EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 16 January 2016

የአሉባልታ ማዕበል ያልገታው የአንድነታችንና የህዳሴያችን ምልክት- ታላቁ የህዳሴ ግድብ!!






በፈድሉ ጀማል


ኢትዮጵያ የምትከለተው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የጋራ ተጠቃሚነትና ተደጋግፎ ማደግን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በተለይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ሁለንተናዊ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተና በአከባቢው የሚኖሩ ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እንዲሆን እየሰራች ትገኛለች፡፡
 
የአባይ ወንዝን ለልማት ለማዋል የሚደረገው ጥረትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በወንዙ እየገነባነው ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እያካሄድነው ባለነው የጸረ ድህነት ትግል ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር እንጂ ማንንም ለመጉዳት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትንና መተባበርን እንዲሁም በጋራ የመልማት ባህልን የሚያሳደግ ነው፡፡ ሱዳንም ሆነች ግብጽ ከግድቡ ተጠቃሚ እንጂ ይህ ነው ሊባል የሚችል ጉልህ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ በሀገራችን በኩል እየቀረቡ ያሉ ተጨባጭ መረጃዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ እውነታ ነው፡፡
 
በአባይ ጉዳይ ከግብፅ ጋር የምናደርጋቸው ድርድሮችና ስምምነቶች በግልፅ ዓላማና መርህ ላይ የተመሰረተውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንን ማዕከል ያደረጉም ጭምር ናቸው፡፡  ኢህአዴግና ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ከውጭ ሀገራት ጋር የሚደረግን ግንኙነት የሚፈልገው የተቀመጡ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግቦችን ለማሳካት ግልፅ ዓላማና ግብ በማንገብ ነው፡፡ 
 
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከግብፅና ሱዳን ጋር እያደረግን ያለው ድርድር በተመሳሳይ ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ቀጥሎ ባለበት ሁኔታ የሀገራችንን ጥቅሞች ከማስጠበቅ አንፃር በርካታ ውጤቶችና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የተመዘገቡበት ነው፡፡ ሀገራችን በድርድሩ በርካታ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ ሁኔታዎች ቀደም ሲል የነበሩበትን፣ አሁን ላይ ያሉበትንና በቀጣይ ሊኖራቸው የሚችለውን ሁኔታ በመተንተን ተቀባይነት የሚኖራቸውንና የማይኖራቸውን ጉዳዮች ከግንባታው መጀመር በፊት አስቀድሞ ተግባራዊ በማድረግ በምናደርጋቸው ድርድሮች ሁሉ ሀገራቱ እንዲገነዘቡትና ቀድሞ የነበራቸውን በአባይ ወንዝ ላይ በብቸኝነት የመጠቀም አካሄድ እንዲሁም ይህንኑ ያረጋግጥልናል ብለው የሚጠቅሱትን ያልተገባና ተቀባይነት የማይኖረውንን የስምምነት ሰነድ ተገቢ አለመሆኑን የማስረዳት መሰረታዊ አቅጣጫን የተከተለ ነው፡፡ ይህ አቋማችን ግድቡን ስንጀምረው የነበረ፣ አሁን ላይም ያለ በቀጣይም የሚኖር እንዲሁም አለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ተወስደው በተፋሰሱ ሀገራት መካከል በመርህና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ያለመ ነው፡፡ 
 
ግድቡን በራሳችን አቅም እንገነባለን ብለን መላ የሀገራችንን ህዝብ በባለቤትነት አሳትፈን እየተጓዝን ባለንበት በእስካሁኑ ሂደት የግድቡ ግንባታም ይሁን በዲፕሎማሲው ረገድ ከሀገራቱ ጋር የሚደረገው ድርድር ከእኛ ፍላጎት አንፃር ያስቀመጥነውን ግብ እንዲሳካ የሚያደርግ ነው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከግንባታው መበሰር አንስቶ ከዚህ የሀገራችን ህዝብና መንግስት ፍላጎት በተቃራኒ የሚሰነዘሩ አሉባልታዎች የእኛ ስኬትና እድገት ደስታ ከማይፈጥርላቸውና ከማይዋጥላቸው ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት መደመጡ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለአብነት የግድቡ ግንባታ ለመላ የሀገራችን ህዝብ በተበሰረበት በመጀመሪያው ምዕራፍ ኢህአዴግ የህዝቡን ቀልብ ለማስቀየስና  ለሌላ የፖለቲካ ፍጆታ ሊያውለው እንጂ ግድቡ ሊገነባ አይችልም፣ መገንባት እንኳ ቢፈለግ የግብፅን ተፅዕኖ መቋቋም አይቻልም ሲሉና ይህንኑ አቋማቸውን በተለያየ መንገድ ወደ ህዝቡ ለማስረፅ ዘመቻ ከፍተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የሚታወቅ ነበር፡፡



እነዚህ ኃይሎች  ዜጎች በህዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን እንዳያደርጉ ለማስቻል የቦንድ ግዢ እንዳይፈፅሙና መንግስት በቦንድ ከዜጎች የሰበሰበውን ገንዘብ ለሌላ አላማ እያዋለው ነው የሚሉ መሰል የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን እየፈበረኩ በተለያየ መንገድ ወደ ህብረተሰቡ ሲነዙ ቆይተዋል፡፡ በተጨማሪም ግብፅን ሲሻቸው ኃያል አድርገው በማቅረብ ሀገራችን በአባይ ላይ የምትገነባው የታላቁ የህዳሴ ግድብ በግብፅ ዘንድ ተቀባይነት ስለማይኖረው እውን ሊሆን አይችልም የሚል ዘመቻ በመክፈት ሲሻቸው ደግሞ ከግብፅ መንግስት ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግ ለሚያካሄዱት የፀረ ልማት ዘመቻ የገንዘብ ድጋፍ  ለማሰባሰብ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በአጠቃላይ የሀገራችን ህዝብና መንግስት ለልማትና ለዴሞክራሲ እድገት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማስቆም በምትኩ ሁከትና ትርምስ የነገሰባትና ሰላሟን ያጣች ሀገር እውን በማድረግ ዘወትር የሚቋምጡለትን ስልጣን በአቋራጭ ለመፈናጠጥ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ቀጥለውበታል፡፡ 
 
ወደኋላ የመመለስና ጭለማ ውስጥ የመክተት አባዜ እንጂ የብርሃን ጭላንጭልን ለህብረተሰቡ የማመላከት ኃላፊነት መወጣት የተሳናቸው እነዚህ አካላት የህዝቡን የዘመናት ቁጭት ጭምር ምላሽ የሰጠ ነው በተባለው የህዳሴ ግድብ ዜጎች ድጋፍ እንዳያደርጉ የሚከለክል ዘመቻቸው ለትዝብት ዳርጓቸው አልፏል፡፡ ብርሃን እያየ ለሚገኘው ህዝብ ጭለማን የማመላከት የንቀትና ኃላፊነት የጎደለው አፍራሽ ዘመቻቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ከንቱ ድካም ብቻ ሆኖባቸው የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ታጅበው በሌሎች የፀረ  ድህነት ትግሎች ላይ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ማስቆም ቀርቶ ላፍታም እንዲገታ ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ የሀገራችን ህዝብም የልማት ቀበኝነታቸውን በሚገባ ተረድቶ እነአጅሬ እያለ ተቀፅላ ስም ከመስጠት ያለፈ ቦታ እንዳልሰጣቸው በሚገባ ገልጾላቸዋል፡፡ 
 
በሌላ በኩል ከአፍራሽ ዘመቻዎቻቸው መካከል በተለያዩ የማደናገሪያ ስልቶች በመጠቀም ህዝቡን ለአፍራሽ ተልዕኳቸው የመጠቀም ሁኔታ አሁንም አልፎ አልፎ ያለ ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበረበት አንፃር በእጅጉ የቀነሰና በቀጣይም በዚህኛው አማራጫቸው ሰለባ ሊሆን የሚችል የህብረተሰብ ክፍል ሊኖር እንደማይችል አመላካች ነው፡፡ 
 
እነዚህ አፍራሽ ኃይሎች በሀገራችን እየተመዘገ ያለው ሁለንተናዊ እድገት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ቀደም ሲል ለተልዕኳቸው ማስፈፀሚያ በዋናነት ሲጠቀሙበት የነበረው ወጣቱን ክፍል ተጠቃሚ እያደረገ መሄድ የህዝቡን ድጋፍ የበለጠ እያሳጣቸው መሆኑን ተረድተው በየወቅቱ ተለዋዋጭና የበለጠ ወደ ህዝቡ ውስጥ ለመግባት የሚያስችላቸውን መንገድ ቀይሰው ተግባራዊ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጭምር በሚገባ መረዳት ይገባል፡፡ አንዳንዴም ተግባራዊ የሚደርጉት የሀገራችንን የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ የማጨናገፍ ዘመቻ የሀገርንና የህዝብን ክብር እንዲሁም የማደግ ተስፋ በእጅጉ በመጻረር የራሳቸውንና የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግላቸውን አካል ርካሽ አላማ ለማሳካት ብቻ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ለአብነት ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከመጀመሪያው አንስቶ ግድቡ በሀገራችን አቅም ሊሰራ አይችልም፣ መንግስት ግድቡን ለፖለቲካ መጠቀሚያ እንጂ አይሰራውም፣ ህዝቡ ለህዳሴ ግድቡ ድጋፉን እንዳያደር፣ ከህዝቡ የተሰበሰበው ገንዘብ ለሌላ አላማ እየዋለ እንደሆነ፣ ከግብፅ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ግድቡ እውን እንዳይሆን በጋራ መወጠናቸውን የመሳሰሉትን እንቅስቃሴዎቻቸውን በሚገባ ከተገነዘብን እውነታውን በግልፅ ያሳያል፡፡
 
እነዚህ ኃይሎች ዓላማቸው የኢትዮጵያን ልማት ማቀደናቀፍ እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የልማት ስራዎች የተለያዩ አጀንዳዎች እየፈበረኩ ልማቱን ከማደናቀፍ ወደ ኃላ እንደማይሉ እሙን ነው፡፡ በተመሳሳይ አሁን ላይ በርካታ ሂደቶችን በማለፍ መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡበት የሚገኘውን ሀገራችን ከግብፅና ከሱዳን ጋር የምታደርገውን የሦስትዮሽ ድርድር አስመልክቶ እነዚህ አፍራሽ ኃይሎች የሚታወቁበትን ተለዋዋጭ የማደናበሪያና ከተቻላቸውም የሁከት መቀስቀሻ ስልታቸውን እንደተለመደው በመጠቀም ቀደም ሲል ኢህአዴግ ለፖለቲካ ፍጆታ ሊጠቀምበት እንጂ ግድቡ በሀገራችን አቅም ሊሰራ አይችልም በሚል ሲገልፁት ከነበረው አቋማቸው በተቃራኒ ግብፅ ባደረገችው ተፅዕኖ ግድቡ እንዲዘገይና በታቀደለት አግባብ እንዳይቀጥል መንግስት ተስማምቷል የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

የእነዚህ አካላት ፍላጎትና ዘመቻ ምንም ይሁን ምን በአባይ ላይ እየገነባነው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላፍታም ቢሆን እንዲዘገይ የሚፈቅድ ህዝብና መንግስት እንደማይኖር በሚገባ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እውነታውም ይኸው ነውና፡፡     ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትና መላው የሀገራችን ህዝቦች በልማት ላይ እየተረባረቡ በመሆናቸው ለወሬና ለአሉባልታ ጊዜውም አይኖራቸውም፡፡ አልተገናኝቶም አለ የሀገሬ ሰው፣ ቸር እንሰንብት፡፡

2 comments:

  1. Great article. Well composed. GERD will be built and the reservoir operation shall be optimal for the benefit of the riparian countries. When Sudanbuilt Merowi , raised the height of Roseries by 10 meters,there were no opposition from any side. Why is the GERD an issue then.

    ReplyDelete