EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday 26 July 2017

የፍቅር እርጓችን ውስጥ ክፉ ዝንብ አትጠልቅም!

ሙሼ በፀጉር ቤቱ ውስጥ ከሚሰማው የማሽኖች ድምፅ ውጪ የነገሰው ዝምታ አላስደሰተውም፡፡ የሆነ ወሬ ፈጥሮ ድባቡን ለመቀየር ቢያስብም ጠብ የሚል ነገር ሊመጣለት ግን አልቻለም፡፡ አዕምሮው ሰንበትበት ወዳሉ ጉዳዮች መለስ ብሎ ሲያጠነጥን አንድ ጉዳይ አስታወሰና ፊቱን ቀጨም፣ ትንፋሹን ሰብሰብ አድርጎ ንግግሩን ጀመረ፡፡
እኔ የምለው ምን አይነት ማስተዋል የጎደለው ሰው ይሆን ዘርን ከዘር አፋጅቼ ስልጣን በእጄ እጨብጣለሁ ብሎ አስቦ ጭፍን ጥላቻን የያዘ ሃሳቡን ፌስቡክ ላይ የሚለጥፍ?” አለና ሙሼ ያችን ጠባብ ክፍል በድምፁ ሞላት፡፡

ፌስቡኩን ከፍቶ ሀገር እንዴት ዋለች ብሎ ሲቃኝ ያገኘውን አንድ ፅሁፍ ሰንበት ያለ ቢሆንም ከዝምታ ይሻላል በሚል ለውይይት መነሻ ሊያደርገው ፈልጎ ነው፡፡
የትግራይ ክልላዊ መንግስት በክልሉ የተለያዩ ጉብኝት ሲያካሂዱ ለቆዩት የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌ ተወካዮች የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አብሮነት እና ወዳጅነት የሚያጠናክር ሽልማት ማበርከቱን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማ አንድ ዲያስፖራ በፌስቡኩ ላይ ያሰፈረው በአፀያፊ ቃላት የተሞላ ፅሁፍ ትዝ ብሎት ነው፡፡
ጉድ እኮ ነው፤ ይሄን የመሰለ ጥዑም ዜና በሰማንበት ጆሯችን እና ባየንበት አይናችን ደግሞ ለሀገሬ ይሄን ሰራሁ ብሎ የሚጠቅሰው የሌለው ሰው ‹‹አማራ እና ትግራይ የማይመስል ፍቅር ውስጥ ገቡ›› ብሎ የፌስቡኩ ግድግዳ ላይ የሚለጥፈው ላይክና ሼር ለመሰብሰብ እንጂ እውን የአማራ እና የትግራይ ክልል ተወላጆች ሻሞላ መዘው የተፋጁበትን የትኛው ፀባቸውን ከታሪክ አጣቅሶ ነው? ሲል አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ ፀጉሩን ለመስተካከል ተራውን ወደሚጠብቀው ኑርሰፋ በጥያቄ አይን ተመለከተ፡፡
የዘወትር ደንበኛው ኑርሰፋ ብለሽ ብለሽ ጸጉር መቁረጥ ትተሸ ፖለቲካ ጀመርሽ? አለ የሀገሬ ሰው ብሎ ሙሼ ላይ ሊሳለቅበት ሞከረ፡፡
ሙሼም ፈጠን ብሎ ምላሽ ከማያጣው አንደበቱ ጆንያ ሙሉ መልስ ዝቆ ወደ ኑርሰፋ ጆሮ ያዘንበው ጀመር፡፡
ወዳጄ ኑርሰፋ አንተ በደህና ጊዜ አለመማርህ፤ ታሪክ አለማወቅህ ጠቅሞሀል፡፡ ሀገር ትቃጠል ብሎ በሰው ሀገር ላይ ተደብቆ ክብሪት ሊጭር የሚሞክር የሀገር ጠላት ፌስቡኩ ላይ እየለጠፈ ህዝብ ሊያደናብር ሲሞክር ሃሳቡን እንደእኔ እያነበብክ ከምትበሣጭ በእውነት እልሀለሁ የኔታ በልጅነትህ ገርፈውህ እርም ብለህ የቀረህባትን ትምህርት ቤት አመስግን::” አለው፡፡
ኑርሰፋ አንተስ ተምረህ የት ደረስክ?” ሊለው አሰበና የሙሼን ምላሽ እንደማይችለው አውቆ ለራሱ ማጉረምረሙን ቀጠለ፡፡
ሙሼ ግን እየውልህ ኑርሰፋ፤ አንተ መቼም በአንዱ ጆሮህ ሰምተህ በሌላው ነው የምታፈሰው፤ በማለት ማብራሪያውን ዘለፋ አክሎበት ቀጠለ፡፡
እነኚህ ሁለት ህዝቦች እኮ ለዘመናት ተከባበረው የኖሩ፤ ተቀራራቢ ባህልና ወግ ያላቸው፤ በስጋና በደም የተዋሀዱ፤ አንድ በሬ ቅርጫ አርደው ፋሲካና መውሊድን፣ ገናና አረፋን በፌሽታ ያሳለፉ፤ ሀዘንና ሰቆቃን አብረው የተሻገሩ፤ ሻደይና አሸንዳን በጥዑም ዜማቸው አብረው ያዜሙ፤ ዛሬ ላይ በውበት ያጌጡ ባህር ዳርና መቀሌን የመሰሉ ውብ ከተሞችን ለመፍጠር አንድ አላማ አንግበው ለእሳት የተማገዱ ታጋዮችን ያመረቱ፤ ፍፁም መነጣጠል የማይችሉ ጥልቅ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ብሎ ቀልቡን ሰብሰብ አድርጎ ፀጉሩ እየሸሸበት የመጣውን ደንበኛውን አናት በጥንቃቄ ማስተካከሉን ቀጠለ፡፡
በዝምታ ተውጦ የሁለቱን እንካ ሰላንቲያ ሲያዳምጥ የነበረው ፀጉር ተስተካካይ ጉሮሮውን ሳል አድርጎ
ይቅርታ አድርጉልኝና፣ እኔ ሰው ለመተቸት ብዬ ሳይሆን እንደው የተሰማኝን ለመናገር ብዬ ነው፤ አለ፡፡ ጨዋታ ሲደራ ደስ የሚለው ሙሼ ፊቱ በደስታ በርቶ ቀጥል፣ ቀጥል፣ ተናገር፣ እኔም ሲናገሩት ይቀላል ብዬ እንጂ የምለፈልፈው ምን የሚያገባኝ መስሎህ ነው፡፡ ሲል አደፋፈረው፡፡
እንግዳውም ለራሱ የሚያወራ በሚያክል ዝቅተኛ ድምፅ፣ የራሱን ፊት መስተዋት ውስጥ እየተመለከተ ወሬውን ቀጠለ፡፡
እውነት እላችኋለሁ ይህ ጉዳይ የፖለቲካ ጨዋታ እንዳይመስላችሁ፡፡ ይህ ጉዳይ ለፖለቲከኞች ብቻ የማንተወው የህዝብና የሀገር ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እሱ (ሙሼን መሆኑ ነው) ያነሳውን የፌስቡክ ፅሁፍ ባላነበውም ከፖለቲካ እና ከስልጣን ጥማት ያለፈ ታላቅ ክፋትን በደም አንቀልባ ያዘለ እኩይ ሀሳብ ነው፡፡ ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰበብ እየዛቀ ችግር እና መከራ የሚመርግባት ስልጣን ፈላጊ ሳይሆን ሰርቶ ሊያሰራ የሚችል መሪ ነው የሚስፈልጋት፤ አለ፡፡
ሙሼም ከሱ በላይ ተናጋሪ እዚች ጠባብ ቤቱ በመግባቱ ተገርሞ ስራውን አቁሞ ያዳምጣል፤ ኑርሰፋ ደግሞ ሰው ሁሉ ፖለቲከኛ ሆኖ የለ እንዴ በማለት እጁን አፉ ላይ ጭኗል፡፡ ሰውየው ግን ንግግሩን አላቆመም፡፡
በፌስቡክ መሽጎ በተሳሳተ ስም እና ውሉ በማይታወቅ አድራሻ በሬ ወለደ እያሉ አርበኛ ለመሆን መሞከር መጨረሻው የማያምር የእሳት ዳር ጨዋታ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እንዲህ አይነቱን ከፋፋይ መልዕክት የሚያሰራጩ ግለሰቦች አላማቸው አንድና አንድ ነው፡፡ በህዝቦች መፈቃቀድ እና መከባበር ላይ የተገነባችውን ይቺን ምስኪን ሀገር ቀዳዳ እየፈለጉ በቀዳዳው መሀል ጣታቸውን እያስገቡ፣ ልብሷን ቦረታትፈው ራቁት ማስቀረት ነው፡፡ ደግሞ ፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡
ኑር ሰፋ ከሰውየው ንግግር መሃል አንድና አንድ ነው ያላት አነጋገር አልገባችውም፡፡ ከአሁን በፊትም እየሰማት ግራ የምታጋባው ብትሆንም ከመጠየቅ ማዳመጥ ይሻላል ብሎ ዝም አለ፡፡ ሰውየው ከዚህ በላይ ለመናገር የፈለገ አይመስልም፡፡ ዝም ብሎ የተስተካከለው ፂሙ ላይ አፍጥጧል፡፡
ሙሼ ግን ጎደለ ያልነውን ተማክረን እየሞላን፤ ተቆረጠ ያልነውን ተማክረን እየቀጠልን፤ በትግራይ ነጭ ማር፣ በጎጃም ወለላ ጉሮሯችንን እያረሰረስን፤ አገው በፈተለው፤ ተንቤን ባመረተው የጥጥ ኩታ እየተዋብን እንኖራለን እንጂ የፍቅር እርጓችን ውስጥ ክፉ ዝንብ አትጠልቅም፡፡ ደሞ ከመቼ ጀምሮ ነው መሀል ጣት እና የቀለበት ጣት የሚጣሉት? በአንድነት ተፋቅረው እንጀራ ይቆርሳሉ እንጂ ጥፍራቸውን ተጠቅመው እርስ በእርስ እንቦጫጨር ብለው አያውቁም:: የትግራይ እና የአማራ ህዝቦችም እኮ ያው ናቸው፤ ብሎ ጨዋታ ማድመቁን ቀጠለ፡፡
ወይ ጉድ!” አለ ኑርሰፋ አፉን በእጁ ይዞ፡፡ ለመሆኑ እኔ የት ሄጄ ነው ግን ቆይ ይሄ ሁሉ ነገር መንደሩን የሞላው?” ሲል ጥያቄውን በአግራሞት አቀረበ፡፡
ሰውየውም ፈጠን አለና፣ ይቅርታ አድርጉልኝና ከንግግራችሁ እንደተረዳሁት አንተኛው {ኑርሰፋን እየተመለከተ} ከመረጃ ብዙ ርቀሃል፡፡ ይሄ የምናወራው ሁሉ የከረመ ወሬ ነው፡፡ እንደውም እኮ አሁን የአማራ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች የአማራና የትግራይ ህዝቦች የማይነጣጠል አንድነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል በተዘጋጀው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ መቀሌ ከተማ ገብተዋል፡፡ ይሄን ሁለታችሁም የሰማችሁ አይመስለኝም፡፡ ቢሆንም ግን አንተኛው {ሙሼን ነው} የእውቀት አድማስህ ሰፋ ያለ ይመስለኛል፡፡ ብቻ ከተሳሳትኩ ይቅርታ፤ አለ፡፡
ሙሼ ቀልጠፍ ብሎ አረ ልክ ነህ፣ ምንም አልተሳሳትክም አለ፡፡
‘’እኔ በእድሜዬ ያላየሁትና ያልታዘብኩት ነገር የለም:: የእድሜህን መዝገብ ከፍተህ አውራ ካልከኝ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ብርሀን በርቶላት ቆሜ በማየቴ ራሴን እንደ እድለኛ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ አንተ ያልከውንም ፍጹም እስማማለው፡፡ በህብረ ብሄራዊነት ያሸበረቀችው ሀገራችን አሁን እየሄደችበት ያለችው ጉዞ አጓጊ እንደ መሆኑ መጠን መሰናክሎች አይጠፉም ነገር ግን በሬ ወለደ በሆኑ ዜናዎች በሬ አስወልዳለሁ ማለት የዘመኑ ልጆች እንደሚሉት ምንም አይነፋም፤ አለ፡፡

ኑርሰፋ ግን ከመረጃ ብዙ ርቀሃል መባሉ አስከፍቶት አኩርፎ ጥግ ይዟል፡፡

No comments:

Post a Comment