EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 29 January 2016

በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ሁሌም የማይናወጥ አቋም ያላት አገር- ኢትዮጵያ




ከአሜሳይ ከነዓን
አፍሪካ ህብረት እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 26 ቀን 2001 ዓም ተመሰረተ፡፡ በአፍሪካ አገራት መካከል አንድነትንና መተሳሰብን ለማጎልበት፣ የህብረቱ አባል አገራት ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ፣ በአባል አገራቱ መካከል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጎልበት አልሞ የተመሰረት ድርጅት ነው የአፍሪካ ህብረት፡፡ አፍሪካውያን አህጉራቸውንና ህዝባቸውን በሚመለከት ጉዳይ ላይ በጋራ እንዲቆሙ አቅም ለመፍጠር አልሞ የሚሰራው ህብረቱ በአለም አቀፍ መድረክ ላይም የጋራ ትብብር በመፍጠር ለጋር ጥቅም መቆም የሚያስችል አቅምን የፈጠረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት እውን እንዲሆን አጥብቃ የታገለች ግንባር ቀደም አገር ናት፡፡ አፍሪካውያን ከራሳቸው በተሻለ ለችግሮቻቸው መፍትሄ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው የምታምነው ኢትዮጵያ ይህ ሃሳብ የበርካታ አፍሪካውያን ሃሳብ እንዲሆን በተግባርም ጭምር ለአፍሪካውያን ችግር ቀድሞ በመሰለፍ ያረጋገጠች አገር ናት፡፡

በመዓድን ሃብቷ የምትታወቀው ኮንጎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1960 የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ኢትዮጵያ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ከ8 ሺህ በላይ የሚሆን ኃይል የያዘ ብርጌድ በመላክ ኮንጎን በማረጋጋት በኩል በግንባር ቀደምትነት ያለማቅማማት ተሰልፋለች፡፡ በሩዋንዳም በተመሳሳይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1994 እና 1995 ኢትዮጵያ በሽግግር ወቅትም ሆና የሩዋንዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማርገብ ኢትዮጵያ አቅሟን ባላደራጀችበት ወቅት እንኳን ለአፍሪካውያን ወንድሞቿ ሰላም ዘብ ቆማለች፡፡ በሩዋንዳ በነበረው ቀውስም ኢትዮጵያ የተጎዱትን በመርዳትና የእለት ምግብ በማዳረስ በኩል የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች፡፡ በቡሩንዲም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ኃላፊነቷ በመወጣት በቡሩንዲ ቀውስ የተጎዱትን እንዲያገግሙ በማድረግ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ፣ የጦርነት ማቆም ስምምነት እንዲደረግ በመምራት በቡሩንዲ ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መሰረት መጣል የቻለች ናት አገራችን ኢትዮጵያ፡፡ 

መቼም ቢሆን በአፍሪካውያን ጉዳይ ላይ ለአፍታም ወደ ኋላ አፈግፍጋ የማታውቀው ኢትዮጵያ ላይቤሪያ በአሰቃቂ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ስትታመስ ኢትዮጵያ ላይቤሪያን መልሶ በማቋቋም፣ እንደገና በመገንባትና ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ እርዳት በማድረግ ወገንተኝነቷን በተግባር አረጋግጣለች፡፡ 

የኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም የማስፈን ወሰን የለሽ ፍላጎትና ቁርጠኝነት በደቡብ ሱዳንና ሱዳን መካከል በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ ዳርፉርን በማረጋጋት በኩል ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል፡፡ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ሳይቀር ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር ያላትን ቁርጠኝነትና ብቃት ጭምር በአቢዬ ግዛት ተነፃፃሪ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ አስመስክራለች፡፡ በአፍሪካውያን ልብ የማይጠፋ አሻራም ማስቀመጥ የቻላች የሰላም ተምሳሌት አገር መሆን ችላለች ኢትዮጵያ፡፡



ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያደረገችው ሰላምን የማስፈን ጥረትም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሸባሪውን አልሸባብን በማንበርከክ በሶማሊያና በመላው አፍሪካ አቅም በማሳጣት ለአፍሪካ ሰላም መከበር የማትተኛ አገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠች አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ያልተቆጠበ ትግልና ቁርጠኝነት ነው አሚሶምም በሶማሊያ መግባት የሚችልበት አቅም የተፈጠረው፡፡ አልሸባብ መሰረቱን እንዲያጣና እንዲሽመደመድ ማድረግ የተቻለውም በኢትዮጵያውያን ሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነው፡፡ ዛሬ የሶማሊያ መንግስትና ሶማሊያውያን አገራቸውን መልሶ በማቋቋም ሰላማቸውን እያጣጣሙ ይገኛሉ፡፡   
 
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም የምትተጋ አገር መሆኗን ከቃል ባለፈ በተግባር ያረጋገጠች አገር ናት፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ታምናለች፡፡ የውስጥ ሰላሟን በማስጠበቅም ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሆነች አገር ከመሆን ባሻገር ለአፍሪካ ሰላም የምትተጋ የሰላም ተምሳሌት ናት አገራችን፡፡ 
 
ኢትዮጵያ አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት /ኔፓድ/ ላይም ስታበረክት የቆየችው አስተዋፅኦም በአፍሪካ ላይ ላላት አቅምና ራዕይ ተጠቃሽ ማሳያ ነው፡፡ ኔፓድ አፍሪካውያን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማታቸውን ለማፋጠን በጋራ የሚሰሩበትና ተቀራርበው በአለም አቀፍ ደረጃም ተፅእኖ ማሳደር እንዲችሉ የሚያደርግ ሲሆን ኢትዮጵያ በቀድሞ ጠቅላይ ምኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት ኔፓድን ከመምራት ባሻገር ተፅእኖ ፈጣሪ መሆንም ችላለች፡፡ ኔፓድ በግብርናና በምግብ ራስን መቻል፣ በአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር፣ ክልላዊ ትስስርና መሰረት ልማት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ ኢኮኖሚያዊና ቅንጅታዊ አስተዳደር፣ በፆታና በአቅም ግንባታ እንዲሁም መሰል ተጓዳኝ መስኮች ላይ በትኩረት የሚሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
 
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ላይ ያላት አቋም ሁሌም ቢሆን የማይናወጥ መሆኑን ለበርካታ አፍሪካውያን ህልፈት መንስኤ የሆነውን ኢቦላን ለመከላከል የሃኪሞች ቡድን ወደ ተጠቂ አገራቱ በመላክ ከማንም ቀድሞ ያላትን አቋም ማሳየትም ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ በየትኛው ዘመንና አጋጣሚ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የማይናወጥ አቋም ያላት አገር መሆኗን እስካሁን የመጣንባቸው ታሪኮች አስረግጠው ያስረዳሉ፡፡ 
 
26ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በመቐለ ከተማ የአፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አጀንዳ 2063 መተግበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመምከርና አቅጣጫ በማስቀመጥ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2063 ሠላም የሰፈነባት፣ በኢኮኖሚ የተሳሰረችና የበለጸገች አፍሪካ የመፍጠር ግብ የተቀመጠ ሲሆን የአፍሪካ አገራት የሚያደርጉት የተቀናጀ ርብርብ ለግቡ መሳካት ወሳኝ እንደሆነ ተመላክቶ አልፏል በውይይቱ።
 
ግብርናን ማዘመን፣ ጥራት ያለው ትምህርትን ማዳረስ፣ የአምራች ዘርፉን በኢኮኖሚው ጉልህ ሚና እንዲጫዎት ማድረግ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ማስፋፋትና ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሴቶችና ወጣቶች የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በአህጉሪቱ የሚስተዋለውን ግጭት መግታትም የውይይቱ የትኩረት ሃሳቦች ነበሩ።
 
26ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል፡፡ ከአፍሪካ ህብረት መሪዎች ስብሰባ አስቀድሞ የሚካሄደው የህብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አባላት የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤና መሰል ተከታታይ ውይይቶች እስከ ትናንት ባሉት ጊዜያቶች ተካሂዷል፡፡
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ "የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ዓመት ልዩ ትኩረት ለሴቶች መብት" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment