EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 25 May 2017

ድርድርና ክርክር- የቆየ ኢህአዴጋዊ ባህል




ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መፅሄት የተወሰደ

ኢህአዴግ ጨቋኝ ስርዓቶች የህዝቦችን ሁለንተናዊ መብቶች ነጥቀው ኃሳቦች በይፋ እንዳይንሸራሸሩ ሁለንተናዊ አፈና በሚደረግበት አስከፊ ዘመን የተፈጠረ ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ከ1983 ዓም በፊት የነበሩ የንጉሳዊና የአምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ የዴሞክራሲና የመ ድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚታሰብ አልነበርም፡፡ የህዝቦችን የለውጥ ተስፋ የጠለፈው የደርግ ስርዓት ሁሉንም መብቶች በአደባባይ የሚያፍን ነበር፡፡ እናም አምባገነኑ ስርዓት ሰላማዊ የፖለቲካ በሮችን ዝግ በማድረጉ ኢህአዴግ ስርዓቱን ከኢትዮጵያ ህዝቦች ትከሻ ለማስወገድ የመጨረሻ ስልቱን የትጥቅ ትግል አደረገ፡፡ በጭቆና ምክንያት የተወለደውና ትክክለኛ ህዝባዊ ዓላማ ያነገበው ኢህአዴግም የኢትዮጵያ ህዝቦችን ከጎኑ በማሳለፍ መራራ ትግልና ከባድ የህይወት መስዋዕትንት በመክፈል  በህዝቦች ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የቆየውን ስርዓት ላይመለስ ግብዓተ መሬቱን በመፈፀም ትግሉን በድል ሊያጠናቅቅ ችሏል፡፡

ኢህአዴግ የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል ቢመርጥም ትግል ከጀመረባት ቀን ጀምሮ ለውይይትና ድርድር በሩን ክፍት የማድረግ ልምድ አለው፡፡ ለህዝቦች ሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ለሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እስከጠቀመ ድረስ ግማሽ መንገድ ሄዶም ቢሆን ይወያይል፤ ይደራደራል፡፡ ኢህአዴግ እንደ ግንባርም ሆነ አባል ድርጅቶቹ የትጥቅ ትግል በሚያካሂዱበት ወቅት እንኳን ጦርነት የመጨረሻ አማራጭ መሆኑን በመገንዘብ እጅቸውን ለድርድር የመዘርጋት ልምድ ነበራቸው፡፡

ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንዱ የሆነው ህወሓት የካቲት 11 ቀን 1967 ዓም በደደቢት በርሃ የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ማግስት ጀምሮ በወቅቱ ከነበሩ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በርካታ ውይይቶችና ድርድሮችን ለማካሄድ እጁን ዘርግቷል፡፡ እስከ 1969 ዓም ከኢህአፓ ጋር ያካሄዳቸው ተከታታይ ውይይቶች በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ህወሓት ከኢህአፓ ጋር ተቀናጅቶ ጸረ ደርግ   ትግልን ለማፋፋም ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ይህ በኢህአፓ በኩል ብዙም ተቀባይትን ባያገኝም በህወሓት ዘንድ ልዩነቶችን ለማጥበብ በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት በርካታ የውይይት መድረኮች በመፍጠር ተወይይተዋል፡፡ በተለይም የብሄርና የመደብ ትግል በሚሉ አጀንዳዎች ላይም በርካታ ክርክሮችን አካሂደዋል፡፡

ኢህአፓ ለመደብ ትግል ቅድሚያ ሰጥቶ ለመታገል አቋም ሲይዝ ህወሓት ‹‹እውነተኛ ብሄራዊ ትግል የመደብ ትግል ይዘት አለው›› የሚል አቋም ይዞ ተከራከረ፡፡ ኢህአፓ በበኩሉ ‹‹የመደብ ትግል ሲፈታ የብሄር ጥያቄም ይፈታል የሚል አቋም በመያዙ›› ሁለቱም ድርጅቶች ተቀራርበው ለመስራት የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር አልቻሉም፡፡

ይሁንና ህወሓት የኢህአፓን አቋም ከአሁን አሁን እየተሻሻለ ይሄዳል በሚል ተቀራርቦ ለመስራት በርካታ ጥረቶች ማድረጉን የቀጠለ ቢሆንም ኢህአፓ ከህወሓት ቀደም ብሎ የተመሰረተ በመሆኑ ህወሓትን አሳንሶ የማየት ሁኔታ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢህአፓ ስር ሆነው እንዲታገሉ ከመፈለግ አኳያ ውይይቶቹ ሊደናቀፉ ችለዋል፡፡


ኢህአፓ ከህወሓት ጋር ተቀራርቦ መስራት አለመፈለግ ብቻም ሳይሆን በአካባቢው ህወሓትን ከህዝብ ለመነጠል በርካታ ስራዎችና ትንኮሳዎች በማድረጉ ሁለቱም ድርጅቶች ባደረጓቸው ውጊያዎች ኢህአፓ ሽንፈትን ሊከናነብ ችሏል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ህወሓት ከኢድዩ ጋርም ተመሳሳይ ውይይቶችን ለማካሄድ የነበረው ፍላጎት ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢድዩ በአጼ ኃይለስላሴና ሌሎች መሳፍንቶች የተመሰረተ በመሆኑ እንደ ህወሓት ካሉ ተራማጅና ህዝባዊ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ሊሰራ አልቻለም፡፡ በዚህም የኢህአፓ ዕጣ ሊደርሰው ችሏል፡፡ ህወሓትን ለማጥፋት ተደጋጋሚ ትንኮሳ ሲያደርግ ቆይቶ በተደረገው ትግል በመጨረሻ በህወሓት ሊደመሰስ ችሏል፡፡

ህወሓት በትግራይ ይንቀሳቀስ ከነበረው ማሕበር ገድሊ ትግራይ(ማገት) የተባለ ድርጅት ጋርም በርካታ ውይይቶችንና ድርድሮችን ማካሄዱን ታሪክ ያወሳል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አሁን ከሻዕብያና በወቅቱ በኤርትራ ከሚንቀሳቀሱ በርካታ ድርጅቶች መሰል ውይይቶችና ድርድሮችን አድርጓል፡፡

ኢህአዴግ እንደ ግንባር መቆም የቻለውም ከፍተኛ ጥረቶችና ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ ነው፡፡ ከኢህአፓ ተነጥሎ የወጣውን ኢህዴን(ብአዴን) እንደድርጅት ሊመሰረት የቻለው በውስጡ በርካታ ውይይቶችና ክርክሮችን አካሂዶ ነው፡፡ ኢህአፓን ጥለው ከወጡ ከመቶ በላይ ሰዎች ውስጥ 37 ታጋዮች ተነጥለው ትግሉን እንደአዲስ ለመጀመር የቆረጡትና ብአዴን እውን መሆን የቻለው እንዲሁ በቀላሉ አልነበረም በርካታ ውይይቶችና ድር ድሮች ከታካሄዱ በኋላ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ኦህዴድም በርካታ ውይይቶችና ክርክሮች ከተካሄደ በኋላ ለምስረታ የበቃ ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ መስራች ታጋዮች ለስምንት ወራት ያህል ጥልቀት ያለው እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር ባያደርጉ ኖሮ የኦህዴድን መመስረት አጠራጣሪ ይሆን ነበር፡፡ በውስጡ በርካታ ፓርቲዎች አቅፎ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደኢህዴግ) በሚል ይንቀሳቀስ የነበረውን ድርጅት የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ተብሎ ከግንባርነት ወደ  አንድ ፓርቲ ለመቀየርም በተመሳሳይ መልኩ በርካታ ውይይቶችና ክርክሮች ተደርጓል፡፡

እንደሚታወቀው ህወሓትና ኢህዴን (ብአዴን)ም ኢህአዴግን ለመመስረት ለበርካታ ወራት የዘለቀ  ብዙ ክርክሮችና ድርድሮች አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢህአዴግ እንደግንባር ሊቆም የቻለው አባል ድርጅቶቹ በነበራቸው ጠንካራ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ባህል ነው፡፡ ኢህአዴግ በሃሳብ ትግል የተፈጠረ፣ የትግል አቅጣጫዎቹን ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆኑ ክርክሮችና ውይይቶች እያጠራ ያደገ ድርጅት ነው፡፡

ኢህአዴግ ከተመሰረተ በኋላም ቢሆን የድርድርና የውይይት ጥሪዎችን ማድረጉን አላቆመም፡፡ የትጥቅ ትግል ይደረገ በነበረበት ወቅት ከደርግ ጋር ለመደራደርና ለመከራከር በርካታ ጥረቶችን ማድረጉም ኢህአዴግ ለውይይትና ድርድር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ አብይ ማሳያ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በ1980ዎቹ መጀመሪያ ኢህአዴግ በርካታ አካባቢዎችን ነጻ እያወጣ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ ካለው ጥልቅ ህዝባዊነት የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን ጦርነት ሊያስቀር የሚችል ማንኛውንም ድርድር ለማድረግና ጦርነቱ የሚያስከ ትለውን ውድመት ለማስቀረት በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ በዓለም ታሪክ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶች ድል እያስመዘገቡ ባሉበት ወቅት ለድርድርና ክርክር እጃቸውን ሲዘረጉ ማየት ያልተለመደ ቢሆንም ኢህአዴግ ግን ከህዝባዊ ባህርይው በመነሳት በተጨባጭ አድርጎታል፡፡

የኢህአዴግ ሰራዊት ወደ ፊት እየገሰገሰ የደርግ ሰራዊት እየተበታተነ በነበረበት ወቅት እንኳን ኢህአዴግ የመደራደር ሃሳቡን አልተውም፡፡ የህዝብ ችግር በሰላም እንዲፈታ ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ ሁሉንም ነገር በጠመንጃ የመፍታት አባዜ የተጠናወተው የደርግ ስርዓት ስሪቱ ድርድሮችንና ውይይቶችን የሚያስተናግድ አልነበረምና እስከ 1981 ዓም በኢህአዴግ ይቀርብ የነበረውን የእንደራደር ጥያቄ ውድቅ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ ይሁንና በሁሉም የጦርነት ግንባሮች የህዝብ ብሶት በወለደው የኢህአዴግ ሰራዊት ሽንፈትን እየተከናነበ የመጣው የመንግስቱ ኃይለማርያም ስርዓት ከ1981 ዓም መጨረሻ ጀምሮ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ፈቃደኝነቱን ማሳየት ጀምሮ ነበር፡፡ 

በደርግ ውድቀት ዋዜማ ላይ ኢህአዴግ ከሁሉም ኃይሎች የተውጣጣ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቅ የሰላም ሃሳብ አቀረበ፡፡ ይሁን እንጂ የሰላም ድርድሩ በደርግ በኩል ተቀባይነት በማጣቱ አልተሳካም፡፡ ኢህአዴግ ሳይሰላች በሩን ለሰላም ክፍት እንዳደረገ ነው፡፡ ሰራዊቱ አዲስ አበባን በቅርብ ርቀት እየተመለከተ እንኳን የውይይትና ክርክር አጀንዳ አልተዘጋም፡፡ እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ከደርግ ጋር በለንደን ድርድሮች ተጠናክረው ቀጥለው የነበሩ ቢሆንም ቀድሞውንም ነገሮችን በሰላምና በውይይት የመፍታት ባህል በሌለው የደርግ ስርዓት እምቢተኝነት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የኢህአዴግ ሰራዊትም የማጥቃት ዘመቻውን አጠናክሮ በመቀጠል አዲስ አበባን ከደርግ ቁጥጥር ነጻ አደረጋት፡፡ አዲስ የሰላም ንፋስ መንፈስ ጀመረ!

የደርግ ስርዓትን መገርሰስ አንደኛው የትግል ምዕራፍ መጠናቀቁን የሚያ በስር ነበር፡፡ በጦርነት የተንኮታኮተውን ኢኮኖሚ መልሶ መገንባት፣ ደርግ በዴሞክራሲ እጦት ምስቅልቅል ያደረጋትን ሀገር ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን የኢህአዴግ ቀጣይ የቤት ስራዎች ነበሩ፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ የትጥቅ ትግል እንዲካሄድ ምክንያት የሆኑት የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጀንዳዎች በመሆናቸው እንዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ለደቂቃም ሳይዘነጋ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት መረባረብ ጀመረ፡፡ ኢህአዴግ በአንዳንድ ሀገሮች እንደሚታየው አምባገነኑን ስርዓት ያስወገድኩት “እኔ ስለሆንኩ” ስልጣን በብቸኝነትና በማን አለብኝነት እይዛለሁ” አላለም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች የትጥቅ ትግል በድል ካጠናቀቁ በኋላ በትጥቅ ትግል የገቡትን ዓላማ በመዘንጋት ራሳቸው አድራጊ ፈጣሪ ለመሆንና በትግሉ ሂደት ያልተሳተፉ ኃይሎችን ያገለለ መንግስት የማዋቀር ሂደት ሲከተሉ ይታይል፡፡  

ትግል መጨረሻ እንደሌለውና የሰማዕታት አደራም ከዳር ደረሰ የሚባለው የሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ከዳር ማድረስ ሲቻል መሆኑን የተገነዘበው ኢህአዴግ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩን ለውይይትና ድርድር ክፍት በማድረግ በአገራችን አዲስና የሰለጠነ፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም መሰረት የሚሆን እርምጃ ወሰደ፡፡ ‹‹ሁሉም ኃሳቦች ለህዝብ ይቅረቡ፤ ህዝብ የሚመቸውን  ይመርጣል›› የሚለው ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ያደበረውን ልምድ በማስቀጠል ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እን ዲያደርጉ አደረገ፡፡ ለመገንጠል አኮብኩበው የነበሩ ከ17 በላይ የታጠቁ ኃይሎችን ጨምሮ በትጥቅ ትግል የተሳተፉም ይሁን ያልተሳተፉ ሃይሎች በሀገሪቱ የፖለቲካና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን አመቻቸ፡፡  

በዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ ኃይሎች የተሳተፉበት የሽግግር መንግስት ተመሰረተ፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተለያዩ መንግስታዊ የስልጣን እርከኖች ጭምር ተቀመጡ፡፡ ሁሉም ኃይሎች የተሳተፉበት የሽግግር መንግስት የምርጫና የህገ መንግስት የማጸደቅ ስራዎች በስኬት ለማከናወን ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል፡፡

ከሶስት ዓመታት የሽግግር መንግስት ቆይታ በኋላ ፓርቲዎችና ህዝቡ ሰፊ ውይይትና ክርክር ያደረጉበት የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው ህገ መንግስት ሊጸድቅ ችሏል፡፡ በአጠቃላይ በድህረ 1983 ዓም ህዝቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት፤ ክርክርና ድርድር በነጻነት የሚካሄዱበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡

ለዘመናት ተነፍገው የነበሩ መብቶች በህገ መንግስቱ ዋስትና አገኙ፡፡ መደራጀት፣ ኃሳብን በነጻት የመግለጽና ሌሎች መብቶች ህገ መንግስታዊ ዋስትና ተሰጣቸው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትም በይፋ ታወጀ፡፡ በዚህም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ በርካታ የግል ነጻ ፕሬሶችም እንደአሽን ፈሉ፡፡ በ1987 እና 1992 ዓም በተካሄዱ ሀገር አቀፍ ምርጫዎች በፓርቲዎች መካከል በርካታ ክርክሮችና ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህም ከሽግግር መንግስት ጀምሮ የኢህአዴግ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እያገኙ ኢህአዴግም በተደረጉ ምርጫዎች አሸናፊ እየሆነ መጣ፡፡

የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቶ ሶስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ ደረሰ፡፡ በዚህም ቀደም ሲል እንደተካሄዱ ሁለት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች የዴሞክራሲ ስርዓቱ ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች ተከናወኑ፡፡ በቅድመ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ የሚፈልገውን እንዲመርጥ በርካታ ክርክሮችና ውይይቶችን አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ያለምንም ገደብ ስልጣን ቢይዙ ስራ ላይ የሚያውሏቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በነጻነት አቀረቡ፡፡ በቀጥታ የቴሌቪዥንና የሬድዮ ስርጭቶች ውይይቶችና ክርክሮች ተካሄዱ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን በተቃራኒው ህገ መንግስቱን ቀደው ለመጣልና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ ብሎም ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ ስልት ነድፈው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡

ኢህአዴግና መንግስት ከመላው ህዝቡ ጋር በመሆን ባደረጉት ርብርብ ምርጫው ነጻ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ ተጠናቀቀ፡፡ መራጩ ህዝቡም ዳኝነቱን ሰጠ፡፡ ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ከተማ ሙሉ በሙሉ ሲሸነፍ በአጠቃላይ ውጤት ግን መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምጽ አገኘ፡፡ ይሁን እንጂ ገና ከመነሻው እኩይ ዓላማ ያነገበው የተቀዋሚ ቡድን በተለይም ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ እና ህብረት የተባሉ ፓርቲዎች ‹‹ስልጣን ወይም ሞት›› ሲሉ ተሰሙ፡፡ በዚህም ድብቁ የጥፋት አጀንዳቸውን ተግባራዊ ወደ ማድረግ ተሸጋገሩ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ አሸንፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምር ውጤት ተሸንፈው እያለ የህዝብን ድምጽ አክብረው ፓርላማ እንደመግባት ለብጥብጥ መስቀል አደባባይን መረጡ፡፡ ኢህአዴግ የተቀዋ ሚዎቹን ድብቅ አጀንዳ እያወቀ በሆደ ሰፊነት መንቀሳቀስ ነበር የመረጠው፡፡ ይሁንና ተቀዋሚዎቹ ለጥፋት በቂ ዝግጅት አድርገው ስለነበር በምርጫው ማግስት በርካታ ሁከቶችና ብጥብጦችን ለመፍጠር ቻሉ፡፡ በዚህም ምርጫ 97 የራሱን ጠባሳ ጥሎ አለፈ፡፡

በድህረ 97 ምርጫ የጽንፈኛ ሃይሉን ፖለቲካና ህጋዊና ህገ ወጥ መንገዶችን እያጣቀሱ በቀለም አብዮት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍራስ የሚደረገውን ሴራ ለማክሸፍ የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ታመነበት፡፡ በዚህም በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መድብለ ፓርቲ ስር እንዳይሰድ የሚያደርገውን የጽንፍ ፖለቲካ አካሄድ ለማስቀረት የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ በፓርቲዎች መካከል ውይይትና ክርክር ተደርጎበት ለማጽደቅም ወደ ስራ ተገባ፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 8 መሰረት የህዝብ የስልጣን ሉአላዊነት ሊከበር የሚችለው በጥብቅ ዲስፕሊን የሚመሩ ስልጣን በምርጫና ምርጫ ብቻ መሆኑን ከልብ አምነውም ለተግባራዊነቱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የ2002ቱ አራተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ኢህአዴግ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ሁሉንም ፓርቲዎች ሊያስማማ የሚችል የስነ ምግባር ኮድ ለማዘጋጀትም ወደ እንቅስቃሴ ተገባ፡፡ የምርጫ አፈጻጸም ድጋፍ ሰጭ ተቋም (IDEA ወይም Institute for Democracy and Electoral assistance) በመባል የሚታወቀው የስነ ምግባር ኮድ እንደመነሻ በመውሰድ ፓርቲዎች የክርክርና የድርድር ጥሪ ቀረበላቸው፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት(መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያውያን ፓርቲ(ኢዴፓ)፣ መድረክ ለፍትህና ለዴሞክራሲ(መድረክ)፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ(ቅንጅት) የድርድር ጥሪ ቀረበላቸው፡፡

ነሐሴ 24 ቀን 2001 ዓም በተካሄደው የቅድመ ድርድር ስብሰባ መድረክ ብቻውን ከኢህአደግ ጋር መደራደር እንደሚፈልግ በመግለጽ ለሌሎች ፓርቲዎችን እውቅና ነፈጋቸው፡፡ በዚህ አቋሙም ከድርድሩ አቋርጦ ወጣ፡፡ በሀገሪቱ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ 65 ተወዳደሪ ፓርቲዎች በምርጫ ስነ ምግባር ደንቡና በማስፈጸምያ ስልቱ ላይ ተወያይተው ማሻሻያ አድርገው መግባባት ላይ መድረስ ችለዋል፡፡ 

በ2001 ዓም የተካሄደው የድርድርና ውይይት ሂደት ቀደም እንዳሉት ዓመታት ሁሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ህጋዊና ህገ ወጥ መንገድ እያጣቀሱ መንቀሳቀስ የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን አሳይቶ አልፏል፡፡ አብዛኛዎቹ በአገሪቱ የሚገኙ ፓርቲዎች ከጽንፍና ፍጥጫ ፖለቲካ ርቀው ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁነታቸውን ሲያረጋግጡ የጥቂት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነውን መድረክ ግን ‹‹ከእኔ በላይ ላሳር›› በሚል ስሌት የድርድር ሂደቱን ለማወክ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ከድርድርና ውይይት ይልቅ የቀለም አብዮት አዝማሚያዎችን ሲያንጸባርቅም ተስተውሏል፡፡

ከ97 ምርጫ በኋላ በፓርላማ መተዳደርያ ደንብ፣ በምርጫ ህግ፣ የምርጫ ቦርድ አባላት በመሰየም፣ በፓርቲዎች ህግና፣ በፕሬስና የመረጃ ነጻነት ህግ ወዘተ….በርካታ ድርድሮችና ክርክሮች ተካሂደዋል፡፡ እናም በምርጫ ስነ ምግባር ኮዱ ላይ የተደረገው ድርድር በፓርቲዎች መካከል እየተጠናከረ የመጣውን የድርድር ሂደት  የቀጠለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 

ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት አድርገውበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ የተደረገው የፓለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ የምርጫ ዴሞክራሲያዊነትን ይበልጥ የሚያጠናክር፣ በህጋዊ መንገድ ለሚሳተፉ ፓርቲዎች ቦታ የሚሰጥና ቀደም ሲሉ የነበሩ የተሳሳቱ አካሄዶችን ለማረም የሚያሰችል ነው፡፡ ፓርቲዎችን ከህገ ወጥ አሰራሮች ለመካለከል የሚያስችልም ነው፡፡

በዚህ የስነ ምግባር ደንብ በመመስረት ደንቡን የፈረሙ የፖለቲካ ፓርቲዊች የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ምክር ቤቱ በድርድር ሂደት  ላይ የሚፈጸሙ ስህተቶች ፈጥነው እንዲታረሙና ከመወነጃጀልና መራራቅ ይልቅ ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል ትልቅ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ይሁንና ጽንፈኛ ኃይሎችና ህጋዊና ህገ ወጥ ተግባራትን እየፈጸሙ ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ በሚያደርጉት ጥረት ገና ከጅምሩ በድርድሩና በጋራ ምክር ቤቱ ላይ አሉባልታዎችን በማሰራጨት አንዳንድ ፓርቲዎች ከምክር ቤቱ እንዲወጡ አደረጉ፡፡ በዚህና በሌሎች በምክር ቤቱ የራሱ ውስንነቶች የሚጠበቅበትን ያህል ውጤታማ ባይሆንም እንኳ ለኢትዮጵያ ሩቅ ሆኖ የቆየውን በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ተቀራርቦ የመስራት ባህል እንዲቀየር የጋራ ምክር ቤቱ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ የተለያየ አቋምና አመለካከት ያላቸው ኃይሎች በተለያዩ ጉዳዮች በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው እንዲመክሩም ዕድል ሰጥቷል፡፡

አሁን ድርድርና ክርክር ለምን?

ኢህአዴግ በቀረጻቸው ትክክለኛ ፖለሲዎች በሁሉም መስኮች አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በሀገሪቱ በሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ህዝብና መንግስት ፊታቸውን ወደ ልማት በማዞር ባደረጉት ርብርብ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ልማት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የትምህርትና የጤና ተደራሽነት ሰፍቷል፡፡ ኢትዮጵያ በሌሎች ሀገሮች ዘንድ በፈጣን ልማቷ በምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡ የዴሞክራሲ ሽታ ርቋት የቆየችው ሀገር አዲስ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ስርዓት በመከተል መልካም ውጤቶችችን ማስመዝገብ ጀምራለች፡፡ መንግስታዊ ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የህዝቦችን ጥያቄ በመመለስ ረገድ ረጅም ርቀት ቢጓዝም የሚፈለገውን ያህል የህዝብ እርካታ ያልተፈጠረባቸው መስኮች አሉ፡፡ በተለይም ከመልካም አስተዳደር፣ ከወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ… ወዘተ ጋር ተያይዞ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጋር ተያይዞም የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የህዝብና የምክር ቤት አደረጃጀቶችን ከማጠናከር እንዲሁም የወጣቶችና ሴቶች ተሳትፎ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ካለ መድረሱ ጋር ተያይዞ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

የ15 ዓመታት የለውጥ ጉዞን የገመገመው ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስና የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ገብቷል፡፡ ኢህአዴግ በ1993 ዓም ከተካሄደ ተሃድሶ በኋላ በነበሩት 15 ዓመታት አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡ ያህል በርካታ ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች መኖራቸውን ገምግሟል፡፡ የችግሮቹ ምንጭ በርካታ ቢሆኑም በዋናነት ለስልጣን ያለው አተያይ የተዛባ መሆኑ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስልጣንን እንደ የኑሮ መሰረት አድርጎ መመልከት ዋናው የችግሩ ምንጭ መሆኑን  መግባ ባት ተደርሶበታል፡፡ ይህንን ችግር የወለዳቸው አድርባይነት፣ መርህ አልባ ግንኙነትና ሙስናም የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በሚፈለገው ፍጥነትና ግለት እንዳይሄድ አደርገውታል፡፡

በተሃድሶ ንቅናቄ ትኩረት ከተሳጣቸው ጉዳዮች አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ማጠናከር የሚል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ የዴሞ ክራሲ ስርዓት ግንባታው ይበልጥ ማጥለቅና ማስፋት እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፎ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል፡፡  በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ኢህአዴግ ከሁሉት አስርት ዓመታት በላይ ርብርብ ሲያደርግበት ቆይቷል፡፡ ከሽግግር መንግስት ጀምሮ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ ትግል አድርጓል፡፡ በ1983 ዓም ሀገር ማስተዳደር እንደጀመረ ህገ መንግስቱ ሳይጸድቅ ነበር ሁሉም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ያደረገው፡፡ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የሚወስን በመሆኑም ሁሉም የቡድንና የግል መብቶች በህገ መንግስቱ ዘንድ ዋስትና እንዲያገኙ ታግሏል፡፡

የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ያለ ምንም ገድብ እንዲከበር፣ በመንግስት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህም እስከአሁን አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ውስንነቶችም ተስተውለዋል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ አለመጠናከር፣ የህዝብ  አደረጃጀቶችም ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ በሚችሉበት ሁኔታ አለመገኘትና መገናኛ ብዙኃንም እንዲሁ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ያለመሆን በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ በሚፈለገው ደረጃ አለማበብ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ እንዲሁም በሀገራዊ ጉዳዮች ከተቀዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ሁኔታም የጋራ ምክር ቤት ካሉት ፓርቲዎች ጋር የተሻለ ቢሆንም ከምክር ቤቱ ውጭ ካሉት ጋር ግን አሁን ብዙ የሚቀረው ነገር እንዳለ ማየት ይቻላል፡፡

ህጋዊና ህገ ወጥ መንገድን እያጣቀሱ የሚሄዱ ፓርቲዎች ከገዢ ፓርቲ ጋር ተቀራርቦና ለሀገር ልማት፣ ሰላም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከመስራት ይልቅ ከውጭ ጽንፈኛ ኃይሎችና መንግስታት ጋር መስራት የሚቀናቸው መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም ያህል እንኳ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዳይጠነክር የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም የፓርላማ መቀመጫ ወንበር ባያገኙም እንኳ የተወሰነም ቢሆን ህዝብ ድምጹን የሰጣቸው በመሆኑ ህዝቡን በማክበር በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መወያየት፣ መከራከርና መደራደር አስፈላጊም ተገቢም ነው፡፡

እናም በጥልቅ ተሃድሶው አቅጣጫ መሰረት ዴሞክራሲን የማስፋትና የማጥለቅ ዓላማ አንግቦ የሚደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ክርክር ኢህአዴግ ገና ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ያደበረው ልምድ እንጂ አንዳንድ ኃይሎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ውጥረት ውስጥ ስለገባ ያቀረበው ጥሪ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ካለው ጥልቅ ህዝባዊነትና የዴሞክራሲያዊነት ባህርይው በመነሳት ያቀረበው ጥሪ ነው፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደተገለፀው ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉን ከትጥቅ ትግሉ በኋላ ለድርድርና ለክርክር በሩ ክፍት እንደነበረ የመጣበት ታሪኩ ተጨባጭ ምስክር ነው፡፡

ዘንድሮም ኢህአዴግ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረበው ጥሪ መሰረት በፓርቲዎች መካከል የሚካሄደው ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ለማድረግ ለማስፈጸም የሚያስችሉ የፓርቲዎቹ የውይይት መድረኮች በመደረግ ላይ  ናቸው፡፡ እስከአሁን ድርድሩንና ክርክሩን ለማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶች እየተካሄዱ ሲሆን በዚህ ውይይት የጋራ ምክር ቤቱ አባል ያልሆኑ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም በህጋዊ መንገድ የሚንቀሰቀቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ 

በ2001 ዓም የፓለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ ላይ በተካሄደው ክርክርና ድርድር ብቻውን ከኢህአዴግ ጋር ካልሆነ በስተቀር ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት መደራደር እንደማይፈልግ በመግለጽ ረግጦ የወጣው መድረክ ዛሬም ምንም ዓይነት የአቋም ለውጥ ሳያሳይ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መጎልበት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አሳንሶ በማየት <<ብቻዬን…>> በሚል አባዜ ውስጥ ይገኛል፡፡ መድረክ ሌሎች ተቀዋሚ ፓርቲዎችን ወክሎ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር እንደሚፈልግም በመግለጽ ከድርድሩ ወጥቷል፡፡

እስከ አሁን የድርድርና ክርክር ለማካሄድ እየተካሄዱ ባሉ የቅድመ ሁኔታ መድረኮች ኢህአዴግና በህጋዊ መንገድ የተደራጁ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጥሩ መንፈስ በመወያየት ላይ ናቸው፡፡ ክርክሩና ድርድሩን የሚመሩ ሰዎችም ከራሳቸው ከፓርቲዎቹ መርጠዋል፡፡

በዚህ ሂደት ድርድሩንና ክርክሩን ለማጠልሸት የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ፓርቲዎች አይኖሩም ባይባልም በአብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ተነሳሽነትና ፍላጎት ምክንያት የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን የሚያጠናክርና ተቀራርቦና ተግባብቶ የመስራት ልምድን የሚያጎለብቱ ተግባራት ይከናወናሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ከትጥቅ ትግል ወቅት ጀምሮ የድርድርና ክርክር ባህል ያዳበረው ኢህአዴግ  በአሁኑ ወቅት የሚካሄዱ ክርክርና ድርድሮች የሀገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ለማጠናከር እንዲያግዙ ለማድረግ የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡ በቀጣይም ይህንን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment