ስንቶች ተኮላሽተው ካረንቋው ዘቀጡ፣
ስንቶች ተቸንፈው ከጐዳናው ወጡ፣
ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው፣
ነግ አልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው
የፋሽስቶች አብሪት ድንፋታው ሳይገታን፣
የከላሾች ሴራ አፈናው ሳይረታን ፣
ግራ አድርባይ መስመር ሳያንበረክከን፣
ጨለምተኛ እምነቶች ከቶም ሳይበግሩን፣
ንፁሁ ደማችን ፈለግ ብርሀን ሆኖን ፣
ብሩኀ አዲስ ዓለም በትግል እናያለን።
የከፋ የከረፋ መአት ይወረድብን፣
ልክ የለሽ መከራ እንቅፋት ይግጠመን፣
የፋሽስቶች ነዲድ ነበልባሉ ይግረፈን ፣
ክልሱ እምነታቸው ውሸቱ ያናፋብን ፣
በትግል በእምቢታ በአመጽ እንጠራለን፣
በንፁህ ደማችን ችቦ እናበራለን።
የኬጂቢ ሴራ ስለላው ይጠረን ፣
የሚሳኤል መንጋ ሚሊዮን መድፉ ይክበበን፣
የባሩድ ጪስ ዳምኖ ሰማይ ጥቀርሻ ይዘል ፣
ጋራው በፈንጅ ይናድ ሳር ቅጠሉ ይቃጠል ፣
በትግል በእምቢታ በአመጽ እንጠራለን፣
በንፁህ ደማችን ችቦ እናበራለን።
ሺዎች ይታረዱ ሺዎች ይጨፍጨፉ ፣
ባህርም ይናወጥ ወንዞች ደም ያጉርፉ::
ከጭቁን ህዝቦች ልብ ፈልቆ የተቀዳው፣
ቀናው መስመራችን ጭቆና የወለደው፣
ድል ማድረጉ አይቀርም የተግባር ሀቅ ነው፣
ድል ማድረጉ አይቀርም የተግባር ሀቅ ነው።
ደራሲው ስለ ግጥሙ እንዲህ ይሉናል
ብዙዎች “የኢሕዴን/ብአዴን ድርጅታዊ መዝሙር ነው” ብለው
ይገልፁታል። ዜማውን የመጨረሻ መልክ ማስያዝ ላይ ሁለት ታጋዮች አግዘውኛል። የኢሕዴን ታጋዮች ያልተንበረከክነውን እንዘምር
በነበረ ጊዜ ሁሉ ድላችን በፍፁም አይቀሬ ለመሆኑ እርግጠኞች ነበርን። ፈተናዎች በተጋረጡብን ጊዜያት በሙሉ ያልተንበረከክነውን
ስንሰማም ሆነ ስንዘምር የትግል ወኔያችን ይታደሳል ።
መዝሙሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በ“መሳሪያ” እየተዘመረ ሪከርድ የተደረገው በሁለት ሀርሞኒካና
ጠረጴዛ አንደ ከበሮ እየተመታና “ ስቱዲዮ “ የነበረውም ሰቆጣ የሚገኘው ዋግ አውራጃ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሲሆን፤ ጊዜውም
ከ1975 ዓ.ም ህዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት በአንዱ ቀን ሌሊት ነው። ለቀረጻ ሥራ ላይ የዋሉት ሁለት ቴፕ ሪከርደሮች ነበሩ
። ሦስቱ ታጋዮች መጀመሪያ በድምፃችን እየዘመርን በቴፕ ተቀረፅን ። ቀጥለንም የቀረፅነውን ድምፃችንን በቴፕ እየተከተልን
(እያዳመጥን) ፤ ሀርሞኒካዎቹን ኡስማንና ታምራት እየተጫወቱና እኔ ጠረጴዛውን እንደ ከበሮ እየደቃሁ ሁለቱንም በሌላ ሁለተኛ ቴፕ
ቀረፅነው። አቀናበርነው ይባል ይሆን? በርግጥም የኢሕዴን ታጋዮች ዛሬ እልፎች ሆነዋል። ያልተንበረከክነውም እርሱን እየዘመሩ
ያለፉ ታጋዮች በሚዘከሩባቸው በአላት ላይ በአማራ ክልልና በታላላቆቹና በዝነኞቹ የፌዴራል ብራስ ባንዶች በየአደባባዩ በድምቀት
የሚሰማ መዝሙር ለመሆን በቅቷል።
ታጋይ መለስ ዜናዊ የኢሕዴንንን 18ኛ ዓመት በአል ምክንያት በማድረግ በህዳር 1991
ከታተመው ፍልሚያ ልዩ እትም መፅሄት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ከግጥሞቹና መዝሙሮቹ ሁሉ እስከ አሁንም ስሰማ ትንሽ እንደ
ኤሌክትሪክ ሾክ አይነት ነገር የሚሰማኝ "ያልተንበረከክነው" በሚለው መዝሙር
ነው፤ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር በማያያዝ ሲታይ ያልተንበረከክነው የሚለው ግጥም የያኔውን ኢሕዴን ከምንም በላይ የሚገልፅ
ነው ... ያኔ የተገጠሙት በሙሉ ተሰባስበው ቢታተሙ ይጠቅማሉ”
በማለት ተናግሮ ነበር።
ብአዴን ጽናቱንና ሕዝባዊነቱን
ጠብቆ
የህዳሴውን ጉዞ ያፋጥናል !
No comments:
Post a Comment