EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 28 February 2019

የአድዋን የድል በዓልን በአዲስ የለውጥ መንፈስ






(ሚራክል እውነቱ)



የአድዋ የድል በዓል  በመላው ሀገራችን በድምቀት ለማክበር እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ከዛሬ 123 ዓመት በፊት ስለተፈጸመው የአድዋ ድል ልዩ ክብር የምንሰጥባቸው በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አድዋ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከጥንታዊ ታሪኳ ጋር ያገናኘ ታላቅ ገድል የተፈፀመበት መሆኑ ከታሪካዊ ዳራው መረዳት ይቻላል:: የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ሲባል አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት እንድንራመድ የጥንት አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር የተመሰከረበት የጦርነት ድል መሆኑን መስካሪ አያሻውም፡፡


መች ይሄ ብቻ ባህላችን ሳይበረዝ ሳይከለስ ተጠብቆ እንዲኖር አስችሎናል- አድዋ:: ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓውያኑ መጤ ባህል ቅኝ ግዛት የመወረር ምልክቶችን ብናይም፤ የመላ አፍሪካዊያን ኩራትና ድል የሆነው የአድዋ ድል በጦርነት ወቅት እምቢ ለሀገሬ በሚል አይበገሬነት መንፈስ ከአራቱም ማዕዘናት ገንፍሎ በመውጣት የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ለአፍሪካዊያን ብሎም ለዓለም ሀገራት ከፍ አድርጎ እንዲታይ ያስቻለ ድል መሆኑ እንድናከብረውም እንድንዘክረውም ምክንያት ሆኖናል፡፡ 

ይህን በዓል እንድናከበር ያስገደደን ምክንያታችን የጣሊያን መንግስት ባህር አቋርጦ ከአፍ እስከ ገደፉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቆ ሀያልነቴንና ታላቅነቴን ለዓለም አሳይበታለሁ ባለው ጦርነት ላይ ኢትዮጵያዊያኑ  በወንጭፍና በጎራዴ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት አንገቱን አስደፍቶ ወደ መጡበት ባህር ማዶ መመለሳቸው ሀገራችን በዓለም ዓቀፍ መድረክ እንድትታወቅና እንድትከበር ምክንያት ስለሆነ ነው፡፡ 

በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የአፍሪካን ምድር እንደ ቅርጫ መቀራመት ብቻ ሳይሆን ሀያልነታቸውን በማሳየት ቀኝ ገዥነታቸውን በየሀገራቱ ያለውን እምቅ ሀብቶችን የግላቸው በማድረግ አሳይተዋል፡፡ በአፍሪካ ምድር ለጠላት ያልተንበረከኩ ሀገራት ቢኖሩ ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ናቸው፡፡ በተለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ነጻነታችንን አስከብረን እንዴት መኖር እንደምንችል አስመስክራበታለች፡፡ ለሌሎች ሀገራት ሕዝቦችም አርዓያ ሆኗቸዋለች፡፡ ለነፃነታቸው በቁርጠኝነት እንዲታገሉ ምሳሌ በመሆን ለዓለም የነፃነት ትግልና ክብር ምሳሌ የሆነች ሀገር ናት - ኢትዮጵያ፡፡ ሌላው የአድዋ ጦርነት ጥቁር ሕዝብ ማሸነፍ እንደሚችልና የሰው ዘር ሁሉ እኩል እንደሆነ አውሮፓውያን ትምህርት ያገኙበት ድል ነው፡፡



ብዙዎቻችን የአድዋ ድል በዓልን ለምን መዘከር እንዳስፈለገን ግልፅ ስለመሆናችን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከዚህ አኳያ አንድ ፅሁፍ ላይ ያነበብኩትን ላካፍላችሁ፤ ‹‹አድዋን ድል የምንዘክረው በታሪካችን ስለምንኮራ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ አንዳንዶችታሪክ ተወቃሽ ትውልድ ላለመሆንም ጭምር እንጂ›› ይላል፡፡ ምን ይሄ ብቻ ሌላም ምክንያት እናስቀምጥ በአለም ህዝቦች ታሪክ ለነጭ ትዕቢት ድንበር አልባ የዘረኝነት መርዝ የማይገዛ ጥቁር ህዝብ መኖሩን ያስመሰከረ የዓድዋ ድል ስለሆነ ልንዘክር ይገባናል ይላል ፅሁፉ።የነጭን አንገት ያስደፋ በሀፍረት ያሸማቀቀ በፍርሀት ያርበደበደ ኢትዬጵያዊነት ኩራት አፍሪካነት ኩራት ጥቁርነት ክብር መሆኑን ያስመሰከረ የአፍሪካውያን ኩራት የዓድዋ ድል መሆኑን ሌላኛው እንደ ምክንያት አድርጎ ያስቀምጠዋል ።




የአድዋ ድል በዓልን ስናከብር በኢትዮጵያችን የመጣውን ለውጥና ህዝቡ እየተመለከተ ያለውን የሰላም፣የአንድነትና የልማት አብሪ ተስፋዎች እንዳይደበዝዙ ከድርጅታችን ኢህአዴግ ጎን የምንሰለፍበት ጊዜ ላይ መሆናችንን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የዘንድሮው 123ኛው የዓድዋ የድል በዓል ስንዘክር በተለየ ወቅት ላይ ሆነን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሀገራችንን አጋጥመውን የነበሩ ችግሮች በይቅርታ በዕርቅ ዘግተን እቺ በአያት ቅድመ አያቶቻችን ደምና ላብ የተገነባች ሀገር ወደፊት ለማራመድ ቆርጠን በተነሳንበት ወቅት ላይ ነው፡፡   ሀገርን የማበጣበጥ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ፊት ለፊት በመታገል ኢትዮጵያችንን ከትርምስ የማዳንና መሰረታዊ ለውጦችን የማስቀጠል ድርብ ሀላፊነታችንን ለመወጣት ዳግም ቃል የምንገባበት የድል በዓል ሊሆን ይገባል መልዕክቴ  ነው፡፡ የአባቶቻችንና የአንድነትና የመተባበር መንፈስ ወርሰን ወደፊት ታላቅ ሀገር እንገንባ፡፡




No comments:

Post a Comment