EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 27 May 2017

በዋጋ የማይተመን መስዋዕትነት

(በወጋገን ሙስጠፋ)
ሮጠው የማይጠግቡበት፣ ሰርተው የማይደክሙበት፣ ነገን አሻግረው በማየት በተስፋ የሚኖሩበት፤ ህልምዎን እውን ለማድረግ የሚተጉበት የእድሜ ክልል ነው ወጣትነት፡፡ አልንበረከክ ባይነት፣ እውነትን የመጋፈጥ ብርታትም አንዱ የወጣትነት መገለጫ ባህሪ ነው፡፡ ውድ አንባብያን ስለወጣትነት ያነሳሁት ያለአንዳች ምክንያት አይደለም፡፡ የምንገኘው ወርሃ ግንቦት ላይ ነውና 26 ዓመታትን በምናብ ወደ ኋላ ተመልሼ ስለዛ ዘመን ወጣቶች ወኔና ተጋድሎ ማንሳት ስለወደድኩ ነው፡፡

ጭቆና ራዕይን ቅዠት የሚያደርግ የማይሸከሙት ህመም ነው፡፡ በተለይ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ለሚያምን ወጣት የነፃነት ደንቃራ ነው፡፡ ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት የነበረው ይሄው ነው፡፡ ለእናት ከልጇ በላይ ተስፋና ደስታ የለም ፡፡ ከ26 ዓመታት በፊት ሀገራችንን ይመራ ለነበረው አምባገነን መንግስት ግን ይህ ተረተ ተረት ነው ፡፡ መካንነት መባረክ የሆነበት ዘመን ሆነ፡፡ እናት ልጇን ከደጃፏ የምትነጠቅበት በለስ ከቀናት ከፊቷ ዞር ብሎ አልያም እዛው ፊቷ ላይ የሚረሽንበት ክፉ ዘመን ነበር፡፡

በአገራችን የነበረው ፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ከሚሸከሙት በላይ የሆነባቸው ወጣቶች የማይገፋ የሚመስለውን አምባገነን ስርዓት ድባቅ ለመምታት የወሰኑት፡፡ ምንም እንኳን ህልማቸው ተምረው ሳይማር ያስተማራቸውን ቤተሰብና ማህብረሰብ በአቅማቸው ጥረውና ግረው መለወጥ ቢሆንም እንደ አገር ያለው ሁኔታ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችላቸው አልነበረምና እምቢ ለጭቆና ብለው ለህዝብ ጥቅም መስዋዕት መሆንን መረጡ፡፡ እነሱ ተምረው እንለውጠዋለን ተስፋ እንሆንለታለን ያሉት ማህበረሰብ በአጭሩ እየተቀጨ፣ ከአጠገባቸው ወጣቱ ያለ ርህራሄ በሚረሽነው አምባገነን መንግስት እየተቀጠፈ መሄዱ እረፍት ነሳቸው፡፡ የትጥቅ ትግል ብቸኛው አማራጭ ነበርና ራሳቸውን ለህዝብ ሊሰዉ በሙሉ መተማመንና ተስፋ በረሃ ወረዱ፡፡

ከአገራቸው አልፈው ለአፍሪካም ጭምር ተስፋ የሚሆን የእምቅ እውቀት ባለቤት የሆኑ ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሳይቀር አቋርጠው በመስዋዕትነት ሜዳ ከተሙ፡፡ ወጣትነት በይቻላል መንፈስ ሲታጀብ ከብረት ይጠነክራልና የተናጠል ራዕያቸውን ወደ ጎን ብለው የህዝቡን ሰቆቃ ለማስወገድ መስዋዕትነት መረጡ፡፡

ያ ትውልድ ድንቅ ነው፡፡ ያ ትውልድ ጀግና ነው፡፡ በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም አላማቸው ግዙፍ ነበርና ጭቆና ያንገፈገፈውን በማነቃነቅ ታሪክ ሰሩ፡፡ ታዲያ በወርሃ ግንቦት ይህ ትውልድ እንዴት ሳይወሳ ይታለፋል? ግንቦት 20 እኮ በመሪር ተጋድሎ በውድ መስዋዕትነት የተገኘች ወርቃማ የድል ቀን ናት፡፡ ለህዝብ ጥቅም ውድ ህይወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት በወሰኑ ወጣቶች ተጋድሎ ድል የተቀዳጀንባት ቀን፡፡ ደርግ ከጉያዋ እየነጠቀ ለአፈር ሲዳርግባት እንባ እየዘራች ምነው መካን በሆንኩ ያለችን እናት እንኳንም ወለድኩኝ ያስባለ ድል የተጎናፀፍንበት ነው ግንቦት 20፡፡

ሁሉም ትውልድ ለአገሩ የራሱን አሻራ እያሰቀመጠ ያልፋል፡፡ የዛ ትውልድ አሻራ ግን በዋጋ የማይተመን፣ በዘመናት መካከል የማይደበዝዝ ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ለዛ ትውልድ ምስጋን ይግባውና ስለ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ከዛም አለፍ ብለን ከሌሎች የዓለማችን አገሮች ጋር አገራችንን እኩል ስለማድረግ ለማሰብ በቅተናል፡፡ አገራችን ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፍቅር በመተሳሰብና በአንድነት ተከባብረው የሚኖሩባት አገር ሆናለች፡፡ ህገ መንግስታችን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ሳይሸራረፍ ያለገደብ እንዲከበር አድርጓል፡፡ በቁጥር አናሳ ለሚባሉ ብሄሮች ጭምር ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት የፌዴራል ስርዓት እውን መሆን ችሏል፡፡ ያኔ በአምባገነን መንግስት ተነፍገው የነበሩና እንደ ሃጥያት ይቆጠሩ የነበሩ የመናገርና የመፃፍ፣ የመደራጀት ሃብት የማሰባሰብ እና መሰል ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ዛሬ ህገ መንግስታዊ እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲከበሩ ተደርጓል፡፡ ይህ ያ ትውልድ በከፈለው መስዋዕትነት የተጎናፀፍንው የግንቦት 20 ድል ነው፡፡

የአንድ ሀገር መጻኢ እድል የሚወስነው የስርዓቱ ባለቤቶች በሆኑ በወጣቶች ነው፡፡ ያ ድንቅ ትውልድ የማይተመን ዋጋ ከፍሎ የምታጓጓና ወደ ፊት እየተስፈነጠረች ያለች አገርን መፍጠር ችሏል፡፡ ይህ በቅብብሎች ወደ ፊት መሻገር መቻል አለበት፡፡ ዛሬ አገራችን እንደ ልጆቿ ወጣት አገር ናት ፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ የአገራችንን ህዳሴ ከዳር ለማድረስ ትልቅ እድል ነውና ጥረታችን ተሻጋሪ ስኬት ማስመዝገብ መቻል አለበት፡፡ የዛሬ ትውልድ ደግሞ ጊዜውን፣ ጉልበቱን፣ እውቀቱንና ሃብቱን አጣምሮ በመጠቀም የሀገራቸውን ባህልና እሴት መጠበቅ፤ የህዳሴ ጉዟችንንም ለማረጋገጥ መትጋት ይገባዋል፡፡ 

ግንቦት 20ን ስናስብም ወደ ኋላ ተመልሰን መስዋዕትነቱን እያሰበን ወደ ፊት ደግሞ አገራችንን ሩቅ ለማድረስ ከራሷ አልፏ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ተስፋ መሆን የጀመረችውን አገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ መከፈል ያለበትን ዋጋ ለመክፈል በመዘጋጀት ሊሆን ይገባል፡፡

ድልና ድምቀት ለ26ኛው ግንቦት 20 የድል በዓል!!

ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!!

No comments:

Post a Comment