በሙሃመድ
ሰጠኝ
ይህን
ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ አንድ የሞራል ታሪኮችን ያሰባሰበ በውጭ ቋንቋ የተፃፈ ፅሁፍ ነው፡፡ ታሪኩ ግለሰባዊ ሚና ለአገር ግንባታ
ያለው አስተዋፅኦ ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌና አስተማሪ ሆኖ ስላገኘሁት ላካፍላችሁ ወደድኩኝ፡፡
አገር
ሁሉም ሰው በልኩ በሚያውለው ትንሽ የምትመስል አስተዋፅኦ ልክ ይገነባል፡፡ እዚህ ላይ የሃሳቤ ማጠናከሪያ ይሆነኝ ዘንድ የአሜሪካው
ፕሬዝዳንት ጆን-ኦፍ ኬኔዲን ጥቅስ ላስታውሳችሁ ‘’ሃገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን ምን አደረኩላት ብልህ ጠይቅ፡፡’’ ይህ አባባል
በተደጋጋሚ ሲባል ሰምተን ይሆናል ግን ሃሳቡ የገዛን በዛም ማዕቀፍ ውስጥ እንድንመራ ያደረገን ምን ያህሎቻችንን ነው የሚለው ለእናንተ
የምተው ይሆናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሁላችንም ለሃገራችን ብልፅግና ምን አደረግን ብለን በመጠየቅ ራሳችን መፈተሹም አይከፋም፡፡
ዛሬ ስለገናናነታቸው
የምናወራላቸው አገራት ታሪክ የሚያስረዳን አገራቱ በዜጐቻቸው ጥረት የተሻለ ደረጃ መድረሳቸውን እንጂ ሲፈጠሩ ለዜጎቻቸው ምቹ ሆነው
የተፈጠሩ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ይህን እዚሁ ላይ ልቋጭና ቀድም ብዬ ላካፍላችሁ ስልፈለግኩት የሞራል ታሪክ ልመልሳችሁ፡፡
ታሪኩ
በአጭሩ ሲቀመጥ አንድ መሪ አገልጋዮቻቸውን አንድ ሰፊ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ ያዙአቸዋል፡፡ በትዕዛዙ መሠረትም ጉድጓዱ ይቆፈርና ፈሳሽ
እንዲይዝ ተደርጐ ይዘጋጃል፡፡ የሚያስተዳድሯቸውን ህዝቦች ይህን ጉድጓድ በሌሊት በመሄድ በቤተሰብ አንድ ብርጭቆ ወተት እንዲሞሉት
ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ በትዕዛዙ መሠረት አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሰው ጉድጓዱን የሚሞላው በሌሊት ስለሆነ ማንም ስለማያየኝና
ሌሎች ወተት ስለሚሞሉበት የእኔን አንድ ብርጭቆ ወተት አላባክንም ይልና አንድ ብርጭቆ ውሃ በጉድጓዱ ደፍቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
ንጉሱ በጠዋት ተነስተው ወደ ጉድጓዱ ይሄዱና ጉድጓዱ እንዲከፈት አገልጋዮቹን ያዛሉ፡፡ አገልጋዮቹ በትዕዛዙ መሰረት ጉድጓዱን ሲከፈቱት
እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ ጉድጓዱ ጢም ብሎ ሞልቷል፡፡ የተሞላው ግን በወተት ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ውሃ ነበር ይህም ሁሉም ቤተሰብ ሌሎች
ወተት ይሞሉታል በሚል እሳቤ ውሃ በመሙላታቸው የተፈጠረ ነበር፡፡
ይህ ሃሳብ
የሚያስረዳው በጋራ በወሰድነው ጉዳይ ላይ አንዳችን ለአንዳችን መግፋት እንደሌለብንና ይህም እንደ አጠቃላይ አደጋ እንዳለውና ወዳልሆነ
ቦታ እንደሚያመራን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በምንም መላኩ ግለሰባዊ ሃላፊነታችንን ሌሎች ያደርጉታል እኔ ባለደርገው ምን ይላል
በሚል ስሜት ለሌሎች መተው ውጤቱ ውድቀት መሆኑን ነው፡፡
ወደ አገራችን
ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ ለጋራ ቤታችን በጋራ የምንሰራቸው የእያንዳንዳችንን አስተዋፅኦ የሚፈልጉ በርካታ ተግባራት አሉን፡፡ ለዚህ
ደግሞ በየግላችን የምናፈፅመው ሃላፊነታችን እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ከቃል በዘለለ በተግባር ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አገራችንን መገንባትና
የተሻለች ማድረግ የምንችለው እኛው ቀን ከሌሊት በለፋነው ልክ ነው፡፡ በተለይ አሁን አገራችን ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ትግል
ውስጥ እኛ የምንከፍለው ዋጋ ነጋችንን ለማሳመር ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
አሁን
የምንገኝበት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የሁላችንም ርብርብ የሚፈልግ ነው፡፡ በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍል ከመንግስት
ኃላፊዎች ጋር በተቀናጀ ሁኔታ በመስራት እንደ አገር የተቀመጠውን ዓላማ ማሳካት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም አንዱ አንዱ ያደርገዋል የእኔ
ሚና ብዙም ፋይዳ የለውም በሚል እሳቤ ሳይሆን በያገባኛል መንፈስ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ያኔ ይሆናል ብለን በእቅዳችን
ያስቀመጥነው ግቡን ይመታል ማለት ነው፡፡
እንደ
አገር የእድገታችን ማነቆ ተብሎ የተቀመጠውን የመልካም አስተዳደር ችግርም ለመቅረፍ የእያንዳንዳችን ሚና የላቀ ነው፡፡ የሲቪል ሰርቫንቱና
አጠቃላይ ህዝቡም የራሱን ግለሰባዊ ሚና ሳያሳንስ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ በእኔ እምነት
የመልካም አስተዳደር ችግር ለማንም ሊተው የማይገባ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት እንደሆነ ጥልቅ እምነት ከተያዘ ችግሩ በቀላሉ የሚፈታ
ይሆናል፡፡
ሁላችንም
እንደአገር ድህነትን የማስወገድና ልማትን የማፋጠን ሩጫችን ሊሳካና ጉድጓዳችንም በትክክለኛውና ውጤታማ በሆነው ፍሬ ሊሞላ ከሆነ
የየራሳችንን ድርሻ መወጣት ግድ ይለናል፡፡ የእኔ ግለሰባዊ ሚና ለሃገሬ ልማት የማይተካ ነው ብሎ ማመን ትልቅ የልማት ሃይል ነውና፡፡
ሰላም፡፡
No comments:
Post a Comment