EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 8 November 2016

የለውጥ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው



(በኤፊ ሰውነት)
 
ባሳለፍነው ሳምንት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በቀጣይ አገሪቷን የመምራትና የህዝባችንን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል የአመራር ብቃትና ክህሎት ያላቸውን የካቢኔ አባላት ሹመት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 


ይህ የካቢኔ ሹመት ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በአንድ በኩል ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የነበረውን አለመረጋጋትና የህዝብ ፍላጎት መነሻ በማድረግ ህዝቡ በተለያየ መንገድ ያነሳ የነበራቸውን ቅሬታዎች መፈታት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችንን የህዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ ድርጅታችን በየጊዜው እየጎለበተ የመጣውን የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዕድገት የሚመጥን አጠቃላይ ፖለቲካዊ ቁመና መገንባት የግድ የሚልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን በመገንዘብ እንደገና በጥልቀት መታደስ እንዳለበት በማመን ሰፊና ዝርዝር ግምገማ ካካሄደ በኋላ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው ባሳለፍነው ዓመት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በተከሰተ አለመረጋጋት ለዓመታት የገነባነውን ሰላም የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች የተስተዋሉ ሲሆን በዚህም በሰውና በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ኪሳራ ደርሷል፡

በተደጋጋሚ ሲጠቀስ እንደተሰማው በአገራችን ያለው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደና እየተከማቸ የመጣ ከመሆኑ ባሻገር እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ አርምጃዎችም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ባገናዘበ ፍጥነትና ሁኔታ እንዳልሆነ ኢህአዴግ በዳግም ተሃድሶው በዝርዘር ገምግሟል፡፡ ከዚህ ባሻገር ምንም እንኳ በኢህአዴግ እምነትና መርህ መሰረት ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ እንደሆነ በማያሻማ መልኩ በግልፅ የተቀመጠ ጉዳይ ቢሆንም ይህንን መሰረታዊ መርህና እምነት ወደ ጎን በመተው ስልጣንን ተገን በማድረግ ኢህአዴጋዊ ያልሆነ ተግባር ውስጥ መግባትና ስልጣንን ለግል ጥቅም ማካበቻነት የመጠቀም ዝንባሌና ድርጊት መታየቱን ኢህአዴግ በጥልቅት ገምግሟል፤ ሁኔታውንም በዝርዝር ለህዝቡ ይፋ በማድረግ ህዝቡም በተሟላ ሁኔታ እንዲሳተፍ የሚያስችለውን አቅጣጫ ቀይሶ በተግባር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ሁላችንም እንደምንገነዘበው ህዝብ የሚያነሳውን ጥያቄ መሰረት ያደረገና በአገራችን ለተፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት ይቻል ዘንድ ራስን በጥልቀት የመገምገምና የችግሩን ምንጭ በአግባቡ የመለየት ተግባር ከሁሉም እርምጃዎች ሁሉ ቀዳሚ እርምጃ መሆን እንደሚገባው የተገነዘበው ኢህአዴግ የችግሮቹን መነሻ ወደየትም ሳይወረውርና ለሌላ መለስተኛና አባባሽ ጉዳዮች ክብደት ሳይሰጥ ራሱን የማየት ብቃቱንና ልምዱን በመጠቀም ራሱን ተጠያቂ ማድረግን መርጧል፡፡ በዚህ መሰረት ኢህአዴግ እንደግምባርም ሆነ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች በተናጠል ራሳቸውን በጥልቀት በማየትና ችግሮቹን ወደ ውስጥ በመመልከት በአገራችን ለተፈጠረው ችግር መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን አንጥሮ የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡ የችግሮቹን መንስኤ ከመለየት ባሻገር ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጦም በዛው ልክ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግና እሱ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የሰሞኑን የካቢኔ ሹመትን ጨምሮ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸውን መሰረታዊ ጉዳዮችን በመለየትም ህዝባዊነቱን በተጨባጭ እያስመሰከሩ ይገኛል፡፡ 
 
በህዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የበጀት ዓመቱ የስራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ጉባኤ ላይና ከዛ በኋላ በተደረጉ ስብሰባዎች የተቀመጡ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች እንደሚያመላክቱት ድርጅታችንና መንግስታችን የህዝባችንን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል የተግባር ምዕራፍ ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡ ከዚህ አኳያም የወጣቱን ስራ አጥነት ችግር መቅረፍ የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በአገራችን ሁሉም ህዝቦች ተደማጭ የሚሆኑበትን የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ይበልጥ ማጎልበት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች ማመቻቸት እንዲቻል የምርጫ ህጉን እስከማሻሻል የሚያደርስ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባና ለዚህም የምርጫ ህጉን ለማሻሻል እንደሚሰራ፣ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የሚያገኘውን ልዩ ጥቅም ለማስከበር የሚያስችልና መሰል ስራን የሚያሳልጡ አዋጆች እንደሚወጡ ይፋ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም መንግሰት ለመንግስት ሰራተኛው ኑሮን መቋቋም የሚችልበትን አቅም ለመፍጠርና መላው ህዝባችንም በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ማናቸውንም አማራጮች ሁሉ በመጠቀም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ ይህ አገራችን ባለፉት ዓመታት የመጣችበት የስኬትና የድል ጉዞ ፈፅሞ በነበረው አቅጣጫና ፍጥነት ወደፊት እንዲገሰግስ ለማድረግ የሚያስችል መሰረታዊ ውሳኔ ነው፡፡ 

ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ የተደረገው የካቢኔ ሹመትም በዚሁ ቅኝት የሚታይ ሲሆን ኢህአዴግ በችግሮቹ ላይ የማያዳግም ዘላቂ እርምጃ ለመውሰድ የጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ ኢህአዴግ በቃሉ የሚኖር ህዝባዊ ድርጅት ስለመሆኑ ባለፉት ዓመታት የመጣባቸው የስኬትና የድል ዓመታት አስረግጠው ቢናገሩም ይህ እርምጃ ደግሞ ዛሬም ኢህአዴግ በቃሉ ላይ ያለ ህዝባዊ ድርጅት ስለመሆኑ የሚያስረዳ ተግባር ነው፡፡ ኢህአዴግ በለውጥ የሚያምነና ራሱን ከነባራዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር እያጣጣመ ነገንም አሻግሮ እያየ በጥንቃቄ ወደፊት የሚራመድ ድርጅት ለመሆኑ ሰሞኑን የተደረጉ እንቅስቃሴዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ውድ አንባብያን በተደጋጋሚ ለመግለፅ እንደተሞከረው እንደ ኢህአዴግ በጥልቀት ለመታደስ ከገፉት መሰረታዊ ምክንያቶች አንዱ ወቅቱ የሚጠይቀውን፣ ሀገራዊ ዕድገቱንና የህዝብን ፍላጎት በአግባቡ ማሟላት የሚችሉ ግንባር ቀደም አመራሮችን ወደ መሪነት የማምጣት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ደግሞ ድርጅቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአግባቡ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ውድ አንባብያን በእኔ እምነት ኢህአዴግ ላለፉት ዓመታት በአገራችን እውን ያደረጋቸው የለውጥ መስመሮች፤ በተግባር ተፈትነው አገራችንን በማያቋርጥ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ማስገባት የቻሉ ናቸው፡፡ ዛሬም እነዚህን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ብቃትና ቁርጠኝነት ባሏቸው መሪዎች ሳይሸራረፉ መፈፀም ከተቻለ አገራችንን ማድረስ ካሰብነው የእድገት ማማ ላይ ከማድረስ የሚገታን አንዳች ሃይል እንደሌለ መደምደም እንችላለን፡፡ ኢህአዴግ የሚከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችልና የተግባራቱ ሁሉ አልፋ ኦሜጋም የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመሆኑ ስኬት ከማስመዝገብ የሚገታው ጉዳይ ቢኖር ፖሊሲዎቹን በተገቢው መንገድ ያለመተግባር ጉዳይ ብቻ ይሆናል ባይ ነኝ፡፡ ይህ መስመር በተግዳሮቶች ውስጥም ሆኖ አበቃላት የተባለችውን አገር መለወጥ አስችሏል፤ አለም የተደመመበት ፈጣንና ተከታታይ እድገት የተመዘገበውም በዚሁ መስመር ነው፡፡

ባሳለፍነው ዓመት በ50 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የድርቅ አደጋ ገጥሞን እንኳን ራሳችንን ደግፈን መቆም የቻልነው ኢህአዴግ ምልአተ-ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ባረጋገጣቸው ስኬቶች አማካይነት እንደሆነ ለመረዳት ተመራማሪ መሆን አይጠይቅም፡፡ የድረሱልን ጥሪ ከማሰማታችንና እጃችንን ከመዘርጋታችን በፊት ችግሩን በራሳችን የውስጥ ዓቅም መቋቋምና ህዝባችንንም መታደግ ችለናል፡፡ ይህ ኢህአዴግ የሚመራበት የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ትሩፋት ነው፡፡ መስመሩ ይሄን ያህል ሃይል ያለውና ነገም አገራችንን በራሳችን መንገድ በተሻለ ሁኔታ መገንባት የሚያስችል ሰፊ እድል የሚሰጥ ዓቅም ነው፡፡ ዳግም በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴውም ከመስመር ጋር የሚገናኝ ሳይሆን መስመሩን ከማስቀጠል አንፃር ቁርጠኛ፣ ብቁና ጊዜው የሚፈልገው አመራር የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡

ውድ አንባብያን አገራችን ምናልባትም በዓለማችን ማንም አልፎት የማያውቀውን የህይወት ምዕራፍ እያለፈች የመጣች የባለብዙ ታሪክ አገር መሆኗ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያችን የምትታፈርና ዓለምን የሚያስደምም የስልጣኔ ባለቤት የነበረችበት አኩሪ ምዕራፍ አንዱ የታሪካችን አካል ነው፡፡ ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ አገራችን ወደ ቁልቁለት የወረደችበት ምዕራፍ ደግሞ ሌላው የራሳችን መጥፎ ገፅታ ነው፡፡ ይህ እንኳን እኛ በውስጧ እየኖር ላለን ዜጎቿ ይቅርና የዓለም ህዝብም በግልፅ የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ አገራችን በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ስትተዳደርብት የቆየችበት፤ ከጦርነትና ከእርስ በእርስ እልቂት ውጭ የሚነገር ሌላ ታሪክ እንኳን ያልነበረበት ያ! የሰቆቃ ዘመንም በምንም መልኩ የሚረሳ አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ግን ምንም እንኳን ብዙ ርቀት መጓዝ የሚጠበቅብንና በርካታ የቤት ስራዎች በማከናወን የሀገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ ብዙ ቀሪ ስራዎች ያሉን ሀገርና ህዝቦች ብንሆንም  ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ አማካይነት ግን አገራችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡ የጦርነትና የረሃብ ታሪኳም ላይመለስ ተቀብሯል፡፡ በህዝቦችና በብሔሮች እንዲሁም በሃይማኖቶችና በፆታዎች መካከል የነበረው አድሎና ጭቆናም በህዝቦች መራራ ትግልና ክቡር መስዋእትነት ግብአተ መሬቱ ተፈፅሟል፡፡ አገራችን የምትመራበት የጠራ መስመር ከማንም የውጭ ተፅእኖ ውጭ ሆኖ የሚፈፀም መሆኑና የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የምንችልበት ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመፈጠሩ ዛሬ ለተመዘገበው ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ታሪካችንን የቀየረልንን መስመር ይዘን በመቀጠል የተከፈተውን አዲስ ምዕራፍ ከዳር ማድረስ ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በምኞት አልያም በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭና በሚያሰራ መስመርና መርህ ላይ ቆሞ አገር የሚመራ፤ ስለብዙሃኑ ጥቅም የሚታገልና የሁሉንም መብትና ነፃነት ለማስከበር የሚተጋ መንግስት ለመሆኑ የመጣባቸው የለውጥ ዓመታት ምስክሮች ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላም ኢህአዴግ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአዲስ መንፈስ አገራችን የጀመረችውን ድህነትን የማስወገድና ህዳሴአችንን እውን የማድረግ ጉዞ በተጠናከረና የህዝብን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ለማስቀጠል በሙሉ አቋምና ብቃት ላይ ይገኛል፡፡ መቼም ቢሆን ችግሮቹ ለቀጣይ ስራዎቹ ትምህርት የሚቀስምባቸውና ወደስኬት ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን ዓቅም የሚያገኝባቸው ናቸው፡፡ አሁን በአገራችን እየሆነ ያለው ሁለንተናዊ ስኬትም ሆነ ተግዳሮት በመለወጣችን የተከሰቱና ወደፊት እየገሰገስንና በቀጣይነት እየተለወጥን እንዳለን የሚያሳዩ የዕድገታችን ምልክቶች እንጂ የህልውናችን ስጋቶች ሰላልሆኑ ችግሮቹን ወደ መልካም አጋጣሚነት፣ ድክመቶቹን ደግሞ ወደ ጥንካሬአችን በመቀየር የህዳሴ ጉዞአችንን እውን ለማድረግ ቀን ተሌሊት የምንተጋበት ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment