EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 25 May 2017

በደማቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ



 ክሩቤል መርኃጻድቅ 

ታክሲ ውስጥ ነኝ፣ አንድ የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓም በኢትዮጵያ ታሪክ ስለተከሰተው ሁኔታ እየተረከ ነው፡፡ አዎ ይህቺ ቀን በታሪክ በየዓመቱ ትዘከራለች፡፡  ከግንቦት ወር 1983 ዓም ቀደም ብለው የነበሩ ዓመታት በኢትዮጵያ ከጦርነት ውጭ ሌላ የሚሰማ መልካም ዜና አልነበራቸውም፡፡ ዘወትር ሁካታ ግርግር የማይለይባት አዲስ አበባ በወርሃ ግንቦት 83 ዓም ትካዜ ገብቶባታል፡፡ ነዋሪቿ ስለቀጣዩ ሁኔታ መገመት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አንዳንዶቹ ለወራት የሚሆን ስንቅ ማዘጋጀታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዜጎች እንደየእምነቶቻቸው ጸሎት እያደረጉ ነው፡፡ በመንግስቱ ኃይለማርያም አገላለጽ ‹‹ወንበዴዎች›› ወደ መሃል ሀገር መጠጋታቸው እንጂ በትክክል የት አካባቢ እንደደረሱ አዲስ አበቤው ማወቅ አልቻለም፡፡

ነዋሪዎቹ በአንድ በኩል ‹‹አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀረን ድረስ እንታገላለን›› የሚለው የመንግስቱ ኃይለማርያም ፉከራ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከመረጃ ምንጮች የሚሰማው የኢህአዴግ ሰራዊት ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሰ መሆኑንና የደርግ መውደቅም አይቀሬ መሆኑን በሚተርኩ መረጃዎች ግራ ተጋብቷል፡፡

ሁኔታዎች በዚህ መልኩ በሚቀጥሉበት ወቅት ግንቦት 13 ቀን ስለቀጣዩ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አንድ ፍንጭ ሰጠች፡፡ ‹‹አንድ ጥይት እስከሚቀረን እንዋጋለን፣ ኢትዮጵያ ወይም ሞት›› ብለው ሲፎክሩ የነበሩት መንግስቱ ኃይለማርያምና  ከሀገር መኮብለላቸውን የኢትዮጵያ ራዲዮ ይፋ አደረገ፡፡ እናም የኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያው የታሪክ ክስተት ሆኖ ስላለፈው ጉዳይ ነው የሚተርከው፡፡

እውነትም የመንግስቱ ኃይለማርያም ሽሽት ቀጣዩን የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አመላካች ነበር፡፡  መንግስቱ ኃይለማርያም ከኮበለለ ከሳምንት በኋላ በኢትዮጵያ አዲስ ብርሃን ታየ፤ አዲስ ታሪክም ተጻፈ፡፡ በተለይም ህዝብ በሚበዛባት አዲስ አበባ የእርስ በርስ እልቂትና ውድመት እንዳይከሰት ፍርሃት ውስጥ ገብቶ የነበረው ህዝብም ‹‹እፎይ›› አለ፡፡ በኢትዮጵያውያ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የቆየው አምባገነናዊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተመነገለ፡፡

በእርግጥ የግንቦት 20 ድል ብዙ ውጣ ውረድ፣ ከባድ መዋዕትነት የተከፈለበት ነው፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ውድ ህይወታቸውን ከፍለውበታል፡፡ አጥንታቸው በጋራዎችና ሜዳዎች ተዘርቷል፡፡ ‹‹እኛ መስዋዕት እንሆናለን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በእኛ መስዋዕትነት የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ ተቋዳሽ ይሆናል›› በሚል ጥልቅ ህዝባዊ ፍቅር ወጣቶች ለጋ ዕድሜያቸውን ከፍለዋል፡፡ ሌሎች በርካቶች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የግንቦት 20 ወርቃማ ድሎችን በአግባቡ ለመገንዘብ በቅድመ 1983 ዓም የነበሩ ሁኔታዎችን በአግባቡ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡ ብዙኃነትን በአግባቡ የሚያስተናግድ የስርዓት እጦት ምክነያት ሀገራችን ወደ ጦር አውድማ በመቀየሯ ምክንያት እናቶች ልጆቻቸውን ወልደውና አሳድገው ለጦርነት በግዳጅ የሚማግዱበት ወቅት በብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶች ዘንድ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ እናቶች ልጅን የሚያክል ውድ ነገር መውለድ ጠቅልለው ለመተው  ‹‹መላኩ ተፈራ፤ የእግዚሄር ታላቅ ወንድም የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም›› ለማለት የደረሱበት አስከፊ ዘመን የታሪካችን አካል ሆኖ አልፏል፡፡ ለዚህም ነው ወልደው በልጆቻቸው መጦርን፣ ለወግ ለማዕረግ አድርሰው መደሰት ሲገባቸው በሀዘን እንዲሸማቀቁና አንገታቸውን እንዲደፉ ተፈርዶባቸዋልና ማህጸናቸው ዳግም የልጅ ፍሬ እንዳይዝ የተመኙት፡፡ 

ህዝቡ ለዘመናት የቀጠለ አስከፊ ጭቆናና በደል ሲደራረብበት፣ ይህን ተከትሎም ለአስከፊ ድህነትና ጉስቁልና ተዳርጎ ቆይቷል፡፡ ጨቋኝ ነገስታት ህዝቡን ለመጨቆንና የስልጣን ጊዜያቸውን ከዘርማንዘራቸው ሳይወጣ ይቀጥል ዘንድ ራሳቸውን ‹‹ስዩመ እግዚአብሄር፤ ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ›› የሚል አስተሳሰብ በህዝቡ ዘንድ እንዲሰርጽ ባደረጉት ጥረት ለበርካታ ዓመታት ህዝቡን ለስቃይ ዳርገውት ቆይተዋል፡፡

ህዝቡን ለሁንተናዊ ችግር የዳረገው የንጉሳዊ ሴረኛ አካሄድ የተገነዘቡ ባለ ብሩህ እእምሮ የሆኑ ወጣቶች የንጉሳዊ ስርዓቱን አምርረው መቃወም ጀመሩ፡፡ በተለይ መሬት ለአራሹና የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት መከበር የሚሉ ጥያቄዎች በእነ ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኮንን እና ሌሎች ወጣቶች የሚመሩ እንቅስቃሴዎች ይደረጉ ነበር፡፡ ንጉሳዊ ስርዓቱ የታቃውሞውን እንቅስቃሴ ወጣቶችን በመግደልና በማሰቃየት ስልጣኑን ለማራዘም ጥረት ቢያደርግም በመጨረሻ በ1966 ዓም ሊወገድ ችሏል፡፡

1966 ዓም በኢትዮጵያ ታሪክ ንጉሳዊ ስርዓት ተወግዶ ህዝቡም ሁለንተናዊ ለውጥ ተቋዳሽ ለመሆን ተስፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ በመባል የሚታወቅ ስብስብ የኢትዮጵያን ህዝቦች የለውጥ ፍላጎት በመጥለፍ አዲስ አፈና፣ አዲስ ጭቆና አወጀ፡፡ የቀድሞ ስርዓት ባለ ስልጣናትን ወደ ህግ እንደማቅረብ በአንድ መስመር የጽሁፍ ትእዛዝ በመግደል ዘመነ ስልጣኑን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በግልጽ በመገናኝ ብዙኃን በማፈን ጀመረ፤ የህዝቡ የስቃይ ጊዜም ዳግም በአምባገነን መንግስት ተራዘመ፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊከበር ይቅርና ‹‹አስበህ ይሆናል›› በሚል ሰው የሚገደልበት ዘግናኝ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡

የህዝቡን የለውጥ ተስፋ መጠለፉን የተገነዘቡ ሩቅ አሳቢ ወጣቶች ደርግን በመቃወም በተለያዩ ድርጅቶች በመታቀፍ ትግል ጀመሩ፡፡ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የተመሰረተው ማህበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማገብት) የደርግ ስርዓት የባሰ አፋኝ መሆኑን በመገንዘብ  ስሙን ወደ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ(ተሓህት በኃላ ህወሓት) በመለወጥ በደደቢት በርሃ የትግል ችቦ ለኮሰ፡፡ ኢህአፓ እና መኢሶንም በየፊናቸው ትግል ማድረግ ጀመሩ፡፡ እነ ኢድዩ ደግሞ ንጉሳዊውን ስርዓት ለመመለስ የሚመስል የትግል እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ በአጠቃላይ  በሁሉም አቅጣጫዎች ዓመጽና ጦርነት ተለኮሰ፡፡

በዚህ የትግል ሂደት በትክክለኛ መስመር እየተመራ የተራዘመ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያካተተ የትጥቅ ትግል የመረጠው ህወሓት ህዝቡን እያሳተፈ ለአምባገነኑ ስርዓት የእግር እሳት ሆነ፡፡ ኢህአፓ፣ መኢሶን እና ሌሎች ድርጅቶችም በተሳሳተ የትግል ስልት ሲፈረካከሱ፣ በተለይም በህዝቡ ዘንድ መዋቅሩን በማስፋት የተሻለ ጥንካሬ ላይ ይገኝ የነበረው ኢህአፓ ትግሉን ‹‹ደርግን መጣል ተራራን እንደመግፋት ነው›› በማለት ተስፋ ቆርጦ ትግሉን ባቆመበት ወቅት ትግሉን የመቀጠል ወኔን የሰነቁ ጥቂት ታጋዮች ኢህዴንን (የአሁኑ ብአዴንን) መሰረቱ፡፡

ህወሓትና ኢህዴንም ኢህአዴግን በመመስረት በጋራ ክንድ ድርግን ለመደምሰስ ተስማሙ፡፡ በመቀጠልም አምባገኑን የደርግ ስርዓት ለማስወገድ የቆረጡ የኦሮሞ ወጣቶች ኦህዴድን የተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረ ሰቦች ድርጅቶች ደግሞ ደኢህዴግ(የአሁኑ ደኢህዴን) መስረተው ኢህአዴግን ተቀላቀሉ፡፡ ኢህአዴግም የትግል አድማሱን በማስፋት መላው የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከጎኑ በማሰለፍ ወድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ አምባገኑን የደርግ ስርዓት አስወገደ፡፡

ያየዝነው የግንቦት ወር በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የከፈተበት ነው የሚባለውም ለዘመናት በኢትዮጵያ ህዝቦች ተጭነው የቆዩት ጭቆናና አምባገነንነት የተወገዱበት ብሎም አዲስ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በር የተከፈተበት በመሆኑ ነው፡፡

በቅድመ ግንቦት 20/1983 ዓም የሀገራችን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ መገምትም ሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ሆኖባቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ህዝቦች ኢህአዴግ ደርሶ ታደጋቸው፡፡ ለብተና ቋፍ ላይ ደርሳ የነበረችው ሀገርም አንድነትዋን ጠብቃ ወደ ልማት ምህዋር ገባች፡፡ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄ መልስ ማግኘት ጀመረ፡፡ በግንቦት 20 ድል ማግስት!

ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓም በኋላ ለዘመናት ዕወቅና ተነፍጓቸው የቆዩ ብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች መብቶቻቸው ያለ ምንም ገደብ ተከበረላቸው፡፡ የኃይማኖት እኩልነት መከበሩ ብቻ ሳይሆን መንግስትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውና ማንኛውም ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል መብት እንዳለው ህገ መንግስታዊ ዋስትና አገኘ፡፡ ‹‹ለምን አሰብክ›› ተብሎ ከባድ እርምጃ የሚወሰድበት ዘመን ተሻግረን አንድ ሰው የፈለገውን የፖለቲካ አቋም እንዲያራምድ፣ በመረጠው የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንዲታቀፍ፣ የመቃውምና የመደገፍ መብት ተከበረለት፡፡

መንግሥታዊ ስልጣን በህዝብ ምርጫ ብቻ የሚያዝበት ህገ መንግስታዊ ስርዓት መገንባት ተቻለ፡፡ ሲያጠፋም በግልጽ ፍርድ ቤት የሚዳኝበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በአንዲት መስመር ትእዛዝ ያስገድሉ የነበሩ የደርግ ባለስልጣናት በግልጽ ፍርድ ቤት ተዳኝተው በጥፋታቸው ልክ ዉሳኔ አገኙ፡፡ የህግ የበላይነትም ተረጋገጠ፡፡ በአጠቃላይ ከእጅግ አምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፈጣን ሽግግር ተደረገ፡፡

በጦርነት የተንኮታኮተውን ኢኮኖሚ ገንብቶ ሀገርን ወደ ፈጣን ዕድገት የማስገባት ጉዞም ተጀመረ፡፡ በዚህም ዓለም በድህነትና በድርቅ የሚያውቃት ሀገር ፈጣን አዳጊ በመሆን ዜጎች ሰርተው የሚለወጡባት፣ በየዕለቱ አዳዲስ ለውጦችና የልማት ብስራቶች የሚሰሙበት፣ ሰላም በራቀው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም የሰፈነባት ብቻም ሳትሆን ለሌሎችም የምትተርፍ ሀገር ለመሆን በቃች፡፡ የፖለቲካ ቀርጠኝነት ያለው መንግስትና ህዝብ ከአስከፊ ድህነት ወደ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት መሸጋገር እንደሚችል በማሳየት ኢትዮጵያ ለዓለም በምስሌነት የምትጠቀስ ሀገር ለማድረግ ተቻለ፡፡

እናም ግንቦት ወር የምትዘከረው የመንግስት ለውጥ የተካሄደበት ብቻ ስለሆነች አይደለም፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም ወደ ዙምባቤ የሸሸባት ወር ስለሆነች ብቻም አይደለም፡፡ ‹‹የዘመናት ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረው የራዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል ተቆጣጥሮታል›› የሚል የብስራት ዜና ስለተሰማባት ብቻም አይደለም፡፡ ይልቁንስ የህዝብ ሁለንተናዊ መብቶችን ቀፍድዶ ዜጎችን ለአፈናና እና ለስቃይ ዳርጎ የነበረውን አምባገነን ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱ የተፈጸመበትና በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አዲስ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ ፈጣን ልማትና የዜጎች ኑሮ የሚለወጥበት አዲስ ዘመን በዚህች በታሪካዊቷ በግንቦት 20 ድል ማግስት እውን ስለሆነ እንጂ፡፡ ግንቦት 20 ለኢትዮጵያ ህዳሴ መሰረት ናት የሚባለውም ኢትዮጵያ እጅግ ጨለማ ከሆነ ዘመን ወደ ብርሃን የተሸጋገረችበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡

በእርግጥ ግንቦት 20 ሲከበር የተመዘገቡ ደማቅ ድሎች ብቻ ሳይሆን የታለፉ ውጣ ውረዶችንም አብሮ መዘከር ተገቢ ነው፡፡ በየበረሃውና ሸንተረሩ የተሰዉ ሰማዕታትን አደራ ከዳር መድረሱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ፈጣን ልማት የተመዘገበውን ያህል፣ አሁንም ቁጥሩ የማይናቅ ህዝብ በድህነት ስር የሚኖር በመሆኑ ፈጣን ልማቱ ለአፍታም ሳይቆም በማስቀጠል ድህነትን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል በሰፊ ርብርብ ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን ይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም በመልካም አስተዳደር መስክ የህዝቡን እርካታ በሚፈለገው ደረጃ ማድረስ ትልቅ ትኩረት የሚሹ የቤት ስራዎች ናቸው፡፡ መልካም የግንቦት 20 በዓል!


No comments:

Post a Comment