EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 14 November 2016

ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ህዳሴ!




በኤፊ ሰውነት
ካሳለፍነው ዓመት መጨረሻ አካበቢ ጀምሮ እስካሁን ባሉት ጊዜያት ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙንን እንቅፋቶች በማሰወገድ አገራችንን ወደ ፊት ለማራማድ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው፡፡

ባሳለፍነው ዓመት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ለዘመናት የገነባናቸውን የጋራ እሴቶቻችንን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ክስተት ኢህአዴግ ከመላው የአገራችን ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ካስመዘገባቸው ስኬቶች አንፃርም ይሁን አገራችንን በሩቅ ለማድረስ ከተቀመጠው ራዕይ አንፃር ሲመዘን ጎታችና የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ ሊያሰናክል የሚችል በመሆኑ ጉዳዩን በአግባቡ መርምሮ ሁነኛ መፍትሔ የማስቀመጡ ሁኔታ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ለዛም ነው ኢህአዴግ ወደ ፊት ከመገስገስ የሚገቱንን ማናቸውንም እንቅፋቶች በማስወገድ የተያያዝነውን ድህነትን የማስወገድና የአገራችንን ገናናነት የመመለስ ራዕያችንን የሚያኮላሽ ማንኛውንም አስተሳሰብና ድርጊት በፅናት መታገል የሚያስችለው ዳግም በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በይፋ ያቀጣጠለው፡፡

ውድ አንባብያን ለመንደርደሪያነት ይህን አልኩ እንጂ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ የተሃድሶ እንቅስቃሴውን ፋይዳ ማብራራት ሳይሆን የተሃድሶ እንቅስቃሴው ጅምር ውጤት የሆነውና በህዝቡ የተነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመፍታትም ሆነ አገራችን ወደ ፊት ማሳካት ከምትሻው አገራዊ ራዕይ አንፃር ያንን ሊመጥን በሚችል መልኩ የተዋቀረውን አዲስ ካቢኔ በተመለከተ አንዳንድ ሃሳቦችን ማንሳት ነው፡፡

የካቢኔ ሹመቱ ይፋ ከተደረገ ወዲህ ከግራም ከቀኝም በርካታ አስተያየቶች በተለያዩ ሚዲያዎች እየተንፀባረቁ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የካቢኔ ሹመቱ ጉዳይ እስካሁን አጀንዳ ሆኖ በተለያዩ ምሁራንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳቦች እየተሰነዘሩበት ይገኛል፡፡ 

በዚህ የካቢኔ ምደባ መሰረት ወደ መሪነት ከመጡ አዲስ አመራሮች መካከል አስር የሚሆኑት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመለመሉና ተቋማቱ ውስጥ በአመራርና በምርምር ስራ ውስጥ ያለፉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አራቱ የኢህአዴግ አባላት ሳይሆኑ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አሁን በአመራርነት የተሾሙት ግለሰቦች ግለታሪካቸው እንደሚያስረዳው በትምህርት ደረጃቸው፣ በስራ ልምዳቸውና በአመራር ክህሎታቸው በተለያዩ ተቋማት ውጤታማ መሆን የቻሉ በሳል ምሁራን መሆናቸውን ነው፡፡ ከአመራርነት ክህሎት ባሻገር ኃላፊዎቹ በሙያዊ ብቃታቸውም አንቱ የተባሉ ናቸውና በተመደቡባቸው ቦታዎች የተሻለ ድጋፍ ለመስጠትም ሆነ አዳዲስና የተሻሉ አሰራሮችን እውን በማድረግ የህዝባችንን እርካታ ለማረጋገጥ በተሻለ ሁኔታ መትጋት የሚችሉ ናቸው፡፡

ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ ግለሰቦች ሹመቱን ፋይዳ ቢስ ለማድረግ የሚያስችላቸው አራምባና ቆቦ የሆኑ ምክንያቶችና ሰበቦች በመደርደር ህዝቡን ለማደናገር ላይ ታች ሲሉ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ በአሁኑ ጊዜ ተሿሚዎቹን እያብጠለጠሉ የሚገኙ ወገኖች ከዚህ በፊት ኢህአዴግ ምሁራንን አያቀርብም፣ ምሁራንን ይፈራል እያሉ ኢህአዴግን በተደጋጋሚ ሲወነጅሉ የነበሩ መሆናቸው ደግም ትችቱ ምን ያህል መርህ የለሽ እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ የሚመድባቸው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የፖለቲካ ስብዕናቸውን ብቻ በመመዘን ከአካዳሚያዊ እውቀታቸው ጋር በሚመጣጠን ቦታ ከመመደብ አንፃርም ችግሮች እንዳሉት በኢነዘህ አካላት በተደጋጋሚ ይወቀስ ነበር፡፡

ኢህአዴግ ባሳለፍነው ወር ባደረገው ሹም ሽር ግን በአካዳሚያዊ እውቀታቸው አንቱታን ያተረፉ ምሁራንን ወደ ፖለቲካ መሪነት አምጥቷል፤ ከስራ ልምዳቸውና ከእውቀታቸው ጋር በቀጥታ በሚገናኝ የስራ ዘርፍ ላይ በመመደብም የተሻለ አቅም የሚሆኑበትን ሰፊ እድል አመቻችቷል፡፡ አንዳንድ በአገር ውስጥና በወጭ የሚገኙ አካላት ግን ይህን መልካም ጅምር በአዎንታ አይቶ ሂደቱን ይበልጥ በማጠናከር የህዝባችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ የሆነ ምላሽ እንዲያገኝ አዎንታዊ የሆነ አስተዋፅዖ ከማድረግ ይልቅ ፀጉር ስንጠቃ በሚመስል አኳኋን ጅምሩን ሲያብጠለጥሉትና ሲያጨልሙት እንታዘባለን፡፡ ለነገሩ ከእነዚህ አካላት ገንቢ አስተያየት መጠበቅ ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደመጠበቅ በመሆኑ ብዙም የሚገርም ነገር አይደለም እንጂ!
የአገር ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የራስን አስተዋፅዖ ማበርከት እንጂ በተደጋጋሚ ስለችግር በማውራትና ሁኔታውን በመውቀጥ ብቻ ዘላቂ መፍትሄ የማምጣት ዕድሉ እጅግ ጠባብ መሆኑ አይቀርም፡፡ ራስን ያለ ምህረት መመልከትና ለዛም የሚመጥን ሁነኛ መልስ መስጠት ግን ብስለትም ስልጣኔም ነው፡፡ ኢህአዴግ በአሁኑ ጊዜ እያደረገ ያለው መሰረታዊ ጉዳይ ራሱን ሳይሸፋፍን በዝርዝርና በጥልቀት መመልከተን ነው፤ ህዝባዊነቱም ያስገድደዋልና፡፡  በዚህ ሂደትም ህዝቡን ያስመረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ፣ ስልጣንን አለአግባብ የመጠቀምና ለግል ሃብት ማካበቻነት የማዋል አስተሳሰብ እየታየ ነው፤ እነዚህን ችግሮች ከስር መሰረታቸው ለመፍታትም የሚሻሻሉ አሊያም የሚወገዱ አሰራሮች፣ አደረጃጀቶችና የሕግ ማዕቀፎች ከማሻሻል አሊያም ከማስወገድ በተጨማሪ የህዝቡን ቅሬታ በአግባቡ መፍታት የሚችሉ ሙያዊ ብቃት ያላቸው አመራሮች የፊት ረድፉን እንዲይዙ በማድረግ እንደሆነ ተገንዝቦም ግንባሩ የካቢኔዎችን ምደባ በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት ፈፅሞታል፡፡ እርምጃውም በማንኛውም መስፈርት ቢለካ ተራማጅና ትክክለኛ ነው፡፡ ይህ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን አሁን እየተተገበረ ያለ ተስፋ የሚጣልበት እርምጃ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የብሄር ታፔላ በመለጠፍ፣ አንዳንዴም ደግሞ አካዳሚያዊ እውቀት አገር ለመምራት በቂ አይደለም በሚል የተውገረገረና ምናልባትም ከዚህ በፊት ሲያራምዱት ከነበረ ሀሳብ ጋር ፍፁም የሚጋጭ አቋም በማራመድና፣ እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ በሹመኞቹ የግል ስብእና ላይ ያነጣጠረ ኢ-ሞራላዊና የኢትዮጵያውያንን ባህል ባልተከተለ ሁኔታ በማንቋሸሽ መርህ የለሽ ትንታኔ በማቅረብ ላይ የተጠመዱ ተቋማትና ግለሰቦችን እየታዘብን ነው፡፡

ውድ አንባብያን ፍፁምነት ለፍጡራን የተቸረ ስጦታ ስላይደለ ማንም ፍፁምና ከስህተት የፀዳ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢህአዴግ ወደ መሪነት ያመጣቸው ምሁራንም ከከፍተኛ ትምህርትና ከምርምር ተቋማት የተገኙ እንጂ ከመላእክት መንደር በተዓምር የወረዱ ስላልሆነ ሰብአዊ ፍጡርነታቸውን አያስቀርላቸውም፣ በተደጋጋሚ እየታዘብናቸው ያሉ አንዳንድ አስተያየቶች ግን አነዚህ ምሁራን እኮ ሰዎች ናቸው የሚል ነው የሚመስለው፡፡ ምሁራኑ በአመራር ክህሎታቸው፣ በእውቀታቸውና በልምዳቸው ብቁና መልካም ስነምግባር ያላቸው መሆናቸው በራሱ ለመሪነት ብቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ነገሮችን እየፈለፈሉ ታፔላ መለጠፍ በእርግጥ እንደዛ የሚሉ ሰዎችስ ፍፁማን ናቸውን የሚል ጥያቄ የሚያሰነሳና ራስንም ትዝብት ውስጥ የሚከት የተሳሳተ አካሄድ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ለነገሩ ግን እኮ በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ይህ ነው የሚባል አስተዋፅዖ ለማድረግ ሳይሆን ኢህአዴግን መቃወም መደበኛ ስራቸው አድርገው የያዙት አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚዎችም እኮ እያሉ ያሉት ስልጣኑ እስካልተሰጠን ድረስ ዕድገትና ብልፅግና እንዲሁም ዴሞክራሲ ብሎ ነገር አይኖርም ነው፡፡ ታዲያ እነሱ ስልጣን ከያዙ አገር የሚቃና እነሱ ከሌሉበት ደግሞ የአገር ህልውና አደጋ ላይ የሚወድቅ አድርገው የሚያስቡት የእነሱ ፖለቲካዊ ብቃትስ በምን ይለካ ይሆነ ጎበዝ! ምሁራን ናቸው ግን እንዳትሉ፤ የትምህርት ደረጃማ ዋጋ እንደሌለው እኮ በግላጭ እየነቀፉን ነው፡፡

ወደ እውነታው ስንመለስ ግን አሁን በአመራርነት የተቀመጡ ምሁራን በተግባር ተፈትኖ ውጤት ያመጣውን የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ለማስቀጠል ያዳግታቸዋል የሚል መነሻ ክርክርም ውሃ አያነሳም፡፡  ለነገሩ የኢህአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም መርሆችና አቋሞች ለመረዳት ቁርጠኝነት፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ ከራስ ይልቅ ለህዝቦች ጥቅም ቅድሚያ መስጠት፣ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና አስፈላጊ የሆነ መስዋዕት ሁሉ ለመክፈል ግንባር ቀደም መሆን ነው የሚፈለገው፡፡ እነዚህ ምሁራንም በነበሩባቸው የስራ መስኮች በተግባር ተፈትነው ውጤታማነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው፡፡

አሁን ከተሿሚዎቹ የሚጠበቀው የመጀመሪያው ነገር በአንድ በኩል ፈጣኑን ልማታችንን በማስቀጠል የሀገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ በሚካሄደው ዘርፈ ብዙ ርብርብ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚደፍቁ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦችና ተግባራትን በፅናት በመታገል የህዝባችንን የልማትና የመልካም አስተዳደር እርካታ ማረጋገጥ ነው፡፡ እናም አንዴ ወደዚህ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደዚያ የሆነ መርህ የለሽ አመለካከት በማራመድ ህዝብን ለማደናገርና የአመራሮችን ማንነት ለማጠልሸት የሚደረገው አፍራሽ ዘመቻ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት የተዛባ አካሄድ ነውና መታረም አለበት፡፡ በዚህ ተግባር ውስጥ የተጠመዱ አንዳንድ ወገኖችም ቆም ብለው በማሰብ በተጀመረው አገራዊ የለውጥ ጉዞ ወስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት ቢያደርጉ ይበጃል ባይ ነኝ፡፡ ፕሮፌሰርነት አልያም ዶክተርናት በራስ ሚዛን ሲሆን የሚከበር ሙያ በሌላው ሚዛን ሲሆን ደግሞ ጥቅም እንደሌለው ለማስመሰል የሚደረገው ሙከራም ከተራ ቅጥፈት የዘለለ ነገር እንዳለሆነ ለማናችንም ቢሆን ግልፅ ነውና በዚህ በኩል እየቀረቡ ያሉ ውትወታዎችም መጨረሻቸው መተዛዘብ ብቻ መሆኑ አይቀርም፡፡
 
በእኔ እምነት ኢህአዴግ ለመስመሩ ሟች ነው፣ መሰረታዊ የህልውናው ምስጢርም ይህ ነውና፡፡ መስመሩ ሃያል መሆኑንና ነገ አገራችንን ከከፍታ ላይ ለማድረስ ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ በፅናት ያምናል፡፡ ኢህአዴግ በመርህ የሚንቀሳቀስ ነገሮችን በብስልትና በጥልቀት የሚያይ ህዝባዊ ድርጅት እንጂ ነገር ለማለዘብ አልያም ከህዝብ ውጭ በሆኑ አካላት በሚወረወር ድንጋይ አሊያም የቃላት ጋጋታ ተደናግጦ በመርሁ ላይ ለሽምግልና የሚቀመጥ ድርጅት አይደለም፡፡ በመሆኑም ከመስመር ውጭ የሆኑ አካላት ስለመስመሩ እምነት እንኳን ሳይኖራቸው የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ብቻ በማሰብ የካቢኔ ሹመቱ ሁሉንም ያካተት አይደለም፣ ሁሉም የኢህአዴግ ደጋፊዎች ናቸው በሚል የተውገረገረ ሃሳብ በመሰንዘር ማጣጣል ከስልጣን ስካር ውጭ ሊሆን አይችልም ባይ ነኝ፡፡ ወይ ጉድ እነዚያ ተቃዋሚዎች በካቢኔው ቦታ ላይ ገብተው ቢመደቡስ ምን ዓይነት የተለየ የትምህርት ደረጃ ይዘው ይቀርቡ ይሆን ጎበዝ!  

ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን በአሁኑ ጊዜ እያደረጉት ያለው ዳግም በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝና የኢህአዴግን ህዝባዊነትንም በተግባር የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ህዝብን ለማገልገል የሚወሰዱ እርምጃዎችን እየተከታተሉ በማብጠልጠል እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እናዳለችው እንትና ሌላውን ነገር ሁሉ እርባና ቢስ ለማድረግ የሚራወጠው አካልም መለስ ብሎ ራሱን በማየት አንዲት ግራም አስተዋፅዖ ለማበርከት ቢነሳሳ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለእኛ የሚበልጠው ሰላማችን፤ ከድህነት ተላቀን ዓለም ያጣጣመውን ዕድገት ማጣጠም እንጂ ዓለም አሽቀንጥሮ የወረወረው የጥላቻ መርዝ ስላለሆነ እንደ አገር ሁሉም ዜጋ ለአገራችን ዕድገትና ብልፅግና በጋራ መረባረብ አለበት ባይ ነኝ፡፡ ወደፊት መገስገስ የሚቻለው ደግሞ እንደለመድነው በልዩነታችን ውስጥ ደምቀንና እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድ ልብ ስንተም ነውና ዛሬም ለአገራችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መረጋገጥ እንትጋ፡፡ ሰላም፡፡

No comments:

Post a Comment