(በክሩቤል)
ሀገራችን ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት
መከተል ከጀመረች ወዲህ በኢህአዴግ አመራር በሁሉም መስኮች ሊባል በሚችል ደረጃ እመርታዊ ለውጦችን ስታስመዘግብ ቆይታለች። ሆኖም
በሂደት በዋናነት ከራሱ ከኢሕአዴግ ውስጥ በመነጩ ችግሮች የተነሳ የተጀመረውን እድገት ሊቀለብሱ የሚችሉ ብሎም ሀገራዊ አንድነታችንን
አደጋ ውስጥ የከተቱ የአመራር ችግሮች ተፈጥረዋል። በፓርቲው በተለይም በከፍተኛው የአመራር እርከን ባጋጠመው የስልጣን አተያይ መዛባትና
የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ መሸርሸር የተማረረው ህዝብ ለተቃውሞ፣ ለዓመጽና ለብጥብጥ እንዲነሳ ሆኗል።
ሙስናና አድሏዊ አሰራር በመስፋፋቱ ጥቂቶች
የሀገርን ሀብት በማንአለብኝነት ሲዘርፉ በተቃራኒው አብዛኛው ዜጋ ከመንግስት ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ መብት እንኳን ሳያገኝ
ቀርቷል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ይሁን በመለስተኛ ደረጃ የእውቀትና ክህሎት ባለቤት ቢሆኑም በሚፈለገው ልክ የስራ ዕድል ያልተፈጠረላቸው
ወጣቶች የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮች እንዲቀረፉ የሚጠይቁ መፈክሮችን አንግበው ተቃውሟቸውን በቁጣ ገልፀዋል። መላ ህዝቡም ከመንግስት
ተቋማት የሚጠብቀው ጥራት ያለውን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻሉና ይህንኑ ቅሬታውን ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ሲያቀርብም ሰሚ
ባለማግኘቱ ቅሬታውን በአደባባዮች ወጥቶ ሲገልፅ ቆይቷል።
ኢህአዴግ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ብሎ የሚወስዳቸው
ርምጃዎች ችግሩን ከስሩ የሚነቅሉ ሳይሆኑ የሚያስታምሙ፤ አንዳንዴም ችግሩን የሚያባብሱ በመሆናቸው ዜጎች በመሪው ድርጅት መፍትሄ
የማመንጨትና የመፈፀም አቅም ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድረዋል። ለዛም ነው እንደ ሀገር ከዕለት ወደ ዕለት በማይበርድ ቀውስና ግጭት
አዙሪት ውስጥ ገብተን ስንዳክር የቆየንው።
ነባራዊ ሁኔታው ድርጅቱን ብሎም ሀገሪቱን ከመስቀለኛ
መንገድ ላይ እንዳቆማቸውና ወቅቱ ግድ የሚለውን መፍትሄ አለመስጠት ሊታረም የማይችል ጥፋት የሚያስከትል መሆኑን የተገነዘቡት የኢሕአዴግ
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባለፈው አመት አጋማሽ ባደረጓቸው ተከታታይ ስብሰባዎች ስር ነቀል ለውጥ ያመጡ ውሳኔዎችን
አስተላልፈዋል።
በሰብአዊ መብት አያያዝ የሚታዩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ
አካሄዶች እንዲቆሙ፣ በተለይም በማረሚያ ቤቶች የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላት እንዲፈቱ መደረጉና “ማዕከላዊ” በመባል
የሚታወቀው ዜጎች ሰቆቃዊ ህይወት የሚገፉበት እስር ቤት እንዲዘጋ መወሰኑ ቀዳሚዎቹ የለውጥ እርምጃዎች ናቸው። ሀገራዊ ሁኔታው እድሉን
ነፍጓቸው በተለያዩ ሀገሮች በመሆን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ
ጥሪ በመደረጉ በርካቶቹ ወደ ሀገራቸው ገብተው በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የየራሳቸውን ሚና መጫወት ጀምረዋል። ለውጡን እንዲመራ ሃላፊነቱን የተቀበለው አዲስ አመራር በዚህ ብቻ ሳይወሰን
በዉሳኔዎቹ መነሻነትና በላቀ ተነሳሽነት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።
በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ ከሀገራችን አልፎ
ለሌሎች ሀገሮችም የተረፈ ነው። የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ሁኔታን በአብነት ብናነሳ ሂደቱ ለዘመናት የተራራቁ ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማዶች
እንዲገናኙ አስችሏል። በሁለቱ ሀገራት አዋሳኝ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ በር ከፍቷል። ይህም ክስተት በአጠቃላይ
በምስራቅ አፍሪካ መካከል በትብብር ላይ የተመሰሩ ስራዎችን እንዲከናወኑ ተጨማሪ እድሎችን ያመቻቸ ነው። በኤርትራና በሱማሊያ፣ በኤርትራና
በጂቡቲ መካከል የነበሩ ቁርሾዎች እንዲቀረፉና አካባቢያዊ ሁኔታው ሰላምና መረጋጋት እንዲታይበት ምክንያት ሆኗል።
ለዚህ እንድንበቃ በኢሕአዴግና በሚመራው መንግስት
የተከናወኑ ስራዎችና ይህን ተከትሎ በሀገራችንና በአካባቢው የመጣው ለውጥ በሀገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ
ተቋማትም ጭምር እውቅና የተቸራቸው ናቸው።
መላው የሀራችን ሀዝቦች ለውጡ እየተጠናከረ
በሄደ ቁጥር ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የታመነ ነው። ለዛም ነው ህዝቡ ለውጡን ለማስቀጠል ያልተቆጠበ ድጋፋን እየሰጠ የሚገኘው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ለውጥ ሲጀመር ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀስ ኃይል መኖሩ ተፈጥሯዊ ነውና በሀገራችን የተጀመረው ለውጥም
እዚህም እዛም ተግዳሮች እያጋጠሙት ነው። የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙና በሙስና የተጨማለቁ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ሲወሰድ ከብሄር
ጋር አስተሳስሮ ርምጃውን በጥርጣሬ ማየትና ማጠልሸት፣ የታጠቁ ሃይሎች የሚያደርጉት የሃይል ትንኮሳ፣ በዩንቨርስቲዎች የሚታየው አለመረጋጋትና
በአንዳንድ አካባቢዎች የሚያጋጥሙ የደቦ ፍትህ እርምጃዎች የዚህ መገለጫዎች ናቸው።
ሀገራዊ ለውጡ ያስገኛቸውን ድሎች በተሟላ ሁኔታ
ለማጣጣም በአንድ በኩል የለውጡን ቀጣይነት ማረጋገጥና ተቋማዊ እንዲሆን ማስቻል፣ በሌላ በኩል ከለውጡ በተቃራኒ ቆመው እንቅፋት
የሆኑ ሃይሎችን ለይቶ መታገል ግድ ይላል። የለውጡን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በመንግስትም በድርጅትም ረገድ ሁለንተናዊ ሪፎርም እየተደረገ
መሆኑ ይገለፃል። በተለያዩ ሴክተሮችም ሴክተር ተኮር የሪፎርም ስራዎች ሲተገበሩ እያየን ነው። ብሄራዊ እርቅና ብሄራዊ መግባባትን
ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተቋማዊ መልክ እየያዙ ናቸው።
ለውጡን የሚገዳደሩ ችግሮችን ከመግታት አንፃር
መንግስትና መሪው ድርጅት በሆደ ሰፊነት የሚያልፏቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ግን ቸል ሊባል
የሚገባው አይደለም። አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ጉዳይ ለድርድር መቅረብ የለበትም። ከሰላማዊ የትግል አካሄድ ባፈነገጠ መልኩ ነፍጥ
አንስተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ስርዓት ማስያዝም ሌላው ለለውጡ ቀጣይነት ሲባል የግድ ሊፈፀም የሚገባው ተልዕኮ
ነው።
እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ በጋራ የሚጠበቁብንን
ሃላፊነቶች እንዲሁም በተናጠል ያሉብንን የዜግነት ሃላፊነቶች በአግባቡ ልንወጣ ይገባናል። አሁን ያለው አድማጭና ተደማጭ የጠፋበት
ሁኔታ ለሰላማችን ሲባል መቀየር ይኖርበታል። ሁሉም ተናጋሪ፤ ሁሉም ትክክል ነኝ ባይነታችንን አቁመን እርስ በርስ መደማመጥ፣ አንዳችን
የሚጎድለንን ከአንዳችን መሙላት፣ እንቅስቃሴዎቻችንን ከህዝብና ከሀገር ጥቅም አኳያ ማየት ይኖርብናል። የፖለቲካ ኃይሎችም በመካከላቸው
የሚታዩ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማስታረቅ ለጋራ ዓላማ መቆም አለባቸው። ህዝቡም ግራና ቀኙን አይቶ ለሀገርና ለህዝብ የሚጥቅም አጀንዳ
ያለውን መደገፍ፤ የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑ አጀንዳዎች እንዲከስሙ መንቀሳቀስ አለበት። በአጠቃላይ የሀገር ሰላምና ግንባታ ጉዳይ
የጋራ ጉዳያችን በመሆኑ የየድርሻችንን ሃላፊነት መወጣት ይኖርብናል።
No comments:
Post a Comment