(በኤስሮም ፍቅሩ)
ሙሼ
ፀጉር ቆራጩ “መቼም ለዚች ሀገር በክፉም ሆነ በደጉ አስተያየት የሚሰጣት
ሰው ብዛት ይቆጠር ቢባል እንዲህ በቀላሉ መጨረስ አይቻልም፡፡ ወይ ጉድ፤ እኔ እኮ ግርም ይለኛል፤ መንግስት ማለት ግን ምን ይሆን?
ህዝብስ ማለት ማነው?’’ እያለ ፀጉር ሊቆረጥ ከስሩ ቁጭ ባለው የዘወትር ደንበኛው ጫኔ ላይ የማያባራ ጥያቄ ያወርድበት ጀመር፡፡
ሙሼ
አንዴ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም፡፡ “ይኸው ትላንትና ሬዲዮኔን ከፍቼ ሃገሩ ምን ይላል ብዬ ጆሮዬን ከወሬ ምንጩ ላይ ብሰካ ይገርማል
አንድ ጉድ ሰማሁ፡፡ አይ ሀገሬ፤ መቼም እንዳንቺ ምስኪን የለም፤ እንዳንቺ መቼም የድህነት እርግማን ባትሮስ ላይ ተዘርግቶ ቅኔ
በተሞላ አፍ የተነበበለት የለም፡፡’’ አለና ሙሼ ትንፋሹ ሰብሰብ አድርጎ የፀጉር ስራውን ቀጠለ፡፡
የጫኔን
ክምክም ያሉ ፀጉሮች በጠር በጠር አደረገና “ብቻ ግን ሀገሬ አይዞሽ፤ አሁን በውድ ልጆችሽ ላብ ቀን እየወጣልሽ ነው፡፡ ግድ
የለም አትዘኚ፤ አሁን የዘነበው እያባራ፣ የደከመው እያጓራ ነው፡፡ ግድ የለሽም ሀገሬ፤ የበሬውን አፍ ሳታስሪ የምታበራይበት፤ የፈሰሰውን
ሳታፍሺ የምትቦርቂበት ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ ያኔ ትላንት የገፋሽ ሁሉ ስለስምሽ ያወራል፡፡’’ አለ ሙሼ ተስፋና ፀፀት በተጫጫነው
ድምፀት፡፡
እንዲህ
ሲብሰከሰክ በብሶት ተነሳስቶ
ወይም ተሳስቶ ፀጉሬን ከነቆዳው እንዳያነሳው ብሎ የሰጋው ደንበኛው ጫኔ “ወዳጄ ሙሼ፤ ምነው ዛሬ ሰላም
አይደለህም እንዴ? ሀገራችንስ ምን ሆነች?’’ ብሎ ጠየቀው:: ሙሼም ወሬ እና ትዳር ሲተጋገዙበት ያምራል በሚል፣
አድማጭ በማግኘቱም እየተደሰተ ያን ፈገግታ የማያጣውን ፊቱን ጨምደድ አድርጎ ብሶቱን ማውራት ቀጠለ፡፡
“ይገርምሀል እኮ፤ ሀገር እንደሌለው፣
ወገን አልባ እንደሆነ፣ በወፍ ተዘርቶ መንገድ ላይ እንደበቀለ የጉሎ ፍሬ ከሀገራችን ውጡልን ብለው አወጁብን አሉ፡፡ እኔ የምለው፤
ካለው ላይ ቆርሶ የሚያበላ፤ አልጋውን ለእንግዳ ለቆ መደብ ላይ የሚያድር ጨዋ ህዝብ ሀገሬን ልቀቅ፣ ደጄን አትርገጥ ተብሎ ዶሴ
የሚከፈትበት ምን በበደለ ነው በል? በማለት ጫኔን ትኩር ብሎ አየው፡፡
“አይይይ፤ ለዚህ ነው እንዴ
እንዲህ የምትብሰከሰከው? እኔስ እንኳን ውጡ አሏቸው ነው የምለው፡፡” አለ ጫኔ፡፡ ይሄኔ ሙሼ አጠገቡ ያለው ሰው ኢትዮጵያዊ ይሁን
ሳውዲ አረባዊ ለማረጋገጥ የፈለገ ይመስል መቀሱን ጠበቅ አድርጎ ይዞ ደንበኛው ላይ አፈጠጠበት፡፡
ጫኔ መቀሱን ፈርቶ ይሁን ለመውጣት
ቸኩሎ ፈጠን ፈጠን እያለ ማውራቱን ቀጠለ፡፡ “የእከሊት ልጅ ከ3ኛ ፎቅ ላይ ተወርውራ ህይወቷ አለፈ፣ የእከሌ ልጅ ስንት አመት
ሙሉ በሰው ሀገር ላይ ላቧን አፍስሳ ቤሳ ቢስቲን ሳትይዝ ተመለሰች፣ የእከሌ ልጅ ተደፈረች፣ የእከሌ ልጅ እንደ ፋሲካ ዶሮ ሙቅ
ውሀ ላይዋ ላይ ተደፋባት የሚል መርዶ ለጠገብን ሰዎች ይሄ እንደውም መልካም አጋጣሚ ነው፡፡” አለና ሙሼን በጨረፍታ ተመለከተው፡፡
ሙሼ መቀሱን ብቻ አይደለም ራሱንም መሸከም ያቃተው ይመስል ፊቱን አንጠልጥሎ ከጀርባው ተገትሯል፡፡ ይሄኔ በረጅሙ ተነፈሰና ወሬውን
ቀጠለ፡፡
“ውጡ ብለውን ይቅርና ምንም
