EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 22 August 2018

ለውጡን ማስቀጠል የሚያስችል ስብዕናን መገንባት ከራስ ይጀምራል






ከኤፊ ሰውነት
ያሳለፍናቸው ሁለትና ሶስት ዓመታት በርካታ ዋጋ ያስከፈሉ፤ በሰውና በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ውድመት ያደረሱ አገራችንን በአስቸጋሪና አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ያስገቡ በጥቅሉ አገራችን ገደል አፋፍ ላይ ቆማ የነበረችበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ እነዛ ጊዜያት አልፈው ዛሬ ላይ አገራችን ህዝቡ ሲያነሳው ለነበረው የለውጥ ጥያቄ ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ህዝቡ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎችም ምላሽ መስጠት ተጀምሯል፡፡ ሆኖም አገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሆናም በዜጎች ላይ የሚደርሰው የህይወትና የንብረት ውድመት መቆም አልቻለም፡፡ “ከክልሌ ውጣልኝ” የሚል ጸረ-ህገመንግስት የሆነ የለውጥ ሂደቱ ጎታችና አደናቃፊ አስተሳሰብ ማራመድ አልቀረም፡፡ አሁንም ዜጎች በአገራቸው ዘራቸው፤ እምነታቸው  እየተቆጠረ መፈናቀላቸው እና ለከፋ እንግልት እና ስቃይ መዳረጋቸው እንዲሁ አላቆመም እየተዳረጉ ነው፡፡ 


መነሻው ምን ይሁን ምን ዛሬም ድረስ አገራችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ቆም ብሎ በማሰብ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል፤ ይህም ለነገ የማይባል ትልቅ የህልውና ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ግርግር ለቀማተኛ ይመቻል እንዲሉ ዛሬም በግርግር ሰበብ የንጹሀንን ህይወት የሚያጠፉ፤ አካል የሚያጎድሉ፤ የህዝብን ሃብት የሚዘርፉ፣ የሚያዘዋውሩ፤ የግለሰቦችን ሃብት ንብረት የሚያወድሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ቀላል አይደሉም፡፡ በሀገራችን የተጀመረው የለውጥ ሂደት በርካታ ሃሳቦችን በማስተናገድ በአገራችን ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለውን አለመግባባት በመፍታት ሰላማዊ ወደሆነ ሁኔታ ከመመለስ ጀምሮ በአገር ውስጥም የህግ ታራሚዎችን በይቅርታ በመፍታት በአገር ውስጥም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ በአገሩ ነፃነት ተሰምቶት እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ አዲስ የለውጥ መንፈስ እንዲሰፍን ተደርጓል፡፡



የለውጥ ሂደቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ መንግስት እየወሰዳቸው ሰው ሰራሽ በሆነ መንገድ ንረ የነበረው የውጭ ምነዛሪን ለማረጋጋትም ይበል የሚያሰኝ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ በተለይ ከዚህ የለውጥ እርምጃ ጋር ተያይዞ ለውጡ ያስደነበረው ኪራይሰብሳቢ ሃይል በበርሜል፣ በካርቶን በዘይት ጀሪካን ጭምር አለአግባብ የተከማቹ የህዝብና የመንግስት ሃብቶችን ለማሾለክ ሲጥር ይስተዋልል፡፡ የፖለሲ ሪፖርቶች እዚህ አካባቢ ይሄን ያህል ህገወጥ ንብረት፤ በዚህ አካባቢ ይሄን ያክል ህገ ወጥ ዶላር ተያዘ በሚል የሚገለጸው ዜና በእርግጥም እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ እርምጃዎች ጥቅማቸውን እየነካባቸው ያሉ ሃይሎች እንዳሉ ማረጋገጫ ነው፡፡

  
በርካታ የአገራችን ህዝብ አሁን በአገራችን እየመጣ ያለው ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ነገን በተስፋ እንዲያ ያደረገ ቢሆንም በሌላ በኩል እዚህ እዚያም የሚሰማው ዜና ሰላም እየነሳው ነገስ ምን ይሆን በሚል ስጋት ውስጥ ህዝቡ እንዲገባ የሚያደርግ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነት እንዲኖር መስራት ይገባዋል፡፡ ዶ/ር አብይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ እንደተደመጠው የመቃቃር የጥላቻና የመገፋፋት ፖለቲካ ቀርቶ አዲስ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሚያሳትፍ ያለፈውን ጠባሳ የሚሽር መንፈስ በአገሪቱ እንዲኖር በመደመር ስሌት ሁሉም የሃሳብ ልዩነቱን ይዞ በአገሩ ጉዳይ ላይ የጋር አስተሳሰብ መያዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡   


በአገራችን ተግባራዊ ተደርጎ ዓመታትን የተሻገረው የፌዲራሊዝም ስርዓት እሴቶችም በህገ መንግስቱ በግልፅ ሰፍሮ እንደሚገኘው አብሮነት፣ መከባበርና መቻቻል በመሆኑ ይህን እሴት እንዳይሸረሸር መስራት ይገባል፡፡ የለውጥ ሂደቱን እንዳይደናቀፍ ከስሜት እና ማን አለብኝነት የፀዳ ስብዕናን መላበስ ግድ ይላል፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለውጥ አደናቃፊ የሆኑ ሁኔታዎችን ከቤቱ ጀምሮ መስመር በማስያዝ አገራችን የጀመረችዉን የለውጥ ሂደት ማሻገር እንዲቻል አጋዥ እንጂ አደናቃፊ መሆን እንደማይገባ ማስተማር ይገባል፡፡ ወጣቱም ገፊ የሆነ ሁኔታ እንኳን ቢኖር ራሱን ከስሜት ራቅ አድርጎ ነገን አሻግሮ ማየት የሚችል ስብዕና ሊላበስ ይገባዋል፡፡ ሰላም፡፡


No comments:

Post a Comment