EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 9 November 2015

ፈጣን ልማታችን ድርቅን መቋቋም አስችሎናል





በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሀገራት በመከሰት ተፅዕኖውን እያሳደረ በሚገኘውና ኤልኒኖ ተብሎ በሚጠራው የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቀበል አለማችን ግድ እንደሆነባት በተለያዩ አካላት ሲገለፅ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሀገራችንም የኤልኒኖ ክስተት ባስከተለው የዝናብ ወቅትና ዓመታዊ የዝናብ መጠን መዛባት ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች ያልተጠበቁ ጉዳቶችን ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግና እርሱ የሚመራው ልማተዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስትም የችግሩን ስፋት አስቀድመው በመገንዘብ ችግሩን ለመቋቋምና በዜጎችና በኢኮኖሚው  ላይ ሊደርስ የሚችለውን  ጉዳት ለማስቀረት የሚያስችል አቅጣጫ ቀይሶ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡


ኢህአዴግ ያስቀመጠው የኢኮኖሚ ልማት አላማ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ ሀገራችንን ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ የዳበረ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መገንባት ነው፡፡ ማንኛውንም አይነት የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ ካፒታል፣ ሰራተኛ የሰው ኃይል፣ መሬትና እነዚህን በውጤታማነት አቀናጅቶ መጠቀም የሚችል አመራር ያስፈልጋል። በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የካፒታል እጥረት መኖሩና የካፒታል እጥረቱም በአጭር ጊዜ እንደማይፈታም ግልጽ ነው፡፡ በአንጻሩ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይልና ለልማት የተመቸ በቂ መሬት አለ። ይህም በመሆኑ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀውን ኢንዱስትሪን ማእከል ያደረገ ልማት የትም እንደማያደርሰን የታወቀ ነበር፡፡

በሀገራችን ከሚኖረው አጠቃላይ ህዝብ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው በገጠር በግብርና ስራ የሚተዳደረው አርሶ አደርና አርብቶ አደር ህብረተሰብ በመሆኑ ተግባራዊ የሚሆነው የኢኮኖሚ አማራጭ ይህንኑ የህብረተሰብ ክፍል በአግባቡ የሚያሳትፍና ተጠቃሚነቱንም የሚያስጠብቅ መሆን ይገባው ነበር፡፡ በዚህም ምክኒያት ያለንን ሰፊ የሰው ጉልበትና መሬትን እንዲሁም ውስን ካፒታል በመጠቀም የህዝቡ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የልማት ስትራቴጂ መከተል የግድ ይል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ ያለንን አቅም ተጠቅመን ሀገራችን ከብተና ሊታደግ የሚችል ገጠርንና ግብርና ማእከል ያደረገ ስትራቴጂ በመከተል ልማቱን የጀመረው፡፡

በሌላ በኩል አንዳንዶች ቀደም ብሎም ይሁን አሁንም የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም እንደሚሉት ይህንን ገጠርንና ግብርና ማእከል ያደረገውን የእድገት አማራጭ የኋላቀርነት መገለጫ አድርጎ በማቅረብ ዘመናዊ ነው ያሉትን ከፍተኛ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚጠይቀውን ኢንዱስትሪን ማእከል ያደረገ የልማት አማራጭ ሀገራችን እንድትተገብር በድፍረት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እርግጥ ነው ሀገራችን ገጠርንና የአርሶ አደሩን አነስተኛ ማሳ መሰረት ያደረገውን አማራጭ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተላቃ ኢንዱስትሪን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚን መገንባቷን ሁሉም ዜጋ የሚመኘው እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግ ከዚህ አማራጭ የተለየ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርፆ ተግባራዊ ሲያደርግ ዜጎችም ቢሆኑ ሀገራችን ኢንዱስትሪ መር የእድገት አማራጭ ቢኖራት የብዙዎች ፍላጎት እንደሆነ ሳያውቀው ቀርቶ ሳይሆን  ማስቻያዎቹ የሚባሉት ከፍተኛ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና የሰለጠነ የሰው ኃይል በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ያልተፈጠሩና በአጭር ጊዜም በተሟላና ተወዳዳሪ መሆን በሚያስችል ሁኔታ ሊፈጠሩ እንደማይችሉና እንዲሁም ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር በሂደት አቅም እየተገነባ መሄድ እንደሚገባው ከማንም በላይ በሚገባ ቀድሞ መረዳት በመቻሉ ብቻ ነው፡፡

ኢህአዴግ የተግባር ድርጅት ነው ሲባልም ህዝብን በማማለል የማይሆነውንና የማይተገብረውን ሁሉ ቃል በመግባት የሚነጉድ ሳይሆን ሊሳካ የሚችለውን በመተግበር በሂደት በሚፈጠር ሀገራዊ አቅም የማይቻል ይመስል የነበረውን በተጨባጭ ሰርቶ በሚያስመዘግባቸው ውጤቶች ማሳየት በመቻሉ ነው፡፡ ይህ እውነታና ድርጅታዊ ጥንካሬው ነው ኢህአዴግን መንግስታዊ ስልጣንን ለመጨበጥ በተደረጉ ተከታታይ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ህዝቡ ይሁንታውን እንዲሰጠው ያደረጉትና በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ምርጫዎች ሲታይ ደግሞ ህዝቡ በሰጠው ድምፅ ኢህአዴግ ላስመዘገባቸውና እያስመዘገባቸው ለሚገኙ ስኬቶች የበለጠ እውቅና በመስጠት የድርጅቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር የሀገራችን ህዳሴ መሆኑ አብዛኛው የሀገራችን ህዝብ መግባባት ላይ የደረሰበት ጉዳይ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

በ1993 የኢህአዴግን ተሃድሶ ተከትሎ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂያችን ነጥሮ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረጉ በሀገራችን ለተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ባለፉት 24 አመታት ያደረግነው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በቀደሙት ስርዓቶች የተረጂነትና የኋላቀርነት መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ የነበረው ግብርናችን የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር አልፎ በሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወት አስችሏል። የሰው ጉልበትን በስፋት በማነቃነቅና መሬትን በአግባቡ በመጠቀማችን ሀገራችን ለ12 ተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ሲሆን ባለፉት አመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደጋችን እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን እንድንችል አስችሎናል።

የተከተልነው ትክክለኛ ፖሊሲያችን ለህዝባችን የመስራትና የመለወጥ ፍላጎት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ምርታማነታችን ከፍተኛ እድገት እየተመዘገበበት መጓዝ ችሏል። በ1983 በዋና ዋና ሰብሎች 52 ሚሊዮን ኩንታል የነበረውን ዓመታዊ የምርት መጠን በ2006ዓም 269 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ችለናል። ከዚህ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ የአርሶ አደሩ እርሻ አማካኝነት መሆኑን ሲታሰብ ኢህአዴግ አርሶ አደሩና የግብርናው ዘርፍ የዕድገት ምንጭ እንዲሆን የተከተለውን ፖሊሲ ትክክለኛነት ያረጋገጠ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እድገቱ ዘላቂና ሁሉን ዜጎች ተጠቃሚ በሚያደርግ አግባብ እውን እንዲሆንና የእድገታችን መሰረት ግብርና በመሆኑ የግብርናው እድገትና ምርታማነት የአለም አቀፉን የአየር ንብረት መዛባት ሊቋቋም በሚችልበት አግባብ ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

በሀገር ደረጃ አርሶ አደሩን በስፋት በማሳተፍ የተፋሰስ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ የአፈሩን ለምነትና እርጥበት በመጨመር የመሬት ምርታማነትን ማሳደግ የተቻለ ሲሆን አለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው የዝናብ ሁኔታ መዛባት ሊፈጠር የሚችለውን የግብርና ምርት መቀነስን መቋቋም የሚያስችል አቅም በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች በመፈጠር ላይ ይገኛል፡፡ በሁሉም የሀገራችን ክልሎች መላው አርሶ አደር ለተፋሰስ ልማቱ እውን መሆን የሚያደርገው ተሳትፎ ከአመት አመት እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን ለግብርናው እድገት ቀጣይነት ዘላቂ ዋስትናን የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ሀገራችን የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ መላ አርሶ አደሩ የዘላቂ ልማቱ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል ስኬታማ አድርጓታል፡፡

