EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 10 March 2016

የፌደራል ስርዓቱ የችግር መፍቻ ቁልፍ እንጂ የችግር ምንጭ አይደለም

የማነ ገብረስላሴ           
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ለእኩልነታቸው፣ መብታቸውና ለነጻነታቸው ሲሉ ታግለዋል፡፡ ትግሎቹ በኢህአዴግ ግንባር ቀደም መሪነት ለድል በቅቷል፡፡ በኢህአዴግ የተመራው ትግል አምባገነኑ የደርግ ስርዓት እንዲንኮታኮት ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አብቅቷል፡፡ በጨቋኞቸ መቃብር ላይ በኢህአዴግ መሪነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊገነባ ችሏል፡፡

በድህረ 1983 ዓም ብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች መብታቸው ሳይሸራረፍ ተከብሯል፡፡ የጋራ ቃልኪዳናቸው የሆነውን ህገ መንግስት በማጽደቅ በኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል፡፡ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አዲስቷን ኢትዮጵያም መስርተዋል፡፡   
“..መጪው የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል ህገ መንግስቱን በተወካዮቻችን አጸድቀነዋል፡፡” በማለት ባለፉት ስርዓቶች የደረሱ በደሎች በአብሮ መኖርና አንድነታቸው ላይ መጥፎ ጠባሳ እንደማያሳድሩም በቃል ኪዳን ሰነዳቸው አስፍረዋል፡፡ የኢፌዴሪ መንግስት ለግልና ለቡድን መብቶች መከበር ጥብቅና የሚቆም በዴሞክራሲያዊነቱ እንከን የሌለው ህገ መንግስት ነው፡፡ ብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች መብታቸውን ያለ ገደብ ተጎናጽፈዋል፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 መሰረት ብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግና ባህላቸውን የመግለጽ እንዲሁም የማዳበርና የማስፋፋት፣ ታሪካቸውን የመንከባበከብ መብት አጎናጽፏል፡፡ በኢትዮጵያ የነበረው ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ የአገርን አንድነት ማጠናከር የሚቻለው ራሳውን በራሳው የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት ሲጎናጸፉ በመሆኑ ይህንን መብት አረጋግጧል፡፡ 

በዚህም ባለፉት 21 ዓመታት ብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግስቱ ባጎናጸፈቸው መብቶች እየተጠቀሙ በአካባቢያቸውና አገራቸው ልማት ንቁ ተሳታፊ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡ በአገራችን እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ልማት ያለ ብሄሮች፣ ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎ የሚታሳብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከራስዋ አልፋ ለሌሎች አገሮች ሰላም መስፈን ቀዳሚ ተዋናይ ለመሆን የበቃችው በህገ መንግስቱ መሰረት ብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱት የፌደራል ስርዓት በአገር ውስጥ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ዋሰትና በመሆኑ ነው፡፡ የፌደራል ስርዓቱ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውን ፍትሓዊ ልማት ዕውን እንዲሆን ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ በህገ መንግስቱ መሰረት የተዋቀረው የፌደራል ስርዓት የኢትዮጵያ አንድነት በጽኑ መሰረት ገንብቶ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ በሚደረግ ጉዞ ላይ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

ህግ መንግስቱ ህዝብ በየደረጃው  ተወያየቶበት የጸደቀና ለመበታተን ጫፍ ደርሳ የነበረችውን አገር አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ያደረገ መሆኑ ሁሉም የሚገነዘበው  ሓቅ ነው፡፡ ይሁንና የህገ መንግስቱ መጽደቅና የብሄሮች ብሄረ ሰቦችና ህዝቦች መብት መከበር ጥቅማቸውን የሚጎዳ የመሰላቸው የትምክህት ኃይሎች ገና ከጅምሩ በህገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ ላይ ዘመቱ፡፡ ህገ መንግስቱ “ከፋፋይ፣ በታኝ…ወዘተ” እያሉ ሰፊ የማጥላላት ዘመቻ አካሄዱበት፡፡

የፌደራል ስርዓቱ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚበታትናት አሟረቱ፡፡ አንዳንዶቹም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን  በኃይል ለመናድና ህገ መንግስቱን ቀደው ለመጣል ቋመጡ፣ ይህ ቅዠታቸውን ዕውን ለማድረግም በስመ ፖለቲካ ፓርቲና ነጻ ፕሬስ እንዲሁም ሌሎች አደረጃጀቶች ተሰባሰቡ፡፡ ህገ መንግስቱ ባጎናጸፋቸው መብት እየተንቀሳቀሱ በግላጭ ከህገ መብግስቱ በተቃራኒ ተሰለፉ፡፡ ህዝቡና ለማነሳሳት ደግሞ የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ ዘመቻዎች አካሄዱ፡፡ በኢትዮጵያ የብሄር እኩልነት እንደሌለ፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች እንደሆነ ለማስመሰል የተለያዩ ፕሮፖጋንዳዎችን በመርጨት በህዝቦች መካከል ቅራኔን ለመፍጠር ተሯራጡ፡፡ የጠባብነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ኃይሎችም እንደ ትምክህት ኃይሎችም ህገ መንግስቱንና የፌደራል ስርዓቱን ከማጥላላት አልተቆጠቡም፡፡

የትምክህትና የጠባብ ኃይሎች እዚህም እዛም የሚያጋጥሙ ችግሮች በማጋነን አገር እንደፈረሰ በማስመሰል ከማስተጋባት ይልቅ የፈደራል ስርዓቱን የሚተካ አማራጭ አላቀረቡም፡፡ የእነዚህን ኃይሎች ባህርይና ነባራዊ ሁኔታውም አማራጭ የአስተዳዳር ስርዓት እንዲያቀርቡ አይፈቅድም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ለቀጣይ አንድነታቸውና ዕድገታቸው ዋስትና መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አምነው የመረጡት ስርዓት ነው፡፡ እናም የአሉባልተኞችን ጩኸት ቦታ የሚሰጡት አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጥፋት ኃይሎቹ መልካም ስራዎችን ማጠልሸት፣ ጥቃቅን ስህተቶችን ማጉላትና ህዝብን የእኩይ ዓላማቸው ተከታይ ለማድረግ በስህተት ከማነሳሳት ያለፈ አጀንዳ እንደሌላቸው የትላንት ታሪካቸውና የዛሬ ባህርያቸው ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡
ለዚህም ነው በአንዳንድ አከባቢዎች በጥቃቅን የአፈጻጸም ስህተቶች ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮች የፌደራል ስርዓቱ ያመጣው ነው በማላት የሚያስተገቡት፡፡ በቅርቡ አንዳንድ አከባቢዎች የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ከመነሻቸው ችግር ያላቸው አይደሉም፡፡ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል መብቱን መጠየቅ የዴሞክራሲያዊ ፌደረላዊ ስርዓቱ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ የጥፋት ኃይሎች የህብረተሰቡን ጥያቄ በመጥለፍ አንድም በአቋራጭ የሚቋምጡጥለትን የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ብሎም እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች በፌደራል ስርዓቱ ምክንያት የተፈጠሩ መሆናቸውን በመግለጽ በህዝቡ ዘንድ ውዥንብር ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ፡፡

የፌደራል ስርዓቱ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄ የመለሰ፣ የአንድነታችንና የሰላማችን ዋስትና ነው፡፡ መላው የአገራችን ህዝቦችም ይህንን ተገንዘብው የፌደራል ስርዓቱ ይበልጥ እንዲጠናከር እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በየትኛውም አከባቢ የፌደራል ስርዓቱን የሚቃውም ህዝብ የለም፡፡ ይልቁንስ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች የፌደራል ስርዓቱ የፈጠራቸው ትክክለኛ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አንዳንዱቹ ጥያቄች የፌደራል ስርዓቱ ካለመጠናከርና የህገ መንግስት ግንዛቤ ካለማደግ የሚፈጠሩ ናቸው፣ ሌሎች ደግሞ በመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም ከጠባብነትና ትምክህት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች ናቸው፡፡


የፌደራል ስርዓቱ ወርቃማ ድሎችን ያጎናጸፈ የህዳሴና የልማት ዋስትና ነው፡፡ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ችግሮች አያንዳንዳቸው በፍጹም ከፌደራል ስርዓቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፡፡ እናም የፌደራል ስርዓቱ ያስገኛቸው ወርቃማና በሌሎች አገር ህዝቦች ጭምር አድናቆት የተቸረባቸው ድሎችን ይበልጥ በማጠናከር አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ዕልባት በመስጠት ያስብነውን ህዳሴ ከማሳከት የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ ምክንያቱ  የፌደራል ስርዓቱ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ እንጂ ችግር ፈጥሮ አያውቅም፣ ሊፈጥርም አይችልምና፡፡

No comments:

Post a Comment