በወጋገን አማኑኤል
የ3ሺህ ዘመን እድሜ እንዳላት የሚታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ
የራሳቸውን ጥቅምና ስልጣን በማስጠበቅ ብቻ ታጥረው በነበሩ ገዢ መደቦች የግዳጅ አስተዳደር ስር በመቶዎች የሚቆጠሩ አመታትን
አሳልፋለች፡፡ የአለም ስልጣኔ ቁንጮ እንዳልነበረች ሁሉ የረሃብ፣ ድህነትና ኋላቀርነት ተምሳሌት ተደርጋም በአለም ህብረተሰብ
ዘንድ ተስላለች፡፡ ለመሆኑ ሀገራችን እንዴት ከነበረችበት የስልጣኔ ማማ ቁልቁል ልትወርድ ቻለች? ሁላችንም ለዚህ ጥያቄ ምላሽ
ስንሰጥ በታሪካችን ላይ ያለን አተያይና አተረጓጎም ሊለያይ ቢችልም ቅሉ መሰረታዊ በሆኑ እውነታዎች ላይ መግባባት የሚከብድ
አይመስለኝም፡፡
ድመት በመስታወት ውስጥ የራሷን ምስል ትኩር አድርጋ ብታይ
የምታየው ምስል ለራስዋ ነብር ሊመስላት ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ነብርም እንደ ድመት ሁሉ ራሱን በመስታወት ቢያይ የድመት ዝርያ
መሆኑን ባለመቀበል ይሄስ እኔ አይደለሁም ሊል ይችላል፡፡ የድመቱም የተጋነነ ነው፣ ነብርም የድመት ዝርያ መሆኑን ቢክድ ሚዛን
አጉድሏል፡፡ ከፊታቸው ያዩትን የራሳቸውን ምንነት መካድ ሚዛናዊነትን ማጣት ነው፡፡ ዛሬ ሀገራችን የደረሰችበትን የለውጥ ደረጃ
እውነተኛ ገፅታ መረዳት የሚቻለው ያለፍንበትን ታሪክ ሳያኮፍሱም ሳያንኳስሱም በሚዛኑ መመልከት ሲቻል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከአለም የስልጣኔ ራስነት ወደማይቆም የማሽቆልቆል ጉዞ
የገባችው በዋናነት የህዝቦቿን ተፈጥራዊ ብዝሃነት ማስተናገድ አቅቷት የመደብ እና የማንነት ቅራኔ ውስጥ በመግባቷ ነው፡፡
ሀገሪቱ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገኛ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ሀገር ሆና ሳለ እነዚህን ልዮነቶች በእኩልነት
ማስተናገድ የሚችል ስርዓት ባለመኖሩ ቁርሾና ቅራኔ እየተፈጠረ መጥቷል፡፡ ይህም የተደራጁ ቡድኖችን ለመብታቸውና ለነፃነታቸው
ሲሉ በየአካባቢው ከገዢው መደብ ክፍል ጋር እንዲጋጩ ምክንያት ሲሆን በተደጋጋሚ በሚከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት እንዲሁም
ለልማት የሚያነሳሳ አስተዳደር እጦት በመላ ሀገሪቱ ዜጎች በሙሉ ጊዜያቸው ለልማት የሚያውሉትን አቅም እንዲመክን በማድረጉ መላ
ሕዝቡ ደግሞ ህይወቱን በድህነትና ጉስቁልና ውስጥ እንዲገፋ አድርጎት ቆይቷል፡፡
ይህ ሁኔታ ፍጻሜ ሊበጅለት ይገባል
ያሉ የህዝብ ልጆች በየወቅቱ የመጨረሻ አማራጭ የነበረውን መራራ የትጥቅ ትግል መርጠው
ራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ ዛሬ ማንም የበላይ ማንም የበታች ከማይሆንበት፤ በመፈቃቀድ፣ በመተባበር፣ በመከባበርና በመቻቻል
ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አብቅተውናል፡፡ የፌደራል ስርዓቱ ብዝኃነት
የሚስተናገድበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ድህነት ከመሰረቱ ለማጥፋት መረባረብ ከጀመሩ ሁለት አስርት
አመታት አልፈዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 26 አመታት ባስመዘገበችው
ሁለንተናዊ እድገት የተነሳ አለም አቀፍ ተቀባይነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ እንደሚታወቀው በቀደሙት አመታት
መሪዎቻችን ወደ አለም ማህበረሰብ ሲያቀኑ አንድም ለጦር መሳሪያ ግዢ አሊያም የእለት ደራሽ እህል ለመለመን ነበር፡፡ ይህ
የማንክደው፤ የማንረሳው የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡
አሁን ይህ ታሪክ ወደ አዲስ የድል ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡
ኢትዮጵያ በአለም መድረክ የራሷ የሆነ የልማት አማራጭ ያላት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተደራዳሪና የአፍሪካውያን ልሳን ሆናለች፡፡
ለመከላከል ቅድሚያ የሰጠው የጤና ፓሊሲዋ ስኬታማነት አለም አቀፍ እውቅና በማግኘት ሳይወሰን ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር
ጀነራልነት ኢትዮጵያዊው ዕጩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሲወዳደሩ መላው አለም በሚባል ደረጃ ድጋፉን ሰጥቶናል፡፡
ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ስንወዳደርም እንዲሁ መላ
አፍሪካውያንና በርካታ የአለም ሀገራት ድምፃቸውን ሰጥተውናል፡፡ በእኔ እይታ ይህ አለም አቀፍ ድጋፍ ከማንም በችሮታ የተሰጠን
ሳይሆን የረጅም ጊዜ ራዕይ ሰንቀን በውስጣችን ባደረግነው ጥረትና ባስመዘገብነው ስኬት የተነሳ አለም ሀገራችን ተስፋ
የሚጣልባትና በአጋርነት ለመስራት የምትመረጥ መሆኗን በማመኑ የተገኘ ነው፡፡
እድገት በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል፤ መሰረቱና ምንጩም ዘርፈ
ብዙ ነው፡፡ የእኛ እድገት መሰረቱ እጅግ ሰፊውን ሕዝባችንን ያሳተፈው የግብርና ልማት ነው፡፡ የሕዝባችንን የለውጥ ፍላጎት፣
ያለንን እምቅ ሃብትና ውስን ካፒታል መነሻ ያደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ነድፈን ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ በመግባታችን፤
እንዲሁም በተግባር ሂደትም ሁሉም ህዝቦች በሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቀሴ ውስጥ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ
በመፍጠራችን ለዚህ ድል በቅተናል፡፡
ከተለምነው ራዕይ ጫፍ ለመድረስ የቴክኖሎጂ አቅማችንን
ማጎልበት፣ የኢኮኖሚ ሽግግራችንን ማፋጠንና በየመድረኩ የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች መፍታት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ እስካሁን
በድርጅታችን ኢሕአዴግ መሪነትና በመላው ሕዝብ ተሳትፎ የተገኙ ውጤቶች መነሻዎቻችንም የሞራል ስንቃችንም ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment