነሱ ተቃራኒ ሆኖ ይገኛል።

የኢፌዴሪ መንግስት ለባንዲራችን ለሚሰጠው ክብር አንዱ  ማሳያ ተደርጐ የሚወሰደው በሀገር ደረጃ በየአመቱ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሚል ስያሜ የሚከበር በአል መኖሩ ነው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን እንደሌሎች ብሄራዊ በአላት የመላው ህዝብ በአል የመሆን ሁኔታው እየሰፋ  እየሄደ እንዳለ ምስክርነት መስጠት ይቻላል። አዲሱ ትውልድም ለባንዲራው ያለውን ክብር በየአመቱ በአል ከማክበር በዘለለ ብሔራዊን ክብርን የሚነካውን ድህነትን በማጥፋት ባንዲራችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ይኖርበታል። ባንዲራ ሀገራዊ መለያና የሀገራዊ ክብር መገለጫ መሆኑ እሙን ነው። ሆኖም ግን ባንዲራችን በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ተገቢ ክብር አግኝቶ የክብራችን ምንጭ መሆን እንዲችል አዋራጅ  ከሆነው ድህነት መውጣት  አለብን። ትንሽ  እድገታችን እየፈጠነ ሲሄድ ምን ያህል በአለም መድረክ የመደመጥ እድል እንዳለን ግልፅ ነው።

1 comment:

 1. ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚገለፅ አርማ ለዘመናት ስንጠቀምበት በነበረው አርንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ ቀለማት በያዘው ታሪካዊ ባንዲራ ላይ እንዲያርፍ ተደርጓል። በህገ መንግስታችን አንቀጽ 3 ላይ ሰንደቅ ዓላማውን በተመለከተ ግልፅ ድንጋጌ እንዲሰፍር ለማድረግም ተችሏል። ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የተመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሀይማኖቶች በእኩልነት በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ብሩህ ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል። የዓርማውን ትርጓሜ በተመለከተ በሰንደቅ አላማ አዋጅ
  ቁጥር 654/2001 የተገለፀው ድንጋጌም ይህንኑ ያመለክታል።
  በአዋጁ አንቀፅ 8 መሰረት ክብ
  የሆነው ሰማያዊ መደብ ሰላምን
  የሚያመላክት ነው፡፡ ቀጥታና እኩል
  የሆኑት መስመሮች የብሔር፣
  ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እንዲሁም
  የሃይማኖቶችን እኩልነት የሚያመላክቱ
  ናቸው፡፡ በሰንደቁ ላይ የተዋቀረው
  ኮኮብ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና
  ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን
  አንድነት የሚያመላክት ነው፡፡
  ቢጫው ጨረር በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት አንድነት ለብሔር፣
  ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፈነጠቀዉን
  ብሩህ ተስፋ የሚያመላክት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰንደቅ ዓላማችን
  የሃገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና
  ሕዝቦች የእኩልነት መብታቸው
  ተጠብቆ፣ ወግ፣ ባህልና ሃይማኖታቸው
  ተከብሮላቸው በፍላጎታቸው በአንድነት
  የሚኖሩ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ባንዲራ ሀገራዊ መለያና የሀገራዊ ክብር መገለጫ መሆኑ እሙን ነው። ሆኖም ግን ባንዲራችን በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ተገቢ ክብር አግኝቶ የክብራችን ምንጭ መሆን እንዲችል አዋራጅ ከሆነው ድህነት መውጣት አለብን። ትንሽ እድገታችን እየፈጠነ ሲሄድ ምን ያህል በአለም መድረክ የመደመጥ እድል እንዳለን ግልፅ ነው።

  ReplyDelete