EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 11 March 2016

ሴቶች የአገር ብልፅግና መሰረቶች





አሜሳይ ከነዓን
 
“ሴቶች ተዝቆ የማያልቅ አቅም አላቸው” ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴቶች የሚመራ ሙሉ የበረራ አገልግሎት ፕሮግራም ሽኝት ሲያደርግ የተናገሩት ነው፡፡  
 
ወደ ኋላ ተመልሰን ያለፉት ዘመናትን በህሊናችን እያመላለስን ብናስታወስ ሴቶች ያለፉበትን የመከራ ዘመን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በአገራችን የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ጨምሮ የባለፉት ዘመናት የሴቶችን እንቅስቃሴ ብንመለከት ሴቶች ዛሬ የደረሱበት ደረጃ በምን አይነት ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ አልፈው እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ሴት ልጅን ከቤት ወደ አደባባይ ማውጣት እንደ ነውር ከመቆጠሩ ባሻገር የቤተሰብ ድምር ኃላፊነት ጭምር የመሸከም ግዴታማ ነበረባት፡፡ ወልዶ ከማሰደግ በዘለለ የቤተሰቡ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ በሴቶች ጫንቃ ላይ የወደቀም ነበር፡፡ በዚህና መሰል ፆታዊ መድሎዎች ምክነያት ሴቶች በትምህርት ራሳቸውን ሳያበቁ፣ በኢኮኖሚ መስክም ከጥገኝነት ሳይላቀቁ ዘመናትን እንዲገፉ ተገደው ቆይተዋል፡፡ 
 
ታሪክ እንደሚያስረዳን በየትኛውም ዓለም የሚኖሩ ሴቶች በአንድም በሌላ መልኩ ለጾታዊ መድልዎ የተጋለጡ ነበሩ፡፡ በተለይ አፍሪካውያን ሴቶች አትችሉም እየተባሉና እጣፈንታቸው ከማጀት የዘለለ እንዳልሆነ እየተነገራቸው በአስከፊ ጭቆና ውስጥ አልፈዋል፡፡ 
 
ለዛም ነው የባለፉት ዘመናት ጭቆናዎች በሴቶች ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ላይ ያሳረፈው አሉታዊ ተፅእኖ ዛሬም ድረስ የሴቶች ተሳትፎ የተሟላ እንዳይሆን እያደረገው በመሆኑ ድጋፉ መጠናከር ይገባዋል የሚባለው፡፡ እርግጥ ነው በጭቆና ውስጥም ሆነው የአንፀባራቂ ድል ባለቤት የሆኑ በአገራችን፣ በአፍሪካም ይሁን በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቂት ሴቶች አሉ፡፡ ይህ ግን ሴቶች ካላቸው አጠቃላይ ቁጥር አንፃር ሲታይ ኢምንት በመሆኑ ይህንን ታሪክ ከስር መሰረቱ ለመለወጥ ዛሬም ጥረቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ 
 
በማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ውስጥ በየትኛውም አጋጣሚና ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎ ውጤታማነት ቢመዘን ሴቶች ተግባራትን በተቀናጀና አስተውሎት በተሞላበት መንገድ የመምራት ክህሎታቸው ላቅ ያለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ የመምራት ብቃታቸው ደግሞ የሚጀምረው ከቤታቸው ነው፡፡ ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ቤተሰባቸውን፣ ማህበረሰባቸውንና አገራቸውን ጭምር የመለወጥ ችሎታ አላቸው፡፡ 
 
በአገራችን የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበት የመጣው ከባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወደዚህ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችንም ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ሴቶችን በትምህርት፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ የማበቃት ተግባር እየከወነ ይገኛል፡፡ ሴቶች መብቶቻቸውን ለማስከበር በከፈሉት ክቡር መስዋዕትነት ዛሬ በአገራችን ከህገመንግስት ጀምሮ የተለያዩ ህጎች የሴቶችን መብቶች የሚያረጋግጡ ሆነው እንዲቀረፁ ማድረግ ተችሏል፡፡ 
 
