EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 14 July 2017

እግረ ቀጫጭኖቹ

(በሚሚ ታደሰ)
እዉነትም ታሪክ ሲናገሩትና ሲጽፉት እጅግ ቀላል፤ ሲፈፅሙት ደግሞ ከሚነገረዉም በላይ ከባድ ነዉ፡፡
ዛሬ ከሶስት አስርት አመታት በላይ የኋሊት ተጉዤ ወደ 70ዎቹ መጀመሪያ አመታት ላይ  መነሻዬን አድርጌያሁ፡፡ የሀሳቤ መነሻ ደግሞ የጓድ ህላዊ ዮሴፍ የስነ ጹሁፍ ስራ የሆነው “ታሪክና ጥበብ” የተሰኘዉ የግጥም መድብል ነዉ፡፡ ክረምት ለንባብ ይመቻል ይባል የለ፤ እኔም እየከበደ ለመጣው የሐምሌ ክረምት ቅዝቃዜ መመከቻ በ2007ዓ.ም ከታተመውና ዘመን ከማይሽረው የጓድ ህላዌ ፅሁፍ ፊት ራሴን ሰይሜያለሁ፡፡ የፅሁፉ መቼት የፀረ ደርግ ትግሉ እንደሆነ ከዚህ ቀደም የማውቀው ቢሆንም ዛሬ ግን በጥልቀት ለመኮምኮም ነው የቆረጥኩት፡፡

ጸሀፊዉ በመድብሉ መግቢያ ላይ የወቅቱን ሀገራዊ የፖለቲካ ሙቀት እንደ ቴርሞ ሜትር እየለካ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ወቅቱ ደርግ በከተሞች ባካሄደው የቀይ ሽብር ዘመቻ መግደል የሚችለዉን ያህል ገድሎ ምድሪቱን በደም ያጨቀየበት ጊዜ ነበር፡፡ ከጭፍጨፋዉ በተአምር የተረፈዉን ምሁርና ወጣት በየእስር ቤቱ፤ በየከፍተኛዉና በየቀበሌዉ መጋዘን ሳይቀር አጉሮ፤ በአጋልጥ ዘመቻ ወጣቱን በጅምላ ያሰቃየበት ክፉም ጊዜ ነበር፡፡ ያ ጊዜ ተስፋ መቁረጥና ጨለምተኝነት በመላዉ ሀገሪቱ እንደ ወረርሽኝ የተንሰራፋበትና በተለይም በወጣቱ ዘንድ በስፋት የሚንጸባረቅበት  ነበር፡፡ ከተስፋ መቁረጥ በተቃራኒዉ መንገድ የተጓዙና ለደርግ ሰይጣናዊ ተግባር እጅ ያልሰጡ ጥቂት አብዮታዊያን ወጣቶችም የነበሩበት ጊዜ ነዉ ይላል ጸሃፊው እኔንም ልክ እንደ ያኔው ወጣቶች አንዴ እያበረታኝ፤ አንዴ ተስፋ እያስቆጠኝ ስሜቴን ከፍ ዝቅ እያደረገ ይዞኝ ጭልጥ በማለት፡፡
ያ ጊዜ አብዛኛዉ ወጣት ደርግ ካደረሰበት ሰቆቃ ባላነሰ በኢሕአፓ ውስት የተፈጠረዉ መከፋፈልና እርስ በእርስ መጠፋፋት ከባድ ጠባሳን ጥሎበት ያለፈበት፤ በየበረሀዉና ዉቅያኖሱ ለስደት መስዋዕት የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ በደርግ የጭካኔ በትርና በኢሕአፓ ክህደት እንደ ቡሄ ዳቦ በሁለቱም አቅጣጫ በእሳት የተፈጀበት መጥፎ ጊዜም ነበር፡፡ የጊዜዉን አብዛኛዉን ወጣት አቅፎ የነበረዉ የወቅቱ የፖለቲካ ድርጅት ኢህሕፓ በተከተለዉ አጉል ጀብደኝነት የተሞላበት የከተማ ትግል ወጣቱን ካስጨፈጨፈ በኋላ ይባስ ብሎ በገጠር የነበረዉንም ሰራዊት በተነ፡፡
ቋራና ጭልጋ አካባቢ ይንቀሳቀስ ለነበረዉ ሰራዊት ለእያንዳንዱ ታጋይ 15 ፓዉንድ /20 የሱዳን ጁኔ/ እየሰጠ ጠመንጃዉን ደርድሮ ወደ ሱዳን እንዲሰደድ አደረገ፡፡ ጸሀፊዉ ጓድ ህላዌ ዮሴፍም የነበረበት የበለሳዉ ሰራዊትና ካድሬም በጎንደር በኩል ወደ እብናት፤ አርባያና አዲስ ዘመን፤ በወሎ ገጽ ደግሞ ወደ አምደ ወርቅ በመሄድ እጁን ለደርግ ሰጠ፡፡ ለስራና ለህክምና በሚል ሰበብ ወደ አሜሪካና አውሮፓ የተጓዙ የኢህአፓ አመራሮች በሄዱበት የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ፡፡ ደርግም በታጋዮች መስዋዕትነት ነጻ ወጥቶ የነበረዉን መሬት አንድ ጥይት ሳይተኩስ ዳግም ተቆጣጠረው፡፡ በመጠኑም ቢሆን የነጻነት ጭላንጭል አይቶ የነበረውን ህዝብ መልሶ ከጫማው ስር አዋለው፡፡
ጸሀፊዉ እንደሚለው ይህ ወቅት እንኳንስ ተደራጅቶት ማቸነፍ ቀርቶ ዳግም ተደራጅቶ መቆም የማይቻልበት አፋፍ ላይ የተደረሰበት፤ አስቸጋሪና ይህ ጊዜ ያልፋል ብሎ ለማሰብ እንኳ አቅም የጠፋበት መስቀለኛ መንገድ ላይ የተቆመበት ወቅት ነበር፡፡ እናም ራስን ማጽናት፤ ማበረታታትና እንደ ጉም የበነነውን ጭላንጭል ዳግም ማደስ ብቸኛው ለአብዮታውያኑ የቀረበ አማራጭ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ጀግኖቹ የኢህዴን ወጣቶች ‹‹ትግሉን መቀጠል›› የሚል ለጆሮ የሚከብድ ከባድ ውሳኔን ያስተላለፉት፡፡ በእርግጥም እንደተባለው ታሪክን ሲጽፉትና ሲናገሩት ኬክ የመቁረስ ያህል ቀላል ተግባር ነው የሚመስለው፡፡ ተግባሩ ግን ተራራን የመግፋት ያህል ከባድና ውስብስብ ነው፡፡ እነዛ ወጣቶች ታዲያ ይህን ከባድ ተልዕኮ ለመፈጸም ነው የወሰኑት፡፡
ጭቁኖቹ የኢህዴን ልጆች ጨለማው ይገፈፋል፤ የብርሀን ቀን ይመጣል፤ አንንበረከክም ሆነ ዝማሬያቸዉ፡፡ ይህ ከባድ የታሪክ ሂደት ለተራማጁ ኢህዴን/ብአዴን ጽንሰት ምክንያት ሆኖ በ1973ዓ.ም ህዳር 11 ቀን ብአዴን ተወለደ፡፡
ብአዴን ገና በጨቅላነት እድሜው መራራ ችግሮች ገጥመውታል፡፡ የድርጅቱ ዋነኛ ሃይል በከባድ መስዋዕትነት ተመናመነ፤ የደርግ የስለላ ቡድን ወጥመዱን ተብትቦ ድርጅቱን የማፈራረስ ሴራዉን አጠናከረ፡፡ ብዙ ብዙ ፈተናዎች…፡፡ ያልተንበረከኩት የኢህዴን ታጋዮች ግን እየሞቱ መኖር፤ እያለቁም መበርከትን፤ እየተመናመኑም መፈርጠምን አርቀዉ በማየት በርካቶችን አስከተሉ፡፡
እግረ ቀጫጭኖቹ የዋግ፤ የላስታ፤ የበለሳ፤ የሰሜን ራያ የአንበሳ ግልገሎች የኢህዴንን መስራቾች ቆራጥነት ተላብሰው፤ ቤተሰባቸውን ትተው ከወንድሞቻቸው ጎን ለትግሉ ተሰለፉ፡፡ የአናብስቱ ግልገሎች የጋለ ስሜት የድሉን ተስፋ ይበልጥ ብሩህ በማድረግ የጽልመቱን ደመና በመግፈፍ ለመራራው ትግል ተጨማሪ አቅምና ደጀን ሆነ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ቀናቶች ወራትን፤ ወራትም አመታትን ወልደው ሰባዎቹ አልፈው የሰማኒያዎቹ አመታት ከች አሉ፡፡ ብአዴን/ኢሕአዴግም ብዙዎች ከመንገድ ቢቀሩበትም በጠራ መስመሩ ጥቂቶች ቆራጦችን አሰልፎ የድል ጉዞዉን ከሌሎች ጭቁን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች ጋር በመሆን ከዳር አደረሰ፡፡
እነሆ ዛሬ ብአዴን/ኢህአዴግ በክልሉ ግምባር ቀደም የልማትና ዴሞክራሲ ፋና ወጊ ሆኖ በድህነትና ኋላ ቀርነት ላይ ታሪክ መስራቱን ቀጥሏል፡፡ ኢህዴግን ከመሰረቱ ድርጅቶች እና ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን በመላ ሀገሪቱ ለተመዘገቡ የልማት፤ የዴሞክራሲና ማህበራዊ እድገቶች የበኩሉን አብዮታዊ ሚና እያበረከተ ይገኛል፡፡
ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማእታት ይሁንና የዛሬ ወጣት ይጠበቅበት የነበረውን ከባድ ሀላፊነት እነዛ በየሸንተረሩ የቀሩ የጭቁን ህዝብ ልጆች ህይወታቸዉንና አካላቸዉን ያለስስት በመገበር እጅግ ቀላል አድርገዉለታል፡፡ ዛሬ ተነጥሎ የቀረውን ድህነትን እንጂ ጠባቂውን የድህነት ዘበኛ ስርዓት መዋጋት አልተጠበቀብንም፡፡ የያኔዎቹ ወጣቶች በከፈሉት ከባድ መስዋዕትነት ፈጣን ልማት፤ ሰላምና ዴሞክራሲን ሣይነጣጠሉ እዉን ለማድረግ የምንችልበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረውልናል፡፡ እንደ ዘመኑ ወጣት ይህን በደምና በአጥንት የተከፈለ እዳና ደማቅ የትግል ታሪክ ማወቅ የሚጠበቅብኝ ሃላፊነት በመሆኑ በ“ታሪክና ጥበብ” የግጥም መድብል 286 ገፅ ታሪኮች ውስጥ ማንነቴን ፈተሸኩ፡፡
በድርጅታችን ዉስጥ ያልተነገረዉና ያልተጻፈዉ ገድል ሚዛን ይደፋል፤ የተቡ ብእረኞች እንዳሉ አምናለሁ፤ ለንባብ አብቋቸዉና እንማርባቸዉ እላለሁ፡፡ ጓድ ህላዌ ዮሴፍን ግን እጅግ አድርጌ ሳላመሰግን አላልፍም፡፡
በመጨረሻም በመድብሉ ውስጥ ከተካተቱት ከ60 በላይ ግጥሞች ውስጥ “መንገዱን ተለመ” የሚለውን ግጥም የተወሰኑ ስንኞች በማቅረብና ቀሪዎቹን እናንተ እንድታነቧቸው በመጋበዝ ተሰናበትኳችሁ፤ ሰላም!

“መንገዱን ተለመ
የኢሕዴኑ ታጋይ፤ የኢሕዴኑ ወጣት፤
አሰሱን ገሰሱን፤ ገለባዉን ትቶ፤
ፍታጊ፤ ጉፋያ፤ ዝርክርኩን ትቶ፤
የሸና፤ ያላበዉን፤ ፈርሳ ፈርሱን ትቶ፤
ሞልቃቃ፤ ዉልቅልቅ፤ ጥግንግኑን ትቶ፤
ልቅላቂ እጣቢ፤ ምናምኑን ትቶ፤
ዝንፍተኛ አድርባይ፤ ጨለምተኛን ትቶ፤
ሰንደቁን ተከለ፤ በሁለት እግሩ ቆመ፤
ወገቡን አጠና፤ መንገዱን ተለመ፡፡

No comments:

Post a Comment