EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 14 August 2018

ዲያስፖራው ለሀገሩ - ሀገር ለዲያስፖራው


 (በኪያ አባቢያ)
ቁጥሩ እየጨመረ ከሚገኘው የዓለም ህዝብ ውስጥ ከ210 ሚሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ካላት የብራዚል ህዝብ ቁጥር የሚልቅ ህዝብ ከአገሩ ውጭ እንደሚኖር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከአሜሪካ ህዝብ 8 በመቶ የሚሆኑት ትውልድ እና እድገታቸው ከተለያዩ አገራት የሚመዘዝ ነው፡፡ 11 ሚሊየን ህዝብ ከሚጠጋ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ህዝብ ውስጥ 10 ሚሊየኑ ከሌሎች አገራት እንጀራን ፍለጋ የመጡ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡ ግለሰቦች አገራቸውን ጥለው ሌላ አገርን ለማማተር የሚገደዱት የፖለቲካ፤ ኢኮኖሚ አሊያም ማህበራዊ ችግሮች   ሲጋርጥባቸው ነው፡፡ የተማረም ሆነ ያልተማረ ዜጋ አገሩን ጥሎ ሲሰደድ ለአገሩም ሆነ ለተቀባዩ አገር ጫናና እና ክፍተት እንደሚፈጥር ሁሉ የተለያዩ እድሎችንም የሚፈጥር ነው፡፡

በተለይም የተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት (Brain Drain) ለተቀባዩ አገር እንደ ሲሳይ የሚቆጠር ቢሆንም በአንጻሩ ታዳጊ አገራት ከዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎቻቸው 20 በመቶውን  በዚህ ምክንያት ለማጣት እንደሚገደዱ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ተቋማት ይጠቅሳሉ፡፡ ያደጉ አገራት በቴክኖሎጂ እና ፈጠራ የልህቀት ሰገነትን እንዲቆናጠጡ ከዜጎቻቸው በተጨማሪ የሌሎች አገራት ዜጎች (የዲያስፖራዎች) ሚና የትየለሌ የመሆኑ እውነታም ብዙዎች የሚያውቁት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአሜሪካ ስመ ጥር የህዋ ሳይንስ ምርምር ማዕከል የ‹‹ናሳ›› ልህቀት እና ግኝቶች ውስጥ የኢትዮጵያን ጨምሮ የሌሎች አገራት ምሁራን ደማቅ አሻራ ስለማኖራቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በአጠቃላይ ደግሞ በአሜሪካ የኢንጅነሪንግ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ውስጥ ወደ ሩብ የሚጠጋው አገርቷን መጠለያ ባደረጉ የሌሎች አገራት ዜጎች የተገኙ ስለመሆናቸው ይወሳል፡፡
በርካታ አገራት በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን ወይም ዲያስፖራውን የሚመለከት የተደራጀ አሰራር እና የፖሊሲ ስርዓት ባይኖራቸውም የዲያስፖራ ትውልድ አገራትም በእነዚህ ዜጎቻቸው ምክንያት ከሚያጡት በላይ የሚያተርፉት እንደሚልቅ የተለያዩ አገራትን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በትውልድ አገራቸው ኢኮኖሚውን የሚደጉም ገንዘብ ከመላክ በተጨማሪ ቴክኖሎጂ እንዲዳብር እንዲሁም ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ዲያስፖራዎች ትልቁን ድርሻ ይጫወታሉ፡፡
በቻይና ለመጣው የቴክኖሎጂ እምርታ በሌሎች አገራት ኑሯቸውን አድርገው የቀሰሙትን እውቀት እና ልምዳቸውን ለአገራቸው ባገሩ ‹‹የባህር ኤሊዎች›› ተብለው በሚጠሩ ቻይናውያን አማካኝነት ስለመቀጣጠሉ ይገራል፡፡ እነዚህ ሰዎች የአገርቷን የቴክኖሎጂ ዘርፍን በበላይነት ከመምራት በተጨማሪ መንግስትን ከሚያማክሩት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ህንድ ከሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ውጭ በዓመት 70 ቢሊየን ዶላር ገዳማ ከዲያስፖራው ታገኛለች፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም ዲያስፖራው እውቀት እና ጉልበቱን ለአገሩ ሲያውል እና አገር ውስጥ ያለውን አቅም መደገፍ ሲችል ታምር መፍጠር እንደሚቻል ምሳሌ የምትሆን ሌላኛዋ አገር አይርላንድ ናት፡፡ በዚህች አገር በ2009ኙ አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ የተንገዳገደው ምጣኔ ኃብቷን ዲያስፖራዎች ከውድቀት እንደታደጉት ይጠቀሳል፡፡ እነዚህን የማሳሳሉ ጥቂት የስኬት ልምዶች ቢኖሩም አገራችንን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ አገራት የዲያስፖረውን አቅም እና እውቀት በሚፈለገው ደረጃ አልተጠቀሙበትም፤ እየተጠቀሙም አይደለም፡፡ 
‹‹በየትኛውም የዓለም ክፍል ኢትዮጵያዊ አይጠፋም›› የሚባልለት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በቁጥር ደረጃ ከሁለት ሚሊዮን የሚሻገር መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ብዙ ልምዶች እና አውቀት ሊቀሰምባቸው የሚቻልባቸው በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በካናዳ ከፍተኛ ቁጥር የሚይዝ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የሚገኝ ቢሆንም ከቁጥሩ ሚዛን ጋር የሚስተካከል  ጥቅም ለአገሩ አስገኝቷል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ጥቂቶች በተናጠል ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር አገርን እና ወገንን የሚጠቅም ተሳትፎ በፖለቲካ ቅራኔ እና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ከዲያስፖራው አልተገኘም፡፡ ከምንም በላይ የአገሩን ፍቅር በልቡ ይዞ የሚኳትነው እና በአካል ርቆ ቢገኝም በመንፈስ ሁሌም ኢትዮጵያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገሩን እና ዲያስፖራውን የሚያቀራርቡ ተግባራት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሰራታቸው በርካታ ቁጥር ላለው ዲያስፖራ ከአገሩ ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር በተግባር ለመኖር ከተስፋ በዘለለ እርግጠኛ መሆን ሳይችል ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት የዲያስፖራው እና የአገራችን ተስፋ እና ምኞት በተግባር እንዲተረጎም ሁኔታዎችን ማመቻቸት ጀምሯል፡፡ ይህ የለውጥ ጅማሮ በአገርቱ እና በዲያስፖራው መካከል የነበረውን ርቀት ለማጥበብ ድልድይ የሚገነባ ሆኖም ተገኝቷል፡፡ ከአገሩ ጋር የተኮራረፈውን የአገር ልጅ ኩርፊያው እንዲሽር ዳግም ከእናት አገር ጋር ያለው ትስስር እንዲታደስ እና በተግባር እንዲኖር መንገድ ተከፍቷል፡፡ በአሜሪካ የኮምፕዩተር እና የቴክኖሎጂ ልህቀት ማነሃሪያ የሚባለው የሲሊከን ቫሊን ገድል በአገራቸው ለመድገም የሚተጉ እና በስኬት ዋዜማ ላይ እንደሚገኙ የህንድ እና የቻይና ዲያስፖራዎች ሁሉ የእኛም ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ይህንኑ እውን ለማድረግ እቅድ መንደፍ የጀመረ ይመስላል፡፡
በቅርቡ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረገው በኢሕአዴግ ሊቀ መንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው ልዑክ በተለያዩ ግዛቶች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ ጋር በአገራችን መጻኢ እድል እና ስለ ዲያስፖረው ድርሻ ተወይይተው ተግባብተዋል፡፡ ዲያስፖራውም ስለ ኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግና ሰርክ የሚተጋ ስለመሆኑ እና በያለበት ለአገሩ አምባሳደር ለመሆን በዋሸንግተን ዲሲ፤ በሎስ አንጀለስ እንዲሁም በሚኒሶታ ስቴቶች ከፍ ባለ ድምጽ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ያቀረቡትን በቀን የአንድ ዶላር ጥሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ከመቀበላቸውም ሌላ በእውቀት ሽግግር እና በኢንቨስትመንት በመሳተፍ ለአገራችን ትንሳኤ ያላቸውን ከማበርከት ወደ ኋላ እንደማይሉ በየመድረኮቹ በእምባ እና በደስታ ሲቃ ገልጸዋል፡፡
ይህንን መገፈፍ የጀመረውን የኩርፊያ ጭጋግ ተረት ለማድረግ እና የዲያስፖራውን አቅም  በማቀናጀት ለታለመው ዓላማ ለማዋል የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የቤት ስራዎች ይጠብቁታል፡፡ አገርን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም አቅም እንዳይባክን ኤምባሲዎች እና ቆንሲላ ጽ/ቤቶች ይህንን ኃይል ከአገሩ ጋር ለማቆራኘት ለሚጠብቃቸው ሰፊ ስራዎች ራሳቸውን ማደራጀት እና ይህንን ማስተናገድ እና መሸከም የሚችል አቅም መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ተቋማትም ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከሙስናና እና አድልዎ በጠራ መልኩ እነዚህን ጨምሮ ለአገር እድገት እና ብልጽግና አስተዋጾ ማበርከት የሚሹ ዜጎች እና ግለሰቦችን ለማስተናገድ ከዚህ በፊት ይስተዋል ከነበረው የተንሸዋረረ አሰራር ሊላቀቁ ይገባል፡፡ እንደ ቻይና፤ ህንድ እና እስራኤል ሁሉ አገር ከአገር ልጅ በርቀት ሳይገደብ እንድታተርፍ እና ለቀጣይ ትውልድ የሚትተርፍ አገር ለመገንባት የተጀመረውን  ሂደት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment