በገነት ደረጀ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ሃብት
ባለቤት እንደሆነች ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው ሃብቷና ውበቷ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ድምር ውጤት የሆነውና 90 ሚሊዮን የሚጠጋው
ህዝቧ ነው፡፡ በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች እንዲሁም ከህዝቡ ማንነት ጋር የተቆራኙ ባህልና
ወጎች ሌሎች ሀገራት ያልታደሏቸውና ሀገራችንን የተለየ ውበት ያጎናጸፉ ሃብቶቿ ናቸው፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ ሀገራችን ሌሎች ቁሳዊና
ቁሳዊ ያልሆኑ በርካታ እድሜ ጠገብ ቅርሶች እንዲሁም ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፤ አስተዳደራዊና ማህባራዊ ነክ የሆኑ የተለያዩ ክንዋኔዎች
የሚተገበሩበት በጥቅሉ የማይዳሰሱ ሃብቶች ባለቤት ነች፡፡
እነዚህ ሃብቶች ከማንነት ነጸብራቅነት
አልፈው በአግባቡ ከተያዙና በተለያየ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ከተቻለ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን
የቀደሙት የሀገራችን ገዢዎች እነዚህን በርካታ ሃብቶች በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት
እንዲችሉ ጥቅም ላይ ለማዋል ቦታም አልነበራቸውም፡፡ እነዚህ ገዢዎች ዜጋው ሃብቱን አበልጽጎ እንዲጠቀም ከማድረግ ይልቅ የያዙትን
ስልጣን እናጣለን ከሚለው ስጋታቸው የተነሳ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቀውን አስተሳሰብና ፖሊሲ በብዙሃኑ ላይ በግዴታ
በመጫን የስርዓቶቹ መገለጫ የባላይነትና የበታችነት አስተሳሰብ የሰፈነበት በመሆን የሀገራችን ቁሳዊ ቅርሶችና ቁሳዊ ያልሆኑ
ወጎች፣ ባህሎችና አስተሳሰቦች ባለቤት የሆነው አብዛኛው ህዝብ ባለው ሃብትና ፀጋ እንዲያፍርበትና ባህልና ወጉን እንዳይተገብር ተገድቦ
እንዲቆይ ያስገደዱ ነበር፡፡
በርካቶች በማንነታቸው እንዲያፍሩ
አልፎም በቋንቋቸው እንዳይጠቀሙ ጭቆናው የከፋ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ከሰሜን ከመጡ ቤተሰብ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል የተወለዱት
አንድ የቀድሞ ታጋይ ለአንድ ጋዜጣ ያካፈሉት የልጅነት ትዝታቸው ይህንኑ
ያረጋግጣል፡፡ ‹‹…ጠዋት ጠዋት ቡና ይፈላል፡፡ አራቴ
አምስቴ ቡና ይፈላል፡፡…እኔ ቡና የተፈላበት ቤት የእናቴን ቀሚስ ይዤ አብሬያት እዞራለሁ፡፡ የመንደሩ ሴቶች ቡና ሊጠጡ መጥተው፤
እኔ ስመልስም፤ ስጠይቅም በሲዳምኛ መሆኑን ያያሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ልጅሽ
ሲዳማ ሆኖ ቀረ ይሏታል-እናቴን፡፡ የዚያኔ ጭኔን በቁንጥጫ አደበኑኝ፤ ጩኸቴን አቀለጥኩት፡፡ የተቆነጠጥኩበት ምክንያት
ለምን በሲዳምኛ አፍህን ፈታህ ነው፡፡›› ይህና መሰል አስተሳሰቦች የብዙዎች ትዝታ ነው፡፡
ሀገራችን ህብረ-ብሔራዊነት የስጋት
ምንጭ ሳይሆን የውበት መገለጫ፤ የአንድነት፤ የጥንካሬና የኩራት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ያረጋገጠችው በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን
ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ተግባራዊ በተደረገው የፌዴራሊዝም ስርዓት ብሔር-ብሔረሰቦች በገዛ ቋንቋቸው በነፃነት እንዲጠቀሙና
እንዲያሳድጉ እንዲሁም ባህላቸውንና ወጋቸውን በነጻነት እንዲተገብሩ በማስቻሉ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ህዝቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆነውን ባህል፤ ቋንቋና ታሪካቸውን የመንከባከብና የማበልጸግ መብት በማጎናጸፉ የተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎችን
ወደ አደባባይ ማምጣትና ከመጥፋት መታደግ ተችሏል፡፡ ለተተኪ ትውልድም በነጻነት ማስተማርና ባህሉንና ወጉን እንዲንከባከብ እድል
ሰጥቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ይህንን በማንነት አሻራ የደመቀውን ህብር ለመልካም አጋጣሚዎች ማዋልም ተችሏል፡፡
ብዘሃነትን ማዕከል አድርገን በህገ
መንግስታችን ጥላ ስር መራመድ ከጀመርን ሲታፋርባቸው የነበሩ የባህል ትሩፋቶቻችን ከባህር ማዶ ሰዎች ጋርም አቆራኝተውን ለነሱ የመዝናኛ
ለኛ ደግሞ የኩራ ምንጭ መሆን ከጀመሩ ውሎ አድሯል፡፡ በአለም መድረክ ቀና ብለን እንድንራመድና እንድንመላለስ አድርገውናል፡፡ በእነዚህ
የባህል ትሩፋቶችና ሃብቶቻችን ምክንያት ስማችን ዳግም በአለም የክብር መዝገብ ሰፍሯል፤ እየሰፈረም ይገኛል፡፡
የባህል ቅርሶቻችንን እኛ ብቻ ሳንሆን
አለምም ‹‹የኔ ናቸው›› ብሎ እየተቀበላቸው ይገኛል፡፡ በሃይማኖት የመስቀል በዓል በቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን የማንነት አሻራ
የታተመባቸው የባህል ክዋኔዎች መካከል የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው የፍቼ ጨምበላላ በዓል ህዳር 22/2008 ዓ.ም
በዩኔስኮ በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ በቀጣይም ከነዚህ ሃብቶቻችን የገዳ ስርዓትን ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
እናም የእኩልነት መሰረት የተጣለበትን ህዳር 29 የብሔር-ብሄረሰቦች ቀንን በድርብ ድል እናከብራለን፡፡
በኢህአዴግ የተተገበረው የፌዴራል
ስርዓት የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና የህዝቦች መብት መከበር ለብተና ይዳርጋል ተብሎ የተፋራውን ህብረ-ብሔራዊነት ከዴሞክራሲያዊ መብትነት
ባሻገር ለኢኮኖሚ እድገት እንደ መልካም አጋጣሚ እንድንጠቀምበትም አስችሎናል፡፡ የእነዚህ ቅስሮች እውቅና ማግኘት እያደገ ያለውን
የቱሪዝም ዘርፍ በእጅጉ ያጠናክራል፡፡ የስራ እድልም እንዲሁ፡፡ በቀጣይም ሌሎች ባህላዊ ቅርሶቻችን አለም አቀፋዊ እውቅና እንዲያገኙ
ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡
በኢህአዴግ መሪነት በፌዴራሊዝም
ስርዓታችን በህብረ-ብሄራዊነታችን ደምቀን የለውጥ ፍሬዎችን ማጣጣም ጀምረናል፡፡ የቀጣይነቱን ዋስትና ደግሞ በህገ መንግስታችን
ጨብጠናል፡፡
No comments:
Post a Comment