የማነ
ገብረስላሴ
ህዳር
1995 ዓም የተዘጋጀው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ሰነድ መግቢያ ላይ ‹‹ይህ የውጭ ጉዳይና አገራዊ የደህንነት ፖሊሲና
ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን የማረጋገገጥ ተልዕኮ ያለው ሆኖ የተቀረጸ ሲሆን፣ መሠረታዊ ይዘቱ
ስር ነቀል የሆነ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር የሚያስገድድ ነው፡፡ ይህ እርምጃ በአገራችን
ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ፖሊሲውም ሆነ ስትራተጂው በዋነኛነት የሚያጠነጥኑት ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን
ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን እውን በማድረግና ለህዝቡ የተመቻቸ ሁኔታን በመፍጠር ዙርያ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል
የፖሊሲውና ስትራተጂው መነሻ በአገሪቱ ህልውና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የአገሪቱ ውስጣዊ ችግሮችና የአደጋ ተጋላጭነት እንደሆነና
ዋነኛ ትኩረቱም በአገር ውስጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ …›› የሚል አስፍሯል፡፡
ሰነዱ
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ዕይታ ከውስጥ ወደ ውጭ በማድረግ የራስን የቤት ስራ አስቀድሞ በመስራትና ውስጣዊ
ጉድሎቶችን በመለየት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂው ክፍተቱን የሚሞላ ሆኖ መዘጋጀቱንም ፖሊሲው አስቀመጧል፡፡ ፈጣንና ህዝቡ በየደረጃው
ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ካልተረጋገጠ፣ ዴሞክራሲ እውን ካልሆነ አገሪቱ ለብተና ልትዳረግ እንደምትችልም ፖሊሲው በሚገባ አስቀምጧል፡፡
ኢህአዴግ
አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ መሰረታዊ ለውጥ ተደርጎበታል፡፡ እንደሚታወቀው በቅድመ
1983 ዓም የአገራችን የውስጥ ችግሮችና የአደጋ ተጋለጭነታችን ተገቢ ትኩረት ሳይሰጣቸው ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ የተከተለው የውጭ
ጉዳይ ፖሊሰ ግን መነሻው በአገሪቱ ህልውና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት የአገሪቱ ውስጣዊ ችግርና የአደጋ ተጋላጭነት እንደሆነና ዋነኛ
ትኩረቱም በአገር ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ ፖሊሲውና ስትራተጂው ፈጣን ልማት ማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ
ስርዓት መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቷል፡፡
ኢህአዴግ
በሚከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውስጣዊ ችግሮች ቅድሚያ በመሰጠቱ ፈጣን ልማትን በማስመዝገብ ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ
አስችሏል፡፡ በተመሳሳይ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ እንዲሁ ትልቅ እምርታ እየመጣ የሚገኝ ሲሆን የህዝቡ ተሳትፎና ግንዛቤ
በየጊዜው እያደገ የአገራችን ዴሞክራሲ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው አስችሎታል፡
ኢህአዴግ
የሚመራው መንግስት የተከተለው ትክክለኛ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከሌሎች አገሮች በመከባበር ላይ የተመሰረተ መልካም
ግንኙነት እንድትመሰርት አስችሏታል፡፡
ባለፉት
24 ዓመታት ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዘገብ የቻለችው ለዘመናት የዕድገት ማነቆ ሆነው የቆዩ ውስጣዊ ችግሮች
ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥ ትክክለኛ ስርዓትና አሰራር በመከተሏ ብቻ ነው፡፡ ለዘመናት ብዝሃነትን ማስተናገድ አቅቷት ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች
እስር ቤት›› እስከ መበል ደርሳ ነበር፡፡ ያለፉት ገዥዎች የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶችን አላከበሩም ብቻ ሳይሆን አገሪቱንና
ህዝቦቿን ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል ፖሊሲና አገራዊ ራዕይም አልነበራቸውም፡፡
በዚህም
ኢትዮጵያ የጦርነት አውድማ ሆና በርካታ ለመገንጠል ያኮበኮቡ ኃይሎች የትጥቅ ትግል የሚያካሄዱባት አገር ሆና ነበር፡፡ ህዝቡ ስር
የሰደደ ድህነትና ኋላቀርነት በፈጠራቸው በርካታና ውስብስ ችግሮች ለሰቆቃና ለእንግልት ተዳርጎ ቆይቷል፡፡ ከ1983 ዓም በፊት የነበሩ
መንግስታት በተለይ ኃላፊነታቸውን መወጣት ተስኗቸው የሚፈጠሩ ውስጣዊ ችግሮችን ለማስተንፈስ ኢትዮጵያን በበርካታ የውጭ ጠላቶች የተከበበች
አድርጎ በማቅረብ ህዝቡን ስጋት ውስጥ የሚከቱም ነበሩ፡፡
ኢህአዴግ
የውጭውን አደጋ ማስቀረት የሚቻለው ውስጣዊ ችግሮች ሲወገዱ መሆናቸውን በማመን የጠራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ ለተግባራዊነቱ ሲረባረብ
ቆይቷል፡፡ በዚህ ለዘመናት ችግር ሆኖ የቆየውን ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ያለመቻል ችግር ዘላቂ መፍትሄውን በማስቀመጥ የውስጥ
ችግር እንዲፈታ አድርጓል፡፡ የአገሪቱ አንድነት ይበልጥ የሚጠናከረው የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት ሲከበር መሆኑን በሚገባ የተገነዘበው ኢህአዴግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች
መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር ታግሏል፡፡ ብዝሃነት በአግባቡ ከተስተናገደ ትልቅ እሴትና ጠንካራ አቅም እንጂ ችግር ሊሆን እንደማይችል
በተጨባጭ ያስመሰከረ ውጤት በአገራችን እንዲመዘገብ ኢህአዴግ ቁልፍ ድርሻ ተጫውቷል፡፡
ብዝሃነትን
በአግባቡ ማስተናገድ የሚችል የፌደራሊዝም ስርዓት በመገንባት ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዕውን ለማድረግ የተከናወኑ
ስራዎች ኢትዮጵያን በርካታ አገሮች በዚህ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቅሳት አገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ህዝቦች ያላቸው አገሮች በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያውያን ተመክሮ ለመውሰድ ወደ አገራችን እየመጡ ነው፡፡
ቀደም
ሲል እንደ ችግር ይታይ የነበረው ብዝሃነትን የማስተናገድ ችግር በአግባቡ በማስናገድ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው
የማስተዳደር ዕድል በመጎናጸፍ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ ብሎም ለአገራቸው ሰላምና ብልጽግና እኩል ተቆርቋሪ እንዲሆኑና በአከባቢያቸውና
አገራቸው ልማት ንቁ ተዋናይ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
የአገራችን ትልቅ ችግር የሆነውን
ድህነት ለማስወገድ ኢህአዴግና እርሱ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲዊ መንግስት ባደረጉት ርብርብ የድህነት መጠንን ከግማሽ በላይ መቀነስ
ተችሏል፡፡ የነፍሰ ወከፍ ገቢ በብዙ ዕጥፍ አድጎ ከ700 የአሜሪካ ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ ለዘመናት የትምህርትና የጤና አገልግሎት
ርቋቸቸው የነበሩ የገጠር ቀበሌዎች ጭምር የአገልግሎቶቹ ተደራሽ ሆነዋል፡፡ የመንገድ፣ የመብራትና የስልክ መሰረተ ልማቶች እየተስፋፉ
ነው፡፡ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ጭምር በራስ አቅም እየገነቡ የታዳጊ አገሮች
ኩራት መሆን ችለዋል፡፡
ለዘመናት ስሟ በተማጽዋችነትና
ረሃብ ተያይዞ ስትነሳ የነበረችው አገር መጥፎ ታሪኳን መቀየር የቻለች ሲሆን ከመነሻው በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋም ‹‹የአሁኑ ውርደታችን
ድህነትና ኃላቀርነት ነው፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እጦት ነው፤
ህዝባችንን ከዚህ ውርደት ለማላቀቅ አንድ የጋራ አገራዊ እምነትና አመለካከት ይዘን ተከባብረንና ተፈቃቅደን በአንድነት
ለመረባረብ አለመቻላችን ነው፡፡›› በሚል በማስፈርና ለተግባራዊነቱም በተደረገው ርብርብ ነው፡፡
በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የፌደራሊዝም
ስርዓት በመከተል አገራችን አስተማማኝ ሰላም አስፍናለች፡፡ ጠንካራ
የመከላከያ ኃይል በመገንባት ከራሷ አልፋም ለጎረቤቶቿና ለሌሎች አገራት ሰላም መስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ የምታበረክት አገር ሆናለች፡፡
በጠንካራ ህዝባዊነት፣ ዲሲፕሊንና የውጊያ ብቃት የተገነባው ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ሌላው የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን ትሩፋት ነው፡፡
የመከላከያ ሰራዊታችን የአገራችንን
የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከየትኛውም አደጋ በመጠበቅ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ህዝባችንንና አገራችንን
ከጥቃት የታደገ ነው፡፡
የአገራችን ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ
ስርዓት ግንባታ እየተጠናከረ በመምጣቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ትልቅ ሚና የምትጫወት አገር ለመሆን ከመብቃቷ በተጨማሪ በአፍሪካ ጉዳዮች
ውክልና በማግኘት ተሰማኒቷም ጨምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ከበርካታ አገራት ያላት
የሁለትዮሽና የእርስ በርስ ግንኙነት በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ለመሆን በቅቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከበርካታ አገሮች ጋር
ያላትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እያሳደገች ትገኛለች፡፡
በኢሊኖ ምክንያት የተከሰተውን
የድርቅ ችግር ተከትሎ የኢፌዴሪ መንግስት በራሱ አቅም ችግሩን ለመቋቋም ጥረት እያደረገ ሲሆን እንደ አሜሪካና ቻይና ያሉ አገሮች
ድጋፍ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ችግር ሲያጋጥም እንደሚደረገው መደጋገፍ መርህ በመመስረት ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸው እየገለጹ
ነው፡፡
ይህ ማለት ግንኝነቱ ሰጪና ተቀባይ
ዓይነት ይዘት አለው ማለት ሳይሆን አንዲት አገር እንደድርቅ፣ ጎርፍና የመሬት መንቀጥቀት ወዘተ ያሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች
ሲገጥማት በሚደረገው የመተባበርና የመተሳሰብ መንፈስ ነው፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ትክክለኛ
የውጭ ጉዳይና ሌሎች የልማት ፖሊሲዎች በመከተሏ በአለማችን አሳፋሪ በሆነው ድህነትና ኋላቀርነት ላይ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ
ድህነትን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ እንደምትችል ያመላከቱ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡ አሁን ላይ አገራችን በፈጣንና ተከታታይ እድገቷ፣
በሰላም ደሴትነቷ፣ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻነቷ የምትታወቅ አገር ሆናለች፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን
ሰፊ ህዝባዊ መሰረት በመያዝ በማደግ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አጠናክራ ከቀጠለች
በ2017 ዓም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንደምትሰለፍ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው፡፡
ኢህአዴግ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው ሲል በተጨባጭ ውጤታማ በሆኑ ፖሊሲዎችና ውጤቶች ተመስርቶ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment