በፈድሉ ጀማል
ሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ እያደረገችው
ያለው የተፋሰስ ልማት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ለስራው የነበረው ዝቅተኛ የህብረተሰቡ ወይም ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የአርሶ አደሩ
ተቀባይነት አሁን ላይ በእጅጉ ጨምሮ እንዲሁም በሂደት በተግባር ምዕራፍ በተካበቱ ልምዶች በመታገዝ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በርካታ
ጠቀሜታዎችን እያስገኙልን ይገኛሉ፡፡ ስራው ያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ለአብዛኛዎቻችን በግልጽ እስከመታየት የደረሱና ምናልባትም
ቀደም ሲል የምናውቃቸው የተራቆቱ አካባቢዎች ጭምር ለምተውና አረንጓዴ ለብሰው በማየት የውጤቱ መስካሪዎች እንድንሆን
እስከማስቻል ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህ እውነታ በርካታ ከተሜዎችን የሚገልፅ ቢሆንም በተፋሰስ ልማቱ የተሰሩ በርካታ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ያስገኙት ጠቀሜታ በአርሶ
አደሩ የሚገለፁት ከዚህ በሰፋ መልኩ ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለው በተግባር ካገኛቸው የራሱ የቀጥታ ተጠቃሚነት ጭምር
የሚለካቸው በመሆኑ ነው፡፡
በየዓመቱ በተፋሰስ ልማቱ በአርሶ አደሩ የሚሰሩ የአፈርና
ውሃ ትበቃ ስራዎች የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ እንዲሁም የአፈር እርጥበትና
ውሃ መጠንን ከማሳደግ አንፃር ያላቸውን ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ ከመስማትና ከማየት ባለፈ በተግባርም ጭምር እያረጋገጥ እንገኛለን፡፡
የተፋሰስ ልማቱ የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ከዚህ የሰፋና ከበርካታ ጉዳዮች ጭምር ሊያያዝ የሚችል እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን
በተደጋጋሚ የሚገልጹት እውነታ ነው፡፡ ለአብነትም የአለም አቀፉን የአየር ንብረት መዛባት ተከትሎ ሀገራት እያጋጠማቸው ያለውን
ያልተጠበቀ የአየር ንብረት መዛባት ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንኳባይቻል ተፅዕኖውን መቀነስ እንደሚቻል ከሚነገሩ ጠቀሜታዎቹ መካከል
ሚጠቀስ ነው፡፡
በተመሳሳይ ከላይ ከተጠቀሱት ጠቀሜታዎች በተጨማሪ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘርፉ የተሰራ ምርምርን መሰረት አድርጎ እንደዘገበው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስፋት ተግባራዊ
ማድረግ ሌላም ጠቀሜታ ለሀገራችን እያስገኘ ለመሆኑ ያሳየናል፡፡ የጎንደር
የአፈር ምርምር ቤተ ሙከራ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ወደ ጣና ሃይቅ ይገባ የነበረውን የአፈር
ደለልና የጎጂ ንጥረ ነገር መጠን በ58 በመቶ መቀነሱን አረጋግጧል፡፡ ይህን ማረጋገጥ የቻለው ባለፉት 4 ተከታታይ ዓመታት
ባካሄደው ምርመራ ነው፡፡ በጎርፍ ታጥቦ ወደ ሃይቁ ይገባ የነበረውን ፎስፈረስ የተባለውን ጎጂ ንጥረ ነገር በግማሽ መቀነስ የተቻለ
ሲሆን ፎስፈረስ የይቁን ብዝሃ ህይወት አደጋ ላይ የሚጥልና የዓሳ ሃብቱን ጨምሮ ሌሎች በሀይቁ ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ እፅዋትን
በመጉዳት ዝርያቸው እንዲመናመን የሚያደርግ ሲሆን ባለፉት ዓመታት የተሰሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የሀይቁን ብዝሃ ህይወት
ከመሰል አደጋዎች መታደግ አስችለዋል፡፡
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው አርሶ አደሩ በማሳው
የሚጠቀማቸው ዩሪያና ዳፕ የተሰኙ የአፈር ማዳበሪያዎች በቀላሉ በጎርፍ ታጥበው እንዳይሄዱ በማስቻሉ ምርታማነትን ከማሳደጉ
በተጨማሪ ወደ ሀይቁ ሊገባ የሚችለውን ፎስፈረስ በከፍተኛ መጠን መቀነስ አስችሏል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በአንድ ሊትር የጎርፍ
ውሃ ውስጥ ይገኝ የነበረው አንድ ሚሊዮን የፎስፈረስ ቅንጣት አሁን ላይ የተሰራውን የተፋሰስ ልማት ተከትሎ መጠኑ በ58 በመቶ
ሊቀንስ ችሏል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት በዚሁ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሀይቁ
የሚገባውን የፎስፈረስ መጠን ወደ ዜሮ በማድረስ ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚቻል አመላካች ነው፡፡
በተመሳሳይ በጎርፍ አማካኝነት ከማሳዎች ታጥቦ ወደ ሀይቁ የሚገባውን ደለል አፈር በከፍተኛ መጠን መቀነስ አስችሏል፡፡
በተካሄደው ጥናት መሰረት በ2004 በአንድ ሊትር ውሃ ውስጥ በአማካይ የተመዘገበው የደለል አፈር መጠን 15 ግራም የነበረ
ሲሆን በ2006 መጠኑ ወደ ሦስት ግራም ቀንሷል፡፡
በአጠቃላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው የአካባቢ መራቆትን
ከመከላከል፣ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የብዝሃ ህይወትን ህልውና ጠብቆ በማቆየት ተጨማሪ አቅም
የሚፈጥር ስለመሆኑ ጥናቱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች አሁን ላይ በስፋት ተግባራዊ
በመሆን ላይ በሚገኘው የተፋሰስ ልማት በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ከእርሻ ማሳዎችና ከተዳፋት መሬቶች በጎርፍ
አማካኝነት በከፍተኛ መጠን ይባክን የነበረውን አፈርና ውሃ ማስቀረት ተችሏል፡፡ በዚህም የአፈር ለምነትንና እርጥበትን በማሳደግ
የግብርና ምርታማነትንና የመሬቱን የእፅዋት ሽፋን በተመሳሳይ ማሳደግ አስችሏል፡፡ በሀገራችን የተፋሰስ ልማቱ እዚህ አመርቂ ሊባል
በሚችል ደረጃ ሊደርስ የቻለው አስቀድሞ ይህን እውን ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ አርሶ አደሩን
በማወያየት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራን ከመስራት አንስቶ በርካታ ተግባራትን በማከናወን በሂደት የሚገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋትና
የተፋሰስ ልማቱ በራሱ ያበረከታቸው ጠቀሜታዎች በግልጽ እየታዩ በመምጣታቸው በርካታ ሚሊዮን አርሶ አደሮች በየዓመቱ ተሳትፎ
በማድረግ በበርካታ ቢሊዮን ብሮች የሚተመን የጉልበት ዋጋ በራስ
ተነሳሽነት ማበርከት በመቻላቸውና መንግስትም ይህን የአርሶ አደር ተሳትፎ በቂ ሊባል በሚያችስል የባለሙያና የአንዳንድ ግብዓቶች
ድጋፍ በማድረግ በተቀናጀ የጋራ ጥረት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment