EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 17 February 2016

ልማትን በማፋጠንና ኪራይ ሰብሳቢነት አምርሮ በመታገል የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተሟላ መልኩ መመለስ ይቻላል




ከአሜሳይ ከነዓን
ሰሞኑን ለስራ ጉዳይ ወደ አንድ ቦታ ተጉዤ ነበር፡፡ የቦታው ርቀት ከመዲናችን አዲስ አበባ ወደ 250 ኪሜ ገደማ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቦታ ከአንድ አምስት ዓመት በፊት እንዲሁ ለስራ ጉዳይ ብቅ ብዬ አውቃለሁ፡፡ በአምስት ዓመት ውስጥ የሚገርም ለውጥ ተመልክቻለሁ፡፡ ያኔ እኔ በመጣሁበት ወቅት ከከተማ ወደ ገጠር ለመጓዝ ቢያንስ አራት ሰዓት በእግር መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ዛሬ መንገዱ ለመኪና ምቹ ተደርጎ በመሰራቱ በሚኒባስ ነው ጉዞዬን ያደረኩት፡፡ በጉዟችን መሃል መንገዱ ፒስታ ስለነበረ መንገጫገጭ ሲመጣ ወግ ተጀመረ፡፡ 

አንድ ከአጠገቤ የተቀመጠ በ50ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገመት ግለሰብ “አይዞሽ እንግዲህ እኛ ያው ለምደነዋል” አለኝ ድንገት፡፡ እኔም ãረ ተመችቶኛል በእግር ከመጓዝ አይሻልም ብለህ ነው አልኩት፡፡ “ይገርምሻል እኛ ወደ ከተማ ገበያ መጥተን ወደ መንደራችን ለመመለስ አራት ሰዓት አህዮቻችንና እኛ መጓዝ አለብን፤ ዛሬ ጥሩ ነው ግን እንደው ይሄ መንገጫገጩ ቢቀርልን እስፓልት ቢሆን ጥሩ ነበር፤ ለፍጥነቱም እስፓልቱ ሳይሻል ይቀራል ብለሽ ነው?” አለኝ፡፡ ሌላውም ተሳፋሪ እየተቀባበለ “ከፒስታውስ እስፓልቱ ቢሆን ጥሩ ነው” ማለት ጀመር፡፡ 

ይህ ሰው ከዓመታት በፊት ለመንገደኛ አስቸጋሪ በሆነበት ቦታ ይኖር የነበረና ከተማ ለመምጣትም በእግር መጓዝ ግድ ይለው የነበረ ሰው ነው፡፡ ዛሬ ጥርጊያ መንገድ ወጥቶ መኪና መግባት እንዲችል ሆኗል፡፡ ግን አሁንም ሌላ ፍላጎት አለ፡፡ ቶሎ ደርሶ ቶሎ ነግዶ በፍጥነት ወደ ቤት የመሄድ ፍላጎት፤ ሳይንገጫገጭ የሸመተውን ይዞ፤ የያዘውን ሸጦ ዘና ብሎ የመመላለስ ፍላጎት፡፡ የዚህ ግለሰብ ፍላጎት የብዙሃኑ በመሆኑ ጥያቄው ወደመንግስት መምጣቱ አይቀርም፡፡ መንግስት ደግሞ ሌሎች የገጠር ከተሞችን እስኪያስተካክልና በልማት እኩል እስኪያደርግ ድረስ ይሄ አካበቢ ምናልባትም አስፓልት ሳይሆን ሊቆይ ይችላል፡፡ ያኔ በማያልቀው የሰው ልጅ ፍላጎትና በመንግስት አቅም በኩል ክፍተት መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ልማት በራሱ የሚፈጥረው የፍላጎት መጨመር ደግሞ ሄዶ ሄዶ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ይመጣል ማለት ነው፡፡ 

ፍላጎት በማንኛውም ሁኔታና የህብረሰተብ ክፍል የማያልቅ ከራስ ለውጥና እድገት ጋር የሚቆራኝ የማያቋርጥ ሂደት ነው፡፡ እኔም ተሳፋሪዎች ሲያነሱ የነበሩትን ሃሳብ እያሰላሰልኩ ከምፈልገው ቦታ ደረስኩኝ፡፡ እዚህም ሌላ አዲስ ለውጥ ተመለከትኩኝ፡፡ እነዛ ያኔ ያስተዋልኳችው ጎጆዎች አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር እንደወትሮው በዝተው አይታዩም፡፡ ደሳስ የሚሉ ቆርቆሮ ቤቶች መንደሩን ሞልተውታል፡፡ እኔም ባየሁት ነገር ደስ ብሎኛል፡፡   

ውድ አንባብያን ስለ ፍላጎት መጨመር ስናነስ በአገራችን ያለውን የኃይል አቅርቦት ለውጥ አንድ ጥሩ ማሳያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአገራችን ኢህአዴግ መንግስት የማስተዳደር ስልጣን እስከተረከበበት 1983 ድረስ የነበረው የኃይል አቅርቦት 370 ሜጋ ዋት ብቻ ነበር ዛሬ ላይ የአገራችን የኃይል አቅርቦት መጠን ወደ 2ሺህ 313 አድጓል፡፡ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ወደ ስራ ሲገቡ ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 10ሺህ ሜጋ ዋት እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡ 

ይህ ሆኖ ሳለ ዛሬም በኃይል አቅርቦት ላይ እጥረት አለ፡፡ የአኗኗር ዘይቤያችን ተለውጧል፡፡ ፋብሪካዎች ተበራክተዋል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማቶች ከፍተኛ የሆነ ኃይል ይጠቀማሉ፡፡ በዚህ በፍላጎት ማደግ ምክንያት የመጣው እጥረት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ሲመጣ ይስተዋላል፡፡ እዚህ ላይ ፍላጎቱን የሚመጥን ስራ መሰረት እንደሚገባው እምነቴ ነው፡፡ ለዛም ነው ከዚህ በኋላም ያለውን የፍላጎት መጨመር ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን የኃይል አቅርቦታችንን ለማሳደግ እየተረባረበ የሚገኘው፡፡ ይህን ያነሳሁበት መሰረታዊ መነሻ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው እየመጡ ያሉት አንዳንድ ጉዳዮች ፍላጎቱ በራሱ የፈጠራቸው መሆናቸውን መገንዘብ ይገባናል ከሚል መነሻ ነው፡፡ 
 
ሌላው ደግሞ አቅርቦቱ እያለም አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል አገልግሎቱን በማዛባት እየተከሰተ ያለው ቀውስ ነው፡፡ ለማሳያነት ያህል አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች መንግስት ሙሉ ለሙሉ ለህዝብ እንዲቀርብ የፈለገውን አገልግሎት በገንዘብ በመሸጥና በመደራደር አገልጎሎቱ የተሟላ እንዳይሆንና እንዲዛባ ያደርጉታል፡፡ ይህ መቀረፍ የሚችለው ኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ብቻ ነው፡፡ በአገራችን የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ማናቸውም ልማቶች በህዝብ ያላሰለሰ ጥረት የተሳኩ ናቸው፡፡ ያለ ህዝብ ተሳትፎ አንድ እርምጃም መጓዝ አይቻልም፡፡ ይህ የድርጅታችን ኢህአዴግ አቋምና ህዝባዊነትም መለያ ባህሪው ነው፡፡ 

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግስት አገልግሎቶችን ህዝብ ሳይስተጓጎል መጠቀም ሲገባው ያለአግባብ ለመጠቀም የሚዳክሩ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አካላት ህዝቡ እንዲስተጓጎልና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኝ ያደርጉታል፡፡ በዚህ ምክንያትም በርከት ያሉ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች እንዲነሱ በር ይከፈታል፡፡ በፍላጎት መጨመር የሚመጣው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ልማታችንን ከህዝብ ጋር በመሆን ህዝብ በሚፈልገው ልክና አገራችን በሚጠብቃት የእድገት ደረጃ ፍላጎት ልክ በመስራት ለመመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ እየታየ ያለውን ችግር ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነትን አጥብቆ በመፀየፍና በመታገል መቅረፍ ይቻላል፡፡ ይህን ማሳካት የሚቻለው ደግሞ ህዝባችን ያለማመንታት ሲታገልና ከመንግስት ጎን ሲሰለፍ ብቻ ነው፡፡

1 comment:

  1. Hi, this weekend is pleasant designed for me, because this time i am reading this wonderful informative article here at my home. rental mobil bogor

    ReplyDelete