EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 8 January 2016

እርምጃችሁ ግስጋሴያችንን አይገታም!!





ከዘመኑ ፈረደ
ሰሞኑን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ሁከትና ሁከቱን ተከትሎ የጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው የህዝብና የሀገር ሃብትና ንብረት ሰላም ወዳዱን ህዝብ ያሳዘነ ሆኖ አልፏል፡፡ ምንም እንኳን በግልባጩ የጥፋት ሀይሎችን ጮቤ ቢያስረግጥም፡፡ ሁል ጊዜም ቢሆን የጥፋት ሀይሎች ዓላማ ይኸው ነውና፡፡ ‹‹ባልበላውም ልፈልሰው››፡፡
የጥፋቱን ስፋት ለማሳየት ያህል በምዕራብ ሸዋ ዞን በምትገኘው ወለንኮሚ ከተማ የደረሰውን መቃኘቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ በዚች ከተማ የሚኖሩ ሰላም ወዳድ ነዋሪዎች ልክ እንደሌሎች አመፅ የተቀሰቀሰባቸው ከተሞች በፀረ ሰላም ሀይሎች ተንገላተዋል፤ ንብረታቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል፤ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ወድቆ ቆይቷል፡፡ የወለንኮሚ ከተማ ከንቲባ እንደገለፁት በከተማቸው ባጠቃላይ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህዝብና የመንግስት ንብረት በፀረ ልማት ሀይሎች ወድሟል፡፡
ወለንኮሚን ለአብነት አነሳን እንጂ ከዚህም በላይ የሚገለፁ ጥፋቶች የደረሰባቸው ከተሞችና ተቋማት አሉ፡፡ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማካሄድ ለአካባቢው ህብረተሰብ ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠሩ ድርጅቶችም ሳይቀሩ በየአካባቢው ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም እንዲሁ አገልግሎት የማይሰጡበት ደረጃ እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ የትራንስፖርት መስጫ ተሸከርካሪዎች፣ ባንኮች፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የህዝብ ሀብት የሆኑ የልማት ማሳለጫ ተቋማት እንዲሁ እንዲዘረፉና እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡ በሀገራችን ያለውን ዘላቂ ሰላምና ለኢንቨስትመንት ምቹነት ተከትለው በሀገራችን መዋዕለንዋያቸውን ያፈሰሱ የውጭ ሀገር ዜጎች በከፍተኛ ዋጋ የሚገመት ንብረት በተለይ በአንድ ሁከት በተከሰተበት አካባቢ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወድሞ ስራ ያቆመበት ሁኔታ ተከስቷል፡፡
አሁን ሁሉም ነገር በሚፈለገው ደረጃ ላይ ነው ለማለት ባያስደፍርም ውጥረቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ መርገባቸውን የክልሉና የፌዴራል መንግስት የስራ ሃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ ያ ሁሉ ጥፋት እንዲደርስ ያደረጉት የጥፋት ሀይሎችም ምንም ሳያተርፉ ከስረው ወደየሰንኮፋቸው ተከተዋል፡፡ ለጊዜው ህዝብም ሆነ መንግስት ነቅተውባቸዋልና ለሌላ ሴራ ዝግጅት ሊያደርጉ መሽገዋል፡፡ ተመሽገው ግን የሚቀሩ አይመስሉም፡፡ መንግስት ከህዝብ፣ ከሚመለከታቸው አካላትና የፀረ ሽብር ትግል ከሚያደርጉ አገራት ጋር በመተባበር ከመሸጉበት እያወጣ በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በይፋ በፀደቀበት ወቅት ከአባላቱ ለተጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ‹‹የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለመተግበር የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨትና ህዝብን በማደናገር የሰው ህይወት እንዲጠፋ አቅደው የመሩ አካላት በህጋዊ ፓርቲ ሽፋን የሻዕቢያን ተልዕኮ ለማሳካት የተሯሯጡ ሀይሎች ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል››፡፡ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው በሰሞኑ ሁከት ከምንም በላይ መተኪያ የሌለውና ውድ የሆነው የሰው ህይወት ከመጥፋት አንስቶ የህዝብና የሀገር ንብረት ወድሟል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ሰላም ወዳዱ ማህበረሰብ ተሸብሯል፡፡ በተለይ ፀረ ሰላም ሀይሎች ቀድመው በዘረጉት መረብ በመጠቀም ባመቻቹት አመፅ ተሳታፊ መሆን ያልፈለገውን ገርፈዋል፣ ቤቱን አቃጥለውበታል፣ በአጠቃላይ በጥቅሙና በሚወደው ነገር ለማስገደድ ሞክረዋል፡፡ ብዙዎች ድርጊቱ የተፈፀመበትን ሁኔታ በማስተዋል ከሽብር ተግባር ጋር አመሳስለውታል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አሸባሪነትን ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲባል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ የወንጀል ድርጊትን ማሰብና መተግበር ሲል ይፈርጃል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በ1999 ባሳለፈው ውሳኔ አሸባሪነትን ለፖለቲካዊ ግብ ሲባል በብዙሃኑ ላይ ፍርሃትን ለመፍጠር የሚታሰብ ወይም የሚፈፀም የወንጀል ድርጊት ሲል በይኖታል፡፡ በእነዚህ ትርጓሜዎች ላይ አለም ይስማማል፡፡ የሌሎች አገራትን ህጎች መሰረት በማድረግ የፀረ ሽብር ህጉን ያወጣው የኢትዮጵያ መንግስትም ከሞላ ጎደል በዚህ ትርጓሜ ይግባባል፡፡
ሰሞኑን በኦሮሚያ የተከሰተው ሁከትና ግርግር እንዲሁም ይህን ተከትሎ የታዩት ሁነቶች በሙሉ በዚህ መስፈርት የሚለኩ ናቸው፡፡ በመሆኑም ድርጊቱን በአጭሩ ‹‹የሽብር ተግባር›› ልንለው እንችላለን፡፡ ድርጊቱ ሽብር እንደሆነ ከተግባባን ሽብርተኞች እንዴት ይፈጠራሉ የሚለውን ብናይ የበለጠ ሁኔታውን ለመረዳት ያበቃናል፡፡
ብሉም የተሰኘው ፀሀፊ ‹‹አሸባሪዎች የሚፈጠሩት በሁለት መንገድ ነው›› ይለናል፡፡ ቀደም ሲል ሲከተሉት የነበሩት የትግል (የውጊያ) ስልታቸው ሲወድቅባቸው አሊያም የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ እንደሆነ ይኸው ፀሀፊ ይተነትናል፡፡ ከእኛው አብራክ የወጡት የራሳቸውን ዜጋ የሚያጠቁ አሸባሪዎቻችንም ከላይ ብሉም በጠቀሰው መንገድ የተፈጠሩ ሽብርተኞች ናቸው፡፡ በ1983 ዓ.ም የሽግግር መንግስቱ መስራች አባላት የነበሩት ኦነግና ኦብነግ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በፖለቲካ ትግላቸውም ሆነ በውጊያ ስልታቸው ሲወድቁ ነበር የዴሞክራሲያዊ የትግል መድረክን ረግጠው በመውጣት በምትኩ ወደ ሽብር ተግባር የተዛወሩት፡፡ አልሸባብም ቢሆን በተደጋጋሚ በገጠመው የውጊያ ሽንፈት በመማረር ነበር ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ሽብር ያዞረው፡፡
በአንድ ወቅት ሀገራችንን ወሮ የነበረው የሻዕቢያ መንግስትም በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በከፈተው ጦርነት ትርፍ ቢያጣበት ነው ተላላኪዎችን እየላከ ቀጠናውን የሚያምሰው፡፡ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉት አሸባሪ ድርጅቶችም ህዝብ በድምፁ ይሁንታውን ሲነፍጋቸውና ያወሩት ሁሉ አልደመጥ ቢላቸው ነው ወደጎራው የተካተቱት፡፡ የሽብር ስራን ስራቸው አድርገው ኪራይ የሚሰበስቡና ጥቅም የሚያጋብሱ እንዳሉም ይታወቃል፡፡

አሁን ‹‹ዴሞክራሲያዊ ትግል እያደረግን ነው›› የሚሉት አንዳንድ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ምቹ ሁኔታ ካገኙ ሀሰተኛ ለምዳቸውን አውልቀው የሽብር ካባን እንደሚደርቡ አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል ባገኙት መድረክ ሁሉ የነሱ ዜማ አቀንቃኝ ተባባሪዎቻቸውን ይዘው ኢትዮጵያ ያፀደቀችው የፀረ ሽብር ህግ እንዲሻር የሚወተውቱት፤ ሁኔታዎችን እያመቻቹም ሰልፋቸውን ሲቀያይሩ የሚስተዋሉት፡፡
ከላይ ያነሳነው መነሻቸው አንደኛው ገፅታቸው ሲሆን ጠላታችን ብለው የፈረጁት አካል የሚቀዳጀው ድልና ስኬትም በእኩይ ተግባራቸው እንዲሰለፉ ይገፋፋቸዋል፡፡ ይህንን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምደን ብናየው ይበልጥ ይገለጥልናል፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ ተቃውሞ ጎራ ውስጥ ካሉት የጠባብም ሆነ የትምክህት ሀይሎች አብዛኞቹ እንዳለመታደል ሆኖ ለልማት ግስጋሴያችን ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ በህዝቦች የተባበረ ክንድ እየተገነባች ላለችው ሀገር ጠጠር ከማቀበል ይልቅ የተገነባውን የመናድ ተግባር ላይ የተሰማሩ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
በርካቶቹ ትናንት ስለዚች ሀገር ሲያሰሙት የነበረው ሟርት የከሸፈባቸው ናቸው፡፡ ልማቱም የመጣው እነሱው በኮነኑትና በረገሙት ድርጅት (ኢህአዴግ) በመሆኑ ይህንን መቀበል ለነሱ መርዝ ከመጠጣት በላይ ይሆንባቸዋል፡፡ በተለይ በተለያየ ማደናገሪያቸው ጠምደው በመያዝ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የህብረተሰብ ክፍል በተጨባጭ የታየውን እድገት ተከትሎ በከፍተኛ መጠን እያገለላቸው መሄድና በተመሳሳይ ሀገሪቱ በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ እያገኘች የመጣችው ተቀባይነት የእነሱን ሟርት የቀበረ ከመሆኑም ባሻገር መተንፈሻ አየር የሚያሳጣቸው ሆኖባቸዋል፡፡
ሌላው መንግስት ያቀደውን ሁሉ እየፈፀመ የህዝብን ጥቅም እያረጋገጠና የህዝብን ተሳትፎ በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ እያጠናከረ መሄዱ ሴራቸው ይበልጥ እየተጋለጠ እንዲሄድ አደረገው፡፡ በመሆኑም ሁሉንም የመንግስት እርምጃ ይቃወማሉ ያጥላላሉ፡፡ የሚያገኙትን ጥቅም ላለማጣትም ሲሉ ይፍጨረጨራሉ፡፡ እንደማያተርፉ ቢያውቁትም የአሸባሪ ባህሪ የታወቀ ነውና ሽብር ይፈጥራሉ፡፡ ከልማት ለመጎተት ያልሞት ባይ ጥረታቸውን ያደርጋሉ፡፡
እንግዲህ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተከስቶ በነበረው ሁከት የየራሳቸውን የዜሮ ድምር ፖለቲካቸውን ለማራመድ የተጉት ሀይሎች ከላይ የገለፅናቸው ናቸው፡፡ ባደረጉት ተሳትፎ ቀደም ሲል ከነበራቸው አሰላለፍም የተለየ ሰልፍ ፈጥረው በመታየት ብዙዎቻችንን አስገርመዋል፡፡ ለወትሮው በትምክህት ባህሪያቸው የተወጠሩትና በጠባብነት የታጠሩት ሀይሎች የየቅል መገለጫ ነው የነበራቸው፡፡ ከሰሞኑ እንዳየናቸው ግን የማይዘልቅ ጋብቻ ሲፈፅሙ ታይተዋል፡፡ ‹‹ዋናው ወያኔን ማስወገድ ነው፡፡ ለነገ ነገ ያውቃል›› ሲሉ ራዕይ አልባ መሆናቸውን እናውቅልሃለን እያሉ በከንቱ ለሚያደነቁሩት ህዝብም አሳውቀዋል፡፡
ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች በሙሉ ላልተቀደሰው ጋብቻቸው መከሰት ተጨባጭ ማሳያዎች ይሆናሉ፡፡ የሞከሩት ሁሉ ከሸፈባቸው፤ በምርጫም ቢመጡ ህዝብ ፊት ነሳቸው፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ የተባሉ ሀያላን አገራት ከጤፍ አልቆጥራቸው አሉ፡፡ ታዲያ ምን ያድርጉ? ከዓላማ ዓላማ የላቸው፤ ከደጋፊ ወገኔ የሚሉት ህዝብ የላቸው፤ ከሀገር የሚገነቡት ሀገር የላቸው፡፡ ‹‹ህዝብም ሆነ ሀገር ከፈለገ ይውደም›› አሉና ወሰኑ፡፡ ወጣቱን እየማገዱም እነሱ ከውጭ በሪሞት እየተቆጣጠሩ “የበርገር ትግል” አካሂደው በትረ ስልጣን መጨበጥ አማራቸው፡፡ ጠባቡና ትምክህቱ ልጅህን ለልጄ ተባብለውም ተስማምቶ የማያውቅ ወደፊትም የማይስማማ ዝምድናን ሊቀላቅሉ ከጀሉ፡፡ ይሆን መስሏቸው ማለት ነው፡፡
የእነዚህ መሰሪዎች ውጥን ሙሉ በሙሉ ከስሯል፡፡ ሟርታቸው እንደተለመደው በኖ ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ጥቂት ስፍራዎች ተከስቶ የነበረው ሁከትም ተረጋግቶ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በህዝቡ ያልተቆጠበ ተሳትፎ ወደ ቀደመ ሰላማቸው ተመልሰዋል። በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉት ህዝባዊ ውይይቶችም ህዝቡ ‹‹ሰላማችንን የነሱትን፤ ልማታችንንና ዕድገታችንን ያደናቀፉትን መንግስት ልክ ያስገባልን›› ሲል ተደምጧል፡፡ ‹‹ለማጋለጡ እኛም አለን›› ብሏል፡፡
የሆነው ሆኖ ነገሩ ጠባሳ ጥሎም ቢሆን አልፏል፡፡ ለነገ ግን መንግስትም ሆነ ህዝብ ሊማሩበት የሚገባ አጋጣሚ እንዳገኙ ይሰማኛል፡፡ መንግስት ለእያንዳንዱ የልማት ስራ ተገቢው የህዝብ ግንኙነት ስራ በተቀናጀ መንገድ ማቀድ ያስፈልገዋል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የሁከቱ መነሻ ምንም ይሁን ምን የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ብቻ ግን አልነበረም ያቀጣጠለው፡፡ የወጣቱ ስራ ማጣትና በየደረጃውና በየፈርጁ የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግሮች የየበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት የጀመረው ጥረት ፍሬ ሊያፈራ ይገባዋል፡፡
ህዝብም ልክ ሁሌም እንደሚያደርገው ጥቅሙን ለማስጠበቅ ጥያቄዎቹንና ቅሬታዎቹን በሰለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በማንሳት ሰላሙ እንዳይታወክ በማድረግ ከመንግስት ጎን መቆሙን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ መጀመሪያ ወደ ሁከትና ግርግር ገብቶ ለሌባ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት በፊት ግን በካርዱ እንዲመራው የወከለውን አካል ራሱ መጠየቅ አለበት፡፡ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ከመንግስት ሊነጥሉት የሚፈልጉ ፀረ ሰለም ሀይሎችን በውል ሊለያቸው ይገባል፡፡
ይህ ከሆነ በመሀል ነፋስ ብሎ ነገር አይገባም፡፡ የተጀመረው ህዳሴያችንም ግቡን ይመታል፡፡ ታላቁ መሪያችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት እንደተናገረው አሁን የጀመርነው እንቅስቃሴ እንደአጀማመሩ ከዘለቀ የዓለም ድንቅ እየተባሉ እንደሚወደሱ ታሪኮች በዓለም ሁሉ እየተነሳ ይኖራል፡፡ ለነዛ በትምክህት ለተወጠሩና በጠባብነት ለታወሩት ሀይሎች በመጨረሻ ይህን ልበላቸው፡፡ ታሪክ ለመስራት ቆመናል፡፡ ታሪክ መስራታችን ይቀጥላል፡፡ የታሪክ መስራት እርምጃችንን ለማደናቀፍ በመንገዳችን የሚቆመውን ሁሉ እየዳጥን፤ የሚካበውን እንቅፋት ሁሉ እየናድን ከግባችን መድረሳችን አይቀሬ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ የእናንተ እርምጃ የኛን ታሪክ የመስራት ግስጋሴ ፈፅሞውንም አይገታም፡፡ እናንተም ላታመልጡ አትሩጡ!!

1 comment: