EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 14 November 2015

እየሞተ ያለው በሃሳብ ድርቅ የተመታው? ወይስ በኢልኒኖ የተጎዳው?

ሠይፈ ደርቤ/ኢዜአ/

ዓለማችን ለድርቅ አደጋዎችና የረሃብ ክስተቶች አዲስ አይደለችም። በረሃብ ሳቢያ ብዙ ሺዎች አሳዛኝና ዘግናኝ በሆኑ ሁኔታዎች የሞቱባቸው ሀገሮችን ጨምሮ ጫማ ቀቅለው እስከ መብላት የደረሱ ህዝቦችን አስተናግዳለች።

እነዚህ ያኔ… የተራቡ፣ ጫማም ቀቅለው እሰከ መብላት የደረሱ ህዝቦች ከዚህ በላይ ውርደት የለም በሚል ቁጭት እጃቸው እስኪላጥ ሰርተዋል፤ ወገባቸው እስኪጎብጥ፣ ዓዕምሯቸው እስኪታወክም ለፍተዋል። እንቅልፍ አጥተው በመትጋት ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለውጠዋል። የዚህ ታሪክ ባለቤት ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርቅ ተደጋጋሚ ጉዳት ሲደርስባቸው ለሚስተዋሉ ድሃ ሀገራትና መንግስታት ችግር ፈጣን ምላሽ እስከመስጠት ደርሰዋል፤ በአንፃሩ በራሳቸው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ተቋቁመው ህዝቦቻቸውን መመገብ ችለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ሀገሮች ያሉትን ያክል ለአሳዛኞቹ አጋጣሚዎች መፈጠር ምክንያት ከመሆን ጀምሮ ተፈጥሮ ለድርቅ ያጋለጠቻቸውን ህዝቦች ስቃይ ለግላዊ አጀንዳዎቻቸው ፍላጎት መሳካት የሚጠቀሙ ቡድኖችና ቡድኖቹን ስፖንሰር የሚያደርጉ እጀ ረጅም መንግስታትም አሉ፡፡ እነዚሁ ቡድኖች ተፈጥሯዊ የሆኑ የድርቅ አደጋዎችንና ከጦርነት ጋር የተያያዙ የእርስ በእርስ ግጭቶችን በጥፋት ድጋፍ አንረው ህዝቦቹን ለከፋ እልቂት በመዳረግ፣ ከችግር ለመውጣትና መፍትሄ ለማፍለቅ የሚቀየሱ የፖሊሲ አማራጮችን ጣልቃ በመግባት ጭምር ውድቅ እስከ ማድረግ፣ ከተቻላቸውም የማያባራ ግጭትና ትርምስ ጭረው የችግሩ ምንጭ ከስርዓቱ የፈለቀ በማስመሰል ዜጎች በሀገራቸው ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው ጥርጣሬ ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ።

በቅርቡ ኢልኒኖ ባስከተለው የአየር መዛባት ሳቢያ በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ድርቅ የተለያየ ወገኖች ለመንስኤና መፍትሄ ያልቀረቡ መላምቶችን ሲሰነዝሩ አስተውለናል፡፡ አስተያየቶቹ ከተጨባጩ ሀቅና እውነታ ያፈነገጡ፣ ዓለም በግልፅ ከሚያውቃቸው እውነታዎችና እየሰነዘራቸው ካሉ ሃሳቦችም ጋር የተፃረሩ ሆነው መገኘታቸው ደግሞ ለትዝብት ሲዳርጉ ተመልክተናል፡፡

ድርቁ ያለበትን ደረጃና ስፋት ክብደት መንግስት ከሚመክትበት አሰራር ጋር አነፃፅረው በሚዛናዊነት ጠቃሚ ድጋፍ የሚያስገኝ ሀሳብ ከመሰንዘር ይልቅ በተለመደ ጨለምተኝነት የሚሰነዘሩ ትችቶች የሀሳቦቹን አመንጪዎች ፍላጎት የሚያጋልጡ ሆነውም ተስተውለዋል፡፡
የሰሞኑ የቢቢሲ ዘጋቢ ደግሞ የየትኛውም ዓለም ጋዜጠኛ እንደሚያደርገው እውነታውን ፈልፍሎ ከማውጣትና ከማሳወቅ ይልቅ በ77ቱ የሀገሬ ረሃብ እነ ጊልዶፍ ምፅዋት የለመኑላትን ኢትዮጵያ ከ30 ዓመት በኋላ ለማየት በመመኘት ከእውነታው ይልቅ ግላዊ ፍላጎቱን አግዝፎ ድርቁ ረሃብ ወልዶ፣ ረሃቡም ሞት አጋብቶ የማየት ህልሙን ሊያጋባብን ሲሞክር አስተውለናል፡፡ ወደዚሁ ጉዳይ በቀጥታ ከመግባታችን በፊት በድርቅና በረሃብ መካከል ያለውን አንድነትና ልዩነት ወደ ማየት እናምራ።

ድርቅና ረሃብን አመሳስለው የሚመለከቱ ወገኖች ያሉ ቢሆንም በሁለቱ ጉዳዮች መካከል እጅግ ሰፊ ልዩነት መኖሩ አሌ የሚባል አይደለም፤ ይሁንና የሁለቱን አንድነትና በመካከላቸው ያለውን ሰፊ ልዩነት ለመረዳት ስለ ጉዳዩ ዘርዘር አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡

በድርቅና በረሃብ መካከል እጅግ በጣም ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የረሀብ መከሰት የድርቅ መኖርን ሊያመላክት ቢችልም፣ የድርቅ መከሰት ግን የረሃብ መኖር ማሳያ ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም። በሌላ አነጋገር ድርቅ ፈፅሞ የረሃብ መከሰት አረጋጋጭ አይደለም። ይህ ሲባል ግን ድርቅ በአግባቡ ተገርቶ ጉዳቱን መቋቋም ካልተቻለ ሰብዓዊ ጥፋት በማስከተል ወደ ረሃብ አይሸጋገርም ማለት አይደለም።

ለረሀብ መከሰት ድርቅ ምክንያት ሊሆንባቸው የሚችሉ አጋጣሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ድርቅ ስለተከሰተ ረሃብ አለ ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ በአሜሪካ በተለይም ለረጅም ዓመታት በካሊፎርኒያ፣ በአውስትሬሊያ፣ በደቡብ አፍሪካና ሌሎች ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሀገሮች የደረሰው ድርቅ ረሃብ አስከትሏል ተብሎ በተነገረ ነበር፡፡

ድርቅን ተከትሎ የሚከሰት የትኛውም አይነት ረሃብ ለዕለት የሚሆን ጉርስ ባለማግኘትና እጅግ አስከፊ በሆነ ፈፅሞ ምግብን ማዳረስ በማያስችል ምክንያት እንዲሁም በሰዎች እልቂት የሚገለፅ ለመሆኑ መቼውንም ከድርቅ አደጋ ፀድቶ የማያወቀው የዓለማችን ተሞክሮ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለተከሰተው ድርቅ ሃሳብ ሊያነሳና ሊከራከር የሚሻ ማንም ወገንም ችግሩን በተጨባጭ በማሳየት የመፍትሄው አካል መሆን የሚችለው፣ እውነታውን ይዞ ለመሞገት ሲዘጋጅ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ምክንያታዊነት ከችግሩ መንስኤ በመነሳት ለውጤት የሚያበቃውን ትክክለኛ አማራጭ የማመላከት እድልም ይሰጣል።

ድርቅና ረሃብ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። አልፎ አልፎ አንዳቸው ለሌላኛቸው የመነሻ ምክንያት የማይሆኑበት ሁኔታም አለ። ባለሙያዎች የድርቅን መነሻዎች በሶስት ፈርጅ ይከፍሏቸዋል። ይኸውም ከሜትሮሎጂያዊ ወይም ከአየር መዛባት ጋር በተያያዘ የሚከሰት ድርቅ፣ ከውሃ መንጠፍ ወይም ወደ በረሃማነት መቀየር ጋር የተያያዘ ድርቅ እንዲሁም ከግብርና ምርት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ድርቅ ናቸው ይላሉ። ሶስቱን የድርቅ መንስኤ አይነቶች ስንመለከት ኢትዮጵያን ያጋጠማት ድርቅ የትኛው እንደሆነ አስቀድመን የምንተነብይበት እድል እናገኛለን፡፡

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ከአየር ንብረት መለወጥ ጋር በተያያዘ በዝናብ እጥረት ምክንያት ያጋጠመ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ዝናብ በተጠበቀበት ጊዜ ስላልመጣ፣ ይልቁንም ጨርሶ ስለጠፋ የደረሰ ነው፤ ዝናብ ታይቶበታል በተባለውም አካባቢ በቂ ባለመሆኑ ለሰብሉ ወይም ለሚፈለገው መኖ መድረስ በቂ አስተዋፅኦ አላበረከተም በሚል ሲገለፅም ሰምተናል፡፡

የዝናቡን መጥፋት ተፈጥሯዊ አድርገን ካየነው፣ ክስተቱን ለመከላከል በቂ የውሃ አቅርቦት አልነበረንም ወይ ወደሚለው መምጣት እንችላለን። በሀገራችን ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የደረሱ ጉዳቶች ቀድሞውኑ ለመስኖ የሚሆን ቅርብ አማራጭ ያልነበራቸው፣ ነገር ግን ዝናብ ሲኖር በውሃ ማቆር ፍላጎትን ከማግኘት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ መሰል ዘዴዎች ውሃና መኖ ሲጠቀሙ የነበሩ ናቸው። አንዳንዶቹም ይኸው አየር ፀባይ ባስከተለው ጉዳት የውሃ ክምችታቸውን ከበቂ በላይ በሆነው ሙቀት ያጡ ናቸው። ዓለም በኢትዮጵያ ተከሰተ በማለት ሲገልፀው የነበረው ድርቅ ይህን አይነቱን ነው፡፡ ዓለም ኢትዮጵያን አጋጠማት እያለ የሚገልፀው የድርቅ አደጋ እንጂ የረሃብ አደጋ አይደለም፡፡ የተረጂዎች ቁጥር ጨምሯል እንጂ የረሃብ ሟች ተፈጥሯል በሚልም አልገለፀም፤ ተጨባጩ እውነታም ይህን ፈፅሞ አላመላከተም፡፡

አንዳንድ ፅንፈኝነት የተጠናወታቸው ቡድኖች ደግሞ መንግስት ምርታማ ነኝ፤ ፈጣን እድገትና ኢኮኖሚ አስመዝግቤያለሁ እያለ ባለበት ወቅት 10 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ ምግብ መፈለጉ ድሮም ልማት እንዳልነበረ ያሳያል ሲሉ ይናገራሉ፤ ችግሩንም የመንግስቱ ባህሪና ፖሊሲው ያመጣው ነው ሲሉ ይገልፃሉ፡፡

የእነዚሁ ወገኖች ትችት እርባና የለሽ መሆኑን የሚያረጋግጠው ሀሰተኛ ባህሪያቸው ብቻ አይደለም፤ ቡድኖቹ ካምፕ ባደረጉባቸው ሀገሮች ያሉ የመገናኛ ብዙሃናት ጭምር ያረጋገጧቸውን ሀቆች ሙሉ በሙሉ ክደው የተለመደውን የበሬ ወለደ ትችት መሰነዘራቸውም ጭምር ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እንዳረጋገጡት በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በሀገራዊ ምርት እጥረት ሳቢያ የተከሰተ አይደለም፡፡ ሀገራዊ ምርት እጥረት ተከስቶ ቢሆን ኢልኒኖ የተባለው ምክንያት ተጠቃሽ ባልሆነም ነበር፡፡ የምርት ውድቀት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና ለተጎጂዎች የሚሆን የምግብ ሰብል በሀገር ውስጥ ባልተገኘም ነበር፡፡ የምርት እጥረት ያስከተለው ጉዳት ቢሆን ኖሮ ለገበያ የሚሆን ምርት ባልቀረበ፣ እድገትም ባለተመዘገበ ነበር፡፡ እነዚህ በድምሩ የቀረቡ ሃሳቦችና እውነታዎች ናቸው ዓለም አቀፍ መንግስታትን በኢትዮጵያ በኢልኒኖ ምክንያት ባጋጠመ የአየር መዛባት የድርቅ አደጋ ተከስቷል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ድርቁን ለመቋቋም አቅም አለው በማለት እንዲመሰክሩ ያደረገው፡፡

ስለሆነም በሀገራችን ድርቅ ቢከሰትም በቂ የምግብ እህል ክምችት በመፈጠሩ ከ8 ሚሊየን የሚልቁ ዜጎቻችን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። ይህም የእህል ክምችቱ እንዲፈጠር ያደረገው አምራች ኃይልና ምርቱን ያስገኘው ትክክለኛ ፖሊሲ ውጤት ትስስር ስኬታማ መሆኑን ያመለክተናል። በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የፖሊሲ ችግር ያላስከተለው፣ የምርት እጥረት ያልፈጠረውና የስልተ ምርቱም ሆነ የመንግስቱ ባህሪ ተፅዕኖ ያላመጣው እንደሆነ ያስገነዝበናል።

ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ጉዳቶችን ምሁራን ኢልኒኖ እና ላኒና በማለት ይገልጿቸዋል። ኢልኒኖ ያልተለመደና ከሚጠበቀው በላይ ሙቀት ሲጨምር የሚከሰት ሲሆን ላኒና ደግሞ በተቃራኒው ከሚጠበቀው ቅዝቃዜ ያለፈ  የቅዝቃዜ ክስተት ሲደርስ የሚያጋጥም ነው፡፡ ኢልኒኖ የዝናብ ስርጭትንና መጠንን በማዛባት የውሃ እጥረት እንዲከሰት በማድረግ የሰብል ምርትን በእጅጉ የሚጎዳ ሲሆን ላኒና ደግሞ የዝናብ መጠንን በመጨመር ለጎርፍና ተያያዥ  አደጋዎች ያጋልጣል፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ያጋጠመው ድርቅ የአየር ንብረት መዛባት ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች አንዱ በሆነው ኢልኒኖ የተከሰተ ነው እየተባለ በባለሙያዎችና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃናት ሲነገር የሚሰማው።

 

በአጠቃላይ ኢልኒኖም ሆነ ላኒና የውስብስብ የአየር ፀባይ ክስተቶች መገለጫ ናቸው፡፡ እነዚሁ ክስተቶች  በተደጋጋሚ እንደሚገለፀው በፓሲፊክ ውቅያኖስ የሙቀት መቀያየር ምክንያት በዓለማችን ሀገሮች በተለያዩ ጊዜያት ተከስተው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህም ሀገራችን አንዷ ናት።

 

ስለሆነም በቅርቡ በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ ኢልኒኖ ያስከተለውና ሜትሮሎጂካል በሆነ መልኩ ለድርቅ የተጋለጥንበት ክስተት ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮም በርካታ ሀገሮች የችግሩ ሰለባ መሆናቸው እየታወቀ የቀኝ አክራሪ አስተሳሰብን ሀገራችን ባለመቀበሏና የማይጠመዘዝ ጠንካራ መንግስት በመመስረቷ ምክንያት ብቻ ምንም አይነት ተፈጥሯዊ ችግር ባጋጠመ ቁጥር ፖሊሲያችን ላይ ጥያቄ የሚያጭሩ ወገኖች ክስ ድርደራ የተለመደ ሆኗል።

ዓለም አቀፍ መንግስታት ሳይቀር ለችግሩ መከሰት ሳይንሳዊ ትንታኔ በመስጠትና የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን የመፍታት አቅም ያለው መሆኑን በመግለፅ ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ ፅንፈኞችና በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የፖሊሲ ልዩነቶች ጥቅሞቻቸውን የነኩባቸው ኃይሎች ያለ በቂ መረጃ ድምር ውግዘት ማሰማታቸው ችግሩን ለመቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረትም ሆነ በዘላቂነት ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገውን ትግል የሚቀለብሰው አይሆንም፡፡

ይልቁንም የእነዚህ ወገኖች ድምር ውግዘት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በመቆርቆር ሳይሆን ድርቁ ሞት እንዲወልድ፣ ሞቱም የፖሊሲና የስርዓት ጥያቄ ሆኖ እንዲወሰድ፣ የሚጠሉት ስርዓትና ኢህአዴግም እንዲወገዝ ካላቸው ወደር የለሽ ፍላጎት የመነጨ መሆኑ በግላጭ ይታያል፡፡ የሰሞኑ የቢቢሲ አስመሳይና አደናጋሪ ዘገባም ከዚሁ ጭብጥ አልባነት የዘለለ ትርጉም እንደሌለው የሚያስረዳ ነው፡፡

ድርቁ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል እየሰራ ያለው መንግስት ዓለም አቀፍ ድጋፍ በሚፈለገው መልኩ እየተገኘ አለመሆኑን በመግለፅና ድጋፉ በሚጠበቀው መልኩ ካልተገኘም ለልማት የያዘውን በጀት በማዞር የዜጎችን ህይወት ለመታደግ እንደሚሰራ እየተናገረ ባለበት፣ ይህንኑም በተግባር ባረጋገጠበት በዚህ ወቅት፣ የውግንና ትርጉም ያልገባቸው ፅንፈኞች አጀንዳቸውን ስተው የፖሊሲ ጥንቆላና ወገዛ ስራ ላይ መግባታቸው ለኪሳራ የሚዳርጋቸው መሆኑ የማይቀርም ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የነበሩ ስርዓቶች አሁን ያለውን ህዝብ ግማሽ ያህል ቁጥር ይዘው እንኳ ሊቋቋሙ ያልቻሉትን ተረጂ፣ በራሱ አቅምና በፈጠረው የግብርና ምርት ክምችት እደጉማለሁ እያለ ሀብት የፈጠረውን መንግስት ፖሊሲና ፖሊሲው የተዋቀረበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አዕማድ ደካማ አድርገው ሊቆጥሩ መከጀላቸውም ከተነሱበት ደካማ መከራከሪያና ውንጀላ አኳያም እነዚህን ወገኖች አትራፊ ሊያደርጋቸቸው አይችልም፡፡

ይልቁንም ቅኝታቸው ስርዓቱ የፈጠረው ከፍታና ሀገራችን በአካባቢው ሀገሮች ያላት ሁለንተናዊ የበላይነት አንሶ እንዲታይ ከመሻት ጋር በእጅጉ የተያያዘ፣ የውርደት ታሪካችንን ቀይረን ለመጓዝ የጀመርነውን መንገድ ለማኮላሸት ያለመ፣ በታሪካችን መዘባበቻ ያደረገንን ተደጋጋሚ ረሃብ በልማታችን አሸንፈን ያሰረዝነው የረሃብ ስም ዳግም መጠሪያችን እንዲሆንና የኩራታችን ምንጭ የሆነው ማንነታችንን ለመፈታተን የተጠነሰሰ ዘመቻ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስም የሚቆምሩትም ሆነ በማህበራዊ ድረገፆች የሚቀነቀኑት ሃሳቦች ከድርቅ፣ ረሃብ ብሎም ሞት አንዲወለድ ከመሻት የሰብዓዊነት መንጠፍ ጋር የተያያዘ አጉል ምኞትን ከማስተጋባት የዘለለ አይደለም፡፡ እነዚህ ወገኖች ከዜጎች ህይወት ይልቅ ድርቁ ሞት ፈጥሮ ማየት የሚገዳቸው የመሆናቸው ጉዳይ ደግሞ ኢልኒኖው ካራቆተው ተፈጥሮ በላይ የሃሳብ ድርቅ ያናወጠውና ያራቆተውን ማንነታቸው እንዲጋለጥ የሚያደርግ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment