EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 29 February 2016

በትላንትናው ስርዓት ላይ የተንጠለጠሉ የትምክህትና ጠባብ ኃይሎች


የህዳሴ ጉዛችን ፈተናዎች ናቸው ብለን ከለየናቸው ችግሮች መካከል ትምክህትና ጠባብነት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በትምክህትና በጠባብ አስተሳሰብ የታወሩ ኃይሎች የግላቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማሳካት የሚሯሯጡ ምንም የህዝብ አጀንዳ የሌላቸው ጸረ- ልማትና ጸረ ሰላም ኃይሎች ናቸው፡፡
የትምክህት ኃይሉ የሚጠቀምበት የመጀመርያውና ላለፉት ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት በስራ ላይ የዋለው ስልት የትላንቷን ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ኢትዮጵያ በእጅጉ የተሻለች እንደሆነች አስመስሎ ማቅረብ ነው፡፡ አንዳንዴ ፍፁም ዴሞክራሲዊ የነበረውን ዘውዳዊ ስርዓትን ያቆነጃጃል፡፡ ከአጼ ሚኒሊክ እስከ አጼ ኃይለስላሴ የነበሩትን ዘውዳዊ አገዛዞች ግፍና በደል ሸፋፍኖ የስልጣኔና እድገት አባቶች አስመስሎ ሊያቀርባቸው ይሞክራል፡፡ ኢትዮጵያ በእነዚህ ግፈኛ ገዥዎች ዘመን በኢኮኖሚያዊ ውድቀት ወደ ፍጹም ድቀት እንዳልተረማመደች የአገሪቱ ዜጎች ለከፋ ሞትና እስራት እንዳልተዳረጉ የማታ ማታ ደግሞ ማንም ሊቆጣጠረው የማይችል የመበታተን አዝማሚያ ተፈጥሮ እንዳልነበር፣ በደፈናው የደርግ፣ የኃይለስላሴ…..ወዘተ መንግስታት የተቀደሱ አስመስሎ ለማቅረብ ጥረት ያደርጋል፡፡ በአንጻሩ አገሪቱን ወደ እድገትና ልማት እንዲሁም ወደ ዴሞክራሲ አዲስ አይነት አንድነት ያመራው የድህረ 1983 ዓም አዲስ ስርዓት አንዳችም የኢትዮጵያዊነት ደብዛ እንደማይታይበት፣ የብሄር፣ ብሄረሰቦች መብት ለማስከበር የተወሰደው እርምጃ ሃገሪቱን ለመበታተን ሲባል የተቀየሰ የጥፋት ውጥን እንደሆነ ለማስመሰል ይዘምታል፡፡ በአጭሩ የትላንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ በጣም የተሻለች እንደሆነች ስለዚህም ደግሞ የዛሬዋ ኢትዮጵያና የምትመራበት ህገ መንግስት ተቀይረው በትላንቷ ኢትዮጵያ መተካት አለባቸው ይላል፡፡ ሞቶ የተቀበረው ስርዓትም ይናፍቃል፡፡


የትምክህት አስተሳሰብ ትላንትን አቆናጅቶ ዛሬን የከፋ አስመስሎ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት የዛሬን መልካም ነገሮች ሁሉ ወደ ጎን በመተው በጀማሪ ዴሞክራሲ እዚህም እዛም የሚፈጸሙትን ጥቃቅን ስህተቶች መንጠላጠያ ያደርጋል፡፡ ዛሬ የመጣውን ትልቅና ህዝቡ የሚጠቀምበትን ለውጥ እየደፈቀ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች መነሻ ያደርጋል፡፡ 

የትምክህት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች በሌሎች ክልሎች አንዲት ትንሽ ችግር ስትፈጠር በዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ መንገድ እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ በፍጥነት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ አጋጣሚ አድርገው ሊጠቀሙበት ይሞክራሉ፡፡ 
በአገራችን በመገንባት ላይ የሚገኘውን ልማታዊና ዴሞክራሲዊ ስርዓት በመፈታተን ላይ የሚገኘው ሌላ አደጋ ጠባብነት ነው፡፡ ጠባብነት በአስተሳሰብ ደረጃ በህዝቦች መካከል ያለውን መሠረታዊ አንድነትና ተመሳሳይነት በመድፈቅ በማንነት ላይ የተመሰረተውን ልዩነት ሕዝቦችን ለማራራቅና ነጣጥሎ ለማናቆር በመጠቀም ላይ የተመሰረተው አስተሳሰብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ብዝኃኑ ሕዝቦች ከቋንቋ፣ ባህል፣ የመኖርያ አከባቢ ልዩነት ባሻገር በብዙ መሠረታዊ ጉዳዮች ተመሳሳይ ነው፡፡

የጠባብነት አዝማሚያ የተጠናወታቸው ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች በህዝቦች መካከል በነበራባዊነት ያለውንና በትግል የተገነባውን አንድነት የሚያጥላሉ ልዩ ልዩ ጠባብና ከፋፋይ አስማሚያዎች ያሳያሉ፡፡ በአንድ በኩል የትምክህት ኃይሉ በሚፈጥራቸው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በራሳቸው የተሳሳተ መንገድ በሚያካሂዱዋቸው ጠባብ ዘመቻዎች በመታገዝ ልማታዊና ዴሞክራሲዊ ስርዓቱን ለማዳከም ይሰራሉ፡፡ 
የጠባብነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ኃይሎች እንደ ትምክህት ኃይሎች ሁሉ ትላንት በተሻረው ስርዓት ላይ የመንጠልጠል ስልት ይከተላሉ፡፡ የትምክህት ኃይሎች የትላንቱን ስርዓት ሲያቆንጃጁ የጠባብነት ኃይሉ ደግሞ ትላንት የተፈጸሙ በደሎችን ሁሉ ዛሬም እየቀጠሉ ያሉ በማስመሰል ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በርግጥ የትምክህት ኃይሉ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በህዝቦች በደል አድርሷል፡፡ ይህ የታሪክ እውነታ ሊካድም ሆነ ሊሸፋፈን አይገባውም፡፡ የሃገራችን ብሔረ- ብሔረሰቦችና ሰፊው የአማራ ህዝብ በትምክህተኛው ስርዓት ብዙ በደሎች የደረሰበት በመሆኑ ይህንን መካድ የበደል ታሪክን መካድ መሆኑ አይቀርም፡፡ የበደል ታሪክን መካድ ደግሞ ከታሪክ አለመማርን የሚያስከትል ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ በደል መፈጸምንም ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ የትላንቱ በደል መካድ የለበትም፡፡ ነገር ግን ትላንት የተፈጸመ በደል የዛሬን እውነታ የሚወክል ሊሆን አይችልም፣ አይገባምም፡፡ የትላንት በደል የሚነሳው ከታሪክ ለመማር እንጂ ከትላንት ተነስቶ አዲሱንና የተለወጠውን እውነት በትናንት መነፀር ለመመልከት ሊሆን አይገባም፡፡ ዛሬ አዲስ ቀን፣ አዲስ ዘመን ነው፡፡ ከትላንቱ በአይነቱ የተለየ በመሆኑም ይህን የተለየ ዘመን በአዲስ መነፀር መመልከት ብቻ ነው ተገቢ የሚነው፡፡
የጠባብነት አስተሳሰብ የተሸከመው ኃይል ግን የትላንቱን በደል መነሻ የሚያደርገው ዛሬም በትላንቱ ቅኝት ለማየትና ለማሳየት ነው፡፡ የብሄር እኩልነት በተከበረበት የሌላ በማስመሰል፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር በፌደራል ደረጃ እኩል የመሳተፍ መብት በተከበረበት በዚህ አዲስ ዘመን እነዚህን መብቶች የሌሉ በማስመሰል የትላንት በደል እየቀጠለ ነው ለማለት ይጥራል፡፡

በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ ኃይሎች የአገራችን ሰላም ለማደፍረስና ፈጣን ዕድገትዋን ለመግታትን ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም፡፡ይሁንና መላው የአገራችን ህዝቦች የእነዚህን ኃይሎች እኩይ ሴራ በሚገባ የሚገነዘቡ በመሆናቸው አምርረው እየታገልዋቸው ይገኛሉ፡፡ ህዝቡ ለልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንጂ ወደ ኃላ ሊመልሱት የሚፈልጉትን እኩይ ዓላማ ያነገቡ ኃይሎች አጀንዳ ለማስፈጸም ጊዜ የለውም፡፡ ህዝብና መንግስት ባደጉት ያለሰለሰ ጥረት የእነዚህን ኃይሎች ሴራ እየተጋከለጠ አጋረችን ሰላምዋ ተጠብቆ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች እንድትቀጥል የቻለችው፡፡ ኢህአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር አገራችንን ሊበትንዋት ዳር ደርሰው የነበሩ የትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብ በመታገል የሀገራችንን ሀገራችን በፈጣን የሕዳሴ ጉዞ እንድትገባ አድርጓል፡፡ የኢህአዴግ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር የሀገራችን ህዳሴ ዕውን ለማድረግ ብቸኛ ዋስትና ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡

(
የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትግላችንና ፈተናዎች ከሚል ሰነድ የተወሰደ)


No comments:

Post a Comment