(በሚሚ ታደሰ)
የክረምቱ ጭጋግ ገና ከማለዳዉ አዲስ አበባ ላይ አጥልቷል፡፡
አዲስ
አበቤዎች ግን ለክረምቱ ብርድ እጅ ሳይሰጡ በአራቱም አቅጣጫ ይተማሉ፡፡ ባለሰማያዊ ቀለሞቹ የመንግስት ሰራተኛ አዉቶቢሶች፣ ቀይ ቢጫዎቹ የከተማ አውቶቡሶችና መልከ
ብዙዎቹ ታክሲዎችም ህዝቡን ተቀብለው አንዱን በአንዱ ትንፋሽ እያሞቁ፣
ለብርዱም ለዝናቡም መጠለያ ሆነውታል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ታዲያ ለክረምቱ መመከቻ ዣንጥላዉን፤ ካፖርቱን፤ የአንገት ልብሱን፤ አንገተ ረጃጅም መጫሚያዎችን አስቀድመው እንደሸመቱ ከአለባበሳቸው ያስታውቃል፡፡ በአንፃሩ በዚህ የክረምት ትእይንት ዉስጥ በአለባበሳቸው እምብዛም ለውጥ የሌላቸው ብጣቂ የሻማ ዩኒፎርም
ብቻ ከላይ ጣል ያደረጉ ወጣት ሴቶችና ወንዶች በዋና ዋና መንገዶች የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማስተናገድ ላይ ታች ሲሯሯጡ
ይታያሉ፡፡ መኪኖችን አስቁመው ሰዎችን፤ ሰዎችን አቁመው መኪኖችን ያሳልፋሉ፤ አቅመ ደካሞችን ደግፈዉ መንገድ ያሻግራሉ፡፡
አዲስ
አበባን ዘወር ዘወር ብሎ ለቃኘ እንዲህ አይነት ሰናይ ተግባሮች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሲሰጡ ያያል፡፡ የአረጋዉያንን ቤት የሚቀልሱ፤
ነጫጭ
ድንኳኖች ዉስጥ ደም የሚለግሱ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያካበቱትን እዉቀት ለታናናሾቻቸዉ የሚያካፍሉ፤ የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ ተፈጥሯዊ ማንነታቸዉ እንዲመለሱ ለማስቻል ችግኝ የሚተክሉ፤
እግረኞች
የመንገድ ህግን እንዲተገብሩ በትህትና የሚጠይቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በአዲስ አበባ ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ ይመለከታሉ፡፡
የአዲስ
አበባ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ወጣት ጥበቡ በቀለ እንደነገረኝ ዘንድሮ በከተማዋ ለ14ኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ900 ሺህ በላይ ወጣቶች እየተሳተፉ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ በመላው ሀገራችን እየተካሄደ ያለው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት
የአዲስ አበባ መገለጫ ነው፡፡ በድሬዳዋ ከተማም 49ሺህ የከተማዉ ወጣቶች በስምንት አይነት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ተሰማርተው
ህብረተሰቡን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡የድሬዳዋ ኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ኃላፊዉ ወጣት ሚካኤል
እንዳለ እንደገለፀው ወጣቶቹ ከተሰማሩበት የበጎ ስራ ጎን ለጎን በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በህገ ወጥ የሰዎች ዝዉዉር ላይ መረጃ የሚያገኙበት የዉይይት መድረክ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
የደኢህዴን ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊዉ ወጣት ተስፋዬ ብላቱ ባለፈዉ አመት
የክረምት ወራት በክልሉ በተሰራዉ የበጎ ፈቃድ ተግባር 99 ሚሊዮን የሚገመት የመንግሰት ወጪን መታደግ መቻሉን
አስታውሶ ዘንድሮም 2ነጥብ 8ሚሊዮን ያክል የክልሉን ወጣቶች ያቀፈ የበጎ ፈቃድ ተግባር መርሀ ግብር በይፋ መጀመሩን ነግሮኛል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልልም በ2008
ዓ.ም. ከ75ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ወጪን ማዳን ተችሏል፡፡ የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነዉ ወጣት ብርሀኑ ቶላ እንደገለፀልኝ ዘንድሮም ከ4ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ይሳተፋሉ፡፡
የእረፍት ጊዜዉን የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ በማደስ፤ ደም በመለገስና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሚያሳልፈዉ ወጣት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ያለኝ ደግሞ የአማራ ክልል ወጣቶች ሊግ ተወካዩ ወጣት ምስጋና ሙላት ነዉ፡፡
የጣና
ሀይቅን ካጋጠመዉ የእምቦጭ አረም ለመታደግ ብቻ
ከ6ሺህ በላይ ወጣቶች የበጎ ፍቃድ ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ ነዉ የተናገረዉ፡፡
የህወኃት
ወጣቶች ሊግ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ኤልሳ ተስፋይ በበኩሏ በክልሉ ከ400ሺህ በላይ ወጣቶች
የጤና ልማትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በበጎ ፈቃደኝነት እየተሳተፉ ነው ብላለች፡፡ ህብረተሰቡም በወጣቶቹ በጎ ምግባር ደስተኛ መሆኑን ተናግራለች፡፡
የወጣቶች የበጎ ፈቃድ ተግባር ባለፉት 9 አመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ምክትል ቢሮ ሀላፊ
ወጣት
ጫላ ኦሊቃ እንደሚገልጸው የተሳታፊዎች ቁጥር በየአመቱ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቶ ዘንድሮ ከ10ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ዉስጥም 2ነጥብ4 ሚሊዮን የሚሆኑት የኢህአዴግ የወጣት ሊግ አባላት ናቸው፡፡ በሰብአዊ ግልጋሎት፤ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በትራፊክ ፖሊሲንግን የተጀመሩት ስራዎች አሁን ሌሎች መስኮችንም
በማካተት እየሰፉ ናቸው፡፡
ሀገር የሚለማዉ
በዜጎች መልካም አስተዋፆና በጎ ምግባር
መሆኑ ግልፅ
ነዉ፡፡ በሀገራችን
ሚሊዮኖች ወጣቶችን ከዳር እስከ ዳር የሚያነቃንቀዉ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ደግሞ ለዚህ ተግባር ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡ በተለይም የየአካባቢዎችን
ቁልፍ ችግሮች በመለየት በተባበረ ክንድ ለመፍታት የሚደረገው ርብርብ የአገልግሎቱን ፋይዳ ድርብ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ በአማራ
ክልል የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ፣ በድሬዳዋ ከተማ ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከል፣ በአዲስ አበባ ደግሞ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ
የተጀመሩ ስራዎች መልካም ማሳያ ናቸው፡፡ እነዚህን አይነት በአፈፃፀሙ የሚታዩ መልካም ልምዶች ማስፋት እንደተጠበቀ ሆኖ አጠቃላይ
አገልግሎቱ ከታጠረበት የክረምት ወቅት በዘለለ የሁልጊዜ ተግባር ሆኖ የሚቀጥልበትን ስልት መንደፍ ቢቻል ታዳጊዎችና ወጣቶች ወደፊት
የሚረከቧትን ብቻ ሳይሆን አሁን የሚኖሩባትንም ሀገር የሚገነቧት ራሳቸው መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ያስችላል፡፡
በርቱ በጋራ እንስራለን !!
ReplyDelete