EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 7 February 2016

የአለም የአየር ንብረት ለውጥ በአገራችን ያስከተለው ተጽእኖ እና አደጋውን በመከላከል የልማት ስኬቶቻችን ፋይዳ





ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ኢምንት አስተዋፅኦ ያላበረከተች ቢሆንም ለዘመናት የሚታወቀው ተስማሚው የአየር ንብረቷ እየተለዋወጠ፤ የአደጋው ሰለባ እየሆነች መጥታለች፡፡ በኢትዮጵያ ድርቅ በተለያዩ ዓመታት መከሰቱ የሚታወቅ ሲሆን እነኚህ የድርቅ ዓመታት ከዓለም ዓቀፍ ኢልኒኖ ክስተት ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት እንደነበራቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በአገራችን በ1965/66፣ 1977፣ 1986/87፣ 1990/91 እንዲሁም በ2001/02 የተከሰቱ የድርቅ ዓመታት የዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ እነዚህ የድርቅ ዓመታትም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ለህልፈተ ህይወትና ለስደት ዳርጓል፡፡ በተለይ በአገራችን ያለፉት መንግስታት በተከተሉትጭቆና ስርአትና የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ምክንያት በነበረው ስር የሰደደ ድህነትና ችግሩን የመቋቋም ብቃት ባለመገንባቱ በዜጎች ህይወት ላይ አስከፊ ጉዳት ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች በመሪ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ፋናወጊነት  ባካሄዱት እልህ አስጨራሽ ትግል አምባገነናዊውን የደርግ ስርአት በማስወገድ ለዘመናት አላንቀሳቅስ ብሎ ቀፍድዶ ይዟቸው የነበረውን ድህነትን በማሸነፍ  ሌላ እልህ አስጨራሽ ትግል ጀምረው በስኬት ጎዳና ወደፊት በመራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ ሂደትም አለምን እያመሰ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ ጊዜያት የድርቅ ችግር በማስከተል ፈተና እየሆነ ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ ሀገር ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ በኢልኒኖ ክስተት ምክንያት የድርቅና የጎርፍ ችግሮች በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ ቢሆንም በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ችግሩ የአለምአቀፍ ማህበረሰብ እገዛ እንደሚያስፈልገው ጭምር በግልፅ በማሳየት በሰው ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ተችሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገራችን የተከሰተው ድርቅም በተፈጠረው የኤልኒኖ ክስተት ምክኒያት 2007 . በጋ ላይ ተጽእኖው መታየት ከጀመረ ወዲህ ከመጋቢት እስከ ግንቦት መዝነብ የነበረበት የበልግ ዝናብ ሳይዘንብ ቀርቷል፡፡ በዚህ ሳይገታ የዋናው ክረምት የዝናብ እጥረትና መቆራረጥ ችግር አጋጥሟል፡፡ አንዳንድ የአገሪቱ ከፍሎችም ከፍተኛ የውሃና የእንስሳት መኖ እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ወቅታዊ ክስተት 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለምግብ እጥረት ተዳርጓል፡፡ መንግስትም የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለማድረግ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ጭምር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
 
በአሁኑ ጊዜ በአለም ደረጃ የተፈጠረው የኢሊኒኖ ክስተት በቀደሙት አመታት ከተከሰቱት ሁሉ የባሰ እንደሆነም እየተነገረለት ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአገራችን የተከሰተው የድርቅ ችግርም ቀደም ባሉት አመታት ተከስተው በከፍተኛ ደረጃ የሰው ህይወት ከቀጠፉት የድርቅ ጊዜያት ያልተናነሰ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በድርጅታችን መሪነትና በመላ ህዝባችን ርብርብ ባለፉት አመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶቻችን ድርቁ ሊያስከትል የሚችለውን የከፋ አደጋ በመከላከልና በመቋቋም ላይ ናቸው፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የተከሰተውን የድርቅ ችግር ተከትሎ ባለፉት አመታት የተመዘገበውን የልማት ስኬት ጥላሸት የሚቀቡና የወደፊቱን የጸረ ድህነት ትግላችንን የሚያደበዝዙ እንዲሁም የድርቁ ችግር የሚያስከትለውን አደጋ ለመመከት የሚደረጉ ጥረቶችን ያላገናዘቡ የተሳሳቱ አመለካከቶችና አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች ሲራመዱ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ በአንድ በኩል የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው አገራችንን የማተራመስ  አላማ ያላቸው የጸረ ሰላምና ጽንፈኛ ኃይሎች የድርቁን ችግር የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ የፈጠራ ወሬዎችንና አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ የማሰራጨት ስራዎችን አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን የድርጅታችንን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ለማጥላላት ተግቶ የሚንቀሳቀሰው የኒዮሊበራል ኃይል ሚዲያውን በመጠቀም ችግሩን ማራገብ ጀምሯል፡፡ በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ ካለማግኘት ጋር ተያይዞ በሚነዙ አሉባልታዎችና የፈጠራ ወሬዎች የመደናገር ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ ስለሆነም በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ለመያዝ የድርቁን ምንጭና አደጋውን ለመከላከልና ለመመከት  በአገራችን የተመዘገበው የልማት ስኬት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ማጤን ይጠይቃል፡፡

በአገራችን በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ድርቅ ቀደም ሲል እንደተገለጸው መንስኤውና ምንጩ በአለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተው የኢልኒኖ ችግር ነው፡፡ ድርቁ ኢልኒኖ በመከሰቱ ምክንያት በአገራችን በዝናብ እጥረትና የዝናብ መዛባት በማስከተሉ   ከአገራችን ቁጥጥር ውጭ በሆነ የአለም አቀፍ ችግርተፈጠረ መሆኑ ጸሃይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አገራችን በተመሳሳይ መንስኤ ቀደም ሲል ጀምሮ በተወሰኑ አመታት ወቅቱን እየጠበቀ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት የበርካታ ዜጎቿ ህይወት ጭምር እንደ ቅጠል ረግፈውባታል፡፡ አሁን በአገራችን የተፈጠረው የድርቅ ችግር ከአደጋው ስፋት አኳያ ሲታይ በአገራችን ቀደም ሲል ከተከሰቱት የድርቅ ችግሮች የሚተናነስ አይደለም፡፡ ካለፉት የሚለየው አደጋውን ለመከላከል ባለፉት አመታት የፈጠርነው አቅምና ድርቁ ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣኑ ልማታችንን የሚያስቀጥል ምርት የሚጠበቅ መሆኑ ነው፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ የተከሰተው ድርቅ መንስኤ ከአገራችን ቁጥጥር ውጭ የሆነ የአለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑና ይህንኑ ችግር ለመከላከል ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የአረንጓዴ ልማት የእድገት አማራጭን በመከተል አብነታዊ ሚና እየተጫወትንበት በምንገኝበትና አገራችን የአፍሪካ ወኪል ጭምር በመሆን አለም አቀፋዊ መፍትሄ እንዲገኝ ትግል እያደረገች ባለችበት ሁኔታ የተከሰተ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

የድርቁን መንስኤና ስፋቱን በዚህ መልኩ ከተመለከትን ቀጥሎ የሚመጣው ጉዳይ ፈጣኑ ልማታችን አደጋውን በመከላከል ምን አስተዋጽኦ አበረከተ? ባለፉት አመታት ተከታታይና ፈጣን ልማት ባናረጋግጥ ኖሮ የድርቁ አደጋ ምን ደረጃ ይደርስ ነበር? የሚለውን በዝርዝርመመልከት ጉዳይ ነው፡፡
 
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የአሁን የድርቅ ችግር ሊያስከትለው የሚችለው አደጋ ቀደም ሲል ተከስተው የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወት ከቀጠፉ አስከፊ ድርቆች የተናነሰ አይደለም፡፡  ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደዚህ አይነት ችግር ሲከሰት መፍትሄው በውጭ እርዳታ ላይ የተመሰረተና የሚፈለገው እርዳታ በሚፈለገው ጊዜ እና መጠን ባልተገኘበት ሁኔታ ሁሉ ዜጎች በርኃብና በበሽታ እንደ ቅጠል መርገፍ እጣ ፋንታቸው ነበር፡፡ አሁን የመፍትሄው አቅጣጫ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ የቅድሚያ መፍትሄው የአገራችን አቅም ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ መንግስት በጀት መድቦ የድርቅ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የምግብ፣ የውኃ፣ የእንሰሳት መኖና የመሳሰሉትን ለድርቁ ተጠቂዎች በስፋት በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በመሆኑ በእስካሁኑ ሂደት አደጋው በተለይ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በማድረግ ስኬታማ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ኢኮኖሚያችንን በፍጥነት ማሳደግ ባንችል ኖሮ የተከሰተው ድርቅ በሰውና በእንስሳት ላይ የመጀመሪያ ምዕራፍ እገዛ ማድረግ ሳይቻል የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችል እንደነበረ መገመት አያዳግትም፡፡ ይህም በመሆኑ የድርቅ አደጋውን ለመከላከል ዋነኛ ዋስትናው ልማታችን ሆኖ የውጭ እርዳታ ደጋፊ ሚና ሊጫወት በሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ከዚህ ደረጃ ላይ ያደረሱንን ስኬቶች አደጋውን ከመከላከል ጋር በማያያዝ መመልከቱ ይህንኑ እውነታ ይበልጥ ለመገንዘብ ስለሚረዳ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንደሚከተለው ተዳሷል፡፡

ኢህአዴግና እሱ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በሀገራችን ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን አስከፊ ድህነት ለማስወገድ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርፆ  ተግባራዊ በማደረጉ  ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡  ባለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ፈጣንና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች በግምባር ቀደምትነት ለማሳካት ችለናል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዘገብ ላይ ካሉ ሀገራት መካከል በመጀመሪያው ረድፍ ተሰልፋለች፡፡
 
አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመከተል የአየር መዛባትን ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በግብርናው ዘርፍ በኩል እየተተገበሩ ያሉ ስራዎች የተጠናከረ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን በመተግበር ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ በስፋት ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ይህ የስነ አካላዊና የስነ ህይወታዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር መሸርሸርን ከመቀነስ ባሻገር የደን ሽፋንን በመጨመር የሚገኘው እርጥበት ወደ መሬት እንዲሰርግ ማድረግና የወንዞችንና ምንጮችን የማጎልበት አቅም እንዲጨምር ማድረግ በመቻሉ ከተፋሰሱ ግርጌ ያሉ ማሳዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አስችሏል፡፡ በዚህም እስከ 2007ዓም መጨረሻ ባለው ጊዜ 3ሚሊዮን ሄክታር በላይ በመስኖ በማልማት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ  አርሶ አደር የቤተሰብ ኃላፊዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ድርጅታችን ሁሉም ዜጋ ከልማቱ  ፍትሓዊ ተጠቃሚ መሆን አለበት በሚል ማዕቀፍ  የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በተመለከተ በሀገር ደረጃና በቤተሰብ ደረጃ ተለይቶ የሚታይ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ አንድ ሀገር በምግብ ሰብል ራሱን ቻለ የሚባለው በሀገር ደረጃ የተመረተው አጠቃላይ ምርት ለጠቅላላው የህዝብ ቁጥር ሲካፋል የሚሰጠው አማካይ ውጤት በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት አንድ ሰው በዓመት ሊያገኘው የሚገባው የካሎሪ መጠን ሲያሟላ ወይም ከዛ በላይ ሲሆን ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የምርቱ መጠን ከቤተሰብ ቤተሰብ ልዩነት ስለሚኖረው በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ተረጋግጧል ለማለት አያስችልም፡፡ በሌላ በኩል በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ተረጋግጧል የሚባለው የቤተሰቡ ገቢ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አባል ለምግብ የሚያስፈልጉት ነገሮች በሙሉ ራሱ አምርቶ ወይም ምግብ ለመግዛት የሚያስችል አቅም ሲኖረው ነው፡፡
ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ሲታይም በኢህአዴግ መሪነትን በመላው ህዝባችን ጥረት ባለፉት አመታት በተደረገው ርብርብ አገራችን በምግብ ሰብል ራሷን ያስቻለ አመታዊ ምርት የማምረት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ እዚህ ደረጃ መድረስ የተቻለው በትክክለኛ ፖሊሲ በመመራት ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ በተደረገው ዘርፈ ብዙ ርብርብ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚሁ ርብርብ 1983 . በዋና ዋና ሰብሎች 52 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ የነበረውን ዓመታዊ የምርት መጠን 2007 . 270 ሚሊዮን ኩንታል በማድረስ ነው በአገር ደረጃ በምግብ ሰብል እራሳችንን የቻልነው።
የልማት ፖሊሲዎቻችን ዋነኛ ማጠንጠኛና ግብም ድህነትን ማስወገድ በመሆኑ እስካሁን በተገኘው ውጤት ተከታታይና ፈጣን እድገት ከመመዝገቡ ባሻገር ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ ባለፉት አመታት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ለዘመናት የልማት ተቋዳሽ ያልነበረውን ህዝብ የመሰረተ ልማትና ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ድህነትን በመቀነስም ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ 1988 . በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 47 ነጥብ 5 በመቶው በድህነት ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን ባለፉት አመታት ባደረግነው ርብርብ ሀገራዊ የድህነት መጠኑ 2007 . ወደ 22 ነጥብ 2 በመቶ ወርዷል፡፡ ድህነት በመቀነስ አመርቂ ውጤት በማስመዝገባችንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከድህነት አረንቋ ወጥተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ያስመዘገበችው ውጤት ከተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) አለም አቀፍ እውቅና ጭምር አስገኝቶላታል፡፡ 
ይህ ከፍተኛ ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች 22 ነጥብ2 በመቶ የሚሆኑት ከድህነት አልተላቀቁም፡፡ ባለፉት አመታት በአጠቃላይ በልማት ስራዎቻችንና በተለይ ደግሞ በድሃ ተኮር የልማት ተግባሮች አማካኝነት በርካታ ቤተሰቦች ከድህነት በመውጣት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የቻሉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም የምግብ ዋስትና ያላረጋገጡ በርካታ ቤተሰቦች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ 
ባለፉት አመታት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ በአጠቃላይ በሚመጣ ልማት ብቻ ሳይወሰን የምግብ ዋስትና ያላረጋገጡ ቤተሰቦች ላይ ያተኮሩ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሥር ለሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር የተጋለጡና በገጠር የሚኖሩ ሕዝቦች ለዘለቄታው ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ መንግስት 1995. ጀምሮ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂና ፕሮግራም ቀርጾ ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አጋዥ የሆኑ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ የቤተሰብ ጥሪት ግንባታ ፕሮግራም፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሠፈራ ፕሮግራም እና የማህበረሰብ ደጋፊ ልማት መርሀ ግብሮች  ሲተገበሩ ቆተዋል፡፡ በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብርምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር የቤተሰብ ጥሪት እንዳይሟጠጥ በመከላከል የምግብ ክፍተቱን መሙላትና የህብረተሰብ ጥሪትመገንባት ዓላማን አንግቦ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ ቤተሰቦች የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ በቀጣይም ፕሮግራሞቹ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

በሀገራችን በተደጋጋሚ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ የተወሰኑ አካባቢዎች በምግብ ዋስትና ችግር ተጠቂ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ምግብ ዋስትና ችግር መከሰት ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሽራተት እና የእርሻ መሬት ጥበት በግንባር ቀደም ምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተፈጥሮና ሰው-ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ድህነት ስር ወድቀው የምግብ ፍጆታቸውን በራሳቸው አቅም መሸፈን ያልቻሉ ማህበረሰቦች በሁለት መልክ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ለአንድ ዓመትና ከአንድ ዓመት በዘለለ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆኑ፣ ሌሎቹ በድንገተኛ አደጋዎች ተጎድተው ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ከጊዜያዊ ክስተት ጋር እስኪያላምዱ እና ጊዜያዊ ችግሩን መቋቋም የሚያስችል አቅም እስኪፈጥሩ ድረስ ብቻ  የአጭር ጊዜ ዕርዳታን  የሚሹ ናቸው።

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ምግብ ዋስትና ዘርፍ የገነባውን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ሥርዓት አቅም ተጠቅሞ ለተለያዩ አደጋዎች በተለይ ለድርቅ አደጋ የተጋለጡ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል፣ እየታደገም ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ በተለያዩ ጊዜያት ለተከሰተው የድርቅ አደጋ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት መቋቋም ተችሏል፡፡ እንዲሁም በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ያጋጠመውን የምግብ እጥረትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመቅረፍ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ተደራሽነቱን አረጋግጧል፡፡ ውጤታማ ሥራዎችንም ሠርቷል፡፡ የቅድሚያ ማጠንቀቂያና ምላሽ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን እያጎለበተ መጥቷል፡፡
 
በዚህም ባለፉት ዓመታት  በአማካይ 5.6 ሚሊዮን  ለሚሆኑ ተረጂዎች ተገቢውን እርዳታ በማቅረብ ሕይወታቸውን መታደግ ተችሏል፡፡ በተለያዩ መንገዶች እርምጃ በመወሰዳቸው የተረጂዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ለዚህም ድርቅንና ሌሎችን አደጋዎች ተከትሎ የሚኖረውን የተረጂዎች ቁጥር ሳይጨምር 1994 ወደ 14 ሚሊዮን የነበረው ቋሚ የተረጂዎች ቁጥር 2007 . ወደ 2.9 ሚሊዮን ማውረድ ተችሏል፡፡ አደጋ ከደረሰ በኋላ ምላሽ በመስጠት ሥራ መጠመድ ብቻ ሳይሆን አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድመው መንስኤዎቹ ላይ በማነጣጠር ለአደጋ ቅነሳ ሥራ ተኩረት ሰጥቶ የሚሠራ አዲሱ ብሔራዊ የአደጋ ክስተት ሥራ አመራር ፖሊሲ ተቀርፆም ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

በአጠቃላይ ፈጣኑ ልማታችን መሰረተ ሰፊና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሰርቶ መለወጥ የሚችልና ጥሪት የሚፈጥር ዜጋ በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ በአገራችን እየተፋጠነ ያለው ልማት የስራ እድል በመፍጠርና ገቢን በማሳደግ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ከምግብ ዋስትና እጦት ችግር እንዲላቀቁ በማስቻል የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲያድግ አድርጓል፡፡
 
በአጠቃላይ የአገራችን የልማት ስኬት በድርቅም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች በሚፈጠር ረሃብ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ከውጭ እርዳታ ውጭ አማራጭ ያልነበረበትን ሁኔታ ቀይሮ አገራዊ ዋስትና እንዲኖር አስችሏል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከችግሩ ስፋት አኳያ የውጭ እርዳታ የደጋፊ ሚና ቢኖረውም በምንም መስፈርት የልማታችንን ስኬት ሊያጣጥለው አይችልም፡፡ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ድርቅ ልዩ ትኩረት የሚሻና የሁላችንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ 
ምንጭ፡-አዲስ ራዕይ ቅፅ 5 ቁጥር 3 

No comments:

Post a Comment