ሀገራችን ለአለም የአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ የእድገት አማራጭ በመገንባት የምታሳየው ስኬታማ ተሞክሮ ለመላው አለም እየቀረበ ሲሆን ሀገራችን አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለምድራችን የሙቀት መጨመርና ለአየር ንብረት መዛባት ዋነኛ መንስኤ የሆኑትን የተበከሉ ጋዞች የልቀት መጠንና ኢ-ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለመቀነስ ዘመቻ እንዲያደርግ ለማንቀሳቀስ በመሪ ተዋናይነት እንድትሰለፍ በማስቻል በዚህም መላ አፍሪካዊያን፣ የአለም ታዳጊ ሀገራትና በመስኩ ጥናት የሚያደርጉ በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲቸሯት አድርጓል፡፡ ይህም በታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ  የተመራ የነበረ ሲሆን አሁንም በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጓድ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግንባር ቀደም መሪነት ተግባራዊ በመሆን እየቀጠለ ይገኛል፡፡ ይህ እውነታም እኛ ብቻ የምንናገረው ሳይሆን መላው የአለም ማህበረሰብ እየመሰከረው ያለ ሃቅ ነው፡፡

የግብርና ምርታችን እያደገ የመጣውን የህዝባችን ቁጥር ከመመገብ አልፎ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኢኮኖሚ መሪነቱን ይዞ ዘልቋል። አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያው አቅም እንዲፈጥር አድርገናል፡፡ ለዚህም ስኬት ገበያ መር የአመራረት ስልት መከተላችንና ይህንኑ ለማገዝ የሚያስችሉ የባለሙያ፣ የተቀናጀ አመራርና የግብዓት አቅርቦት ማሟላታችን በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በ1994 ዓም  14 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የተረጂዎች ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ መጥቶ በ2006 ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል። ይህም ህይወቱ በሚሰፈርለት እርዳታ ላይ ተመሰረቶ የነበረውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ድርቅ በተከሰተ ቁጥር የበርካታ ዜጎች ህይወት ሲቀጠፍበት የነበረውን ሁኔታ በማስቀረት ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት ሲሆን ይህም ኢህአዴግ አርሶ አደሩና የግብርናው ዘርፍ በሀገሪቱ የዕድገት ምንጭ እንዲሆን የተከተለውን ፖሊሲ ትክክለኛነት በተጨባጭ እንዲታይ ያደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ በ1988 በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 47 ነጥብ 5 በመቶው በድህነት ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን የድህነትን ተራራ ለመናድ ባደረግነው ርብርብ ሀገራዊ የድህነት መጠኑ በ2005 ወደ 26 በመቶና በ2007 መጨረሻ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 22 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚወርድ ማድረግ የተቻለው በተከተልነው ፖሊሲ ውጤታማነት ነው።

ቀድሞ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ዘይቤ ውስጥ የነበሩ በርካታ አርሶ አደሮች አሁን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ወደ መገንባት ተሸጋግረዋል። በአለባበስ፣ በአመጋገብና በአኗኗር ለውጥ አምጥተዋል። ተንቀሳቃሽና መደበኛ ስልክ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ እንዲሁም ሌሎች ቴክኖሎጂዎችንና መገናኛ ብዙሃን መጠቀም ጀምረዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት ማፍራት የጀመሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችም በየአካባቢው ተፈጥረዋል። ባፈሩት ሃብት በተለያዩ መስኮች የሚሳተፉ ኢንቨስተሮች ለመሆን በቅተዋል።

ግብርናው በሚያመነጨው ሃብትና ጥሬ ዕቃ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች በፍጥነት እያደጉ ናቸው። ኢኮኖሚያችን ገና ታዳጊ ቢሆንም በእነዚህ ድምር ውጤት ከአንዳንድ የበለጸጉ ሀገሮች በተሻለ ሁኔታ የሥራ አጥነትን ችግር ተቋቁመን በህዳሴ ጉዞ ወደፊት መገስገስ ቀጥለናል። የመሬት ፖሊሲያችን ለዘመናት የምንታወቅበት የረሃብ ታሪክ እንዲቀየር ከማድረጉም ባሻገር እንደርስበታለን ብለን ባስቀመጥነው ግብ አቅጣጫ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራችን ሽግግር መሰረት እየጣለ ነው።

በሌላ በኩል ወትሮም ቢሆን የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ኢህአዴግን ለመተቸት ዘግይተው የማያውቁትና የራሳቸውን አማራጭ ፖሊሲ ለህዝብ ከማቅረብ ይልቅ በኢህአዴግ ላይ የሚስተዋሉ ጥቃቅን የአፈፃፀም ጉድለቶችን አጋኖ በማቅረብ የሚታወቁ አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወቅታዊውን የኤልኒኖ ክስተት እንዲሁ የኢህአዴግ የፖሊሲ ውድቀት ማሳያ ነው እንዲሉ እድሉን በማግኘት የተለመደውን የኢህአዴግን ስኬቶች የማጠልሸት ዘመቻቸውን እንዲከፍቱ አስችሏቸዋል፡፡  በመሆኑን ይህን መሰረተ ቢስ ዘመቻቸውን በትክክል ለመገንዘብ እንዲረዳ ኢህአዴግ የሚከተለውን የእድገት አማራጭና ያስገኛቸውን ስኬቶች እንዲሁም ወቅታዊውን የኤልኒኖ ክስተት በተናጠልና ሊኖራቸው ስለሚችል ግንኙነት ማየት ተገቢ ነው፡፡

የሀገራችንን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታዎች በአግባቡ በማገናዘብ ቀርጸን ተግባራዊ እያደረግን ያለነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ ሀገራችን በእድገት ጎዳና እንድትጓዝ በማድረግ ለአህጉራችንም ይሁን ለመላው አለም የእድገት ተምሳሌት እንድትሆን እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአለምን የሙቀት መጨመር ተከትሎ በበርካታ ሀገራት በመከሰት የዝናብና የሙቀት ሁኔታ መዛባትን በማስከተል ላይ ባለው የኢልኒኖ ክስተት ምክንያት የተፈጠረው የድርቅ ሁኔታ በየትኛውም መመዘኛ የኢህአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድክመት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ አንባቢያንም ይህን በትክክል መረዳት እንዲችሉና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማገዝ ስለ ኢልኒኖ ክስተትም በአጭሩ ማብራራት አስፈላጊ ስለሚሆን እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የአለማችን የአየር ንብረት መዛባት ከሚያስከትላቸው ክስተቶች አንዱ ኤልኒኖ (El Niño) ነው፡፡ ለኤልኒኖ ክስተት ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው የምስራቃዊ ውቅያኖስ የሙቀት መጨመር ነው፡፡ በአለማችን ኤልኒኖ በአማካይ በ10 ዓመት አንዴ የሚከሰት ሲሆን በአብዛኛው ከ9 እስከ 18 ወራት ሊቆይ የሚችልና ረጅም ርቀት ሄዶ በበርካታ ሀገራት ተጽእኖ የማሳደር አቅም ያለው ውስብስብ የአየር ፀባይ ክስተት ነው፡፡ ኤልኒኖ በአለማችን በተለያዩ ጊዜዎች ተከስቶ ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የምስራቅ ፓሲፊክ ውቅያኖስ የሙቀት መጠን ከመደበኛው ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ2.5-3.0 ድግሪ ሴልሸስ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ሀገራችንን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት የኤልኒኖ ክስተት አጋጥሟል፡፡ በዚህም በተለያዩ ሀገሮች የተለያዩ ተፅዕኖዎችን እያሳደረ ሲሆን የዝናብ ወቅትና መጠን በማዛባት፣ በጣም ከፍተኛ የሆነ ወይም ቀዝቃዛ የሙቀት ሁኔታውን እንዲኖር በማድረግ ተፅዕኖውን በማሳረፍ ሀገራት ችግር ውስጥ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

በሀገራችን ኤልኒኖ መከሰቱ ከታወቀበት ከግንቦት 2007 ጀምሮ በዋናነት መደበኛ የዝናብ ስርጭት እንዳይኖር በማድረግ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን መደበኛ የግብርና እንቅስቃሴዎችና የእንሰሳቱን ሁኔታ ውስብስብና አስቸጋሪ እንዲሆን እያደረገ ነው፡፡ በተለይ በሀገራችንን ሰሜናዊና ስንጥ ሸለቋማ አካባቢ የሚገኘውን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ማህበረሰብ በባሰ መልኩ የችግሩ ተጋላጭና ተጠቂ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከኤልኒኖ ክስተት መረዳት የሚቻለው ሀገራት ክስተቱን ማስቀረት የሚችሉበት ሁኔታ የሌለ መሆኑንና ከተከሰተ በኋላ የሚፈጥራቸውን ችግሮችና ጉዳቶች ለመቋቋም የሚከተሉት አማራጭና ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የሚኖራቸው ሀገራዊ አቅም መነጋገሪያ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ በሌላ በኩል የኤልኒኖ ክስተት በቀጥታ የአንድን ሀገር የፖሊሲ ድክመትና ጥንካሬ መለኪያ ተደርጎ ሊቀመጥ እንደማይችል መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን በኤልኒኖ ክስተት የተፈጠረውን ችግርና ጉዳት ሀገራት በራሳቸው ለመታደግ የሚኖራቸው አቅም አጠቃላይ የሀገራዊ የእድገት አማራጭ ፖሊሲያቸው ውጤታማነት መለኪያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑ ነው፡፡

በኢልኒኖ ክስተት በተፈጠረው ድርቅ ምክንያት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን በምግብ እህል ተረጂ የሚሆኑ ዜጎች ሀገራችን በራሷ አቅም ይህንኑ ለመቋቋም ባከማቸችው እህል መታደግ የቻለችበት ሁኔታ የምትከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማነት የሚያሳይ እንጂ የውድቀት መለኪያ ተደርጎ ሊቀመጥ አይችልም፡፡ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የድርቅ ሁኔታ ሲከሰት ዜጎችን ለመታደግ የውጭ ሀገር እርዳታን እንደዋነኛ አማራጭ በመውሰድ ጥሪ የሚደረግበት ሀገራዊ ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሮ ሀገራችንና ዜጎቿ ባደረጉት ከፍተኛ የልማት ርብርብ ያስገኘው ፈጣንና ተከታታይ እድገት በፈጠረው አቅም በእጅጉ መቀየር በተቻለበት ማንም ይህን የድርቅ ክስተት የኢህአዴግን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥንካሬ ማሳያ ከማድረግ በዘለለ በድክመት እንዲተች ማሳያ ለማድረግ አያስችለውም፡፡


በሀገራችን በተለያዩ ወቅቶች ድርቅ የተከሰተ ሲሆን እነኝህ የድርቅ ዓመታት ከዓለም አቀፍ ኢሊንኖ ክስታት ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት እንደነበራቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ  ከ20 ዓመታት በፊት  ሲከሰት የነበረው ድርቅ ዜጎችን ለሞት፣ ለአስከፊ ሰቆቃና ችግር  እንዲሁም ለስደት ሲዳርግ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 


እኤአ በ1953 ዓም የተከሰተው ኢሊኖ በኢትዮጵ በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እኤአ በ1953፣ 1957-58፣ 1965ና 1969 ድርቅን አስከትሏል፡፡ እንዲሁም እኤአ በ1972-73 ዓም የተከሰተው የኢሊኖ ክስተት እስከ 1979 ዓም በተለያዩ ወቅቶች የድርቅና የጎርፍ ችግር አስከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል፡፡ እኤአ በ1982 እና 1983 ዓም በተመሳሳይ መልኩ የኢሊኖ ክሰተት የታየ ሲሆን ይህ ክስተት በተለይ እኤአ 1982ና 83 በመቶ ሺዎችም የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞትና ለስቃይ ደርጓል፡፡


ኢህአዴግ ሀገር ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ የኤሊኖ ክሰተት የሚያስከትለው ድርቅ በተለያዩ ጊዜያት የታየ ቢሆንም  በሰዎች ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በተሰሩ ስራዎች ድርቅ የከፋ ችግር አላደረሰም፡፡ እኤአ በ1987-88፣ 1989-90፣ 1991-92፣ 1993-94፣ በ1996 እንዲሁም በ1997-98 ዓም ኢሊኖ ያስከተው ድርቅ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ድርጅታችንና እርሱ የሚመራው መንግስታችን ተቋቁመውታል፡፡ 

ፈጣኑ ልምታችን ድርቅ በሰዎች ህይወት ላይ እንዳያደርስ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የ1977 ዓም ዓይነት አይደለችም፡፡ በብዙ መስኮች አመርቂ ድሎች የተጎናጸፈችና በፈጣን ዕድገት ላይ የምትገኝ ናት፡፡ የተከሰተው  ድርቁ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገችም ትገኛለች፡፡ በቀጣይም ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅና ኢኮኖሚውንም ወደ ኢንዱስትሪ መሪነት ለማሸጋገር በመትጋትም ላይ  ነች፡፡

No comments:

Post a Comment