ሆነን ብንመለስ እጃችንን ስሞ የሚቀበል ጨዋ ህዝብ ነው ያለን፡፡ ዛሬ ሀገራችን እንኳን ለዜጎቿ ይቅርና ለባእዳንም የምትተርፍ በረከት
የሞላት ባለ ብዙ ጡት እናት ሆናለች፡፡ ማንም እውቀቱን ተጠቅሞ ቢሰራባት መልካም ነገር የሚያገኝባት፤ አፈሯ ዘርተውበት የማያሳፍር፤
የድህነት ጨለማን በልጆቿ ፋኖስ ለመደምሰስ የምትጥር፤ እለት እለት በጎ ገፅታዋና ቀና ማለቷ የሚወራላት ሀገር ሆናለች፡፡ ታዲያ
ምን ገዶን ነው በሰው ሀገር ላይ ነብር እንዳየች ሚዳቆ ሌት ከቀን በስጋት እና በፍርሀት የምንኖረው? ለምንድን ነው በገዛ ገንዘባችን
መከራን የምንገዛው? ለምንድንስ ነው ለዚህ ሁሉ ችግር መንግስት ላይ ብቻ ጣታችንን የምንቀስረው?” አለና ለጥያቄው ምላሽ በመሻት
ወደ ሙሼ ዘወር አለ፡፡
ሙሼ ጭልጥ ብሎ ሌላ አለም ውስጥ
ገብቷል፡፡ የኔታ ሊመክሩት እንደጠሩት ህፃን አቀርቅሮ መሬት እያየ ስራውንም ዘንግቶታል፡፡ ከወረዱበት ጥያቄዎችም የሰማውን የመጨረሻውን
ብቻ ነበር፡፡ “በላ መልስልኝ፤ ምነው ዝም አልክ?” ሲል አምባረቀበት፡፡
“እውነትህን ነው ወዳጄ ጫኔ፤
ከተናገርከው ውስጥ አንድም ጠብ ያለብህ ነገር አላገኘሁም፡፡ ዛሬ ዜጎቻችን በሰው ሃገር ላይ ለመሰቃየታቸው እኛም ጆሯችን ሰቆቃ
ለመስማቱ ተጠያቂዎቹ እኛው ራሳችን ነን፡፡ መንግስት ብቻውን ሃላፊነቱን ሊወስድ አይችልም፡፡ መንግስት እኮ ማለት እኛው ነን፡፡
ተራራው፣ አፈሩ፣ ፎቁ፣ መንገዱ፣ ዛፍና ቅጠሉ መንግስት ሊሆን አይችልም፡፡ “ይሄ መንግስት” እያሉ ማማረር መፍትሄ አይሆነንም፡፡
መንግስት ማለት ራሱ ህዝቡ ነው፡፡ ለሚፈጠረው ነገር ሁሉ መንግስትን እንደ ምክንያት መቁጠር ዞሮ ዞሮ እራስን መውቀስ ነው፡፡ ዛሬም
ዜጎቻችን በሰው ሃገር ላይ በረሃ ሲበላቸው ተጠያቂው መንግስት ሳይሆን ከአፈር ላይ ማር ይዛቅ ይመስል፤ ከኮሽም ላይ ጣፋጭ ይቆረጥ
ይመስል፣ ከስደት ላይ በረከት የሚገኝ ይመስል በርቱ ይቅናችሁ እያልን፣ ገንዘብ እያዋጣን ዘመድ ወዳጆቻችንን በበረሃና በባህር የምንልከው
እኛው ነን፡፡” እያለ ሙሼ በሃሳቡ መስማማቱን ማረጋገጡን ቀጠለ፡፡
ጫኔ ግን ድንገት ወደ ግድግዳው
ሰዓት ዞሮ ብሎ ተመለከተና “ወይኔ ጉዴ፤ የቀጠሮ ሰዓት ሊያልፍብኝ እኮ ነው፡፡ በል ሙሼ፤ እንግዲህ እኔና አንተ ተግባብተናል፡፡
ቆም ብለን አስበን ልሰደድ ባዩን እግር መክረን ልናበርደው፤ ተሰዶ የሄደውንም ተመለስ ሁሉ በሀገር ያምራል ልንለው ይገባል፡፡ በሳውዲ
ያሉት ዜጎቻቸንም የምህረት አዋጁ ሳያልቅ ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ልናሳስባቸው ይገባል፡፡ አሁን ደግሞ ፈጠን አርገህ አስተካክልና
ሸኘኝ አለ፡፡” ከተቀመጠበት ለመነሳትም እየዳዳው፡፡
ሙሼም የራሱም መንቀርፈፍ፣ የደንበኛውም
መቸኮል ቢረዳውም ጨዋታው ስለጣመው መቀሱም ምላሱም ስራ አልፈቱም፡፡ “እነርሱ ይምጡ እንጂ ካለን ላይ ተካፍለን፣ ከጋገርነው ላይ
ተቋርሰን መብላት አያቅተንም፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን የወንድሞቻችንና የእህቶቻችን ደም በከንቱ ፈሶ መርዶ ብንሰማ ልናለቅስ የሚገባን
በራሳችን ነው፡፡’’ እያለ ሳለ ድንገት መብራት ጠፋ፡፡
ጫኔ ግማሹን ተላጭቶ፣ ግማሹን
ተበጥሮ መስተዋት ላይ የተገተረውን የራሱን ምስል ሲያይ ደንግጦ “አይ ይሄ መንግስት” ብሎ ጮኸ፡፡
No comments:
Post a Comment