EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 24 February 2016

ትምክህትና ጠባብነት የፀረ-ድህነት ትግላችን እንቅፋቶች




ከአሜሳይ ከነዓን
 
ከዛሬ 24 ዓመት በፊት ከሁኔታዎች በመነሳት በአገራችን ያሟረቱ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ ትሆናለች ያሉም ቀላል አልነበሩም፡፡ አንዳንዶቹ የትምክህት ኃይሎች በኢትዮጵያ ህዝቦች መራራ ትግል ላይመለስ የተቀበረውን ስርዓት ለመመለስ የዳከሩበት፤ የጠባብነት አስተሳሰብ ተሸካሚ ኃይሎች ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝብ የተገኘውን ስኬት በዜሮ በማጣፋት ህዝባችንን የጋራ ጠላቱ በሆነው ድህነት ላይ የሚያደርገውን ጉዞ ለመግታት በታኝና አፍራሽ አስተሳሰብ ይዘው አገራችንን ወደማያባር ጦርነት ውስጥ ለመከተት ሲዳከሩ የታየበት ሁኔታ ነበር፡፡ 

 
ይህንን አስፈሪ ድባብ ከመሰረቱ በመለወጥና ዜጎች ፈቅደውና ወደው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃልኪዳን ሰነድ የሆነውን ህገ መንግስት በማፅደቅ የወሰዱት አስተዋይነት የተሞላበት ርምጃ የትምክህትና የጠባቡን ኃይል ቅስም የሰበረና ትክክለኛ ማንነታቸውንም ያጋለጠ ነበር፡፡ 
 
የእነዚህ አፍራሽና በታኝ አስተሳሰቦች ተሸካሚ የሆኑ ጥቂት ኃይሎች በአገራችን በመገንባት ላይ በሚገኘው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ ደንቀራ በመሆን ዛሬም ድረስ በአገራችን ትርምስ በመፍጠር መሹለኪያ ቀዳዳ ሲፈልጉ ይታያል፡፡ እነሱ ህዝብ ከህዝብ የሚያናክስ አጀንዳ ሲያገኙ ሁኔታውን ለማባባስ ነዳጅ በማርከፍከፍ ቅንጣትም ታክል በሚጠፋው ንብረትና የሰው ህይወት ደንታ ሳይሰማቸው እኩይ ተግባራቸውን ሲፈፅሙ ይስተዋላል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ አስተሳሰባቸውን ሊሸከምላቸው የሚችል ህዝብ እንደሌለ እርግጠኞች በመሆናቸው በየአካባቢው ብልጭ የሚሉ ግጭቶች ላይ መንጠልጠልን ይመርጣሉ፡፡ ለዛም ነው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማራገብ እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት፡፡ 



ጠባብነት በአስተሳሰብ ደረጃ በህዝቦች መካከል ያለውን መሰረታዊ አንድነት በመድፈቅ በማንነት ላይ የተመሰረተውን ልዩነት ህዝቦችን ለማራራቅና ነጣጥሎ ለማናቆር በመጠቀም ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ነው፡፡ ህዝባችን ከቋንቋ፣ ባህል፣ መሰል ልዩነቶች ባሻገር በርካታአንድ የሚያደርጉት መሰረታዊ ጉዳዮች አሉት፡፡ በዋናነት ደግሞ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከድህነትና ከኋላቀርነት ጋር የሚያደርጉት ትግል በመሰረታዊነት አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደ አገር ድህነት ሊቀረፍ፣ ዴሞክራሲ ሊሰፍን፣ ሰላም በዘላቂነት ሊረጋገጥና ሁሉም በእኩል የሚጠቀሙበት ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊገነባ የሚቻለው በተነጣጠለ ጥረት ሳይሆን በጋራ አገራዊ ጥረት ነው፡፡ ዛሬ በመላ አገራችን በመገንባት ላይ ያለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና የመስመሩ ትሩፋቶችን ማጣጣም የተቻለው በህዝባችን የጋራ ርብርብ ነው፡፡ ይህ ሃቅ እንደተጠበቀ ሆኖ የጠባብነት አዝማሚያ የተጠናወታቸው ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች በህዝቦች መካከል በነባራዊነት ያለውንና በትግል የተገነባውን እሴት በማጣጣል ጠባብና ከፋፋይ አዝማሚያዎችን ሲያራምዱ ይስተዋላል፡፡
 
ይህ የጠባብ አስተሳሰብ ተሸካሚ ኃይል ዛሬን በትናንቱ መነፅር በማየት የብሔር እኩልነት በተከበረበት አገር እኩልነት የሌለ በማስመሰል፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና እኩል የመሳተፍ መብት ተከብሮ ሳለ እነዚህ መብቶች የሌሉ በማስመል የእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ የሚሆን ተከታይ ለማፈራት ሲራወጡ ይስተዋላል፡፡  
 
እንደጠባብነት ሁሉ ትምክህትምኛ ጥገኞች አገር ለማተራመስ የሚጠቀሙበት ሌላው ስልት ነው፡፡ ትምክህት የአንድን ብሔር የበላይነትና የሌላውን ወገን የበታችነት ማስፈን ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የተጠናወተው ኃይል በአገራችን የተገነባውን የእኩልነት ስርዓት በመናድ የአንድን ወገን የበላይነት ለማረጋገጥና በአገራችን በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግል የተቀበረውን የቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት ዳግም ለመመለስ በጥቂት ርዝራዥ ጥገኞች የሚቀነቀን አስተሳሰብ ነው፡፡ 
 
አሁን ባለን ነባራዊ ሁኔታ አገራችን ኢትዮጵያ ከ23 ዓመታት በላይ የዴሞክራሲያዊ እኩልነትና ህዝባዊ አንድነት አቅጣጫ ተከትላ በመገንባቷ ጊዜያው ትርምስ ከመፍጠር ያለፈ የእነዚህ አፍራሽ ኃይሎች ህልም  ፈፅሞ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ የትምክህት ኃይሉ ላለፉት ዓመታት በአገራችን ያለውን ተጨባጭ ስኬት በማንኳሰስና እንደሌለ አድርጎ በማቅረብ   የትናንቷ ኢትዮጵያ ከዛሬዋ ኢትዮጵያ የተሻለች እንደሆነች አስመስሎ ያራግባል፡፡ የትምክህት አስተሳሰብ ትላንትን አቆንጅቶ ዛሬን የከፋ አስመስሎ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት የዛሬን መልካም ነገሮች ሁሉ ወደ ጎን በመተው እዚህም እዚያም የሚፈፀሙትን ጥቃቅን ስህተቶች መንጠልጠያ ያደርጋል፡፡ ዛሬ የመጣውን ትልቅና ህዝቡ የሚጠቀምበትን ለውጥ እየደፈቀ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጥቃቅን ግጭቶችን መነሻ ያደርጋል፡፡ 
 
በአጠቃላይ በአገራችን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን የትምክህትና ጠባብ ኃይሉ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ ያለው ብቸኛ አማራጩ አድርጎ በመውሰድ ግጭቶችን ለማፋፋም ያግዘኛል የሚለውን ቀዳዳ በመጠቀም ሁከትና ብጥብጥ ሲያባብስ ይስተዋላል፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት መቼም ቢሆን የትምክህትና ጠባብ ኃይሉ ምኞት ሊያሳካ የሚችል ነባራዊ ሁኔታ በአገራችን እንደሌለ ያምናል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የሚያፋፍሙትን ጊዜያው ትርምስም ቢሆን ከህዝብ ጋር በመሆን እልባት እየሰጣቸው ይገኛል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መንግስታችን በሰጠው አቋም መሰረት ችግር በማራገብ ህይወት በሚቀጥፉና ንብረት በሚያወድሙ ፀረ ህዝቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል፡፡ ለህዝብ ሰላም ሲባል ድርጅታችን ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያው መንግስታችን  በህገወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ህዝባችን የመንግስትን አቋም በመገንዘብ ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን የጀመረውን ሰላሙን የማስጠበቅ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙትን በማጋለጥ ለሰላሙ ዘብ መቆም ይገባዋል፡፡   
 
ህዝባችን አሁንም የእነዚህን የጠባብና የትምክህት ኃይሎች የጥፋት ተልዕኮ በመረዳት ሊነጥላቸውና ከፀረ ድህነት ጋር የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ የህዝብ ንብረት በማቃጠል ህይወት እንዲጠፋ እሳት በመለኮስና ህዝባችን ለዓመታት የገነባውን ሃብትና ንብረት በማውደም፣ እኩይ ተግባር በመፈፀም ህዝባችን ወደ ኋላ እንዲመለስ ማድረግ ፈፅሞ ፀረ ህዝብ የሆነ ተግባር በመሆኑ ድርጊቱ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡   

No comments:

Post a Comment