EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 31 December 2015

በፀረ ሰላም ኃይሎች ግርግር የሚባክን ጊዜ አይኖርም




ከአሜሳይ ከነዓን
አገራችን ከአምባገነናዊ ስርአት ተላቃ  የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው ልክ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው አካላት በፖለቲካ ምህዳሩ ገብተው የሚሳተፉበት እድል መመቻቸት ችሏል፡፡ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶቻቸው ሳይሸራረፍ የሚከበርበት ህገ መንግስታዊ ዋስትና በትግላቸው ካረጋገጡ በኋላ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሰላማዊ፣ ልማታዊና እያበበ የመጣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአገሪቱ መስፈን ችሏል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድሎችም የአገራችን ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፤ በልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ያለምንም ገደብ መሳተፍ፤ ሃብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን በአገራቸው ላይ ማፈሰስ በመጀመራቸው የመጣ ነው፡፡ 

በአገራችን ባለፉት ስርዓቶች አይደለም መቃወምና ከገዢው መንግስት አስተሳሰብ ውጭ መሆን ፍዳ ይከፈልበት የነበረው ያ ዘመን በህዝባችን ትግል ላይመለስ ከተቀበረ ጀምሮ በአገራችን ስልጣን በህዝብ ውሳኔ ብቻ የሚያዝበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት የታገሉለትና በትግል እውን ያደረጉት ድል በመሆኑ ከዚህ ውጭ ያሉ አማራጮችን የሚሸከም ጫንቃ እንደሌላቸው በተለያየ መንገድ በተግባር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
 
በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን ገና ለጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚፈልግ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው አካላት ህጋዊ በሆነው መንገድ ህገ መንግስታችን በሚፈቀደው መጠን በሚያግባቧቸው ጉዳዮች ላይ እንደአገር ተግባብቶ በመስራት ልዩነት ባላቸው ጉዳዮቻቸው ላይ ልዩነታቸውን በሚያስተናግደው ስርዓት በመታገዝ ስልጡን በሆነ መንገድ ለህዝብና ለሀገር በሚጠቅም ተግባር ላይ መረባረባቸው መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ህዝብ የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው አካላት ህግ በሚፈቅድላቸው መንገድ ተመዝግበው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዱ የህዝብን ጥቅም በሚያረጋግጡ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋሙን ሲያራምድ ሌላው ደግሞ ዳር ቆሞ በአምስት አመት አንዴ ብቻ ምረጡኝ የሚል ዜማ ብቻ ከማሰማት እና ዳር ቆሞ ከመመልከት ያለፈ ተግባር የማይፈፅም ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በስልጣን ጥም ሰክሮ በአቋራጭ ወንበር የሚፈናጠጥበትን መንገድ ብቻ የሚያማትር ሆኖ ይገኛል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በአገራችን አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁና የአገራችንን ሰላም ለማተራመስ ለማይተኙ አካላት ጭምር ጉዳይ አስፍፃሚ እስከመሆኑ ይደርሳል፡፡

ውድ አንባብያን ይህን ሃሳብ ያነሳሁት ሰሞኑን በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የተቀናጀ የልማት ትስስር ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የግል እይታዬን ማንፀባረቅ ስለፈለኩኝ ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአገራችን ሊካዱ የማይችሉ ዘረፍ ብዙ ድሎች በህዝባችንና በመንግስት የጋራ ያርብርብ ተመዝግበዋል፡፡ የእነዚህ ሁለንተናዊ ድሎች መነሻውም መድረሻውም የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአገራቸው ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ በያገባኛል ስሜት በመሳተፋቸው የመጣ ነው፡፡ ይህ ታዲያ አልጋ በአልጋ የተገኘ ድልም አይደለም በብዙ ተግዳሮቶች እያለፈ የተመዘገበ እንጂ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰሞኑ በአዲስ አበባና ዙሪያ የተቀናጀ የልማት ትስስር ዙሪያ የኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢ ህዝብ የጠራ መረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ለብዥታ ተጋልጧል፡፡ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ መፈጠር መነሻ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች ቢኖሩም ጉዳዩን በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ የሚቻልበት እድል ግን ፈፅሞ ዝግ አልነበረም፡፡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እያለ ሁሌም ቢሆን የሚስተዋሉ ክፍተቶችን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሰላማችንን ለማደፍረስ ሌተ ተቀን የሚባዝኑ የጥፋት ኃይሎች  የህዝብን ጥያቄ አቅጣጫውን በማስቀየር ለእኩይ አላማቸው ማሳኪያ አድረገው ሲጠቀሙበት ተመልክተናል፡፡ 


እነዚህ አፍራሽ ተልዕኮን አንግበው ውስጣችንን ለማተራመስ ሲባዝኑ የነበሩ አካላት ጫፍ ወጥተው አሰላለፋቸው አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ አካላት ጋር ጭምር ሴራ በመሸረብ ሊያሰናክሉን ጥረዋል፡፡ የአገራችን አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በሰሞኑ ጉዳይ ትዝብት ውስጥ ገብተው አይተናል፡፡ በህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ነኝ ሽፋን ህገወጥ ተግባርን የሚፈፅሙት እነዚህ አካላት አገርና ህዝብ መውደድ ትርጉም ስለተምታታባቸው ላፍታም ቢሆን እንደ አገር ድህነትን ለማስወገድ የሚከናወኑና ለህዝብ የሚጠቅሙ ተግባራትን እንኳን መደገፍ ሽንፈት ሲሆንባቸው ይታያል፡፡

እርግጥ ነው አንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ነኝ የሚል አካል ከገዥ ፓርቲ የሚለይ ርዕዮተ አለማዊ ቁመና ይኖረዋል፡፡ ይህ አቋምና አስተሳሰብ በህዝብ ዘንድ ተቀባይ እንዲሆንለት የማስረዳት፣ የማስገንዘብና የማሳመን መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ማለት ነው፡፡ ሃሳቡን የመደገፍና የመቃወም መብት ደግሞ የብዙሃኑ ህዝብ ይሆናል፡፡ የአገራችን አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደ አገር ለህዝብ ጠቃሚና ድህነት ለማስወገድ የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት እንቅስቃሴዎችን ሳይቀር መደገፍ ራስ ምታት ሲሆንባቸው ይታያል፡፡ በመቃወም፣ የሚወጡ ህጎችንና መመሪያዎችን ያለምንም ማመዛዘን ማብጠልጠል፤ ብቻ ምንአለፋችሁ በተፃራሪ መቆም የመንግስትን ስራ እየተከታተሉ ማጥፋትና በማጠልሸት ከፍታቸውን የጨመሩ ስለሚመስላቸው በከንቱ ምኞት ተጠምደው እናያቸዋለን፡፡
 
ለአብነት ብናነሳ በአገራችን የበርካቶቻችንን ህልም እውን ያደረገው የኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብን «ኢትዮጵያዊነት ታፔላቸው ነው እንዴ፤ እነዚህ ሰዎች ዜግነታቸው ምንድን ነው?» እስኪያስብል ድርስ ሲያብጠለጥሉትና በተቃራኒው ሲቆሙ፤ ህዝቡን አልተሳካላቸውም እንጂ ከድርጊቱ ሊገቱት ያልቆፈሩት ጉድጓድ እንዳልነበረ ተመልክተናል፡፡ ከዚህ ባሻገር እንደ አገር የበርካት አገራትን ተሞክሮ በማየት የተሻለውንና በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያስኬደውን የፀረ ሽብር አዋጅም ሲዘምቱበት ተመልክተናል፡፡ መቼ ይሄ ብቻ በአንድ ወቅት መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በህዝብ ስም የሚመጣን ገንዘብ ለግል ጥቅም ከማዋልና በአስተዳደር ወጪ ስም እንዳይመዘበር ከዚህ ባሻገርም የእጅ አዙር ፀረ ሰላም ተግባር ላይ በመግባት በውስጥ ጉዳያችን እንዳይፈተፍቱም ጭምር ገደብ የሚጥለውንና ሰላማዊና ድብቅ አጀንዳ ለሌላቸው መንግስታዊ ተቋማት ጥቅም እንጂ ጉዳት የሌለው አዋጅ ሲወጣ ከህዝብ በተቃራኒ በመቆም ለምን ብለው ሲሞግቱ አይተናል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአገራችን የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን መንገዱን፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታውን፣ ብቻ በመንግስትና በህዝብ የተከወኑ የልማት ስራዎችን ሁሉ በማጠልሸት ተጠምደው አስተውለናል፡፡ በዚህ ለአክራሪነትና ለሽብርተኝነት ዘብ እየቆሙ በሌላ ጎኑ ከእኛ በላይ ለህዝብ ሲሉም አድምጠናል፡፡ ለእነሱ መቃወም ማለት እንግዲህ ይሄ ነው በድፍን ጥላቻ ተጠምዶ መልካሙን ሁሉ ማጨለም፡፡  
 
ሰሞኑን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎችና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ሁለት አጎራባች ወረዳዎች የተፈጠረውን ብጥብጥ አስመልክቶ ሲያራምዱ የነበረው አቋምም ከዚህ ሁሉን ከመቃወም አባዜያቸው የተለየ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በእኔ እይታ መንግስትን ለማብጠልጠል ለእነሱ ምቹ የሚሏቸውን አጋጣሚዎችን ሁሉ እየጠበቁ ብቅ ማለታቸው የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ በእርግጥም ሁኔታው ለእነሱ ምቹ ስለነበረ ከስር ከስር ጋዝ ማርከፍከፉ ቀላል ሆኖላቸዋል፡፡ ሁከቱና ብጥብጡን ያባብስልናል ብለው የሚያስቡትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በህዝብ ዘንድ በመርጨት ሁኔታው እንዲባባስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በህዝባችን ጥረት ባይከሽፍ ኖሮ ማለቴ ነው፡፡ በእነሱማ እይታ በ2007 አገራዊ ምርጫ የተመኙትን የስልጣን ጥማቸውን ማርካት ባለመቻላቸውና ህገመንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ የሚመራውን መንግስት በካርዱ በማረጋገጥ ገና ናችሁ አገር የመምራት ብቃት የላችሁም በሚል ፊቱን ያዞረባቸው ህዝበ ውሳኔ ባይዋጥላቸው የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገው በአቋራጭ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ነበር፡፡ ቅሉ ግን ህዝባችን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን ቆም ብሎ የሚያስብ ህዝብ ነውና ከንቱ ውጥናቸውን አምክኖባቸዋል፡፡ 
 
በእርግጥ ሁለት ፅንፍኛና ርዕዮተ ዓለማዊ ትስስር የሌላቸው በምንም መስፈርት ጭራሽ አንድ መሆን የማይችሉ ሃይሎች አጣነው የሚሉትን የስልጣን ጥም በአቋራጭ ለማርካት ካላቸው ፍላጎት ያለአቻ ጋብቻ ሲመሰርቱ ማየታችን ይህ የመጀመሪያ አለመሆኑ ይታወሳል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት በአገራችን በተካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫና ከዛ በፊት እንደአገር በነበሩ ሁነቶች ውስጥ ከመንግስት በተቃራኒ ለመቆም ተፈላልገው ሲዛመዱ አይተናል፡፡ ዓላማቸው የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው በመሆኑ በየትኛውም መንገድ ይሁን የስልጣን ጥማቸውን ማርካት ብቻ በመሆኑ ዓላማቸው የአንድ ሰሞን የተጋባን ሆይ ሆይታቸው የተለመደና ትዝብት ውስጥ ሲከታቸው የመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ከሰሞኑ የተመለከትነውም እንደልማዳቸው የጠላቴ ጠላት የእኔ ወዳጄ ነው በሚል የተመሰረተና ጥምረት ከአንድ ሳምንት የበለጠ ዘለቄታ እንደማይኖረው እሙን ነው፡፡   

እርስ በእርስ የሚጣረስ ሃሳብ ሲያራምዱ ያስተዋልናቸው እነዚህ የተቃዋሚ ኃይሎች ፋይዳ ቢስ ነው በሚል የፌደራል ስርዓቱን በፈለጋቸው መንገድ ሲያብጠለጥሉት የነበሩ አንዴ ለቅማንት ህዝብ ለምን ነፃነት ተሰጠ ሲሉ በሌላ ጎኑ ደግሞ በማስተር ፕላን ሽፋን የፌደራል ስርዓታችን ውጤት የሆነው የኦሮሚያ ክልል መብቱን የተነጠቀ አድርገው ሲዘምሩ ተሰምተዋል፡፡ የቅማንት ብሄረሰብ እንደ አንድ የአገራችን ብሄሮች መወሰድ የለበትም ከአማራ ብሄር መነጠል የለበትም የሚል ኃይልና የኦሮሚያ ክልል መብት በማስተር ፕላን ስም ተነጠቀ መሬት ሊቆረስ ነው፣ ሊቀላቀል ነው የሚል እርስ በእርሳቸው የሚጠፋፉ አቋሞችን አንጠልጥለው ሲውተረተሩ አየን፡፡ ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንዲሉ አንቅሮ የተፋቸው ህዝብ በራሳቸው የጥፋት መንገድ ዛሬም ብስለታቸው ጥያቄ ምልክት እንዲገባ ሆኗል፡፡
 
ውድ አንባብያን በህገመንግስታችን በግልፅ እንደተደነገገው ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው ሳይሸራረፍ በመከበሩ ታይቶ የማይታወቅ የለውጥ ማዕበል ውስጥ መግባት ችለዋል፡፡ ልክ እንደሌሎች ክልሎች ሁሉ የኦሮሚያ ክልልየፌደራል ስርአቱ ውጤት ነው፡፡ ከሌሎች የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ታግሎ  በተጎናፀፈው ህገ መንግስታዊ መብት ነው የኦሮሚያ ክልል የራሱ ስልጣን ያለውን አስተደደርን መስርቶ ባህሉን ታሪኩንና ማንነቱን ጠብቆ ልማቱን እያሳደገ ይገኛል፡፡ የፌደራል መንግስትና የክልሎች ስልጣንም በህገ መንግስቱ በግልፅ ተደንግጎ ሁሉም ክልሎች በዛ ማዕቀፍ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በህገ መንግስቱ ከተደነገገው ማዕቀፍና ከክልሉ ህዝብና መንግስት እውቅና ውጪ የክልሉ የአስተዳደር ወሰንማንም አካል የሚቀነስ አልያም የሚጨመር እንደማይሆን ይታወቃል፡፡


ውድ አንባብያን የአገራችን አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ነን ባዮች በሰሞኑ የአገራችን ክስተት እንደእኔ በእናንተም ትዝብት ውስጥ መውደቃቸው እንደማይቀር አልጠራጠርም፡፡ እነዚህ አካላት ከራሳቸው ጥቅም ባሻገር ስለህዝብ ጥቅም የማይጨንቃቸው በመሆናቸው በማስተር ፕላን ሰበብ በህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን የመረጃ ክፍተት እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ጥያቄው ከዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ ውጭ እንዲወጣ እሳት የማቀጣጠል ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከዳር ሆነው የሚቻላቸውን ሁሉ መርዝ ወደ ህዝቡ በመርጨት የህዝብ ጥያቄ እንዲዛባ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ሁለት የማይታረቁ ኃይሎች የጠባብ ሃይሉ ህዝብን የማይወክል አስተሳሰብ በማራመድ ኦሮሚያ ብቻ በሚል ኢትዮጵያዊነትን በማይቀበል አፍራሽ አስተሳሰብ ተሰልቦ በማስተር ፕላን ስም ፀረ ህዝብ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲታገል ኢትዮጵያ ብቻ የሚለው አካል ደግሞ በቅማንት ብሄር ማንነት መከበር ላይ ጥያቄ በማንሳት አገር ይከፋፈልና አገር አንድ ይሁን የሚሉ የማይታረቁ አስተሳሰቦች አንድ ሆነናል በሚል ሲራወጡ ተስተውለዋል፡፡ በእኔ እይታ እነዚህ አስተሳሰቦች በራሳቸው ጠላትነት ያላቸው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያነት ሽፋን የኦሮሚያን ህልውና የማይቀበል አካል ኢትዮጵያዊነትን ከማይቀበል አካል ጋር በምን መስፈርት ይዛመዳል

ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ በሰሞኑ ጉዳይ የጠባብ ሃይሉ ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ የሚለው አዲስ አበባን ጨምሮ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ለዚህ ሃይል የአዲስ አበባና ዙሪያው የልማት ትስስር አጀንዳው ሊሆን አይገባምም አይችልምም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ብቻ በሚል የብሄር ማንነትን የሚጨፈልቀው ሃይልና የብሄር ማንነትን ቋንቋና ባህልን መሰረት በማድረግ የተመሰረተው የፌደራል ስርአት ስህተት ነው ብሎ የሚያምነው አካል የማስተር ፕላኑ ጉዳይ እውን ቢሆን ሊያስደስተው እንጂ ምን አወራገጠው፡፡ አንድነትን እንሰብካለን ብሄርን መሰረት ያደረገ አከላለል ትክክል አይደለም፤ኢትዮጵያ አከላለል በጂኦግራፊ ነው መሆን ያለበት ሲል የነበረ አካል ምነው ታዲያ እንዲህ ግብግብ አድርጎ ከመቃወም ተርታ አስገባው ያስብላል፡፡ በዚህ የቅማንትን ብሄር ማንነትና መብት አለመቀበል የሚመስል አቋም እያራመዱ በዚህ ጎኑ ደግሞ በኦሮሚያ ጉዳይ ከፅንፈኛው ጋር አብሮ መሰለፍ ምን ይሉታል፡፡ ጭልጥ ያለ ጥበትና ጭልጥ ያለው ትምክህት የማይዘልቅ ጋብቻ ማለት ይሄ ነው፡፡
 
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ከሁከትና ብጥብጥ ብዙሃኑ ህዝብ ሳይሆን ከዳር ሆኖ የሚያራግበው አካል ነው ትርፍ ሊያገኝበት የሚችለው፡፡ ሁሌም ቢሆን የአገራችን ሰላም ራስ ምታት የሚሆንባቸው አካላት በአገር ውስጥ የሚደረግ ማንኛውንም ተቃውሞና ማተራመስን ለመደገፍ ዳጎስ ያለ ገንዘብ መደጎማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ዶላር ሲያይ እንደ አበደ ውሻ የሚያክለፈልፈው ፀረ ሰላም ሃይል ደግሞ ለሁከቱ ይመቸኛል የሚለውን እኩይ ተግባር ሁሉ መፈፀሙ አይቀሬ ነው፡፡ አሳዛኙ ጉዳይ በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀት የሌለውና በሃሰት መረጃ ተወናብዶ የእነዚህ የፀረ ሰላም ሃይሎች መሳሪያ የሚሆነው አካል ነው፡፡ 
 
መንግስት በአገራችን መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን እንቅፋት ሆኖ ያለው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ተደምጧል፡፡ ይህን ያነሳሁት ያለአንዳች አይደለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ውስጥ የተዘፈቀ ማንኛውም ሰው ሰላማዊና የተረጋጋ ከባቢ እንደሚረብሸው እሙን ነው፡፡ ጥቅሜ ተነካ ብሎ እስካሰበ ድረስ የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ በአቋራጭ ኪሱን ማደለቡን አያቋርጥም፡፡ በመሆኑም የሰሞኑ ብጥብጥና ሁከትም  ለኪራይ ሰብሳቢው ሃይል የተመቸ በመሆኑ ጉዳዩን ከማባባስ ያለፈ የማረጋጋት ስራ ይሰራል ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡ 
 
ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል የስርዓቱ አደጋ የሆነውን ጥበትና ትምክህትን ማራገፍ እንደአገር ለሚኖረው ሰላማዊ ሁኔታ ወሳኝ ናቸውና ይህን ማረጋገጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሊነሱ የሚችሉ ህዝባዊ ጥያቄዎች መልካቸውን እንዲቀይሩ ጋዝ ሲያርከፈክፉ የነበሩ አካላትን ማሸነፍ የሚቻለው ከእነሱ በተቃራኒ በመቆም መሆኑን በመገንዘብ የአፍራሽ አጀንዳቸው ሰለባ ላለመሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ብሂሉ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ማሳካት ያልተቻለውን ፍላጎት በአቋራጭ ለማርካት የሚቅበዘበዘውን ኃይል በጋራ መመከት ግድ የሚልበት ወቅት ነው፡፡

አገራችን አሁን ያላት አንገብጋቢ አጀንዳ ከድህነት መላቀቅና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንዳይሰናከልና ችግሮች ሲፈጠሩም በተረጋጋና በሰከነ መንገድ መፍታት የሚቻልበት ባህላችን እንዳይደፈርስ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ህዝብና መንግስት በጋራ ጥምረት ሊፈቷቸው የሚገቡ አያሌ ጉዳዮች ስላሉ ወደ እነዛ ፊትን በማዞር ስራ ላይ ነን ልንላቸው ይገባል፡፡ ለአፍታም ቢሆን በፀረ ሰላም ሃይሎች ግርግር የሚባክን ሰዓት ሊኖረን አይገባም፡፡ አጀንዳንችን ሰላማዊና በመቻቻል ምልክት በሆነችው አገር ላይ ልማትን በማረጋገጥ ድህነትን ማስወገድ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ሰላም!


No comments:

Post a Comment