የአለም
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ የአለማችን ዋናኛ አጀንዳ
ሆኗል፡፡ ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞም በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የድርቅ፣ የጎርፍ፣ የሰደድ እሳትና የመሳሰሉት አደጋዎች
እየተከሰቱ የበርካታ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፤ በአገሮች ኢኮኖሚም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ አገራችንም የዚሁ ችግር ሰለባ ሆናለች፡፡
በአሁኑ ጊዜም የተከሰተው ድርቅ በአለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክኒያት የተከሰተ ነው፡፡
እንደሚታወቀው
አየር እንደ ናይትሮጂን፣ ኦክሲጂን፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ሜቴን፣ ሀይድሮጂን፣ እና ሌሎች የተለያዩ የጋዝ ዓይነቶች ቅይጥ ነው፡፡
ከእነዚህ ጋዞች በተጨማሪ በመጠን በጣም አነስተኛ ቢሆንም በአየር ውስጥ አንዳንድ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮችና ውህዶች እንዲሁም ጥቃቅን
ጠጣር ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በከባቢ አየር የአየር ቅይጥ ውስጥ የሚገኙት እንደ የውሃ ተን፣ ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ሜቴን፣ ናይትረስ
ኦክሳይድና ፍሎራይድ የመሰሉት ጋዞች ሙቀት አምቆ የመያዝ ባህርይ ስላላቸው ሙቀት አማቂ ጋዞች (Green House Gases) በመባል
ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ጋዞች የከባቢ አየር ሙቀትን ከመቀየር አንጻር የተለያየ መጠን፣ ጥንካሬ፣ የቆይታ ጊዜና ጫና የመፍጠር ባህርያትም
አላቸው፡፡ የሙቀት መጨመርና መቀነስ የአየር ግፊት ከፍ እንዲል ስለሚያደርገው የንፋስ አቅጣጫንና የዝናብ ስርጭትን ይወስናል፤ ይህም
የአየር ንብረት ሁኔታ እንደየመስተጋብሩ እንዲወሰን ያደርገዋል፡፡
የአየር
ንብረት ለረጅም ዘመን የዘለቀ አማካይ የአየር ሁኔታን የሚመለከት ሲሆን ይህ በተለያየ መንገድ አልያም ለአየር ንብረት ለውጥ ወሳኝ
ሚና በሚጫወቱት በካይ ጋዞች አማካኝነት የሙቀት መጠን ሲዛነፍና ሲለወጥ የአየር ንብረት ለውጥ ተከሰተ ይባላል፡፡ የአየር ንብረት
ተፈጥሮአዊ በሆነም መንገድ ሊለዋወጥ ይችላል፤ ሲለዋወጥም ቆይቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን አለማችንን እያሳሰበው ያለው በሰው
ሰራሽ መንገድ በከባቢ አየር ውስጥ ያሉት ሙቀት አማቂ ጋዞች ባህርያት በመለወጡ እየተፈጠረ ያለው የአየር ንብረት ለውጥና መዘዙ
ነው፡፡
የዚህም
ዋናው ምክኒያት ያደጉት አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ለመገንባት የተከተሉት የእድገት አማራጭ፣ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኢነርጂ አላቂ
ከሆኑት የካርበን ኬሚካሎች በማመንጨት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡ የፈረጠመ የኢኮኖሚ ጡንቻ ባለቤት የሆኑትና የአለምን ኢኮኖሚ
እያንቀሳቀሱ ያሉት አገራት የድንጋይ ከሰል፣ የተፈጥሮ ነዳጅና ጋዝን በሰፊው በማቃጠል ካርቦን ዳይኦክሳይድ የተሰኘውን ጋዝ ወደ
አየር በመልቀቅ የከባቢ አየር ተፈጥሮአዊ ሂደት እንዲዛባ ምክኒያት ሆነዋል፡፡
የከባቢ አየር የሙቀት መጠን እየጨመረ ለመሄዱ በተለያዩ ጊዜያት
ይፋ የሆኑ የምርምር ውጤቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950 ዓ.ም የአለም አቀፍ ተመራማሪዎች በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘው
የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን መጨመሩን ካሳወቁ በኋላ የከባቢ አየር የጋዞች ይዘት ምጥጥን ላይ ላለፉት 50 ዓመታት በተደረገው ክትትል
የምድር ከባቢ አየር አማካይ ሙቀት በ0 ነጥብ 13 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እየጨመረ በመምጣት ላለፉት መቶ አመታት ከታየው ለውጥ እጥፍ
መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ በይነመንግስታዊ ፓናል (IPCC) በሰው ሰራሽ መንገድ እየጨመረ
ስላለው የአየር ንብረት ለውጥ ትንበያዎችን አድርጓል፡፡ በዚህም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጠን ላይ ተመስርተው የቀረቡት ትንበያዎች
የምድር አማካይ የሙቀት መጠን እስከ ክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ ከአንድ እስከ ሦስት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ጭማሪ እንደሚያሳይና
እየባሰ እንደሚሄድ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የአለማችን የሙቀት መጠን በመጨመሩ የባህር ጠለል ከፍታ በአማካይ
የሁለት ሚሊሜትር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር የዝናብ መጠን በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል፣ በሰሜን አውሮጳና በሰሜንና
መካከለኛው ኤስያ በእጅጉ እየጨመረ መሄዱ በአንጻሩ ከሰሃራ ደቡብ ካለው ቀጠና፣ በሜዲትራንያን ባህር ክልል፣ በደቡብ አፍሪካ፣ ከፊል
ደቡብ ኤስያ የዝናብ መጠን እንዲቀንስ ሆኗል፡፡ ይህም ከ1970ዎቹ ወዲህ በድርቅ የሚጠቁ የአለም አካባቢዎች ቁጥር እንዲጨምርና
በዝናብ መጠን መጨመር የሚደርሰው የጎርፍና የድርቅ ጉዳትም መጠኑ እያደገ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡
የአየር ንብረት መዛባት ከሚያስከትላቸው ክስተቶች ውስጥ ኢልኒኖ እና ላኒና ይጠቀሳሉ፡፡ ኤልኒኖ (El Niño) እና ላኒና (La Niña) ውስብስብ የአየር ፀባይ ክስተቶች ሆነው በኢኳተር አከባቢ ባለው የፓሲፊክ ውቅያኖስ የሙቀት መቀያየር የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ኤልኒኖ ያልተለመደና ከአማካይ በላይ የሙቀት መጨመር ክስተት ሲሆን ላኒና ደግሞ በተቃራኒው ከአማካይ በላይ የቅዝቃዜ ክስተት ነው፡፡ ኢልኒኖና ላኒና በአለማችን በተለያየ ጊዜ ተከስተዋል፤ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅእኖም አሳድረዋል፡፡ ኢልኒኖ በተወሰኑ ዓመታት መካከል የሚፈጠርና በአብዛኛው ከ9 እስከ 18 ወራት ሊቆይ የሚችልና ረጅም ርቀት ሄዶ ተጽእኖ የማሳደር አቅም ያለው ውስብስብ የአየር ፀባይ ክስተት ነው፡፡ ለኢልኒኖ መከሰት የምስራቃዊ ውቅያኖስ መሞቅ አንዱ ሲሆን በዋነኝነት ከውቅያኖስ በታች (200-300ሜ) የሚገኝ የውሃ አካል መሞቅ እንደ መንስኤ ይጠቀሳል፡፡
የኢልኒኖ ክስተት በክረምቱ የኢትዮጵያ ዝናብ
ላይ የነበረው ተጽእኖ ከዚህ እውነታ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች ላይ የተከሰተውን ብንመለከተው በክረምት
ወራት ምዕራባዊ የህንድ ውቅያኖስ በመደበኛ ጊዜ መሞቅ የሚገባውን ያህል ሳይሞቅ ይቀራል፤ አረቢያን ባህርና ሜድትራኒያን ባህር አካባቢም
በተመሳሳይ በመደበኛ ወቅት መሞቅ የነበረበትን ያህል አይሞቅም፡፡ በአጠቃላይ ከእነኚህ ስርዓቶች መዳከም ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ
በተለይም በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ ከነበረው መደበኛ ሁኔታ ጋር ሲነጸጸር በመጠንና በስርጭት ተዳክሞ እንዲታይ አድርጎታል፡፡
ኢልኒኖ የዝናብ ስርጭትንና መጠንን በማዛባት የውሃ እጥረት እንዲከሰት የሚያደርግ በመሆኑ የሰብል ምርትን በእጅጉ በመጉዳት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መናጋት የሚዳርግ ክስተት ነው፡፡ ላኒና በተቃራኒው መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ የዝናብ መጠንን በመጨመር ለጎርፍና መሰል አደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡
ከአዲስ ራዕይ ቅፅ 5 ቁጥር
3 የተወሰደ
No comments:
Post a Comment