የአገራችን ሴቶች ራሳቸውን በትምህርት በማብቃትና በህገመንግስቱ የተጎናፀፉትን ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ መብት ተጠቅመው ለችግሮቻቸውም መፍትሄ በማስቀመጥ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ በአገራችን በመፈጠሩ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል፡፡
 
በዚህም በርካታ የከተማና የገጠር ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ዜጎችም ጭምር አቅም መሆን የሚያስችላቸውን ሃብት ማካበት ችለዋል፡፡ ከማጀት ወጥተው የማያውቁ በርካታ የአገራችን ሴቶች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በአደባባይ ወጥተው ስለመብቶቻቸው መሞገት ጀምረዋል፡፡ በህዝብ ምክር ቤቶች የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡ ምሁራን ሴቶችም ተበራክተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በአገራችን መፈጠር የቻለው ስርዓታችን ሴቶችን የሚያበረታታና ሴቶች በራሳቸው ጥረት ጎልተው መውጣት የሚችሉበት እድል የህግ ማዕቀፍ ከማስተካከል በተጨማሪ የመንግስት አሰራሮችም ጭምር ሴቶችን የሚያበረታቱ ሆነው በመመቻቸታቸው ነው፡፡ 
 
በአገራችን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በተሰማሩበት የስራ መስክም ውጤታማ ተግባር በመፈፀም በሁሉም ዘንድ የይቻላል መንፈስ እንዲዳብር አቅም መሆን ጀምረዋል፡፡ ነገም ይህን ጥንካሬያቸው አብቦና ጎምርቶ፤ ዛሬም ከማጀት ያልወጣችውን፣ ከጥገኝነት ያልተላቀቀችውንና በትምህርት ወደ ኋላ የቀረችውን እንስት እንድትበረታ በማንቃት ወደ ተሻለ የለውጥ ምዕራፍ መሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ 
 
ከሰሞኑ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ105ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ40ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል፡፡ በአገራችንም ይህ ቀን በተለያዩ ሁነቶች ታጅቦ ያለፈ ሲሆን ሴቶች ተሳትፏቸውን በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባቸው መልዕክት ተላልፏል፡፡
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማርች 8ን በማስመልከት ለሁለተኛ ጊዜ በሴቶች የሚመራ በረራ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ አድርጓል፡፡ የበረራውን ዓላማ አስመልክቶ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክነያት በማድረግ ሴቶችን ማበረታታ ቀጣይነት ላለው እድገት በሚል ሃሳብ በሴቶች የሚመራው በረራ ወደ ኪጋሊ መብረሩ ሴቶች ማንኛውንም ኃላፊነት መወጣት እንደሚችሉና በፆታ የተገደበ የስራ መስክ እንደሌለ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም በዚህ ዘመን የፆታ ልዩነት ሳይሆን ትምህርት ሁሉንም እኩል እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡ 
 
በሌላ በኩል የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን "አጀንዳ 2063: ለፆታ እኩልነት ቃል መግባት" በሚል መሪ ሐሳብ አክብሯል፡፡ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአህጉሩ ሴቶች ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፈትቶ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥና ወደ መሪነት ለማምጣት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው ገልፀዋል ሲል ኢዜአ በድረ ገፁ አስነብቧል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ የሴቶችን መብት ማክበርና እኩል እንዲሆኑ መፍቀድ የአህጉሩን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት፣ የማህበራዊና የባህል ሽግግር ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ሊቀመንበሯ አመላክተዋል፡፡
 
በአዲስ አበባ ለአራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በሀገር አቀፍ የከተሞች ውበት፤ ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አለምአቀፍ የሴቶች ቀንን ምክነያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ በከተማዋ ፅዳትና ውበት ላይ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ አለባቸው፣ ከሴቶች ብዙ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውን፣ ከዛም ማህበረስብና አገር የማበልፀግ ክህሎት አላቸው ይህንን ክህሎታቸውን በሁለንተናዊ መልኩ ተሳትፏቸውን በማጎልበት ወደ ተሻለ የለውጥ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment