EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 22 May 2017

የኢትዮ-ቻይና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት

(በወጋገን ሙስጠፋ)
ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሸቲቭ በሚባል የሚታወቀው የቻይና መንግስት አዲሱ አለም አቀፍ የልማት ፕሮጀክት አሁን ሀገሪቱን በመምራት ላይ ባሉት ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ተቀርፆ በፈረንጆቹ 2013 መስከረም ላይ ይፋ የሆነ ከ4-8 ትሪሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ የሚገመት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት አውሮፓንና ኢሲያን ማዕከል አድርጎ በአፍሪካና ሌሎች ክፍለ አህጉሮች የሚገኙ ከ65 በላይ ሀገራትን የየብስና የውሃ ትራንስፖርትን ጨምሮ በዘርፈ ብዙ መሰረተ ልማቶች ለማስተሳሰር የተነደፈ እቅድ ነው፡፡ ዋንኛ አላማው ደግሞ በሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ ነው፡፡

የሀገሪቱ መሪዎች በተደጋጋሚ እንደገለፁት የቤልት ኤንድ ሮድ የመጀመሪያ ፍኖተ ካርታ 65 ሀገራት ላይ የሚያርፍ ቢሆንም ማንኛውም ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆነ ሀገር የሚቀላቀልበት ይበልጥ እየሰፋ ለመሄድ ክፍት የሆነ ሁሉን አቀፍ የልማት ስትራቴጂ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ፕሮጀክት ማዕቀፍ ከቻይና ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍቃደኝነቷን ገልፃለች፡፡ ሰሞኑን በዚሁ ፕሮጀክት ላይ ያጠነጠነ የመጀመሪያው አለም አቀፍ ጉባዔ በቻይና ቤጂንግ ሲካሄድም ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስቴር ሃ/ማርያም ደሳለኝ የሚመራ የልኡካን ቡድን ልካለች፡፡ በዚህ ከ100 በላይ ሀገራት እና የ28 ሀገራት መሪዎች በተሳተፉበት ጉባኤ ጎን ለጎን ታዲያ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አቢይ አላማም የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን ስምምነት የተመለከተ ነው፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት (Comprehensive Strategic Cooperative Partnership) ለማሳደግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  ሺ ጂንፒንግ የሁለቱ ሀገራት ትብብር በአጠቃላዩ የአፍሪካና የቻይና ትብብር ውስጥ የመሪነት ሚና እንዳለው አንስተው ሀገራቸው ያቀረበቸው አዲሱ የአጋርነት ሃሳብም ሁለቱ ሀገራት ያላቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ከፍተኛ የመተማመን ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል ብለዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በቻይና በኩል የቀረበውን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀብለው ሀገራቸው ይህን አጋርነት ለማሳካት ሃላፊነቷን በብቃት እንደምትወጣ አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩባቸው መስኮች የኢንተርኔት መረብ ዝርጋታ፣ የምርታማነት አቅምን ማሳደግ፣ ንግድና ኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የአየር ትራንስፖርት ይሆናሉ፡፡
ባለፈው አመት ጆሃንስበርግ ላይ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ላይ ቻይና ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያላትን ግንኙነት ወደዚህ ደረጃ ለማሸጋገር ውሳኔዋን አሳውቃለች፡፡ ከኢትዮጵያም ጋር ቢሆን የትብብር አጋርነት የጀመረችው እ.አ.አ በ2003 ነው፡፡ አሁን ሁለቱ ሀገራት የደረሱበት ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት (Comprehensive Strategic Cooperative Partnership) ግን በተናጠል ከአንድ ሀገር ጋር የተደረገ ሲሆን በአይነቱም በአፍሪካ ከሞዛምቢክ ጋር ባለፈው አመት ከተደረገው ስምምነት ቀጥሎ የሚታይ ነው፡፡
ለመሆኑ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ማሳደግ ለምን ፈለገች? በዚህ ፅሁፌ ምክንያቶቹን ለመዘርዘር እሞክራለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በአለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሀገራት በቀዳሚነት ከሚጠሩ አንዷ ስትሆን በእድገት ሞዴልነቷ ለሌሎችም ምሳሌ የሆነችበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ሀገሪቱ የቀረፀቻቸው ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የተጣጣሙ ፓሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውጤት ነው፡፡ የሀገሪቱ ፈጣን እድገት የፓሊሲ ውጤት ነው ሲባል ከሀገሪቱ ህዝብ ብዙውን እጅ የሚይዘው አርሶ አደር የተሰማራበት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ የሚያበረክትበት፤ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር መሳለጥም ግብርናው ሚናውን የሚወጣበት፤ በኢኮኖሚ አቅም ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም የተለወጠ ሃብታም አርሶ አደር የሚፈጠርበት ስልት የተቀየሰበት ስለሆነ ነው፡፡ በዚሁ ፖሊሲ አማካኝነት የኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩበት ነው፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ ረጅም ርቀት ለተጓዘችውና ወደ ግዙፍና ውስብስብ ቴክኖሎጂ ምርት ለገቡት ኢንዱስትሪዎቿ ግብዓትና ገበያ እጅጉን ለምትፈልገው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የሚፈጠር አጋርነት ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ ግንኙነታቸው በትብብርና አጋርነት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ሁለቱም ሀገራት ለስኬት በሚያደርጉት ግስጋሴ ወሳኝ አቅም ይሆንላቸዋል፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ኢትዮጵያ የምትመራበት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፓሊሲና ስትራቴጂ ያስመዘገበው ስኬት ነው፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ የሚመነጨውም ሆነ ቅድሚያ የሚሰጠው ለውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሲባል ውስጣችን ሲጠናከር በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነታችን ያድጋል፣ ከውጪ የሚመጣን ጫና መቋቋም እንችላለን የሚል መንፈስ ያለው ነው፡፡ ከውስጥ መጠንከር ማለት ደግሞ በመሰረታዊነት የህዝቦችን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ የሚመነጭ ነው፡፡ ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ሲሆኑ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ፣ ለቀጣይ ልማትም ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ሀገሪቱ የራሷን ሰላም አስከብራ ለሌሎች ጎረቤትና የአፍሪካ ሀገራት ሰላም መረጋገጥ መስራቷ የውጭ ሀገራትና ባለሃብቶቻቸው ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ባለሃብቶች ያለስጋት ሰርተው ሊያተርፉባት የሚችሉ ሀገር መሆኗን በማመን በስፋት እየገቡ ሲሆን ቻይናውያን ደግሞ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡
በሌላ በኩል ሀገሪቱ ከውጭ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ዋነኛ ማጠንጠኛም ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን ከውጭ ለመሳብ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ስኬት ከተመዘገበበት ውስጥ የኢትዮጵያና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ አቅዳ የሰራችው፣ በውጤቱም ተጠቃሚ እየሆነች ያለችበት የፖሊሲ ስኬት ነው፡፡ ቻይና በዚህ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ አጋርነት ውስጥ መቆየትን ቀዳሚ ምርጫዋ ማድረጓ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኗ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደ መግቢያ በር የሚያስወስዳት አንፃራዊ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልና ከኢትዮጵያ ጋር መስራት ወይም ስልታዊ ግንኙነት መፍጠርን አስፈላጊ ያደርገዋል፡፡

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ለማሳደግ ምክንያት የሚሆናት ግን አሁን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ እድገቱ በአጭሩ የማይገታ መሆኑንም ማረጋገጥ ይጠበቅባታል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሰፊ መሰረት ባለው ግብርና እንጂ በአላቂ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ያለመመስረቱ፣ ከሃይል ጀምሮ በአጠቃላይ መሰረተ ልማት የተደረገው ኢንቨስትመንት ሩቅ አሳቢ መሆኑ፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የኢኮኖሚ ሽግግር ተመጋግቦ መሄዱና በአጠቃላይ በሀገሪቱ የተመዘገበው እድገት ተፅእኖ ፈጣሪነት ወደማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱ ሁለቱን ሀገራት ለዚህ ትልቅ ግምት የሚሰጠው የአጋርነት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል፡፡

1 comment: