በፈድሉ ጀማል
በገጠር ልማት
ፖሊሲና ስትራቴጂ በግልፅ እንደተቀመጠው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎቻችንን ውጤታማ ማድረግ ዋነኛ የምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ
ስልታችን ነው፡፡ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሀገሪቷንና የዜጎችን ገቢ ለማሳደግ የተሰራው ስራ ውጤት እያስገኘ የመጣው
ተሃድሶውን ተከትሎ ልክ በሌሎች ዘርፎች እንደተደረገው ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ልዩ ትኩረት የሰጠ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከተቀየሰ
በኋላ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ በተግባር ምዕራፍ እንደ ሀገር በተለይም ከሀገሪቱ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አብላጫውን የሚወክለውን
አርሶ አደር በተፋሰስ ልማቱ ዋነኛ ተዋናይና የስራው ባለቤት እንዲሆን በማስቻል ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የተገኘው
ውጤት ቀላል የማይባልና ለበርካታ ሀገራትም በምርጥ ተሞክሮነት እየቀረበ ያለ ቢሆንም አሁንም ብዙ መስራትነና መትጋትን
ይጠይቃል፡፡
አርሶ አደሩ ለሌሎች
መደበኛ የግብርና ተግባራት ከሚሰጠው ትኩረት ባላነሰ በየዓመቱ በጋራ በወል መሬቶችም ይሁን በግል ማሳው የተለያየ አይነት የአፈርና
ውሃ ጥበቃ ስራዎችን እንዲሰራ በማድረግ ምርታማነት እንዲጨምር በመደረጉ ከተፈጥሮ ሀብት ልማት አኳያ ከዚህ በፊት ዝናብን
ተከትሎ በሚፈጠር ጎርፍ አማካኝነት የሚኖርን የአፈር መሸርሸርና የውሃ ብክነትን መከላከል የተቻለ ሲሆን የደን ሽፋንን በማሳደግ
ሽፋኑ ከነበረበት 3 በመቶ ወደ ከ15 በመቶ በላይ ማሳደግ ተችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት አለም አቀፍ ስጋት
የሆነውን ያልተጠበቀ የዝናብ ሁኔታ መዛባትን ተከትሎ የሚፈጠረውን
የምርት መቀነስ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ተፅዕኖውን በመቀነስና ሁኔታውን በተወሰነ ደረጃ በማስተካከል ምርትና ምርታማነትን
ከማፋጠኑም በላይ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው የአፈር ለምነትንና የእርጥበት መጠንን የማሳደግና ለአርሶ አደሩ የእንሰሳት መኖ
ግኝት አቅም እንዲጠናከር አስችሏል፡፡
ስለ ተፈጥሮ ሀብት ልማት
ጥበቃና ልማት ስራ ግንዛቤ የያዘው በተለይም መላው አርሶ አደርና አርብቶ አደር መንግስት ከአካባቢ የተፈጥሮ ሀብት ልማት
አንፃር የሚከተለው ስትራቴጂና ስልት የመላው ህዝብ ፍላጎት ነፀብራቅና መገለጫ መሆኑን እንዲያረጋግጥ አስችሏል፡፡ በየዓመቱ
በሚከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራ የሚሳተፈው የህብረተሰብ ቁጥር እና የሚያበረክተው የስራ ድርሻ በከፍተኛ መጠን
እየጨመረ መሄድ የዚህ ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ በተለይ ቀደም ሲል በመጀመሪያ የተሰሩ የተፈጥሮ ህብት ጥበቃና ልማት ስራዎች ምርትና
ምርታማነትን በማሳደግ ያላቸው ፋይዳ በቀላሉ መታየት በመቻሉ የአርሶ አደሩ ግንዛቤ ያደገበትና ስራውን እንደ አንድ መደበኛ
የግብርና ስራ በመውሰድ በየዓመቱ በሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች አርሶ አደሩ የሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ
የቀጠለበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡
የሀገራችን የግብርና
ስራ ውጤታማነት በየዓመቱ እየተከናወነ ካለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራ ጋር እጅጉን የተቆራኘ መሆኑን በአግባቡ
የተረዳው ድርጅታችን ለዘርፉ ልማት ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ባለራዕዩ መሪ
የቀድሞው የድርጅታችን ሊቀ-መንበር ጓድ መለስ ዜናዊ በአለም አቀፍ ደረጃ የያዘው አቅጣጫ የአህጉራችንና የሀገራችንን ህዝቦች
ፍላጎት በተጨባጭ በማንፀባረቅ ክብካቤውን ለልማታችን ስንል የምናከናውነው መሆኑን አሳይቷል፡፡ ይሁንና ይህ ሁሉ ጥረት በአንድ
ጊዜ ውጤት የተገኘበትና አልጋ በአልጋ ሲጓዝ የከረመ አይደለም፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት በርካታ ጥረቶችን
ጠይቋል፡፡ ተከታታይ ስልጠናዎችና በምርጥ ተሞክሮዎች የተደራጀ የመስክ ላይ የተግባር ሙከራዎችን እንደ 1ለ5 ባሉ አደረጃጀቶች
በመቀመር ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራውን ለማስፋፋትና በሽፋንም የተሻለ ውጤት እንድናስመዘግብ አግዟል፡፡
በሌላ በኩል
በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማነት በተጨባጭ መታየት መቻላቸው በአርሶ አደሩ የፈጠሩት እምነት የግብርናው ህልውና ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም በቀጣይም ቢሆን
በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ ህብረተሰቡን አሳምኖና ተሳታፊ አድርጎ ለማስቀጠል ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ ለዚህ ጥሩ
ማሳያ የሚሆነው ህብረተሰቡ በየአካባቢው የተጎዱ መሬቶችና ሊለሙ የሚችሉ ተፋሰሶችን ለይቶ በተከታታይ ጥቂት ዓመታት የቀደመ
ገፅታቸውን ለማላበስ ያደረገው ጥረት በበረሃማነት ወይም ደረቅ በሆነ አካባቢነታቸው ይታወቁ የነበሩ ስፍራዎችን ጭምር የውሃ
ማፍለቂያ ምንጭ እስከመሆን እንዲደርሱ አድርጓል፡፡
ከተፈጥሮ ሀብት
ልማት ክብካቤ ጋር በተያያዘው ስራ ብቻ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀሩ የጓሮ አትክልትና
ፍራፍሬዎችን በማልማትና ንብ በማነብ የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለሆነም የሀገራችን የኢኮኖሚ
ዋነኛ መሰረት በሆነው ግብርናችን የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና ክብካቤ ስራ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቦ ያለፈውን ተሞክሮ
በመቃኘትና ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በተያያዝነው የእቅዱ
የመጀመሪያ ዓመት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በሁሉም አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማስተባበር በከፍተኛ ትጋት ወደ ስራ እንዲገባ ማድረግ
ቁልፍ ተግባር መሆኑን ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስታችን በሚገባ ተረድቶ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች መላ አርሶ አደሩንና
አርብቶ አደሩን ወደ ተግባር ለማስገባት በተደረገው ጥረት የተፋሰስ ልማቱ ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡
አለም አቀፍ ለሆነው
የአየር ንብረት መዛባት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ዘላቂና ጠንካራ ሀገራዊ እድገት እውን በማድረግ የህዳሴ
ጉዟችንን እናስቀጥላለን!!
No comments:
Post a Comment