EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 2 November 2018

ጀግኒት! ከማጀት እስከ አደባባይ


በኤፊ ሰውነት
ከጥንት ከጠዋቱ የአገር ምሰሶ የቤት አለኝታ ሴት ናት፡፡ በባህልና ወግ ተጠፍንጋም ሴት ለቤቷ መሰረት ናት፡፡ ትዳር አጋሯን ጨምሮ ቁጥራቸው ይነስም ይብዛም ልጆቿን እንደአመላቸው አቅፋ ለወግ የምታበቃው ሴት ናት፡፡ የሴቶች ሁሉ ቁንጮ የሆኑት እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ አገራችን በወጣቻቸው እና በወረደቻቸው አባጣ ጎርባጣዎች ሁሉ የአገራችን ሴቶች ግምባር ቀድም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ደጀን ከመሆን ራስን በጦር ግምባር እስከመማገድ የደረሰ ብስለትና ብቃታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡

ይህ ጥንካሬያቸውን ዓለም በቅጡ ሳይገነዘበው፤ የተገነዘበውም አካል በሚገባ ዋጋ ሳይሰጠው በሴቶች ላይ የተዛባ አመለካከት ዘመናትን አስቆጥሮ ዛሬም ድረስ እኩልነታቸውን የሚጠራጠሩ ቀላል አይደሉም፡፡
አገራችንን ከጥንት ጀምሮ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ካደረጓት በመሪነት ቦታ ላይ ከነበሩት እነእቴጌ ጣይቱ፣ እቴጌ መነንን ጨምሮ መሰል ሴቶች በየደረጃው አገራቸውን በሙያቸው ተግተው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ህዝባቸውን በማገልገል ላይ ያሉ ሴቶች በርካቶች ናቸው፡፡ ይሁንና ሴቶች የአስተዋጽኦቸውና የልፋታቸውን ልክ ክብርና ዕውቅና ሳይሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በሴቶች ማብቃት ዙሪያ አመርቂ ስራዎች አከናውኗል፡፡ ይሁንና ከነበረው ስር የሰደደ የሴቶች ችግርና እንዲሁም ‹‹ሴቶች ይችላሉ›› የሚለው እውነታ በብዙዎች ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አልተመዘገበም፡፡
ካሳለፍነቻው ጥቂት ወራት ወዲህ በአገራችን በሁለንተናዊ መልኩ እየነፈሰ ያለውን የለውጥ አየር ከእኛ አልፎ የዓለም ትኩረትን በመሳብ ላይ ይገኛል፡፡ በየቀኑ ‹‹በአገሪቱ ምን አዲስ ነገር ይበሰር ይሆን?›› ሲል ሁሉም ጆሮውን ወደ አገራችን አዘንብሏል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ለውጡን ይበልጥ የሚያደምቁ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡ አንስቶች በሰሩት ልክ ዋጋ የማይሰጥበት፣ ሴት ልጅን በሁለንተናዊ መልኩ ማብቃት እንደ ችሮታ የሚታይበት አስተሳሰብና አሰራር ተቀብሮ ዛሬ ሴቶች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ከፍ ብለው ደምቀውና ፈክተው እየታዩ ይገኛሉ፡፡
በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውና በስልጣን እርከን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሆነ ከፍተኛውን የስልጣን እርከን ተረክበዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ እየተቀጣጠለ መሆኑን በአንድ ድምፅ ዘግበዋል፡፡
ከመደበኛ ትምህርት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሴቶች ተሳትፎ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም አሁንም በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም እንዲሁ ስራ የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገራችን የጥንት አባባል ከባለቤቱ ያወቀ ነውና ነገሩ ሴቶች ወደ ስልጣን ላይ መምጣት በፖሊሲ ደረጃ ተፅእኖ ከመፍጠር ባሻገር በቀጥታ ሴቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስልት በቅርብ ለይቶ ለመንደፍ እድል የሚሰጥ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት 37 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችን በውስጡ የያዘው የኢፊዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዝዳነት ሹመት አፅድቋል፡፡ ፕሬዝዳነት ሳህለ ወርቅ ዘውዴም በተለያየ አጋጣሚ በሚያደርጉት ንግግር እንዲሁም በሹመታቸው ወቅት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ወደጎን ትቶ ድህነትን ማሸነፍ እንደማይቻል በመጥቀስ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ አሳትፎ መንቀሳቀስ እንደ አገር የሚታቀደውን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ሲገልፁ ተሰምተዋል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርት እና በተለያዩ የልማት ስራዎች ረጅም እቅድ በማቀድ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ የልማት እቅዶች ስኬትም ይሁን ውድቀት በዋናነት የሚነካው ከግማሽ በላይ ቁጥር ያላቸው ሴቶችን መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን በአገራችን ያለውን የለውጥ ሂደት ማስቀጠል የሚችል ብቃትና የህሊና ዝግጁነትም በተሻለ ሴቶች ላይ እንደሚኖር መገመት አያዳግትም፡፡ በተለያየ አጋጣሚ እነዚህ አንስቶች የአመራርነትም ሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ ሲያቀነቅኑ የነበረበት ሁኔታ በመሆኑ ዛሬ ላይ ይህ አጋጣሚ በተሻለ ሁኔታ ውጤት ለማምጣት እድል የሚሰጣቸው መሆኑን ሹመኞች በተለያየ አጋጣሚ ሲጠቅሱ ይደመጣል፡፡
ሰሞኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚንስቴር ጀግኒት በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ ለማካሄድ የማህበረሰብ ንቅናቄ ፕሮግራም በይፋ አስጀምሯል፡፡  “ጅግኒት አለመች፣ አቀደች አሳካች” በሚል መሪ ቃል የሚከናወነውን ሀገራዊ የህብረተሰብ ንቅናቄ ዝግጅትን አስመልክቶ ዘጠኙ ሴት ሚኒስትሮችና የሁለቱ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴቶች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ የሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ የፊታችን ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት እንደሚካሄድም ተገልጿል።    
ይህ ንቅናቄ የሴቶችን ተሳትፎ ይበልጥ በማጠናከር በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚቻልበትን ሁኔታም በመፍጠር በኩል ስብሰቡ አቅም እንደሚሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በአገራችን በየደረጃው አቅም ያላቸው ሴቶችን ይበልጥ ወደ ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች እንዲመጡ በማድረግ በኩልም ይህ ንቅናቄ የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የሰላም ሚንስትሯ ክብርት ሙፈርህያት ካሚልም ተናግረዋል፡፡
"ጀግኒት አለመች፣አቀደች አሳካች" የሚለው መሪ ቃል በእርግጥም በተግባር ተተርጉሞ ቀጣዩ የስራ ጊዜ እቅዱ ሁሉ አየር ላይ የሚንሳፈፍበት ሳይሆን በተግባር የሚተረጎምበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ አድጎ የአገራችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ ጥያቄዎቻቸው የሚመለሱበት የተደራጀ አሰራር ተፈጥሮ ሁሉም ሴቶች ይበልጥ ከፍ ብለው የሚታዩበት የስኬት ዓመት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ሰላም፡፡

No comments:

Post a Comment