EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 9 October 2018

በታሪካዊ ምዕራፍ የተካሄደ ታሪካዊ ጉባዔ


ከኤፊ ሰውነት
ሰሞኑን የበርካቶች ቀልብ ሀዋሳ ላይ ነበር፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የፓርቲ አመራሮች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የውጭ ሀገራት ልዑካን ወዘተ ሀዋሳ ላይ ከትመዋል፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የመገናኛ ብዙኃንም የብዝኃነት ተምሳሌት በሆነው በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ ቀድመው ተገኝተዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ስብስብ ዋና ዓላማ 11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ድርጅታዊ ጉባዔ ለመታደም ነው፡፡

ሀገራችን በፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን እልባት የሚሰጥ አቅጣጫ ይቀመጣል የሚል እምነት በሁሉም ላይ አድሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አንድነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው ይወጣሉ የሚልም የብዙዎች ተስፋ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ጉባኤው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች በብዙዎች ዘንድ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡

ከመስከረም 23-25 ቀን 2011 ዓም ‹‹ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ኢህአዴግ አገራችንን ወደፊት ማሻገር የሚችልበት አቅም ገንብቶ የወጣበት፤ አመራሩም ቃሉን ያደሰበት መድረክ ነው፡፡ ጉባዔው የለውጡ ትሩፋቶች የሚጠናከሩበት ሁኔታ ላይም መክሯል፡፡ የተጀመረውን ፈጣን ልማት ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ ላይም ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ በተለይ የዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበር መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑ በጥልቀት ተመልክቷል፡፡ የስራ አጥነት ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በተለይም ለወጣቶች የስራ እድል ማስፋት እንደሚገባ አመላክቷል፡፡ ብሔረሰባዊ ማንነት ማክበር እንደተጠበቀ ሆኖ የሀገራችን አንድነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ለማከናወንም መግባባት ላይ ደርሷል፡፡

ጉባኤ ባለፉት ጥቂት ወራት እንደአገር የመጡ ለውጦች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው መሆኑን የተመለከተ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ውሳኔዎች መሬት እንዲነኩ ቆራጥ አመራር በመውሰድ የራሳቸውን ሚና መወጣታቸውን አስምሮበታል፡፡

ጉባኤተኛው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መስተካከል አለባቸው ይሄ የእኛ ክፍተት ነው ያላቸውን ነጥቦች በሙሉ በማውጣት ውይይት እንዲደረግበት አድርጓል፡፡ በየደረጃው የሰብዓዊ መብት፣ የህግ የበላይነት፣ የፌዴራሊዝም ስርዓት አፈፃፀም፣ የልማትና መሰል ጥያቄዎች በጉባኤተኛው ያለ ገደብ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ጉባኤው በእህት ድርጅቶች መካከል ያለውን መጠራጠር ያጠበበ ነው ማለትም ይቻላል፡፡

ጉባዔተኛው በአገራችን እዚህ እዚያም የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮችን በመፍታት የአገራችንን ልማት ማፋጠን እንደሚገባም አስምረውበታል፡፡ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ በሀዋሳ ስታዲየም በርካታ የአካባቢውና የአጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች በተገኙበት በሲዳማ የባህል ጭፈራና የምስጋና ስነስርዓት ተጠናቋል፡፡ የሲዳማ አባቶችም የቄጤላ ስነስርዓት በማካሄድ ምስጋናቸውንና አክብሮታቸውን ገልፀዋል፡፡  

ቄጤላ የሲዳማ ሽማግሌዎች የሚጫወቱት ጨዋታ ስርዓት ወይም የጨዋታው ስያሜ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ግጥም እየደረደሩ ያሞግሳሉ፡፡

አብይ ዳኤ ቡሹ
አብይ አህመዲ ቤቶ ዳኤ ቡሹ
አብይ ባጢሉ ቤቶ
አብይ ሲዳማ ባጣኖ፡፡ ሲዳሙ አብይ ባጣኖ
አብይ ኢትዮጵዩ ማኒ በጣኖሲ
በማለት አብይ የአህመድ ልጅ እያሉ አክብሮታቸውን ገልፀዋል፡፡ አብይ ሲዳማን ይወዳል ሲዳማም አብይን ይወዳል፣ አብይ ኢትዮጵያን ይወዳል እያሉ በፍቅር አዚመዋል፡፡ …..ዳኤ ቡሹ እያሉ ያላቸውን አክብሮትም ገልፀዋል፡፡

በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይም የሲዳማ አባቶች ፍቅርን ሰብከዋል፡፡ መልካም ምኞትና ጸሎታቸውንም አድርሰዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢህአዴግ ጉባኤ ግቡና ያሳካና ታሪካዊ ነበር፡፡ ለነገ ስንቅ የሚሆኑ ውሳኔዎችን የተላለፉበት ለጋራ ጎጆአችን በጋራ ለመትጋት ቃል የተገባበትም ነው፡፡

ሀገራች በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት የተካሄደው ይሄ ታሪካዊ ጉባዔ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ ውሳኔዎች የተላለፉበት ነው፡፡ ለጉባዔው ውሳኔዎች መተግበር ደግሞ ሁሉም ሀላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን የሀገራችንን ከፍታ በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

No comments:

Post a Comment