ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይንና ጆሯችን ያለው ሳውዲ አረቢያ ላይ ሆኗል፡፡ ሁላችንም ዜጎቻችን ምንም እንግልት ሳይደርስባቸው ለሀገራቸው ምድር እንዲበቁ ምኞታችን ነውና ልክ እንደ ወላድ ቀን መቁጠሩን ተያይዘንዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተናጠልም ተደራጅተውም ወንድም እህቶቻቸውን ‹‹ያለፈው ይበቃናል፤ ዳግም በደላችሁን መስማትም አንፈልግም፤ እባካችሁ ኑልን›› እያሉ ናቸው፡፡ መንግስትም ዜጎቹ ወደ ሀገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ብቻ ሳይሆን ከመጡም በኋላ የሚደገፉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሁሉንም አይነት ጥረቶች በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የእምነት ተቋማት፣ የተለያዩ ማህበራትና ድርጅቶችም ከሕዝብና መንግስት ጎን ቆመው የወገናቸውን ክፉ ላለማየት የሚበጀውን አስቀድመው በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ በሳውዲ አረቢያ ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው ህዝብ አንፃር እስካሁን ወደ ሀገር ቤት የገባው ሰው
ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ስደት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደመሆኑ መጠን ዓለም አቀፋዊ ገፅታ ያለውና ከሰዎች በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራት መብት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ ክፍለ አህጉራት እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ ገሚሶቹ ህይወት መስመር ይዛላቸው ተደስተው ሲኖሩ ሌሎቹ ደግሞ እድል ፊቷን አዙራባቸው አንገታቸውን ደፍተው የመከራ ኑሮን ይገፋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከራሳቸው አልፈው ለወገናቸውና ለሀገራቸው እድገት መከታ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ እግራቸው ከሀገር ቤት የተነቀለበትን ቀን እየረገሙ በፀፀት ይኖራሉ፡፡ ስደት ለአንዱ ሀዘን ለሌላው ደስታ የሆነ ባለሁለት ገፅታ ነው፡፡
ስደተኞች በኑሯቸው ደረጃ ቢለያዩም ቅሉ ሁሉንም አንድ የሚያደርጓቸው ጉዳዮችም አሏቸው፡፡ ሁሉም ስደተኞች በአካል ከሀገር፣ ከዘመድና ከወዳጅ ቢለዩም በመንፈስ ግን ሁሌም ከትውልድ ሀገራቸው ናቸው፡፡ እንደ ብቸኝነት፣ ናፍቆት፣ መከፋትና አይዞህ ባይ ማጣት ያሉ ከሀገርና የራስ ሕዝብ መለየት የሚያመጣቸው መዘዞች ሰለባ ናቸው፡፡ ከስደት ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ህገ ወጥ ስደት ነው፡፡ ከሚሰደዱበት ስልት፣ ከተሰደዱበት ምክንያት ወይም ከተቀባይ ሀገር ሁኔታ በመነሳት ስደተኞች በደረሱበት ቦታ የሚኖራቸው አቀባበል በህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርሳል፡፡ ህገ ወጥ ስደተኞች ከሌሎቹ በባሰ የኑሮ ሸክም የሚበዛባቸውም ይሄው ከስማቸው በፊት የሚቀጠል ህገ ወጥ የሚል ስያሜ የሚያስከትለው ጣጣ ነው፡፡
