“የህዳሴ ጉዟችንና ውጪያዊ ሁኔታዎች” በሚል ርእስ በ2003 (ገፅ15)
የወጣው የኢህአዴግ ልሳን አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና በግልፅ አብራርቷል፡፡
«አፍሪካ በኢንዱስትሪ ያልበለፀገች ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የካርቦን
ልቀቷም በጣም ትንሽ ነው፡፡ ልቀቱም በአብዛኛው እንጨት በማቃጠል የሚፈፀም ነው፡፡ እንጨት ሲቃጠል ካርቦን ዳይኦክሳይድ ከመልቀቁም
ባሻገር ካርቦን ዳይኦክሳይድን ከአየር የሚመጡና ክምችቱን የሚቀንሱ እፅዋት እየተቆረጡ ሲሄዱ ካርቦኑን የሚመጥ ሃይል እየቀነሰ ይመጣል፡፡
ስለሆነም አፍሪካ በዚህ ረገድ ያላት ድርሻ በደን ማቃጠል ላይ የታጠረና ከቁጥር የማይገባ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአየር ንብረት
ለውጡ ገና በሰፊው ከመጀመሩ በፊት ክፉኛ እያተራመሰ ያለው አፍሪካን ሲሆን ለወደፊቱም አፍሪካን በይበልጥ ይጎዳታል ተብሎ ይገመታል፡፡
አፍሪካ በለውጡ ይበልጥ ተጎጂ የሆነችው ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ
አንፃር የአየር ንብረቷ ተጋላጭ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ለውጡን ለመቋቋም ያላት ገንዘብና ቴክኖሎጂ ውሱን ስለሆነ በድህነቷ
ምክንያት ይበልጥ ተጠቂ ነች፡፡ እድገቷን በአዲስ አማራጭ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለመገንባት ያላት አቅምም ከበለፀጉት አገሮች በእጅጉ ያነሰ
ነው፡፡» በሚል አስቀምጦታል፡፡
የወደፊቱን እየመዘነ ሁሌም አገራችን
ተሽላና ልቃ እንድትገኝ ከህዝባችን ጋር እየተጋ ያለው ኢህአዴግ የሚከተላቸው የልማት ፖሊሲዎች ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለነገም ዋስትና
የሚሰጡ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን እየተከተልን ያለነው፡፡
ቀደም ሲል የጠቀስነው የድርጅታችን
ሰነድ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን አስመልክቶ የሚከተለውን አስፍሯል፡፡
‹‹…በካርቦንና አላቂ የሃይል
ምንጮች ላይ የተመሰረተ እድገት በአየር ንብረት ለውጥ መስክ ከሚያስከትለው ችግር ባሻገር ሄዶ ሄዶ ተንገራግጮ መቆሙ የማይቀር ስለሆነ
የአገራችን የልማት አቅጣጫ በአዲስና ታዳሽ ኃይል ምንጭ ላይ መመስረት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አገራችን ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል እምቅ ሃብት ያላትና የካርቦን ነክ የኃይል ምንጮች
ግን ትርጉም ባለው መጠን የሌላት መሆኑ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን እንድንከተል የሚያደርገን ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡…››
በዚህ መሰረት የልማት እቅዳችን
እኤአ በ2025 ኢትዮጵያ ትርፍ ካርቦን ዳይኦክሳይድ የማትለቅበት (Zero net emission) ደረጃ ላይ እንዲደርስ ግብ አስቀምጠን
እየሰራን እንገኛለን፡፡ ግቡ በየትኛውም አጋጣሚና ሁኔታ ሊከሰትና የአየር ንብረት ለውጥ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ
የሚያስችል ይዘትም እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ የዜሮ ልቀት ግቡም በሶስት ዋና ዋና ስትራተጂዎች ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን በግልጽ
ተቀምጧል፡፡ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ኃይልን ከታዳሽ ምንጮች በሰፊው በማምረት ለራሳችን ከሚያስፈልገን በላይ የሆነውን ለጎረቤት
አገሮች በመሸጥ የዳበረ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረን የሚያደርግ ነው፡፡ አገራችን ያላትን ሰፊ የሃይድሮ ፖወር እምቅ አቅም በመጠቀም
የኤሌክትሪክ ኃይልን ከውሃ ሃብት ለማመንጨት ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመሯ የሚታወቅ ነው፡፡ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የግልገል
ጊቤ ሶስትና በግንባታ ላይ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ከዚህ በፊት ተገንብተው አግልጋሎት እየሰጡ ያሉና በመገንባታ
ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ስናይ ወንዞቻችንን ለኤሌክትሪክ ኃይል ጥቅም ለማዋል በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተረባረብን ለመሆናችን
ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከነፋስ፣ ከጂኦተርማል፣ ከስኳር ተረፈ ምርትና በትንሹም ከጸሓይ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት እየሰራን
እንገኛለን፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለባቡር ትራንስፖርት ጭምር የምንጠቀምበት ስልት ቀይሰን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ በኤሌከትሪክ
የሚሰራው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የዚሁ ስልት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ሁለተኛው ስትራቴጂ ነዳጅን ከእጽዋት
ማምረትን የሚመለከት ሲሆን ከሸንኮራ አገዳ ኤታኖልን በማምረት፤ ቤንዚንን በከፊል መተካትና እንደ ጃትሮፋ ካሉ ምርቶች ናፍታን በከፊል
የሚተካ ምርት የማምረት ቴክኖሎጂዎች የመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ ይህ
የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ በእንጭጩ ያለ ቢሆንም በቀጣይ በስፋት ለመስራት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እያደረግን እንደሆነ ግን እሙን
ነው፡፡
ካርቦንን ከአየር የመምጠጥ አቅማችንን
በከፍተኛ መጠን መጨመር ሶስተኛው ስትራቴጂ ነው፡፡ ምንም እንኳ የኢነርጂ
ምንጫችን በሂደት ሙሉ በሙሉ ከታዳሽ ምንጮቻችን እንደሚሆን ብናስቀምጥም እስከዚያው ድረስ እንደ አቅማችን አላቂ ምንጮችን መጠቀማችን
የማይቀር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለወትሮም ቢሆን በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ከሰል ያሉ ምርቶች በተወሰነ ደረጃ መጠቀማችን አይቀርም፡፡
ስለሆነም ልቀታችንን ዜሮ ለማድረስ የለቀቅነውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ከአየር መልሰን መምጠጥ አለብን፡፡ የደን ተከላን በማስፋፋትና
በመንከባከብ ካርቦንን በሰፊው የሚመጥ አቅም የመፍጠር አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራችንን በማጠናከር እጅግ ተመናምኖ
የነበረው የደን ሽፋናችንን ለመመለስ ባደረግነው ርብርብ አመርቂ ወጤቶች አስመዝግበናል፡፡ በዚህ ረገድ በገጠር የሚኖረው ህዝባችን እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ በተደራዳሪነት
ከመቅረብ ባለፈ የራስዋን የቤት ስራ በመስራትም ለሌሎች ላደጉትና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት አርአያ መሆን የቻለች ሀገር ናት፡፡
ለዚህ ዋነኛው ማሳያ ደግሞ በ2011 ደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ላይ ይፋ ያደረገችዉ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ
ኢኮኖሚ ስልትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ ስልት አላማ ያደረገው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ፈጣንና ተከታታይ በመሆኑ ይህ እድገት
በአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ እንዳይጓተት ለማድረግና ኢኮኖሚው የሚኖረውን የልቀት መጠን መቀነስ በማስቻል በ2017 ዓ/ም መካከለኛ
ገቢ ካላቸዉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ ነው፡፡ ይህንን ስልት በመተግበርም በ2030 የህዝብ ብዛቷ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሆኖ መካከለኛ
ገቢ ያላት ሀገር ሆና የልቀት መጠኗ ግን ከ2010 ማለትም ከ150 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንዳይበልጥ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
ሀገራችን ስልቱን መተግበር ከጀመረች 4ኛ ዓመቷን የያዘች የሲሆን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ 2030 ባለዉ ጊዜ ውስጥ
64 በመቶ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችላትን ሰነድ አስገብታለች፡፡ ይህም በማደግ ላይ ካሉ አገሮች መካከል የመጀመሪያዋ
ያደርጋታል፡፡
በአጠቃላይ ሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት
በተግባር በማሳየቷ በአርአያነት ተጠቃሽ ሆናለች፡፡ በአለም አቀፍ
ደረጃም ያላሰለሰ ትግል በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ ያበረከተው አስተዋጽኦ በአለም ደረጃ እውቅና የተቸረውና ታሪክ ሲያስታውሰው
የሚኖረው አኩሪ ተግባር ነው፡፡
ምንጭ፡-አዲስ ራዕይ ቅፅ 5 ቁጥር 3
No comments:
Post a Comment