EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 19 February 2016

የሰማዕታትን አደራ እያሰብን ቃላችንን እናድስ




የማነ ገብረስላሴ
የካቲት 11 የትግራይ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሓት እየተመራ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የነበረውን አስከፊ የጭቆና ስርዓት ለማስወገድ ትግል የጀመረበት ቀን ነች፡፡ በዚህች ቀን 11 ታጋዮች በደደቢት በረሃ የመጀመርያውን የትግል ችቦ ለኮሱ፡፡ ጥቂት ታጋዮች ሲጀምሩ ከጥቂት ኋላ ቀር መሳርያዎች በስተቀር የታጠቁት ትጥቅም ሆነ የወሰዱት ወታደራዊ ስልጠና አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ መሳሪያ እንዴት እንደሚተኮስ እንኳን በቅጡ የሚያውቁ አልነበሩም፡፡ ስንቃቸው ዓላማና የህዝብ ፍቅር ብቻ ነበር፡፡ ትክክለኛ ህዝባዊ መስመር አንግበው ለበርካቶች የማይወጣ የሚመስለውን ተራራ ከህዝብ ጋር ሆነው ሊወጡት ወደ በረሃ አመሩ፡፡ የትግራይ ህዝብም አላሳፈራቸውም፣ የሚመራው የተደራጀ ኃይል ማጣቱ እንጂ ልቡ ትግል ካሰበ ቆይቷልና፡፡ ከጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ ብሎም እጅጉን ያስመረረውን ድህነት ለማስወገድ ጨቋኙን ስርዓት ማስወገድ ግድ የሚል ነበርና የህወሓትን ትግል መጀመር ህዝቡ በደስታ ነበር የተቀበለው፡፡
ህወሓት ትግል ከጀመረ በኋላ በከተማና በገጠር ህዝብን የማደራጀት ስራዎችን ማከናወን ጀመረ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህዝቡ ድጋፍ በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ መጣ፡፡ የትግራይ ህዝብ ለህወሓት ድጋፉን የሰጠው በወቅቱ በአከባቢው የሚንቀሳስ ድርጅት እርሱ ብቻ ስለነበረ አልነበረም፤ ይልቁንስ የህዝብን ዓላማ ከዳር ሊያደርስ የሚችል ትክክለኛ መስመር ያነገበው ህወሓት ብቻ ስለነበር እንጂ፡፡ ለዚህም ነው እንደ ኢድዩ፣ ኢህአፓ፣ ማሕበር ገድሊ ትግራይና ሌሎች ድርጅቶች ሲከስሙ ህወሓት ከሌሎች ህዝባዊ ደርጅቶች ጋር በመሆን የደርግ ስርዓት ግብዓተ መሬት እንዲፈጸም ያደረገው፡፡



የህወሓት የድል ምስጢር ትክክለኛ ህዝባዊ ዓላማ ነው፡፡ ያነገበው ህዝባዊ ዓላማ ደግሞ የህዝብ ድጋፍና ትጥቅ ሊሆን ቻለ፡፡ ከህዝብ ፍቅር የመነጨ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የመሆን ጽናትም ሌላው የህወሓት የድል ምስጢር ነው፡፡ የህወሓት ታጋዮች የህዝብን ንብረት የማይነኩና ለህዝብ ከፍተኛ ከቤረታ የነበራቸው በመሆኑ ህዝቡ ይበልጥ አቀረባቸው፣ አቅፎም አታገላቸው፡፡ 
ለ17 ዓመታት በቀጠለው የትጥቅ ትግል ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በትግሉ ወቅት የደርግ አምባገነናዊ መንግስት መንደሮችን በእሳት አጋይቷል፡፡ ሰላማዊ ዜጎች በከተሞች በጠራራ ፀሐይ በአውሮፕላን ቦምብ ተጨፍጭፈዋል፡፡ በእስር ቤት ተገርፈዋል፣ ተገድለዋል፡፡ በተለይም  የደርግ አውሮፕላኖች ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓም ‘‘ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን” በሚል ስሌት በሐውዜን ከተማ በፈጸሙት የአውሮፕላን ድበደባ 2ሺ 500 ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ይህ አሰቃቂ ድርጊት የተፈፀመበት የትግራይ ህዝብ አሁን ለተገኘው ሰላምና ልማት የከፈለው ውዱ መስዋዕትነት ምን ያህል እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የአምባገነኑ የደርግ ስርዓትን ጭካኔም ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፡፡
ህወሓትና የትግራይ ህዝብ እስከ አፍነጫው የወቅቱን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው የደርግ ስርዓት የሚያደርሰውን ጭፍጨፋና ግድያ ፈርተው ወደ ኋላ አልሸሹም፤ ይበልጥ ክንዳቸውን አጠንክረው ‘‘ትግላችን ረጅምና መራራ ነው፣ ድላችን አይቀሬ ነው” በሚል የዓላማ ፅናት አስከፊውን ስርዓት እስከመጨረሻው ተፋላሙት፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከ65 ሺ በላይ ዜጎች ለሞት ሲዳረጉ ሌሎች ከ100ሺ በላይ ዜጎች ደግሞ ለአካል ጉዳት ተደርገዋል፡፡ 
ዛሬ የካቲት 11ን እያከበርን እንገኛለን፡፡ ይህን በዓል ስናከብር ሰማዕታት የተሰውለት ዓላማ ምንድን ነው?  አደራቸውስ ምን ነበር? ብለን እየጠየቅን መሆን አለበት፡፡ ታጋይ የህዝብ ልጆች የተሰውለት ዋነኛው ዓላማ ጨቋኙን ስርዓት በማስወገድ ሰላምን ማስፈን፣ ልማትን ማምጣትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው፡፡ ታጋዮች በህዝቡ ይደርስ የነረበውን ጭቆና እያዩ እንዳላዩ መሆን ስላቃተቸው ነው ትግልን የመረጡት፡፡  በተለይ የትግሉ መስራቾች የተሻለ የግል ህይወት መኖር የሚችሉበት ዕድል እያለ ነው ትግልን የመረጡት፡፡ እነዚህ የህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ለህዝብ መቆርቆርን፣ መስዋዕት መሆንንና ህዝባዊ ፍቅርን በተግባር አሳይተውናል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት ህወሓትም ሆነ ኢህአዴግ ያነገባቸውና ታጋዮች መስዋዕት የሆኑለትን ዓላማ ከዳር ከማድረስ ረገድ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በታጋዮች መስዋዕትነት የሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ዜጎች ያለመሳቀቅ ሰርተው ህይወታቸውን መምራት የሚችሉበትን እድል ያመቻቸ ነው፡፡ በዚህም በአገራችን ድህነትን የማስወገድ ትግላችን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፉት ለ12 ተከታታይ ዓመታት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ የታጋዮቹ መስዋዕትነትና ተጋድሎ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሙሉ አቅማቸውን ለአገራቸው ልማትና እድገት እንዲያውሉ በማስቻሉኢትዮጵያ እንደ አገር ፈጣን ዕድገት እንድታስመዘግብ ብሎም የነበራት አሉታዊ ገጽታ በአዎንታዊ ገጽታ እንዲቀየር አስችሏል፡፡
የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት እስከመባልና ለመበታታን ቋፍ ላይ ደርሳ የነበረችን አገር ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመፈቃቀድና በመከባበር አንድነታቸውን አስጠብቀው  የሚኖሩባት አገር መሆን የቻለችው በታጋዮች መስዋዕትነት በተገኘው አስተማማኝ ሰላም መሆኑም መገንዘብ ይገባል፡፡ 
የካቲት 11ን ስናከብር የትግሉ ሰማዕታትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ቃላችን እያደስን መሆን አለበት፡፡ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ፣ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ እህት ድርጅቶችና የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግን ስርዓት ለማስወገድ ያደረጉት መራራ ትግልን ማስታወስ ያስፈልገናል፡፡ የሰማዕታትን አደራ አንግበን ሰላማችን ለማስጠበቅ ቆርጠን ካልተነሰን፣ የጀመርነውን የጸረ ድህነት ትግል ከዳር ለማድረስ የምናደርገውን ትግል ካላጠናከርን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንን በአስተማማኝ አኳኋን ለመገንባት ካልተረባረብን ሰማዕታትን መዘከራችን፤ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የስርዓታችን አደጋዎች ብለን የለየናቸው ትምክህተኝነት፣ ጠባብነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የኃይማኖት ጽንፈንነት በቁርጠኝነት ለመታገል ቃላችን ካላደስን የካቲትት 11 ማክበራችን ትርጉም አይኖረውም፡፡
የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወደውና ፈቅደው ባፀኑት የቃልኪዳን ሰነዳቸው በመታቀፍ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን ድህነት አስወግደው በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ያላትን አገር ለመገንባት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ባለፉት ዓመታት አመርቂ ስኬቶች መመዝገብ ችለዋል፡፡ በዚህ ፍጥነት የጋራ ርብርባቸውን ከቀጠሉ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ የስልጣኔ ስፍራዋ እንደምትመለስ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ሊሆን የሚቻለው ግን መላው የአገራችን ህዝቦች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመጠበቅና በማስጠበቅ ጸረ - ሰላምና ጸረ-ልማት ኃይሎችን በንቃት መታገል ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ እስካሁን ያሳካናቸውን አስጠብቀን በመዝለቅ በህዝባችን ዘንድ እርካታ ያልፈጠርንባቸውን መስኮች ደግሞ በጋራ ርብርብ ውጤታማ ስራ በመስራት ሰማዕታት መስዋዕት የሆኑለትንና እኛም የምንፈልጋትን የበለፀገችውን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ህዝቡ ከታገለላቸው ዓላማዎች አንዱ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑንም በዚህ በዓል ዳግም ማስታወስ ይገባል፡፡ እናም መልካም አስተዳደር አስፍኖ የህዝቡን እርካታ ማረጋገጥ አለመቻል በዚህ መስክ  የትግሉን ዓላማ ማሳካት እንደ አለመቻል ይቆጠራል፡፡ እናም እንደ ትግሉ ጊዜ ሁሉ የህዝብን ንብረት ባለ መንካት፣ እንደ ታጋዮች ሁሉ ለግል ህይወት ከማለት ይልቅ ህዝብን ለማገልገል ቁርጠኛ በመሆን መልካም አስተዳደር ማስፈን ይገባል፡፡ 
ሰማዕታት የህይወት መስዋዕትነት የሚጠይቀውን ከባዱን ትግል ፈጽመው አልፈዋል፡፡ አሁኑ ትግሉ ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ልማትን በማፋጠንና ህዝብን በማገልገል እርካታ የሚገኝበት እንጂ፡፡

1 comment:

  1. what about Ethiopian Muslim. be hayimanotu talka algebahum kale. ehadig yekomelet alam wishet new.

    ReplyDelete