ለጤና ቀውስ፣ ለሰብዓዊ መብቶች መጣስ፣ ለከፋ እንግልትና ጥቃት የሚጋለጡት እንዲህ አይነቶቹ ስደተኞች ናቸው፡፡ ይህን አይነቱ ግፍና በደል የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቤት አንኳኩቷል፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ከስደት ጋር በተያያዘ የተጋፈጥናቸው መሪር ትዝታዎች ቀላል አይደሉም፡፡ ቤተሰባቸውን ቀርቶ ራሳቸውንም ማወቅ እስኪያቅታቸው ድረስ የአዕምሮ መቃወስ ያገጠማቸውን፣ ሙሉ አካል ይዘው ወጥው አካለ ጎደሎ ሆነው የተመለሱትን፣ የተሻለ ነገን ለመፍጠር ሲታትሩ በበረሃና በባህር ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
‹‹ያለፍቃዴ መኖር አትችሉምና በፍጥነት ሀገሬን ለቅቃችሁ ውጡ›› በሚል የሳውዲ አረቢያ መንግስት ያስቀመጠው የ90 ቀን የመውጫ ገደብ (እነርሱ የምህረት ጊዜ ይሉታል) ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜ ከአንድ ሳምንት አይዘልም፡፡ የሳውዲ መንግስት የ90 ቀን የምህረት አዋጅ አውጥቻለሁ ሲል በጀርባው ያዘለው መልዕክት በ91ኛው ቀን በሀገሬ ምድር ካገኘኋችሁ አልምራችሁም የሚል እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የሀገሪቱ መንግስት የስራና የመኖሪያ ፈቃድ በሌላቸው የማናቸውም ሀገር ዜጎች ላይ ያወጣው ይህ አዋጅ አስገዳጅና ከመፈፀም ወደኋላ የማይል መሆኑ በተደጋጋሚ እየተገለፀ ባለበትም ዜጎቻችን በሚገባው ልክ ሀገሪቱን ለቀው ያለመውጣታቸው ስጋታችንን ብቻ ሳይሆን ፍርሃታችንንም የሚያንር ነው፡፡
ካለፈው ስህተቱ የማይማር ፈንጅ አምካኝ ብቻ ነው ሲባል እሰማለሁ፡፡ አሁን የሚታየውም ነገር ከዚሁ ጋር እየተመሳሰለብኝ ነው፡፡ ፈንጅ አምካኝስ ለጉዳቱ መንስዔ የሆነውን ስህተት ለማስተካከል እድሉን ስለማያገኝ በተሳሳተባት ቅፅበት እጣ ፈንታው ሞት ይሆናል፡፡ እኛ ግን ባለፉት ጊዜያት አውቀንም ሆነ ሳናውቅ፤ በራሳችንም ይሁን በሌሎች አሳሳችነት፣ ከነአካቴው ስህተት ፈፅመንም ይሁን ሳንፈፅም፤ ከፊታችን ከተደቀነው አደጋ የምናመልጥበት እድል ክፍት ሆኖልናል፡፡ ግና ይህን እድል ለመጠቀም ያልመረጥነው ለምንድን ነው? ያሳለፍነው መከራ በተለይም በአረብ ሀገራት በየእለቱ በወገኖቻችን ላይ ስለመፈፀሙ የምንሰማው ዘግናኝ ድርጊት ህገ ወጥ ስደትን ስሙን ለመጥራት እንኳን ከምንፈራበትና ከምናፍርበት ደረጃ የሚያደርስ ቢሆንም ቅሉ ስደትን እንድንፀየፍና ቆም ብለን እንድናስብ ያላስተማረን ለምንድን ነው?
የስደት መንስዔዎች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዘርፉን የሚያጠኑ ምሁራን እነዚህን ውስጣዊ ገፊ ምክንያቶችና ውጫዊ ሳቢ ምክንያቶች በሚል ሁለት ሰፋፊ አውዶች ዙሪያ ያደራጇቸዋል፡፡ በሰለጠኑና ባደጉ ሀገራት ውስጥ የሚታዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች በተቃራኒ ጎራ ያሉ ሀገራት ዜጎችን እንዲሳቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ የድሃ ሀገራት ዜጎች የእድገት አማራጮች በሰፉባቸው የበለፀጉ ሀገራት በመግባት የተሻለ ክፍያ ለማግኘትና ኑሯቸውን ለማሻሻል የትውልድ ሀገራቸውን ለቀው ይሰደዳሉ፡፡ እነዚህ ውጫዊ የሆኑ ሳቢ ምክንያቶች ከላኪ ሀገራት ቁጥጥር ውጭ ናቸውና ማስቀረት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ገፊ ምክንያቶችን መቀነስ ይቻላል፡፡
እንደሚታወቀው ሀገራችን ገና በማደግ ላይ ያለች ነች፡፡ አንዴ ቁልቁል ስትወርድ በሌላ ጊዜ ባለችበት ስታዘግም ቆይታ አሁን የቁልቁለት ጉዞዋን በመግታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምትጥር፤ በጥረቷም ልክ ስኬቶችን እያስመዘገበች ያለች ሀገር ነች፡፡ የእስካሁኑ ስኬታችን የቁልቁለት ጉዟችንን የቀለበሰና የሕዳሴ ጉዟችንን በቅርብ ርቀት እንደምናሳካው ተስፋ የሰጠን ይሁን እንጂ የዜጎች ሁለንተናዊ ፍላጎቶች ማሟላት ያስቻለን አይደለም፡፡ ዜጎች የተሻለ ህይወትን አልመው ውጪ ማማተራቸው ተፈጥሯዊም ነባራዊም ምክንያት ያለው ነው፡፡
ነገር ግን የማይቀር አደጋ ከፊት የተደቀነበትን የህይወት አማራጭ የምንመርጥበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ ፍላጎታችን የራሳችንን ብሎም የቤተሰባችንን ህይወት መለወጥ ሆኖ ሳለ ምርጫችን በግፍ መገዛትና በውርደት መባረር ብሎም ለአካልና ህይወት ማጣት መዳረግ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ እንዲሆን የሚያስገድድ ገፊ ምክንያትም የለንም፡፡ ይልቁንም ሀገራችን ህይወታችንን ለመለወጥ የምንችልባቸው እድሎች የተከፈቱባት፣ ከሰሩ ማደግ እንደሚቻል በተግባር እየታየባት ያለች ሀገር ሆናለች፡፡
የይቻላልን መንፈስ ሰንቀው ለጊዜያዊ ችግሮችና እንቅፋቶች ሳይንበረከኩ የደከሙ ዜጎች ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው አልፈው ለሀገራቸው እድገት ዋልታና ማገር መሆናቸውን እያየን ነው፡፡ በእነሱና ሁሉን አቀፍ በሆነው ጥረታችን ዛሬ ከትናንቷ የተሻለች ኢትዮጵያን ገንብተናል፡፡ እኛም በሀገር ውስጥ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምና ገና ያልነካናቸውን እንዲሁም አሟጠን ያልተጠቀምናቸው ሃብቶቻችንን በመለየት ተባብረን ከሰራን ከዛሬዋም ፍፁም የተሻለ ሀገር እንደምንገነባ ጥርጥር የለውም፡፡
በእኔ እምነት መለወጥ ከማመን ይጀምራል፡፡ ለስራችን ቀርቶ ለህይወታችን ዋስትና በሌለበት የሰው ሀገር ደክመን ሀብት ማፍራት እንደምንችል ካመንን በየአካባቢያችን ያለውን እምቅ አቅም ማጤንና መጠቀም እንዴት ይሳነናል? ታላቁን የሕዳሴ ግድባችንን ከማጋመስ አልፈን ወደ ማገባደዱ የተቃረብንውስ የአይቻልም መንፈስን ሰብረን አይደለምን?
ውድ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፤ የቆማችሁበት ምድር እሾህ እንደሆነባችሁ እንረዳለን፡፡ በዚህ የጭንቅ ቀን ላይ ሆነን ያንን መለወጥ ይቻላል የሚለውን ጠንካራ እምነታችሁን ወደምትተገብሩባት ኢትዮጵያችሁ ኑልን ስንላችሁ መንገዶቹ ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናሉ በሚል ታሳቢ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ መንገዶቹ ሁሉ እሾህ እንደማይሆኑባችሁ፤ የሚያጋጥሟችሁ እንቅፋቶች ቢኖሩም እስካሁን ከፀናችሁበት ብርታት ባነሰ ጉልበት የሚፈቱ መሆናቸውን እርግጠኞች ስለሆንን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment