EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 10 November 2016

ተሃድሷችን በተጀመረበት ጥልቀትና ስፋት እንዲቀጥል እንትጋ!




(በሁሴን ገዳ)
ጉዟችንን ስንጀምር ፀረ ዴሞክራሲያዊና የድህነት ዘበኛ የነበረውን ስርዓት በትጥቅ ትግል ዳግም ላይመለስ ትቢያ አፈር አልብሰነው ቢሆንም ተሰናባቹ ስርዓት በአገዛዙ ወቅት የሀገሪቷን ሃብትና ንብረት ሁሉ በጦርነት አሟጦ ባዶ ካዝና ነበር ያገኘነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከባዶ፤ በባዶ ተነስተን የጀመርነው ጉዞ እጅግ አድካሚና ውጣ ውረድ የበዛበት እልህ አስጨራሽ ሆኗል፡፡ ሆኖም ይህንኑ አቀበታማ፣ ኮረብታማ እንዲሁም እንቅፋት የበዛበትና አስቸጋሪውን ጉዞ አስፈላጊው መስዋዕትነት ሁሉ እየከፈልን ከሃያሉ መስመራችን ሳንዛነፍ ከመጓዝ ውጭ አማራጭ አልነበረንምና ጀመርነው፡፡

ጉዟችን ወቅት ከውስጥም ከውጭም ባጋጠሙን አስቸጋሪ ፈተናዎችም ሆነ በየምዕራፉ አጋጥመውን ለነበሩት ተግዳሮቶች ሳንንበረከክ ተጉዘናል፡፡ እንደ ድርጅት ባዳበርነው ግምገማ ውስጣችንን እየፈተሸንና እያስተካከልን ፈተናዎችን በድል እየተወጣን፤ ህዝባዊ ዓላማዎቻችንን እያሳካን እነሆ ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ይህ ጉዞ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ነው። ከመሠረቱ ይዘን የተነሳናቸው የዴሞክራሲ፣ የሰላምና የልማት ዓላማዎቻችን ህዝባዊ ብቻ ሳይሆኑ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄብቸኛ አማራጮች በመሆናቸው የሀገራችንን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የህዳሴው ጉዞ ዋነኛ ተዋናይና የድሉ ፍሬዎች ተቋዳሽ ማድረጋቸው በተግባር ተረጋግጧል፡፡
በታሪካዊው የህዳሴ ጉዟችን ባለፉት 26 የትግልና የድል ዓመታት የገነባነው የፌዴራል ስርዓት ሀገራችንን ከእርስ በርስ ጦርነትና ከብተና ስጋት አውጥቷታል፡፡ ዋነኛው የጋራ ጠላታችን በሆነው ድህነት ላይ እንድንዘምትም አስችሎናል፤ ብዙሃነታችንን ያማከለ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በፅኑ መሰረት ላይ ገንብተናል፡፡
ይህ ሂደት ከዛሬ ነገ ትበታተን ይሆናል ተብሎ የተሰጋላት ሀገር፤ ከማሽቆልቆል ጉዞ ወጥታ ዓለምን ባስደነቀ የእድገት ምህዋር ውስጥ እንድትገባ አስችሏል፡፡ መሰረተ ሰፊ ዴሞክራሲ በመስፈኑ ብዙሃነት በአዲስ ቅኝት የዴሞክራሲያዊ አንድነት መሰረት መሆን ችሏል፡፡ ለ26 ዓመታት የሰላም አየር የተነፈሰችና ዜጎቿ የጦርነት ትውስታዎቿን መርሳት የጀመሩባት ሀገር ተገንብታለች። በዚህ ጉዞ ነው ከራሷ አልፋ የጎረቤቶቿን ሰላም በማስከበር ዓለም አቀፍ አድናቆትን የተቸረት ኢትዮጵያን እውን ያደረግነው፡፡
ባለፉት የስኬት አመታት በህዝባችን ውስጥ እጅግ የሚያስመካ የልማት ፍላጎትና የዴሞክራሲ ጠበቃነት አስተሳሰብ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመን በሀገራችን ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ሜጋ ፕሮጀክቶቻችንን በራሳችን አቅም መገንባት ችለናል፡፡ ዛሬ ላይ የህዳሴ ጉዟችን በማንም ሆነ በምንም ሁኔታ ሊደናቀፍ የማይገባው ውጤታማ ጉዞ መሆኑ ገሀድ የወጣና ማንም ሊክደው የማይችል እውነታ ሆኗል።
ከላይ ያስቀመጥናቸው ተጨባጭ እውነታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ መንግሥትና ገዢው ፓርቲያችን ኢህአዴግ አሁን በደረስንበት የእድገት ደረጃ በህዳሴ ጉዟችን ላይ የተጋረጡ አደጋዎች እንዳሉ በግምገማ አረጋግጠዋል። በድርጅታችንና በመንግስት መዋቅር ውስጥ ስልጣናቸውን ለግል ጥቅም የማዋል አባዜ የተጠናወታቸው አመራሮች ተንሰራፍተው መኖራቸው ለሙሰኞች መበራከት፣ ለአድልዎና ብልሹ አሰራር ዳርጎን መልካም አስተዳደርን በማጥፋት ህዝቡን ለቅሬታ ዳርጓል።
ከዚህም የተነሳ ቀላል የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እራሳቸው በመረጡት መንግሥት ላይ እምነት እስከማጣት ደርሰዋል። ኢሕአዴግ የነዚህ ችግሮች ምንጭ ስልጣንን ለግል ጥቅም መገልገል፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ሌሎችም አንገብጋቢና ዋነኛ ተግዳሮቶች በመሆናቸው በጥልቅ ተሃድሶ መቀልበስ የሚገባቸው መሆኑን ወስኗል። በዚሁ መሠረት በጥልቀት የመታደስ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ተጀምሯል።
በመሆኑም በጥልቀት ለመታደስ ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በሚቀርፍ ቁመና ላይ እስከምንገኝና የዳግም ተሃድሶ ግቦቻችን እስኪሳኩ ድረስ በጀመርነው ጥልቀትና ስፋት መቀጠል ይኖርብናል፡፡

No comments:

Post a Comment