EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday 24 February 2019

መደማመጥ ለአገራዊ አንድነት መሰረት

(ፑላሎ ፓፒ)

በአገራችን ባህልና ወግ ማልደው ሲነሱ ቸር አውለኝ ማለት የተለመደ ነው፡፡ እናም እኔም ቸር አውለኝ ብዬ መልካም መልካሙን እያሰብኩ ወደ መስሪያ ቦታዬ የሚወስደኝ ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ የታክሲው ረዳት ሂሳብ ሲል ሁሉም ወደኪሱ እየገባ ሂሳቡን እየሰጠ መልስ ያለውም መልሱን እየተቀበለ ቀጠልን፡፡ በመሃል መልስ ሰጠኽኛል አልሰጠኸኝም ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ሁሉም ያወራሉ፡፡ ረዳቱም ተሳፋሪውም፡፡ ቀጠል አለና ደግሞ ሌላው ተሳፋሪ ‹‹ተረጋጋ ሰጥቶሃል›› አለው፡፡ አሁን ጭቅጭቁ ከአንድ ወደ ሁለት ሰፋና ሌሎች ተሳፋሪዎችም ታክለውበት መጯጯ ሆነ፡፡ አዳማጭ በሌለበት እንዴት መግባባት ይቻላል፡፡ ወይ መደማመጥ ደጉ አልኩኝ፡፡ ሾፌሩ በመሃል ገብቶ በቃ ተወው ስህተት ባትሆን ይሄ ሁሉ ሰው አይናገርህም አለና ረዳቱን ሊያቀዘቅዘው ሞከረ፡፡

ይሄ ትንሽ የሚመስል የታክሲ ገጠመኝ ነገሩን አገራዊ ወደሆነው ሁኔታችን እንደስበው አስገደደኝ፡፡ እኛስ ከስሜት ወጣ ብሎ በአስተውሎት ነገሮችን መመዘን፤ እንደ አገርም ለመግባባትም ላለመግባባትም መደማመጣችን በህይወታችን ውስጥ ያለውን ትሩፋት በመገንዘብ ነው ወይ እየተጓዝን ያለነው፡፡ ይህ ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ለሃሳብ ነፃነት  እውቅና የሰጠች፤ ሰዎች የመናገር የመፃፍ መብታቸው የማይገፈፍ መሆኑን በህገመንግስቷ የደነገገች አገር ናት፡፡ ይህ የሃሳብ ነፃነት አንዱ በአንዱ ላይ ተፅእኖ እንዲያሳድር ሳይሆን ሰዎች ሰብዓዊ የሆነ መብታቸውን በመጠቀም አንዱ የአንዱን መብት አክብሮ መንቀሳቀስ እንዲችል ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ የአገራችን ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙትን ፈተናዎች በአስተዋይነቱ ሲሻገራቸው የቆየ ህዝብ ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ ችኩልነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው በምሳሌ ሳይቀር እየተነገረው ነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያድገው፡፡ የቸኮለ አፍሶ ለለቀመ እንደዲሉበችኩልነት ውስጥ አስተዋይነት የለም፡፡ ራስን ስሜትና ፍላጎት ከመጫን ባለፈና አምባገነን ከመሆን የዘለለ ትርፍ የለውም፡፡ 


አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታም የራሰን ስሜትና ፍላጎት ሌላው ላይ ለመጫን የሚደረግ መውተርተር ነው፡፡  አገራችን የሚያስፈልጋት ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ሆኖ ሳለ አንዱ ወገን በጉልበት እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በሚል እሳቤ የሚደነፋበት መደማመጥ የሌለበት የፉክክር ጊዜ ሆኗል፡፡ አገራችንና ህዝቦቿን ከገቡበት ቀውስ ማውጣት የሚቻለው መንግስትን ያዳክማሉ ተብለው የሚታሰቡ ተግባራትን በመከወን ሳይሆን በጋራ ዓላማን ግብ አገር የሚያቃና ተግባር በመፈፀም ነው፡፡  

ዛሬ በቡድን ተዋቅሮ ጎራ ለይቶ መነቋቆር ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ነገ በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት ማጥበብ  እንደ ማስነው ጉድጓድ የሚቀል አይሆንም፡፡ ሁላችንም እንደምናስተውለው አሁን አገራችን ጉራማይሌ በሆነ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ባለፉት ዓመታት በአገራችን የተከሰተውን ችግር ከመሰረቱ መቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ህገመንግስቱ በግልፅ ያስቀመጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚሸራረፉበት ሁኔታ እንዳይኖር ያለፈውን አፈፃፀም ማስተካከል በሚቻልበት ሁኔታ ማስተካከያዎች ተደርገዋል፡፡   

አገራችን የምትከተለው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያግቧቸው ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው መነጋገር የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አገር ማኩረፊያ እንጂ ከአገር አኩሩፎ በባዕድ አገር መኖር እንዲበቃ በውስጥ ትግል ዴሞክራሲያዊ የሆነች አገር ለመገንባት የሚያስችል ስራ ተሰርቷል፡፡ እነዚህና መሰል ተግባራት በለውጥ ሂደት ውስጥ የተፈፀሙ እና እየጎለበቱ የሚሄዱ ናቸው፡፡

አሁን ላይ መንግስት እየወሰዳቸው ያለውን የሪፎርም ስራዎችን በአስተዋይነት መመልከት ይገባል፡፡ መንግስት ጆሮ ስጡኝ ሲል ህዝብ ጆሮ ሊሰጠው ይገባል፡፡ መንግስትም ህዝብን የሚዳምጥበት ሁኔታዎችን በማመቻቸት አገራችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ በአስተዋይነት መሻገር ይገባል፡፡

ይህ የመደማመጥና ገንቢ ትችት እየተሰጣጡ የመተራረም ባህል ከጠፋ ቆመንለታል ያለነውን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ ከመውደቀ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከቤቱ ጀምሮ የሚከፍለው ማናቸውም የጊዜና የእውቀት መስዋዕትነት ነገውን የተሻለ ለማድረግ ካለው ጉጉት የመነጨ ነው፡፡ ይህን የግልም ሆነ አገራዊ ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው የመደማመጥ ባህል በማዳበርና ችግሮችን በአስተዋይነት በመሻገር ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በሁሉም አቅጣጫ እየተሸረሸረ የመጣው የመደማመጥ ባህላችን እንዲያንሰራራ ማድረግ ይገባል፡፡ መደማመጥ ከሌለ መስማማት አይኖርም፤ የጋራ የሆነ እምነት መገንባት አይቻልም፡፡ መደማመጥ ከሌለ ሃሳቡን ሳይሆን ከሃሳቡ በስተጀርባ ያለውን አሉታዊ ትርጉም ወደማሰለሰል ይኬዳል፡፡ መደማመጥ ለሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ መደማመጥ የሩቅ አሳቢነት ምልክት ነው፡፡ መደማመጥ የአስተዋይነት ምልክት ነው፡፡ መደማመጥ የስልጣኔ መለኪያ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment