EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 1 March 2016

የዓድዋ ድል ጽናት በጸረ- ድህነት ትግሉ ላይ መድገም ይገባል!

በአሜሳይ ከነዓን
የካቲት ወር የአፍሪካውያን የድል ወር ተደርጎ ይወሰዳል፡ ነጮች አፍሪካን ለመቀራመት፣ የአፍሪካውያንን ሃብትና ጉልበት ለመመዝበር የማይፈነቅሉት ጉድጓድ አልነበረም በዚያን ዘመን፡፡ አፍሪካውያን በግፍ የሚረገጡበት፣ እንደ ሸቀጥ የሚሸጡበትና በባርነት የሚገዙበት፤ ለአፍሪካውያን የጨለማና ክፉ ዘመን ነበር ያ! ዘመን፡፡ አፍሪካውያን በአገራቸው  በጉልበታቸው አምርተው፤ የአገራቸው ምድር የሰጠቻቸውን ገፀ በረከት በነፃነት መጠቀም ሲገባቸው ባይተዋር ሆነው እየተገረፉና እየተናቁ በነጮች ባርነት ሲገዙ የነበረበት ክፉ ዘመንም ነበር፡፡

በርካታ አፍሪካውያን በነጮች ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው መራራውን ጊዜ በሚገፉበት በዚያን ዘመን ባርነት ለምኔ በማለት "እምቢኝ! ለግዞት!" ያሉት ጀግኖች አባቶቻችን የቅኝ ገዢዎችን ቅስም በመስበር አገራችን በጠላት ወረራ የማትደፈር መሆኗን አስረግጠው መልዕክት ያስተላለፉበት፣ ለአፍሪካውያንም ኩራት የሆኑበትን ድል የተጎናፀፉበት ወር ነው ወርሃ የካቲት፡፡

ታሪክ እንደሚያስረዳን ጣሊያን እንደሌሎች አምባገነን የአውሮፓ አገራት ሁሉ ኢትዮጲያን በቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ  ውጫሌ  ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በተወካይዋ ኮንተ አንቶሌኒ መሰረት የውጫሌ ውል የሚባለውን ተዋዋለች፡፡ የውሉ አንቀፅ 17 የአማርኛ እና የጣልያንኛ ትርጓሜው እንዲለያይ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስትን የማሳሳት ሴራ በጣሊያን ተሸረበ፡፡ የጣሊያን መንግስት ለግዞት የሚመቸውን ኢትዮጵያን በጣሊያን ሞግዚት አስተዳደር ስር መሆኗን በሚያትት መልኩ በመቅረፅ የአውሮፓ መንግስታት ጭምር እንዲያውቁት ተደረገ፡፡ 

በወቅቱ የጣሊያኖች ሴራ ስለተደረሰበት የውሉ አንቀጽ 17 እንዲቀር ተወሰን፡፡ ጣሊያን መንግስት በመሪው በኮንተ አንቶሎኒ አማካኝነት የውሉን መቋረጥ እንደውርደት እንደሚቆጥረው በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አወጀ፡፡ ለውጭ ወራሪ ሃይል የማይንበረከከው የኢትዮጵያ ህዝብ የታወጀበትን ጦርነት ከቁብ ሳይቆጥር ከዳር አስከ ዳር ነቅሎ ተነሳ፡፡  የአድዋ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 .ም በይፋ ተጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ ጀግኖች በመሳሪያ የተደራጀውን የጣሊያንን ጦር መፋለም ጀመሩ፡፡ የጣሊያን ጦር እየተረታ፤ የጣሊያን ወታደሮችም የኢትዮጵያ ጦር የሚያደርገው ወኔ የተሞላበት ድርጊት እያስበረገጋቸው በመሸሽ የኢትዮጵያ የበላይነት እየታወቀ መምጣት ጀመረ፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 . ከጣሊያን ጋር በተካሄደው ጦርነት የአገራችን ጀግኖች አባቶቻችን እንደዛሬው ዘመናዊ ትጥቅ ሳይኖር፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያም ሳይሸከሙ በባዶ እግራቸው አድዋ ዘምተው አስፈሪውን የጣሊያንን ጦር ድል በማድረግ የማይገፋውን ገፍተው ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነ ድል ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እስከ 1960ዎቹ በቅኝ ግዛት ሲማቀቁ፤ሲበዘበዙ፤ሲጨቆኑ እኛ ግን ከባርነት ቀንበር ነፃ በመውጣት ሰላማዊ አየር እንድንተነፈስ አስችሎናል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን አቋቋመን ለሌሎች ነጻ ማውጣት ጭምር የላቀ አስተዋፅኦም አበርክተናል፡፡

ይህ ጀግኖች አባቶቻችን የፈጸሙት አኩሪ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬ ትውልድ ደግሞ በመለወጥ ላይ ያለችውን አገራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማደረስ አዲስ ታሪክ መፃፍ ይገባዋል፡፡ ዛሬ ግዞተኛ ሊያደርግን ጦር የሚሰብቅብን ወራሪ ሃይል የለንም፡፡ ጠላታችን ድህነት ነው፡፡ ድል ለማድረግ የምንተጋውም ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ነው፡፡

ኢህአዴግ አገር የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ ከአገራት ጋር ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት በመተባበርና በመደጋገፍ ላይ እንደሚሆን በግልፅ በማስቀመጥ ሰላማዊ ከባቢን ለመፍጠር የምትትጋ አገር ሆናለች አገራችን፡፡ ትናንት አባቶቻችን ከጠላት የጠበቋትን አገር ዛሬ ደግሞ የድህነትና የኋላ ቀርነት ታሪኳን ከስር መሰረቱ ነቅሎ ለመጣል ርብርብ የጀመርንበት ጊዜ ነው፡፡ በድህነት ላይ የጀመርነው ዘመቻ አገራችን አድጋና በልጽጋ እስክናያት ድርስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአገራችን ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ አገራችንን የተሻለች አገር አድርጎ ማስቀጠል የዚህ ትውልድ አደራና ግዴታ ነው፡፡


በአድዋ አባቶቻችን የጠላት ወራሪን ለመመከት የከፈሉትን ዋጋ ዛሬ ድህነትን በማስወገድና አገራችን ካደጉት አገራት ተርታ በማሰለፍ የታሪክ ባለቤት ልንሆን ይገባል፡፡ 

1 comment:

  1. የአድዋ ድል ባይኖር ኖሮ ያሁኗ ኢትዮጵያ ጥያቄ ውስጥ ነበረች፡፡

    ReplyDelete